በኢንተርኔት መጠናናት በእርግጥ አደገኛ ሊሆን ይችላል?
የወጣቶች ጥያቄ . . .
በኢንተርኔት መጠናናት በእርግጥ አደገኛ ሊሆን ይችላል?
“በኢንተርኔት እየጻፈላችሁ ስላለው ሰው ማንነት በትክክል ማወቅ አትችሉም።”—የ17 ዓመቱ ዳን *
“ሰዎች በኢንተርኔት ሊዋሹ ይችላሉ። ያልሆኑትን ሆኖ መቅረብ ቀላል ነው።”—የ26 ዓመቱ ጆርጅ
በኢንተርኔት የፍቅር ግንኙነት መመሥረት በመላው ዓለም ያለው ተወዳጅነት እየጨመረ መጥቷል። ይህን ጉዳይ አስመልክቶ በዚህ ዓምድ ሥር ከዚህ ቀደም በወጣው ርዕስ እንደተብራራው እንዲህ ባለ መልኩ በቀላሉ ፍቅር ሊመሠረት ቢችልም እውነታው ሲገለጥ ግንኙነቱ ይቋረጣል። * ሆኖም ጉዳዩን አሳሳቢ ያደረገው የኋላ ኋላ ሳይሳካ መቅረቱ የሚያስከትለው ብስጭት ብቻ አይደለም። በዚህ መንገድ የፍቅር ግንኙነት መመሥረት ከባድ ለሆነ አካላዊ፣ ስሜታዊ ወይም ደግሞ መንፈሳዊ አደጋ ሊዳርጋችሁ ይችላል።
ምንም ጉዳት የሌለው የሚመስለው በገዛ ቤታችን ውስጥ የሚገኝ ኮምፒውተር እንዴት አደጋ ሊያስከትል ይችላል? የሚያስከትላቸው አንዳንድ አደጋዎች በጣም አስፈላጊ ከሆነ አንድ የመጽሐፍ ቅዱስ መሠረታዊ ሥርዓት ጋር የተያያዙ ናቸው። ሐዋርያው ጳውሎስ ‘በሁሉም ነገር ሐቀኞች ሆነን መኖር እንፈልጋለን’ በማለት ጽፏል። (ዕብራውያን 13:18 NW) ይህ ጥቅስ የተጠቀሰው፣ ኢንተርኔት መጠቀም ሐቀኝነትን ማጓደል ነው ወይም ደግሞ ኢንተርኔት መጠቀማችሁ አጭበርባሪ እንድትሆኑ ያደርጋችኋል ለማለት ተፈልጎ አይደለም። ይሁን እንጂ ሰዎች በአብዛኛው ሐቀኞች እንዳልሆኑ መገንዘብ ይገባናል፤ በመግቢያው ላይ የተጠቀሱት ምሳሌዎች እንደሚያሳዩት በኢንተርኔት ሐሰት የሆኑ ነገሮች ውሸትነታቸው እንዳይታወቅ አድርጎ መጻፍ ቀላል ይመስላል። በተለይ በፍቅር ግንኙነት ረገድ ሐቀኛ አለመሆን በጣም አደገኛ ነው።
ለምሳሌ ያህል “ከማይረቡ ጋር አልተቀመጥሁም፤ ከግብዞችም ጋር አልተባበርሁም” በሚለው የመጽሐፍ ቅዱስ ጥቅስ ላይ የተጠቀሰውን የማታለል ተግባር ልብ በል። (መዝሙር 26:4) “ግብዞች” ሲል ምን ማለቱ ነው? አንዳንድ መጽሐፍ ቅዱሶች ይህን ቃል ‘እውነተኛ ማንነታቸውን የሚሰውሩ’ ብለው ተርጉመውታል። አንድ የማመሳከሪያ ጽሑፍ ይህ አባባል “ዓላማቸውን ወይም እቅዳቸውን ከሌሎች የሚደብቁ እንዲሁም እውነተኛ ባሕርያቸውንና ፍላጎታቸውን የሚሸሽጉ ሰዎችን” ሊያመለክት እንደሚችል ገልጿል። በኢንተርኔት አማካኝነት እንዲህ ያለ ሐቀኝነት የጎደለው ድርጊት የሚፈጸመው እንዴት ነው? ይህስ የፍቅር ግንኙነት የመመሥረት ዓላማ ባላቸው ሰዎች ላይ ምን አደጋ ያስከትላል?
