በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

ወጣቶች በችግር ተተብትበዋል

ወጣቶች በችግር ተተብትበዋል

ወጣቶች በችግር ተተብትበዋል

▪ በዩናይትድ ስቴትስ አንድ የ15 ዓመት ተማሪ በክፍል ጓደኞቹ ላይ ተኩስ ከፍቶ ሁለቱን ሲገድል 13ቱን አቆሰለ።

▪ በሩሲያ የሰከሩ ወጣቶች አንዲት የዘጠኝ ዓመት ልጅ በአሰቃቂ ሁኔታ ሲገድሉ አባቷንና የአጎቷን ልጅ ደግሞ ደበደቡ።

▪ በብሪታንያ አንድ የ17 ዓመት ልጅ በዕድሜ ከእርሱ የሚያንስን ወጣት ከደበደበ በኋላ በጩቤ ወጋው። ይህ ልጅ ለፖሊሶች ቃሉን ሲሰጥ “በመጀመሪያ ልገድለው አላሰብኩም ነበር፤ ደሙን ካየሁ በኋላ ግን ራሴን መቆጣጠር አቃተኝ” ብሏል።

እነዚህን የመሰሉ አስደንጋጭ ድርጊቶች አልፎ አልፎ ብቻ የሚፈጸሙ አይደሉም። በጣት የሚቆጠሩ ጋጠ ወጥ ወጣቶች የሚፈጽሙት ድርጊት ነው ተብሎ በቸልታ የሚታለፍ አይደለም። ፕሮፌሽናል ስኩል ካውንስሊንግ በተባለ መጽሔት ላይ የወጣ አንድ ጽሑፍ “ወጣቶች የሚፈጽሙት ዓመጽ የማኅበረሰባችን ዋነኛ ችግር ሆኗል” ይላል። ይህ አባባል በአኃዛዊ መረጃዎች የተደገፈ ነው።

የዩናይትድ ስቴትስ የትምህርት ስታትስቲክስ ብሔራዊ ማዕከል በአገሪቱ በትምህርት ቤት የሚፈጸሙ ጥቃቶች በመጠኑ እንደቀነሱ ባይክድም “በ2001 ከ12 እስከ 18 ዓመት ባለው የዕድሜ ክልል በሚገኙ ወጣቶች ላይ ትምህርት ቤት ውስጥ እንደ ድብደባ ወይም ስርቆት ያሉ 2 ሚሊዮን የሚያክሉ ለሞት የማያደርሱ ወንጀሎች ተፈጽመውባቸዋል” ሲል ገልጿል። በተጨማሪም በትምህርት ቤቶች የጉልበተኞች ቁጥር እንደጨመረ ተዘግቧል።

ይሁን እንጂ በዩናይትድ ስቴትስ ወጣቶች የሚፈጽሟቸው ጥቃቶች በተማሪዎች ላይ ብቻ የሚሰነዘሩ አይደሉም። ይኸው የመረጃ ምንጭ “ከ1997 እስከ 2001 ባለው የአምስት ዓመት ጊዜ ውስጥ 817,000 ስርቆትንና 473,000 አካላዊም ሆኑ ስሜታዊ ጥቃቶችን ጨምሮ በጠቅላላው 1.3 ሚሊዮን የሚያክሉ ለሞት የማያደርሱ ወንጀሎች በመምህራን ላይ እንደተፈጸሙ” ገልጿል። ከዚህም በላይ “ከአንደኛና ከሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤት መምህራን መካከል 9 በመቶ የሚሆኑት አካላዊ ጥቃት እንደሚፈጽምባቸው ከተማሪ ዛቻ የተሰነዘረባቸው ሲሆን 4 በመቶ የሚሆኑ ደግሞ ተደብድበዋል።”

