በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

አምላክን ማገልገል የሚያስከትለውን ፈተና ተቋቋምኩ

አምላክን ማገልገል የሚያስከትለውን ፈተና ተቋቋምኩ

አምላክን ማገልገል የሚያስከትለውን ፈተና ተቋቋምኩ

ኢቫን ሚኪትኮቭ እንደተናገረው

“በከተማችን የምትቆይ ከሆነ ወደ እስር ቤት ትመለሳታለህ።” እንዲህ ሲል የዛተብኝ የሶቪዬት ሕብረት የደኅንነት ኮሚቴ (ኬጂቢ) መኮንን ነበር። ከ12 ዓመታት የእስር ቤት ቆይታ በኋላ ገና መለቀቄ ነበር። አባትና እናቴ በጠና በመታመማቸው የእኔን እርዳታ ይሻሉ። ታዲያ ምን ባደርግ ይሻላል?

የተወለድኩት ሞልዶቫ ውስጥ በምትገኘው ጻዑል በተባለችው መንደር፣ በ1928 ነው። * የአንድ ዓመት ልጅ ሳለሁ አባቴ አሌክሳንደር በሩማንያ የምትገኘውን ያሽን ለመጎብኘት ሄዶ በነበረበት ወቅት ዛሬ የይሖዋ ምሥክሮች ተብለው ከሚጠሩት የመጽሐፍ ቅዱስ ተማሪዎች ጋር ተገናኘ። ወደ ጻዑል ከተመለሰ በኋላ ከእነርሱ የተማረውን ነገር ለቤተሰቦቹና ለጎረቤቶቹ ነገራቸው። ብዙም ሳይቆይ በጻዑል አንድ አነስተኛ የመጽሐፍ ቅዱስ ተማሪዎች ቡድን ተቋቋመ።

ከአራት ወንዶች ልጆች መካከል ትንሹ እኔ ስሆን ያደግሁት ጥሩ ምሳሌ በሚሆኑኝ መንፈሳዊ አመለካከት ባላቸው ሰዎች ተከብቤ ነው። ይሖዋን ማገልገል ተቃውሞ እንደሚያስከትልና አስቸጋሪ እንደሆነ ከልጅነቴ አንስቶ በግልጽ ገብቶኝ ነበር። ፖሊስ የተደበቁ ጽሑፎቻችንን ለማግኘት በተደጋጋሚ ቤታችንን ይፈትሽ እንደነበር በደንብ ትዝ ይለኛል። እነዚህ አጋጣሚዎች ፍርሃት አላሳደሩብኝም። የአምላክ ልጅ የሆነው ኢየሱስ ክርስቶስ እንዲሁም የእርሱ ደቀ መዛሙርት ስደት ደርሶባቸው እንደነበር መጽሐፍ ቅዱስ ስናጠና ተምሬያለሁ። የኢየሱስ ተከታዮች ስደት ሊገጥማቸው እንደሚችል በስብሰባዎቻችን ላይ ብዙ ጊዜ ይነገረን ነበር።—ዮሐንስ 15:20

ስደትን ለመጋፈጥ ብርታት አገኘሁ

በ1934 ማለትም የስድስት ዓመት ልጅ ሳለሁ በጀርመን ያሉ ወንድሞቻችን በናዚ አገዛዝ ሥር እየደረሰባቸው ያለውን ሰቆቃ የሚገልጽ ደብዳቤ በጻዑል ለሚገኘው ጉባኤያችን ተነበበ። ለእነርሱ እንድንጸልይ ማበረታቻ ተሰጠን። ምንም እንኳ ትንሽ ልጅ የነበርኩ ቢሆንም ደብዳቤውን ፈጽሞ አልረሳውም።

ከአራት ዓመት በኋላ ለመጀመሪያ ጊዜ የአቋም ፈተና ደረሰብኝ። ትምህርት ቤት ውስጥ በሃይማኖታዊ ትምህርት ክፍለ ጊዜ የኦርቶዶክስ ቄስ የሆነው አስተማሪያችን አንገቴ ላይ መስቀል እንዳስር ደጋግሞ ይነግረኝ ነበር። ይህንን ባለማድረጌ በክፍል ውስጥ ያሉት ልጆች መስቀል ማድረጋቸው ጥሩ የቤተ ክርስቲያን አባል መሆናቸውን የሚያሳይ ስለሆነ መስቀላቸውን እንዲያሳዩ ጠየቃቸው። ከዚያም ወደ እኔ እያመለከተ ተማሪዎቹን እንዲህ አላቸው:- “እንዲህ ዓይነት ልጅ ክፍላችሁ ውስጥ እንዲኖር ትፈልጋላችሁ? እስቲ የማትፈልጉ እጃችሁን አውጡ።”

