በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

ከዓለም አካባቢ

ከዓለም አካባቢ

ከዓለም አካባቢ

የውሻ ኑሮ ነው

“አውስትራሊያ ለውጭ እርዳታ ከምታወጣው ገንዘብ ይልቅ ለቤት እንስሳት የምታወጣው ገንዘብ ይበልጣል” ሲል ዘ ሲድኒ ሞርኒንግ ሄራልድ የተባለው ጋዜጣ ዘግቧል። “አውስትራሊያውያን ለቤት እንስሳት የሚያወጡት ገንዘብ በዓመት ወደ 1.7 ቢሊዮን ዶላር እንዲያሻቅብ ካደረጉት ሸቀጦች መካከል የውሻ ነፍስ አድን ጃኬት፣ የቤት እንስሳት የአልማዝ ጌጣጌጥና የትንፋሽ ጠረን ማስለወጫ መድኃኒቶች ይገኙበታል።” የቤት እንስሳት ሸቀጣ ሸቀጥ ሻጭ የሆኑት ጄሰን ግራም ባለፉት አሥር ዓመታት ሰዎች ለቤት እንስሳት የነበራቸው አመለካከት መለወጡን ገልጸዋል። “ውሾች ጓሮ ታስረውና ቁንጫ ወሯቸው የደረቀ አጥንት ሲግጡ ይውሉ ነበር። አሁን ግን መኖሪያ ቤት ውስጥ ምቹ አልጋ ላይ ተኝተውና ከመስታወት የተሠራ ጌጥ አድርገው ይውላሉ” ብለዋል። ይሁን እንጂ ጄሰን፣ ውሾች እንደ ቤተሰብ አባላት ስለሚታዩና በጣም ውድ የሆኑ ዕቃዎች ስለሚገዙላቸው ለንግዳችን በጅቶናል ብለዋል። አንዳንድ የቤት እንስሳት “የሚያዙት የሰው ዓይነት ፍላጎቶችና ምርጫዎች እንዳሏቸው ተደርገው ቢሆንም ውሾች 5 ብር ከሚያወጣ አሻንጉሊት 50 ብር የሚያወጣ አሻንጉሊት እንደሚመርጡ የሚያሳይ ማስረጃ የለም። ቢሆንም እንዲህ ዓይነቱ ቅንጦት የእንስሳቱ ባለቤቶች ፍቅራቸውን የሚያሳዩበት አጋጣሚ እንዲያገኙ አስችሏቸዋል” ሲል ጋዜጣው ዘግቧል።

የድምፅ ብክለት

የጫጫታ መብዛት በከተሞች የሚኖሩ ሰዎችን የሕይወት ጣዕም እየቀነሰባቸው ነው። ኤቢሲ የተባለው ጋዜጣ፣ የዓለም ጤና ድርጅትን ዋቢ በማድረግበጤናቸውም ላይ ጉዳት ሊያስከትል እንደሚችል ዘግቧል። የስፔይን የሕገ መንግሥት ፍርድ ቤት የከተማ ነዋሪዎችን ፀጥታ ረብሿል ተብሎ በተከሰሰ የሕዝብ መዝናኛ ድርጅት ላይ ባስተላለፈው ብይን የድምፅ ብክለት በጤንነት ላይ ለሚያደርሰው ጉዳት እውቅና ሰጥቷል። ፍርድ ቤቱ ከመጠን ያለፈ “ጫጫታ አንድ ግለሰብ ያለውን የሥነ ምግባር ደንብና አካላዊ ጤንነቱን የመጠበቅ መብት፣ የራሱንና የቤተሰቡን ሰላም እንዲሁም የመኖሪያ ቤቱን ያለመደፈር መብት ይጥሳል” ብሏል። በፍርድ ቤቱ ብይን መሠረት ከባድ ጫጫታ “የማዳመጥ ችሎታ እክል፣ የእንቅልፍ ማጣት፣ የነርቭ መቃወስ፣ ከፍተኛ የደም ግፊትና የግልፍተኝነት ባሕርይ” ሊያስከትል ይችላል።

ወጣት የጦርነት ሰለባዎች

የተባበሩት መንግሥታት የሕፃናት መርጃ ድርጅት፣ በሩዋንዳ በጎሣ ግጭት ሳቢያ ከተገደሉት 800,000 ሰዎች መካከል 300,000 የሚሆኑት ሕፃናት ናቸው የሚል ግምት እንዳለው ላይፕሲገር ፍልክስጻይቱንግ የተባለው የጀርመን ጋዜጣ ዘግቧል። በሩዋንዳ ከ100,000 በላይ የሚሆኑ ልጆች የሚኖሩት የሚያስተዳድራቸው ትልቅ ሰው በሌለበት ቤት ውስጥ ነው። ጋዜጣው “የዕለት ተዕለት ኑሯቸውን እየገፉ ያሉት በጣም ከፍተኛ በሆነ ድህነት እየማቀቁ ነው” ብሏል።