የበግ ለምድ የለበሱ ተኩላዎች
ማይክል የተባለ አንድ አባት በርካታ ቁጥር ያላቸው ልጆች፣ ወላጆቻቸው መጥፎ የሆኑ የኢንተርኔት ድረ ገጾችን እንዳይመለከቱ ሲያዟቸው እሺ እንደማይሉ በአንድ ትምህርታዊ ጉባኤ ላይ መስማቱ በጣም አስደንግጦታል። “ከምንም በላይ ያሳሰበኝ ሕፃናትን የሚያስነውሩ ሰዎች ልጆቹ ወራዳ በሆኑ የጾታ ድርጊቶች እንዲካፈሉ ለማባበል በኢንተርኔት ሊጠቀሙ እንደሚችሉ ማወቄ ነው” ብሏል። ወጣቶች በኢንተርኔት አማካኝነት ከሰዎች ጋር ለመተዋወቅ ሲጥሩ እነርሱ ከሚገምቱት በላይ ለአደጋ ሊጋለጡ ይችላሉ።
እንዲያውም በጾታ የሚያስነውሩ ትልልቅ ሰዎች፣ ሰለባ የሚያደርጓቸውን ልጆች በኢንተርኔት በሚያድኑበት ጊዜ ወጣት መስለው እንደሚቀርቡ አንዳንድ የዜና ዘገባዎች ይገልጻሉ። አንድ ጥናት እንዳመለከተው “ኢንተርኔት ከሚጠቀሙ አምስት ልጆች አንዱ በጾታ ድርጊት እንዲካፈል ጥያቄ ቀርቦለታል።” አንድ ጋዜጣም እንዲሁ ከ10 እስከ 17 ዓመት የዕድሜ ክልል ውስጥ ከሚገኙት 33 ልጆች አንዱ በኮምፒውተር በሚደረግ የሐሳብ ልውውጥ አማካኝነት ሥነ ምግባር የጎደለው ድርጊት እንዲፈጽም ተደጋጋሚ ማባበያ እንደሚቀርብለት ዘግቧል።
በኢንተርኔት የፍቅር ግንኙነት ጀምረው የነበሩ የተወሰኑ ወጣቶች ፈጽሞ ያልጠበቁት ነገር ገጥሟቸዋል። እንደ እነርሱ ወጣት መስሎ የቀረባቸው ሰው ለካስ እስር ቤት ውስጥ የነበረ በዕድሜ የገፋ ሰው ነው። ሌሎች ወጣቶች ደግሞ ሳያውቁት በጾታ ከሚያስነውሩ ሰዎች ጋር ወዳጅነት መሥርተዋል። እነዚህ መጥፎ ሰዎች ከወደፊቱ የጥቃት ዒላማቸው ጋር በመጀመሪያ እንዲሁ የጓደኝነት መልእክቶችን በኢንተርኔት በመላላክ እንዲያምናቸው ያደርጉና ለጥቃት ያመቻቹታል። ውሎ አድሮ ርካሽ ምኞታቸውን ለማሳካት ሲሉ ፊት ለፊት ለመገናኘት ሐሳብ ያቀርባሉ። የሚያሳዝነው በእነዚህ ሰዎች እጅ የወደቁ ወጣቶች ተደብድበዋል፣ በጾታ ተደፍረዋል አልፎ ተርፎም ተገድለዋል።
በእውነትም ክፉ ሰዎች የጥቃት ሰለባዎቻቸውን በኢንተርኔት ለማግኘት ሲሉ ‘እውነተኛ ማንነታቸውን ይሰውራሉ።’ እንዲህ ያሉት አታላዮች ኢየሱስ ‘ነጣቂ ተኵላዎች ሆነው ሳሉ የበግ ለምድ ለብሰው በመካከላችሁ ይገባሉ’ በማለት የጠቀሳቸውን ሐሰተኛ ነቢያት አስታውሰዋችሁ ይሆናል። (ማቴዎስ 7:15) ከማያውቁት ሰው ጋር በኢንተርኔት አማካኝነት በሚደረግ የሐሳብ ልውውጥ እንዲህ ያለውን የማታለል ድርጊት ለይቶ ማወቅ አይቻልም። ቀደም ሲል የተጠቀሰው ጆርጅ “በአካል አግኝታችሁ የምታነጋግሩት ሰው ፊቱ ላይ የሚነበበው ስሜትና የድምፁ ቃና ስለ እርሱ አንድ ነገር እንድትገነዘቡ ያስችላችኋል። በኢንተርኔት ግን እንዲህ ማድረግ አትችሉም። በቀላሉ ልትታለሉ ትችላላችሁ” ብሏል።
“አስተዋይ ሰው አደጋ ሲያይ መጠጊያ ይሻል፤ ብስለት የጐደለው ግን በዚያው ይቀጥላል፤ መከራም ያገኘዋል” የሚለው የመጽሐፍ ቅዱስ ምክር በእርግጥም ጠቃሚ ነው። (ምሳሌ 22:3) በኢንተርኔት የምታገኘው ሰው ሁሉ ስውር ዓላማ ያለው እንደማይሆን እሙን ነው። ይሁን እንጂ ሰዎች ‘እውነተኛ ማንነታቸውን የሚሰውሩባቸው’ ሌሎች መንገዶችም አሉ።