ተማሪዎቹ በሙሉ ቄሱን በመፍራት እጃቸውን አወጡ። ከዚያም ወደ እኔ ዞሮ “አየህ ማንም ከአንተ ጋር ምንም ዓይነት ግንኙነት እንዲኖረው አይፈልግም። በል ይህንን ሕንፃ በቶሎ ለቀህ ውጣ” አለኝ። ከጥቂት ቀናት በኋላ የትምህርት ቤቱ ርዕሰ መምህር እኛ ቤት መጣ። ከወላጆቼ ጋር ከተነጋገረ በኋላ ወደ ትምህርት ቤት መመለስ እፈልግ እንደሆነ ጠየቀኝ። እኔም መማር እንደምፈልግ ነገርኩት። “የትምህርት ቤቱ ርዕሰ መምህር እኔ እስከሆንኩ ድረስ መማር ትችላለህ፣ ቄሱ ሊከለክልህ አይችልም” አለኝ። ቃሉን በመጠበቅም እርሱ ርዕሰ መምህር እስከነበረበት ጊዜ ድረስ ቄሱ አንዳች ችግር አልፈጠረብኝም።

ስደቱ እየከፋ ሄደ

እንኖርባት የነበረችው ቤሳረቢያ በ1940 የሶቪዬት ሕብረት አካል ሆነች። በሰኔ 13 እና 14, 1941፣ በፖለቲካው መድረክ አሊያም በኅብረተሰቡ ዘንድ ከፍተኛ ተደማጭነት የነበራቸው ሰዎች ወደ ሳይቤሪያ ተጋዙ። በዚህ ወቅት የይሖዋ ምሥክሮች አልተነኩም ነበር። ሆኖም ከዚያን ጊዜ ጀምሮ የስብከት ሥራችንንና ስብሰባችንን በጥበብ ማከናወን ጀመርን።

የናዚ ጀርመን ጦር በ1941 ሰኔ ወር መጨረሻ ላይ እስከዚያ ጊዜ ድረስ አጋሩ በነበረችው በሶቪዬት ሕብረት ላይ ድንገተኛ ጥቃት ሰነዘረ። ብዙም ሳይቆይ የሩማንያ ሰራዊት ቤሳረቢያን መልሶ ያዘ። ይህ ደግሞ በድጋሚ በሩማንያ አገዛዝ ሥር እንድንወድቅ አደረገን።

በአቅራቢያችን በሚገኙ መንደሮች የሚኖሩ የይሖዋ ምሥክሮች በሩማንያ የጦር ኃይል ውስጥ ገብተው ለማገልገል ፈቃደኛ ባለመሆናቸው የተያዙ ሲሆን አብዛኞቹም 20 ዓመት ተፈርዶባቸው የጉልበት ሥራ ወደሚሠራበት ካምፕ ተልከዋል። አባቴን ወደ ፖሊስ ጣቢያ ጠርተው የይሖዋ ምሥክር በመሆኑ ያለ ምንም ርኅራኄ ደበደቡት። እኔ ደግሞ ከትምህርት ቤት በግድ ተወስጄ በቤተ ክርስቲያን የቅዳሴ ሥርዓት ላይ እንድገኝ ተደርጌ ነበር።

ሁለተኛው የዓለም ጦርነት ድንገት አቅጣጫውን ቀየረ። በመጋቢት 1944 የሶቪዬት ጦር በአጭር ጊዜ ውስጥ ሰሜናዊ ቤሳረቢያን ተቆጣጠረ። ነሐሴ ላይ ደግሞ አገሪቷን በሙሉ ተቆጣጠሩ። በዚያን ጊዜ በአሥራዎቹ አጋማሽ ላይ እገኝ ነበር።