“ፈጣን አእምሮ” ይዞ መኖር

ቶሮንቶ ስታር የተባለው ጋዜጣ “ሁለት ቋንቋ መናገር መቻል በዕድሜ መግፋት ምክንያት የሚመጣውን የአእምሮ መደነዝ ይቀንሳል” ሲል ዘግቧል። የዮርክ ዩኒቨርሲቲ የሥነ አእምሮ ሊቅ የሆኑት ኢለን ባያሊስቶክ ተመሳሳይ የትምህርት ደረጃና የገቢ መጠን ያላቸውን ከ30 እስከ 59 ዓመት ባለው የዕድሜ ክልል ውስጥ በሚገኙ 104 ሰዎችና ከ60 እስከ 88 ዓመት ባለው የዕድሜ ክልል በሚገኙ 50 ሰዎች የአእምሮ አሠራር ላይ ጥናት አካሂደዋል። በሁለቱም ቡድኖች ከሚገኙት ሰዎች ግማሽ የሚሆኑት ሁለት ቋንቋ መናገር የሚችሉ ነበሩ። እያንዳንዱ ሰው ሁለት ተቃራኒ አማራጮች ያሉት አንድ ቀላል ሥራ እንዲሠራ ተጠይቆ ሥራውን ለማከናወን የፈጀበት ጊዜ ይለካል። ጋዜጣው እንደገለጸው “ሁለት ቋንቋ ተናጋሪዎች ከአንድ ቋንቋ ተናጋሪዎች ይበልጥ ፈጣን ሆነው ተገኝተዋል።” ባያሊስቶክ እንደሚሉት ከሆነ ሁለት ቋንቋ ተናጋሪዎች ምንጊዜም ሁለት ምርጫ ስላላቸው መልስ በሚሰጡበት ጊዜ አንጎላቸው ከሁለቱ ቋንቋዎች በየትኛው እንደሚጠቀም መወሰን ይኖርበታል። “ይህ የአእምሮ ጂምናስቲክ ለረዥም ጊዜ ሲቆይ ከዕድሜ መግፋት ጋር የሚመጣውን የአእምሮ ዘገምተኛነትና መደነዝ ይከላከላል።”

ተወዳጅነት ያገኘ መጽሐፍ ቅዱስ?

“ምዕመናን ስለ ሦስተኛው ዓለም የዕዳ ጫና፣ ስለ ፍትሐዊ ንግድና ስለመሳሰሉት ጉዳዮች እንዲያስቡ ለማድረግ ሲባል ከመጽሐፍ ቅዱስ የተውጣጡ ጸሎቶችና መዝሙራት በሚገኙበት የእንግሊዝ ቤተ ክርስቲያን የጸሎት መጽሐፍ ላይ ብዙ ለውጥ ተደርጓል” ሲል ሮይተርስ የተባለው የዜና አገልግሎት ዘግቧል። ዘ ፖኬት ፕሬየርስ ፎር ፒስ ኤንድ ጀስቲስ የተባለው መጽሐፍ በጌታ ጸሎት ላይ የሚገኘውን “የዕለት እንጀራችንን ዛሬ ስጠን” የሚለውን የኢየሱስ ቃል “መሬታችንን መልሰን ስናገኝ ወይም የተሻለ ደመወዝ ማግኘት ስንችል የዕለት እንጀራችንን ሰጠኸን ማለት ነው” በሚል ቃል ለውጦታል። በተመሳሳይ “በሞት ጥላ ሸለቆ ውስጥ፤ ብሄድ እንኳ” የሚለው የመዝሙር 23 ቃል እንዲወጣ ተደርጎ “ድብልቅልቅ ያለ ጠብና ብጥብጥ ቢነሳ እንኳን አልፈራም” በሚል ቃል ተተክቷል። የለውጡ ተቃዋሚዎች አዲሱን ባለ 96 ገጽ መጽሐፍ “አሳሳችና ሃይማኖትን የሚያቃልል” እንዲሁም “አስነዋሪና ከስድብ ተለይቶ የማይታይ” እንዳሉት የለንደኑ ዘ ዴይሊ ቴሌግራፍ ገልጿል።