በሌሎች አገሮች ያለው ሁኔታስ ምን ይመስላል? አንድ የዜና አገልግሎት “በ2003 ቻይና 69,780 የሚያክሉ ወጣት ጥፋተኞችን ያሰረች ሲሆን ይህ አኃዝ በ2002 ከነበረው የ12.7 በመቶ ጭማሪ አሳይቷል” ሲል ገልጿል። “ከወጣት ጥፋተኞቹ መካከል 70 በመቶ የሚሆኑት በቡድን የተደራጁ ወመኔዎች ናቸው።” በተመሳሳይ ከጃፓን የተገኘ የ2003 ሪፖርት ባለፉት አሥር ዓመታት ከተፈጸሙት ወንጀሎች መካከል ግማሽ ያህሉ በወጣቶች የተፈጸሙ እንደሆኑ ይገልጻል።

አደገኛ ዕፅ—በወጣቶች ለጋ ሰውነት ላይ የሚፈጸም ጥቃት

በርካታ ወጣቶች በራሳቸው ሰውነት ላይ የሚፈጽሙት ጥቃት ሌላው ችግር ነው። የዩናይትድ ስቴትስ ብሔራዊ የዕፅ መቆጣጠሪያ ተቋም ያወጣው ሪፖርት በአገሪቱ ከሚኖሩ በአፍላ የጉርምስና ዕድሜ ላይ ከሚገኙ ወጣቶች መካከል ግማሽ ያህል የሚሆኑት የሁለተኛ ደረጃ ትምህርታቸውን ከመጨረሳቸው በፊት በሕግ የተከለከለ ዕፅ ወስደው የሚያውቁ መሆናቸውን ገልጿል። ይኸው ሪፖርት በማከል እንዲህ ብሏል:- “በዘመናችን ባሉ ወጣቶች ዘንድ አልኮል መውሰድ በጣም ተስፋፍቶ ይገኛል። ከአምስት ተማሪዎች መካከል አራቱ (77%) የሁለተኛ ደረጃ ትምህርታቸውን ከመጨረሳቸው በፊት አልኮል ጠጥተው የሚያውቁ ሲሆን ግማሽ ያህል (46%) የሚሆኑት ደግሞ 8ኛ ክፍል ከመጨረሳቸው በፊት ይጠጣሉ።”

ልቅ የጾታ ግንኙነት

ኤድስ በተስፋፋበት በዚህ ዘመን ልቅ የጾታ ግንኙነት አደገኛ መሆኑ አያጠያይቅም። ይሁን እንጂ በርካታ ወጣቶች ወሲብን የሚመለከቱት ምንም ጉዳት እንደማያስከትል ተራ ጨዋታ አድርገው ነው። ለምሳሌ በአሜሪካ የሚኖሩ አንዳንድ ወጣቶች በአጋጣሚ ስለሚፈጸም የጾታ ግንኙነት ሲናገሩ “አብሮ መውጣት” ይላሉ። እንዲህ ያለው አነጋገር ወሲብ ተራ ግንኙነት እንደሆነ ያስመስላል። አንዳንድ ወጣቶች ጓደኝነታቸው በቋሚነት አብሮ ከመውጣት ያለፈ እንዳልሆነ ይናገራሉ።

ስኮት ዎልተር የተባሉት ደራሲ ከከተማ ወጣ ብለው የሚኖሩ ወጣቶች ወላጆቻቸው ከሥራ ከመመለሳቸው በፊት ስለሚያዘጋጅዋቸው የጾታ ብልግና የሚፈጸምባቸው ቅጥ ያጡ ፓርቲዎች ገልጸዋል። እንዲህ ባለው አንድ ፓርቲ ላይ አንዲት ወጣት “እዚያ ካሉት ወንዶች ጋር በሙሉ የጾታ ግንኙነት መፈጸም እንደምትፈልግ ተናግራለች። . . . የ12 ዓመት ልጆች ሳይቀሩ እንደነዚህ ባሉት ፓርቲዎች ላይ ይገኛሉ።”