ወዲያውኑ፣ በመንደራችን የሚገኙ ጤናማ የሆኑ ወንዶች በሶቪዬት ጦር ውስጥ እንዲገቡ ተመለመሉ። የይሖዋ ምሥክሮች ግን የገለልተኝነት አቋማቸውን ለመጣስ ፈቃደኛ አልነበሩም። ስለዚህ አሥር ዓመት ተፈርዶባቸው ወኅኒ ወረዱ። በግንቦት 1945፣ የጀርመንን ሽንፈት ተከትሎ በአውሮፓ ሁለተኛው የዓለም ጦርነት አበቃ። ይሁንና በሞልዶቫ የሚገኙ ብዙ የይሖዋ ምሥክሮች እስከ 1949 ድረስ በእስር ቤት ቆይተዋል።

ከጦርነቱ በኋላ የነበረው መከራ

ጦርነቱ በ1945 ካበቃ በኋላ ሞልዶቫ በከባድ ድርቅ ተመታች። ከድርቁ በተጨማሪ የሶቪዬት መንግሥት ገበሬዎች ካመረቱት ምርት ላይ አብዛኛውን ክፍል በግብር መልክ ይወስድ ነበር። ይህም አሰቃቂ ረሃብ እንዲከሰት ምክንያት ሆኗል። በ1947 በጻዑል ጎዳናዎች ላይ በርካታ ሬሳዎች አይቻለሁ። ወንድሜ ዬፊም በረሃብ ሲሞት እኔ ደግሞ አቅም ከማጣቴ የተነሳ ለበርካታ ሳምንታት መራመድ አቅቶኝ ነበር። ይሁንና የረሃቡ ጊዜ አለፈ፤ በሕይወት የተረፍነው የይሖዋ ምሥክሮችም አገልግሎታችንን ቀጠልን። እኔ ምሥራቹን በምንኖርበት መንደር ውስጥ ስሰብክ በሰባት ዓመት የሚበልጠኝ ወንድሜ ቫሲሌ ደግሞ በአቅራቢያችን ወደሚገኙት መንደሮች ሄዶ ይሰብክ ነበር።

በአገልግሎት የምናደርገው ተሳትፎ እያደገ ሲሄድ ባለ ሥልጣናቱ ይበልጥ በዓይነ ቁራኛ ይከታተሉን ጀመር። የስብከት ሥራችን፣ በፖለቲካ ውስጥ ተሳትፎ አለማድረጋችን እንዲሁም በውትድርና አገልግሎት የማንካፈል መሆናችን የሶቪዬት መንግሥት መጽሐፍ ቅዱሳዊ ጽሑፎችን ለማግኘት ሲል ቤታችንን እንዲበረብርና ከዚያም አልፎ ማሰር እንዲጀምር አነሳስቶታል። በ1949 በአቅራቢያችን ከሚገኙ ጉባኤዎች አንዳንድ የይሖዋ ምሥክሮች ወደ ሳይቤሪያ ተጋዙ። በዚህ ጊዜም ከእስር የተረፍነው አገልግሎታችንን ከበፊቱ በበለጠ በጥንቃቄ ማከናወን ጀመርን።

ይህ በእንዲህ እንዳለ እየተባባሰ የሚሄድ ከባድ የጤና ችግር አጋጠመኝ። በመጨረሻም ዶክተሮች የአጥንት ቲቢ እንደያዘኝ ነገሩኝ፤ ከዚያም በ1950 ቀኝ እግሬ በጀሶ ታሠረ።

ወደ ሳይቤሪያ በስደት መጋዝ

እግሬ አሁንም በጀሶ እንደታሠረ ቢሆንም ሚያዝያ 1, 1951 እኔና ቤተሰቤ ተይዘን ከሌሎች የይሖዋ ምሥክሮች ጋር ወደ ሳይቤሪያ ተጋዝን። * ዝግጅት የምናደርግበት ጊዜ ስላልነበረን መያዝ የቻልነው በጣም ትንሽ ምግብ ብቻ ነበር፤ እርሷም ብትሆን ቶሎ አለቀችብን።