በኢኮኖሚ ጫና ምክንያት የሚፈጸሙ ውርጃዎች

ብዙዎች ከሚያስቡት በተለየ ሁኔታ “በአውስትራሊያ አብዛኛውን ውርጃ የሚፈጽሙት ከብዙ ወንዶች ጋር የሚወጡ ወጣቶች ሳይሆኑ መካከለኛ ገቢ ያላቸው ያገቡ ሴቶች ናቸው” ሲል ዘ ሲድኒ ሞርኒንግ ሄራልድ ጋዜጣ ዘግቧል። ባሎች ሙሉ ቀን ሥራ ስለሚውሉና ሚስቶችም ቢሆኑ ለተወሰነ ሰዓት ስለሚሠሩ በአብዛኛው ልጅ ላለመውለድ የሚወስኑት በኢኮኖሚ ምክንያት ነው። በአውስትራሊያ ብሔራዊ ዩኒቨርሲቲ የሥነ ሕዝብ ፕሮፌሰር የሆኑት ፒተር ማክዶናልድ “እናት መሆን በአንዲት ሴት የሥራ እድገትና የገቢ መጠን ላይ ለውጥ ያስከትላል” ብለዋል። “ልጅ የሌላቸው ሴቶች የሚያገኙት የገቢ መጠን ከፍተኛ ሲሆን ልጅ ሲወልዱ ግን ያን የሚያክል ገቢ ማግኘት አይችሉም።” ሄራልድ እንደሚለው ከሆነ በአውስትራሊያ ከ3 እርግዝናዎች መካከል አንዱ በውርጃ ይጨናገፋል።

“የልጃችሁን ጓደኞች እወቁ”

በዩናይትድ ስቴትስ “ከጓደኞቻቸው ግማሽ ያህል የሚሆኑት ሩካቤ ሥጋ የሚፈጽሙ እንደሆኑ የተናገሩ በአፍላ ወጣትነት ዕድሜ ላይ የሚገኙ ልጆች ለመስከር ያላቸው ዕድል በ31 እጥፍ፣ ለማጨስ ያላቸው ዕድል 5 ተኩል እጥፍ እንዲሁም ማሪዋና ለመሞከር ያላቸው እድል 22 ተኩል እጥፍ ይጨምራል” ሲል ዘ ኒው ዮርክ ታይምስ ዘግቧል። በኮሎምቢያ ዩኒቨርሲቲ የሱስና ሱስ የሚያስይዙ ቅመሞች ብሔራዊ ማዕከል ባደረገው በዚህ ጥናት 500 ወላጆችና ዕድሜያቸው ከ12 እስከ 17 የሚደርስ 1,000 የሚያክሉ ወጣቶች ተካፍለዋል። የማዕከሉ ሊቀ መንበርና ፕሬዚዳንት የሆኑት ጆሴፍ ካሊፋኖ “ከ12 እስከ 17 ዓመት ባለው የዕድሜ ክልል ውስጥ የሚገኙ ልጆች ያሏቸው ወላጆች ሊያስተውሉት የሚገባ ግልጽ መልእክት አለ፤ ልጃችሁ ከማን ጋር እንደሚቀጣጠርና የት እንደሚውል እወቁ። የልጃችሁን ጓደኞች ለማወቅ ሞክሩ። ገበታ ላይ ስለ ልጆቻቸው ጓደኞችና ሱስ ስለሚያስይዙ ነገሮች አንስተው የሚነጋገሩ ወላጆች ልጆቻቸው ከአደንዛዥ ዕፆች ርቀው እንዲያድጉ የማድረግ ዕድላቸው ከፍተኛ ነው” ብለዋል።

በራሳቸው ላይ ጉዳት የሚያደርሱ ወጣቶች

የለንደኑ ዘ ታይምስ “በራሳቸው ላይ ጉዳት በሚያደርሱ ወጣቶች ብዛት ረገድ ከአውሮፓ የአንደኝነቱን ቦታ የያዘችው ብሪታንያ ነች” ብሏል። በብሪታንያ የአደጋና የድንገተኛ ሕክምና ክፍሎች ሰውነታቸውን እንደ መቁረጥ ባሉ መንገዶች በራሳቸው ላይ ጉዳት በማድረሳቸው ሕክምና የተደረገላቸው ሰዎች በየዓመቱ 150,000 ይደርሳሉ። ችግሩ በብዛት የሚታየው በወጣቶች ዘንድ ነው። “በገዛ ራሳቸው ላይ ጉዳት የሚያደርሱ ወጣት ሴቶች ቁጥር ከወንዶቹ ሰባት እጥፍ ቢበልጥም የወንዶቹ ቁጥር ከ1980ዎቹ ወዲህ በእጥፍ አድጓል” ሲል ዘ ታይምስ ዘግቧል። እነዚህ ግለሰቦች በራሳቸው ላይ ጉዳት የሚያደርሱት “የደረሰባቸውን የስሜት መቃወስ ለመቋቋም ወይም በሚሰማቸው የስሜት ድንዛዜ ተገፋፍተው ነው።” የአእምሮ ጤና በጎ አድራጎት ድርጅት ባልደረባ የሆኑት አንድሩ ማክሎክ እንደሚሉት ይህ አኃዝ “ወጣቶቻችን የተደቀኑባቸው ችግሮች ምን ያህል እየበዙ እንዳሉ ወይም ችግሮቹን የመቋቋም አቅም እያጡ መምጣታቸውን ያመለክታል።”