በጣም የሚያስደነግጥ ነገር አይደለም? የወጣቶችን የወሲብ ባሕርይ ለሚያጠኑ ተመራማሪዎች ግን ይህ አስደንጋጭ አይደለም። ዶክተር አንድሪያ ፔኒንግተን “ባለፉት 20 ዓመታት ወጣቶች ወሲባዊ ድርጊቶችን የሚፈጽሙበት ዕድሜ እየቀነሰ ሲመጣ ተመልክተናል። ገና በ12 ዓመት ዕድሜያቸው ወሲብ የሚፈጽሙ ወንድና ሴት ልጆችን ማግኘት እንግዳ ነገር መሆኑ ቀርቷል” ሲሉ ጽፈዋል።

በተለይ ዩ ኤስ ኤ ቱዴይ በተባለው ጋዜጣ ላይ የወጣው ሪፖርት በጣም አሳዛኝ ነው። “የአፍ ወሲብ የሚፈጽሙ ታዳጊ ወጣቶች ቁጥር በአገሪቱ በጣም እየጨመረ መጥቷል። . . . ‘እንዲህ ያለው ድርጊት ከወሲብ እንደማይቆጠር’ ወጣቶች ራሳቸውን አሳምነዋል።” በ10,000 ወጣት ሴቶች ላይ በተደረገ አንድ ጥናት “ሰማንያ በመቶ የሚሆኑት ድንግል እንደሆኑ ቢናገሩም ከእነዚህ መካከል 25 በመቶ የሚሆኑት ግን የአፍ ወሲብ ፈጽመዋል። ሃያ ሰባት በመቶ የሚሆኑት እንዲህ ያለው ድርጊት ‘ከአንድ ወንድ ጋር እንደ ጨዋታ የሚፈጸም ነገር’ እንደሆነ ተናግረዋል።”

እንዲህ ያለው አመለካከት በሌሎች አካባቢዎችም ተስፋፍቷል። ዩኔስኮ “ብዙ የእስያ ወጣቶች የጾታ ግንኙነት መፈጸም የሚጀምሩበት ዕድሜ እያነሰ በመሄዱ ገደብ የለሽ ወሲብ በመፈጸም ምክንያት ለኤች አይ ቪ የሚጋለጡ ወጣቶች ቁጥር በጣም እየጨመረ መጥቷል” የሚል ሪፖርት አውጥቷል። ሪፖርቱ በማከል “በአፍላ የጉርምስና ዕድሜ የሚገኙ ወጣቶች ከጋብቻ በፊት፣ አብዛኛውን ጊዜ ከተለያዩ ሰዎች ጋር ሩካቤ ሥጋ በመፈጸም የወላጆቻቸውን ‘ባሕላዊ የሥነ ምግባር እሴቶች’ አሽቀንጥረው ጥለዋል” ይላል።

ወጣቶች በችግር ተተብትበው መያዛቸውን የሚያሳይ ምን ሌላ ምልክት ይኖራል? የካናዳው ውመንስ ኸልዝ ዊክሊ “ከ16 እስከ 19 ዓመት ባለው የዕድሜ ክልል ከሚገኙ ሴት ልጆች መካከል 25 በመቶ የሚሆኑት ቢያንስ አንድ ጊዜ ከፍተኛ የመንፈስ ጭንቀት ያጋጥማቸዋል” ብሏል። ይሁን እንጂ የመንፈስ ጭንቀት ሴቶችን ብቻ ለይቶ የሚያጠቃ ሕመም አይደለም። ዩ ኤስ ኒውስ ኤንድ ወርልድ ሪፖርት እንደሚለው ከሆነ በየዓመቱ በዩናይትድ ስቴትስ ብቻ አምስት ሺህ የሚያክሉ ወጣቶች ራሳቸውን ይገድላሉ። ምክንያቱ የታወቀ ባይሆንም “ራሳቸውን የሚገድሉ ወንዶች ቁጥር ከሴቶች በስድስት እጥፍ ይበልጣል።”

በዛሬው ጊዜ ያለው ወጣት ትውልድ በችግር አረንቋ ውስጥ የተዘፈቀ ለመሆኑ ምንም አያጠራጥርም። የዚህ ሁሉ ችግር መንስኤ ምንድን ነው?

[በገጽ 3 ላይ የሚገኝ የሥዕል ምንጭ]

STR/AFP/Getty Images