በመጨረሻም ለሁለት ሳምንታት ያህል በባቡር ከተጓዝን በኋላ በቶምስክ አውራጃ ወደምትገኘው አሲኖ ደረስን። እዚያ ስንደርስ ከባቡሩ ላይ እንደ ከብት አራገፉን። የአየሩ ጠባይ በጣም ቀዝቃዛ ቢሆንም ንጹሕ አየር በማግኘታችን ደስ አለን። በግንቦት ወር በወንዙ ላይ ያለው የበረዶ ግግር መቅለጥ ሲጀምር 100 ኪሎ ሜትር ርቃ ወደምትገኘው ቶርባ ማለትም በደን ወደተሸፈነው የሳይቤሪያ ክፍል ወይም በአርክቲክ አቅራቢያ ወዳለው ጫካ በመርከብ ተጭነን የተወሰድን ሲሆን በዚህ ቦታ የእንጨት መሰንጠቂያ ካምፕ ይገኛል። በተበየነብን ፍርድ መሠረት በዚህ ሥፍራ የጉልበት ሥራ መሥራት የጀመርን ሲሆን ቀሪውን የሕይወት ዘመናችንን እዚሁ እንደምናሳልፍም ተነግሮን ነበር።

በእንጨት መሰንጠቂያ ካምፕ የጉልበት ሥራ መሥራት እስር ቤት ከመሆን የተለየ ቢሆንም በዓይነ ቁራኛ እንጠበቅ ነበር። ማታ ማታ የእኛ ቤተሰብ የሚያድረው የባቡር ፉርጎ ውስጥ ነበር። በዚያ የበጋ ወቅት መጪውን ክረምት የምናሳልፍበትን ቤት የሠራን ሲሆን የቤቱ ግማሽ አካል ከመሬት በታች ግማሽ አካሉ ደግሞ ከመሬት በላይ ነበር።

እግሬ በጀሶ በመታሠሩ ምክንያት ጫካ ካለው ሥራ ተገላግዬ ምስማር እንድሠራ ተመደብኩ። ይህ ሥራ የመጠበቂያ ግንብ መጽሔቶችንና ሌሎች መጽሐፍ ቅዱሳዊ ጽሑፎችን በድብቅ በማባዛቱ ሥራ ተሳትፎ እንዲኖረኝ አስችሎኛል። ጽሑፎቹ እኛ ካለንበት በሺህ ኪሎ ሜትሮች ርቆ ከሚገኘው ከምዕራብ አውሮፓ ያለማቋረጥ በድብቅ ይገቡ ነበር።

ተይዤ ታሰርኩ

በ1953 እግሬ ላይ ያለው ጀሶ ተፈታልኝ። ሆኖም ምንም ያህል ጥንቃቄ ባደርግም መጽሐፍ ቅዱሳዊ ጽሑፎችን በማባዛቱ ሥራ የማደርገውን ተሳትፎ ጨምሮ መንፈሳዊ እንቅስቃሴዬን በአጠቃላይ ኬጂቢ ደረሰበት። በዚህም ምክንያት ከሌሎች የይሖዋ ምሥክሮች ጋር ተያዝኩና ለ12 ዓመታት እስር ተፈርዶብኝ ወደ እስረኞች ካምፕ ተላክሁ። ለፍርድ ቀርበን በነበረበት ወቅት ሁላችንም ስለ አምላካችን ስለ ይሖዋና እርሱ ለሰው ልጆች ስላለው ፍቅራዊ ዓላማ ግሩም ምሥክርነት ሰጥተናል።

ከጊዜ በኋላ በዚያ የምንገኝ እስረኞች በስተ ምሥራቅ በመቶዎች የሚቆጠር ኪሎ ሜትር ርቆ በሚገኘው በኢርኩትስክ ወዳሉ የተለያዩ ካምፖች ተላክን። እነዚህ ካምፖች የተቋቋሙት የሶቪዬት መንግሥት ከባድ ጠላት ናቸው ተብለው የሚታሰቡ ሰዎችን ለመቅጣት ነበር። ከሚያዝያ 8, 1954 እስከ 1960 መጀመሪያ ድረስ 12 በሚያክሉ እንደዚህ ባሉ የጉልበት ሥራ የሚሠራባቸው ካምፖች ቆይቻለሁ። ከዚያም በስተ ምዕራብ ከ3,000 ኪሎ ሜትር በላይ ርቆ ወደሚገኘው የሞርዶቪያ ግዙፍ እስር ቤት የተዛወርኩ ሲሆን ይህ ቦታ ከሞስኮ ደቡብ ምስራቅ 400 ኪሎ ሜትር ላይ ይገኛል። እዚያም ከበርካታ የሶቪዬት ሕብረት ክፍሎች ከተሰበሰቡ ታማኝ የይሖዋ ምሥክሮች ጋር የመገናኘት አጋጣሚ አግኝቻለሁ።