ማታለልና ራስን መደበቅ
በኢንተርኔት የፍቅር ግንኙነት መመሥረት የሚፈልጉ ሰዎች፣ ስለ ራሳቸው አጋንነው ወይም የሌላቸውን መልካም ባሕርይ እንዳላቸው አድርገው መናገራቸው እንዲሁም ከባድ ድክመቶቻቸውን አቃልለው አሊያም ደግሞ ደብቀው መቅረባቸው የተለመደ ነው። ዘ ዋሽንግተን ፖስት አንድ ደራሲ የተናገሩትን በመጥቀስ እንዲህ ብሏል:- “በኢንተርኔት የሚደረግ የፍቅር ግንኙነት ሰዎች እንዲታለሉ መንገድ ስለሚከፍት መጥፎ ሊሆን ይችላል። ሰዎች ብዙውን ጊዜ ጾታቸውን ደብቀው ይቀርባሉ። . . . የገቢያቸውን መጠን፣ . . . ዘራቸውን፣ የፈጸሙትን ወንጀል፣ ከአእምሮ ጤንነት ጋር በተያያዘ አጋጥሟቸው የነበረውን ነገርና የጋብቻቸውን ሁኔታ ለረጅም ጊዜያት ደብቀው ይቆያሉ።” በርካታ ሰዎች ሌሎችን ለማስጠንቀቅ ሲሉ በኢንተርኔት የፍቅር ግንኙነት በመሠረቱበት ጊዜ ያጋጠሟቸውን አሳዛኝ ክስተቶች ተናግረዋል።
ሰዎች መንፈሳዊነታቸውን የመሰሉ በጣም አስፈላጊ ነገሮችን በተመለከተ ይዋሻሉ? አዎን፣ የሚያሳዝነው አንዳንዶች
እውነተኛ ክርስቲያን ሳይሆኑ እውነተኛ ክርስቲያን መስለው ይቀርባሉ። በዚህ መንገድ ያልሆኑትን ሆነው ለመቅረብ የሚጥሩት ለምንድን ነው? አንደኛው ምክንያት ኢንተርኔት ለዚህ ዓይነቱ ሸፍጥ ምቹ ሁኔታ ስለሚፈጥር ነው። በአይርላንድ የሚኖር ሾን የተባለ ወጣት “በኮምፒውተር ያልሆንከውን እንደሆንክ አድርገህ መጻፍ በጣም ቀላል ነው” በማለት እውነታውን ገልጿል።ብዙ ሰዎች፣ መቼም ፍቅር ለመጀመር በመጠኑም ቢሆን መዋሸት ያለ ነገር ነው በሚል ሰበብ ይህን ድርጊት አቅልለው ይመለከቱታል። ይሁን እንጂ አምላክ ውሸትን እንደሚጠላ አስታውስ። (ምሳሌ 6:16-19) ይሖዋ ውሸትን የሚጠላበት በቂ ምክንያት አለው። በዚህ ምድር ላይ ያለው አብዛኛው ሥቃይና ችግር መዋሸት ያስከተለው ውጤት ነው። (ዮሐንስ 8:44) ውሸት በማንኛውም ግንኙነት ረገድ በተለይ ደግሞ ዕድሜ ልካቸውን ለመጣመር ላሰቡ ሰዎች መጥፎ መሠረት ነው። ከሁሉ የሚከፋው ደግሞ ይህ ባሕርይ መንፈሳዊ አደጋ የሚያስከትል መሆኑ ነው፤ ሐሰት የሚናገር ሰው ከይሖዋ አምላክ ጋር ያለው ወዳጅነት ይበላሻል።
የሚያሳዝነው አንዳንድ ወጣቶች በሌላ መንገድ ሐቀኝነታቸውን ያጓድላሉ። በኢንተርኔት ካገኟቸው ሰዎች ጋር ወዳጅነት ይመሠርቱና እንዲህ ማድረጋቸውን ከወላጆቻቸው ይደብቃሉ። ለምሳሌ ያህል በአሥራዎቹ ዕድሜ ውስጥ የሚገኝ የአንድ ወጣት ወላጆች፣ አንድ ቀን ከእነርሱ የተለየ እምነት የምትከተል ወጣት ከ1,500 ኪሎ ሜትር በላይ ተጉዛ በድንገት ቤታቸው ስትመጣ በጣም ደነገጡ። ልጃቸው ከእርሷ ጋር ለስድስት ወራት በኢንተርኔት የፍቅር ግንኙነት ያደርግ ነበር፤ ይሁን እንጂ እስከዚያች ደቂቃ ድረስ ስለ ግንኙነታቸው የሚያውቁት አንዳች ነገር አልነበረም!