የይሖዋ ምሥክር ያልሆኑ እስረኞች ከምሥክሮቹ ጋር በነፃነት ሲገናኙ እነርሱም የይሖዋ ምሥክር እንደሚሆኑ ሶቪዬቶች አስተዋሉ። ስለዚህ ይህ የሞርዶቪያ እስር ቤት ሕንፃ እስከ 30 ኪሎ ሜትር ተራርቀው የሚገኙ የተለያዩ የሥራ ካምፖች ያሉት በመሆኑ ከእስረኞቹ ጋር በቅርብ መገናኘት እንዳንችል ለማድረግ ጥረት አደረጉ። እኔ በነበርኩበት ካምፕ ውስጥ ከ400 በላይ የይሖዋ ምሥክሮች ነበርን። ከእኛ ጥቂት ኪሎ ሜትሮች ርቀው መቶ የሚያክሉ እህቶች በእስር ቤቱ ሌላ ካምፕ ውስጥ ይገኙ ነበር።

በእኛ ካምፕ ውስጥ ክርስቲያናዊ ስብሰባዎችን በማደራጀትና በድብቅ የሚገቡትን መጽሐፍ ቅዱሳዊ ጽሑፎች በማባዛት ሥራ ላይ በንቃት እንቀሳቀስ ነበር። ይህን እንቅስቃሴዬን የካምፑ ባለ ሥልጣናት ደረሱበት። ብዙም ሳይቆይ በነሐሴ 1961 ከሞስኮ ሰሜናዊ ምሥራቅ 200 ኪሎ ሜትር ርቆ በሚገኘው በዛሮች ዘመን በተቋቋመው በአሰቃቂነቱ ወደሚታወቀው ቭላድሚር እስር ቤት ለአንድ ዓመት ተላክሁ። አሜሪካዊው ፓይለት ፍራንሲስ ግሬይ ፓወርስ በግንቦት 1, 1960 በሩስያ ላይ የስለላ አውሮፕላን ሲያበር ተመትቶ ከወደቀ በኋላ በዚሁ እስር ቤት እስከ የካቲት 1962 ድረስ ቆይቶ ነበር።

በቭላድሚር እስር ቤት እያለሁ ምግብ የሚሰጠኝ ሕይወቴን ለማቆየት ያህል ብቻ ነበር። በልጅነቴ ያጋጠመኝ ነገር ስለነበር ረሃቡን ተቋቁሜ ያሳለፍኩት ቢሆንም በ1961/62 የክረምት ወራት የነበረው ቅዝቃዜ ግን በጣም ከብዶኛል። የማሞቅያ መሣሪያው በመበላሸቱ እኔ የነበርኩበት ክፍል ቅዝቃዜ ከዜሮ በታች ወርዶ ነበር። አንድ ዶክተር ያለሁበትን አደገኛ ሁኔታ ከተመለከተ በኋላ ለቀሩት በጣም ብርዳማ ሳምንታት ሻል ወዳለ ክፍል እንድዛወር አደረገ።

ፈተናውን የምቋቋምበት ብርታት አገኘሁ

አንድ እስረኛ ከበርካታ ወራት እስር በኋላ አሉታዊ አስተሳሰቦች ተስፋ ሊያስቆርጡት ይችላሉ፤ የእስር ቤት ኃላፊዎች ደግሞ የሚፈልጉት ይህንኑ ነው። ይሁንና በጸሎት በመጽናቴ የይሖዋ መንፈስና የማስታውሳቸው ጥቅሶች እንድጠነክር ረድተውኛል።