ወላጆቹ “እንዴት ሊሆን ይችላል?” በማለት በጣም በመገረም ተናገሩ። ‘ልጃችን አይቷት ከማያውቃት ሴት ጋር ፍቅር ሊይዘው አይችልም’ ብለው ያስቡ ነበር። በእርግጥም ልጃቸው እውነተኛ ማንነቱን በመሰወር እያታለላቸው ነበር። በዚህ መንገድ የተመሠረተ የፍቅር ግንኙነት ዘላቂነት ሊኖረው ይችላል ብለህ ታስባለህ?
በኢንተርኔት ከሚሆን ይልቅ ፊት ለፊት መገናኘቱ ይመረጣል
በኢንተርኔት የሚጀመር የፍቅር ግንኙነት ሌሎች አደጋዎችንም ያስከትላል። አንዳንድ ጊዜ በኢንተርኔት የምትጻጻፉት ሰው በየዕለቱ በአካል ከምታገኟቸው ሰዎች ሊበልጥባችሁ ይችላል። ቤተሰቦቻችሁን፣ ጓደኞቻችሁንና ያሉባችሁን ኃላፊነቶች ቸል እስከማለት ትደርሳላችሁ። በኦስትሪያ የምትገኝ ሞኒካ የተባለች አንዲት ወጣት “በኢንተርኔት ከተዋወቅኳቸው ሰዎች ጋር ብዙ ጊዜ አሳልፍ ስለነበር የቅርብ ወዳጆቼን ችላ ማለት ጀምሬ ነበር” ብላለች። ይህንን እውነታ በተገነዘበች ጊዜ በጣም ከማዘኗም በላይ ሰዎችን በኢንተርኔት መተዋወቅና መልእክት መለዋወጥ አቆመች።
በርካታ ሰዎች በኢንተርኔት አጠቃቀማቸው ረገድ ሚዛናዊ እንደሆኑ እሙን ነው። ከወዳጆቻችንና ከዘመዶቻችን ጋር ያለን ግንኙነት እንዳይቋረጥ በመርዳት ረገድም ኢ-ሜይል ትልቅ ሚና ይጫወታል። ይሁን እንጂ ፊት ለፊት ተገናኝቶ መነጋገርን የሚያክል ነገር እንደሌለ እንደምትስማሙ ምንም ጥርጥር የለውም። የጾታ ስሜት የሚያይልበትን ‘አፍላ የጉርምስና ዕድሜ ካለፋችሁና’ ማግባት የምትፈልጉ ከሆናችሁ በሕይወታችሁ ውስጥ በጣም ከባድ ውሳኔ ከምታደርጉባቸው ጉዳዮች አንዱን ተጋፍጣችኋል ማለት ነው። (1 ቆሮንቶስ 7:36 NW) በተቻላችሁ መጠን ጥንቃቄ የታከለበት ውሳኔ አድርጉ።
መጽሐፍ ቅዱስ “ተላላ ሰው ሁሉን ያምናል፤ አስተዋይ ግን ርምጃውን ያስተውላል” የሚል ምክር ይሰጣል። (ምሳሌ 14:15) ፈጽሞ አግኝታችሁት የማታውቁት ሰው የጻፈላችሁን ነገር ሁሉ ከማመን ይልቅ እርምጃችሁን በጥንቃቄ መመዘን ይኖርባችኋል። ፊት ለፊት በመገናኘት ጓደኝነት መጀመር ከሁሉ የተሻለ ነው። በተለይ ለመንፈሳዊ ነገሮች በምትሰጡት ግምትና በግቦቻችሁ ረገድ በእርግጥ የምትስማሙ ጓደኛሞች ልትሆኑ ትችሉ እንደሆነና እንዳልሆነ መርምሩ። እንዲህ ባለ መንገድ ለጋብቻ መጠናናት እውነተኛ ደስታ ያለበት ትዳር ለመመሥረት ያስችላል።
[የግርጌ ማስታወሻዎች]
^ አን.3 አንዳንዶቹ ስሞች ተቀይረዋል።
^ አን.5 በግንቦት 2005 ንቁ! እትም ላይ የወጣውን “የወጣቶች ጥያቄ . . . በኢንተርኔት ለትዳር ለመጠናናት ብሞክር ምን ችግር አለው?” የሚለውን ርዕስ ተመልከት።
[በገጽ 18 ላይ የሚገኙ ሥዕሎች]
በኢንተርኔት መልእክት እየጻፈልሽ ያለው ሰው በእርግጥ ማን እንደሆነ ታውቂያለሽ?
[በገጽ 20 ላይ የሚገኝ ሥዕል]
ለትዳር ለመጠናናት ፊት ለፊት ከመገናኘት የተሻለ ምንም ነገር የለም