በተለይ ቭላድሚር በተባለው እስር ቤት በነበርኩበት ጊዜ ሐዋርያው ጳውሎስ “ከየአቅጣጫው ብንገፋም አንንኰታኰትም፤ ግራ ብንጋባም ተስፋ አንቈርጥም” ብሎ ሲናገር ምን ማለቱ እንደነበር በደንብ ሊገባኝ ችሏል። (2 ቆሮንቶስ 4:8-10) ከአንድ ዓመት በኋላ ወደ ሞርዶቪያ ካምፕ ተመለስኩ። ሚያዝያ 8, 1966፣ ለ12 ዓመት ተፈርዶብኝ የነበረውን እስራት በዚህ ካምፕ አጠናቀቅሁ። ከእስር መለቀቄን በሚያመለክተው ወረቀት ላይ “ፈጽሞ የማይሻሻል” የሚል ተጽፎበት ነበር። ይህ ለይሖዋ ታማኝ ሆኜ መኖሬን የሚያረጋግጥ ማስረጃ እንደሆነ አድርጌ ቆጠርኩት።

በሶቪዬት ካምፖችና እስር ቤቶች ውስጥ ጥብቅ ክትትል ይደረግብን የነበረ ቢሆንም ጽሑፎች የሚደርሱንና ከዚያም የምናባዛው እንዴት እንደሆነ ብዙ ጊዜ ጥያቄ ይቀርብልኛል። ፖትማ በሚባለው የሴቶች እስር ቤት ለአራት ዓመት የታሰረች የላትቪያ የፖለቲካ እስረኛ እንዳለችው ሁኔታው ለብዙዎች ምስጢር ነበር። በ1966 ከእስር ከተለቀቀች በኋላ “ምሥክሮቹ ብዙ ጽሑፎች ያገኙ ነበር” ስትል ጽፋለች። መደምደሚያዋ ላይም “ሌሊት መልአክ በዚያ እየበረረ ሲያልፍ ጥሎላቸው የሚሄድ ነው የሚመስለኝ” ብላለች። በእርግጥም ሥራችንን ማከናወን የቻልነው በአምላክ እርዳታ ነበር።

አንጻራዊ ነፃነት የተገኘበት ወቅት

ከእስር ከተለቀቅሁ በኋላ ለስብከቱ ሥራ አመራር የሚሰጡት ወንድሞች ሞልዶቫ አጠገብ ወደምትገኘው ምዕራባዊ ዩክሬን እንድሄድና የሞልዶቫ ወንድሞቻችንን እንድረዳ ጠየቁኝ። ይሁን እንጂ እስረኛ ስለነበርኩና ኬጂቢ በዓይነ ቁራኛ የሚከታተለኝ በመሆኑ መሥራት የምችለው ነገር በጣም ውስን ነበር። ከሁለት ዓመት በኋላ በድጋሚ የመታሰር አደጋ ሲያጠላብኝ የሶቪዬት ሕብረት ሪፑብሊክ ወደ ሆነችው ወደ ካዛክስታን ሄድኩ፤ በዚያ የነበሩት ባለ ሥልጣናት ጥብቅ ቁጥጥር አያደርጉም ነበር። ከዚያም በ1969 ወላጆቼ በጣም ስለታመሙ እነርሱን ለመንከባከብ ወደ ዩክሬን ተመለስኩ። ድነትስክ ከሚባለው ትልቅ ከተማ በስተ ሰሜን በሚገኘው በአርትዮመስክ እያለሁ አንድ የኬጂቢ መኮንን መግቢያዬ ላይ የጠቀስኩትን በማለት በድጋሚ ወደ እስር ቤት እንደሚልከኝ ዛተብኝ።

መኮንኑ እንዲሁ ለማስፈራራት ብሎ የተናገረው ነገር እንደሆነ ከጊዜ በኋላ ገባኝ፤ ምክንያቱም እርምጃ ለመወሰድ የሚያበቃ ምንም ማስረጃ አልነበረውም። ክርስቲያናዊ አገልግሎቴን ለመቀጠል ቁርጥ ውሳኔ አድርጌ ስለነበር የትም ሄድኩ የት የኬጂቢ አባላት ይከታተሉኝ ነበር፤ ስለዚህ እዚያው ሆኜ ወላጆቼን መጦሬን ቀጠልኩ። አባቴና እናቴ እስከ መጨረሻው ለይሖዋ ታማኝ ሆነው አንቀላፉ። አባቴ ኅዳር 1969 ሲሞት እናቴ ግን እስከ የካቲት 1976 ድረስ በሕይወት ነበረች።

ወደ ዩክሬን ስመለስ ዕድሜዬ 40 ዓመት ነበር። ወላጆቼን ለመንከባከብ እዚያ በነበርኩበት ጊዜ በጉባኤያችን ውስጥ ማሪያ የምትባል አንዲት እህት ነበረች። እንደ እኛ ቤተሰብ ሁሉ እርሷና ወላጆቿ በ1951 ሚያዝያ ወር መጀመሪያ አካባቢ ከሞልዶቫ ወደ ሳይቤሪያ በተጋዙበት ወቅት የስምንት ዓመት ልጅ ነበረች። ማሪያ ጥሩ አድርጌ እንደምዘምር ነገረችኝ። ጓደኝነታችን የጀመረው በዚህ መልክ ሲሆን ምንም እንኳ ሁለታችንም ጊዜያችን በአገልግሎት የተያዘ ቢሆንም ወዳጅነታችንን ለማጠናከር ጊዜ አላጣንም። እንድንጋባ ያቀረብኩላትን ጥያቄ በ1970 በደስታ ተቀበለች።

ብዙም ሳይቆይ ሊዲያ የምትባለው ልጃችን ተወለደች። ከዚያም በ1983 ሊዲያ የአሥር ዓመት ልጅ እያለች ከዚህ ቀደም የይሖዋ ምሥክር የነበረ ሰው ለኬጂቢ አሳልፎ ሰጠኝ። በዚህ ወቅት በምሥራቃዊ ዩክሬን በወረዳ የበላይ ተመልካችነት ሳገለግል ወደ አሥር ዓመት ገደማ ሆኖኝ ነበር። ክርስቲያናዊ እንቅስቃሴያችንን የሚቃወሙ ሰዎች በችሎት ፊት የሐሰት ምሥክሮችን በማቅረብ ለአምስት ዓመት አስፈረዱብኝ።

እስር ቤት ውስጥ ከሌሎች ምሥክሮች ጋር እንዳልገናኝ ተደረግሁ። በዚህ ሁኔታ ለዓመታት ተገልዬ ብኖርም እንኳ የትኛውም ኃይል ከይሖዋ ጋር ያለኝን ግንኙነት ሊያግድብኝ አልቻለም፤ እርሱም እንድጸና አስችሎኛል። በተጨማሪም ለሌሎች እስረኞች የመስበክ አጋጣሚ አግኝቻለሁ። በመጨረሻ ለአራት ዓመት ከታሰርኩ በኋላ ተፈትቼ ይሖዋን በታማኝነት እያመለኩ ከነበሩት ከባለቤቴና ከልጄ ጋር ተገናኘሁ።

ወደ ሞልዶቫ ተመለስኩ

በዩክሬን ሌላ አንድ ዓመት ከቆየን በኋላ በሞልዶቫ ተሞክሮ ያለውና የጎለመሰ ወንድም ያስፈልግ ስለነበር በቋሚነት ወደዚያ ተመለስን። በዚህ ጊዜ የሶቪዬት መንግሥት ከቦታ ወደ ቦታ የመንቀሳቀስ ሰፋ ያለ ነፃነት ሰጥቶ ነበር። በ1988፣ ማሪያ ከ37 ዓመት በፊት ትኖርባት ወደነበረችው ባውቲ ወደ ተባለች ከተማ መጣን። ማርያ ወደ ግዞት የተወሰደችው ከዚህች ከተማ ነበር። በሞልዶቫ በትልቅነቷ ሁለተኛ በሆነችው በዚህች ከተማ በ1988 የነበሩት የይሖዋ ምሥክሮች 375 ሲሆኑ በአሁኑ ጊዜ ግን 1,500 ደርሰዋል። የምንኖረው በሞልዶቫ ቢሆንም እንኳ በዩክሬን የወረዳ የበላይ ተመልካች ሆኜ ማገልገሌን አላቆምኩም ነበር።

በመጋቢት 1991 ሶቪዬት ሕብረት ውስጥ ሃይማኖታዊ ድርጅታችን ሕጋዊ እውቅና ያገኘ ሲሆን በወቅቱ የኮሚኒዝም ሥርዓት መውደቅ በሺህ የሚቆጠሩ ሰዎች ተስፋ እንዲቆርጡ አድርጓቸዋል። ብዙዎች ግራ ተጋብተውና የወደፊቱን ጊዜ በተመለከተ ተስፋ አጥተው ነበር። ሞልዶቫ ራሷን የቻለች ሉዓላዊ አገር ስትሆን ቀደም ሲል ስደት ያደርሱብን የነበሩትን ሰዎች ጨምሮ ጎረቤቶቻችን ለመጽሐፍ ቅዱስ እውነት ፍላጎት አደረባቸው። በ1951 በስደት ወደ ሳይቤሪያ ስንጋዝ በሞልዶቫ የቀሩት ጥቂት የይሖዋ ምሥክሮች ብቻ ሲሆኑ ዛሬ ግን 4,200,000 የሚያክሉ ነዋሪዎች ባላት በዚህች ትንሽ አገር ውስጥ ከ18,000 በላይ የይሖዋ ምሥክሮች ይገኛሉ። በአሁኑ ጊዜ ያገኘናቸው አስደሳች ተሞክሮዎች ቀደም ሲል የደረሰብንን ሥቃይና መከራ እንድንረሳ አድርገውናል።

በ1990ዎቹ አጋማሽ ላይ ጤና እያጣሁ በመምጣቴ በወረዳ የበላይ ተመልካችነት መቀጠል አልቻልኩም። የጤናዬ ሁኔታ ተስፋ ያስቆረጠኝ ጊዜያት ነበሩ። ይሁንና አንድ የተገነዘብኩት ነገር ቢኖር ይሖዋ እኛን ለማበርታት ምን እንደሚያስፈልገን የሚያውቅ መሆኑን ነው። የሚያስፈልገንን ማበረታቻ በተገቢው ጊዜ ያቀርብልናል። ሕይወቴን በአዲስ መልክ የመኖር አጋጣሚ ባገኝ የተለየ ሕይወት እመርጥ ነበር? በፍጹም። እንዲያውም ይበልጥ ደፋርና ንቁ ሆኜ ማገልገል እችል እንደነበር አስባለሁ።

ይሖዋ እንደባረከኝ ይሰማኛል እንዲሁም ሁኔታቸው ምንም ይሁን ምን ሕዝቦቹ ባጠቃላይ የተባረኩ ናቸው። ብሩህ ተስፋ፣ ሕያው የሆነ እምነት እንዲሁም በቅርቡ ይሖዋ በሚያዘጋጀው አዲስ ሥርዓት ውስጥ ሁሉም ሰው ፍጹም ጤንነት እንደሚያገኝ ዋስትና አለን።

[የግርጌ ማስታወሻዎች]

^ አን.4 በዚህ ርዕስ ውስጥ አገሪቱን የምንጠራት በቀድሞ ስሟ ማለትም ሞልዴቪያ ወይም የሞልዴቪያ ሶቪዬት ሶሻሊስት ሪፑብሊክ ብለን ሳይሆን አሁን በምትታወቅበት ሞልዶቫ በሚለው መጠሪያ ነው።

^ አን.21 ሶቪዬቶች በ1951 ሚያዝያ ወር ላይ በመጀመሪያዎቹ ሁለት ቅዳሜና እሁዶች በአገሪቱ ምዕራባዊ ክፍል የሚኖሩ 7,000 የሚያክሉ የይሖዋ ምሥክሮችንና ቤተሰባቸውን ለመሰብሰብ ከዚያም በስተ ምሥራቅ በሺህ የሚቆጠሩ ኪሎ ሜትሮች ርቆ ወደሚገኘው ወደ ሳይቤሪያ በባቡር ለማጋዝ በደንብ የታሰበበት ፕሮግራም አውጥተው ነበር።

[በገጽ 23 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

በ1953 በግዞት እያለን በቶርባ፣ ሳይቤሪያ የነበረን ቤት። አባትና እናቴ (በስተ ግራ)፣ ወንድሜ ቫሲሌና ወንድ ልጁ (በስተ ቀኝ)

[በገጽ 23 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

በ1955 በእስር ቤት እያለሁ

[በገጽ 25 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

በሳይቤሪያ የነበሩ እህቶች፣ ማሪያ (ከታች በስተ ግራ) ያኔ 20 ዓመቷ ገደማ ነበር

[በገጽ 25 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

ከልጃችን ከሊዲያ ጋር

[በገጽ 25 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

በ1970 በሠርጋችን ዕለት

[በገጽ 25 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

በአሁኑ ወቅት ከማሪያ ጋር