የተጫዋችነት ባሕርይን በማዳበር ሕመምን መቋቋም
የተጫዋችነት ባሕርይን በማዳበር ሕመምን መቋቋም
በስፔይን የሚገኘው የንቁ! ዘጋቢ እንደጻፈው
ኮንቺ ከካንሰር በሽታ ጋር ለሰባት ዓመታት ስትታገል የቆየች በመካከለኛ ዕድሜ ላይ የምትገኝ ፍልቅልቅ ሴት ነች። ተመርምራ የጡት ካንሰር እንዳለባት ካወቀችበት ጊዜ አንስቶ በሽታው እንዳይሰራጭ ለማገድ ሰባት ጊዜ ቀዶ ሕክምና ማድረግ አስፈልጓታል። ይህን ሁሉ ልትቋቋም የቻለችው እንዴት ነው?
ኮንቺ እንዲህ በማለት ተናግራለች:- “ዶክተሮቹ ቀዶ ሕክምና እንደሚያስፈልገኝ ባረዱኝ ቁጥር አልቅሽ አልቅሽ ካለኝ ሐዘኔ እስኪወጣልኝ ድረስ ስቅስቅ ብዬ አለቅሳለሁ። ከዚያም ወደ ወትሮው እንቅስቃሴዬ በመመለስ የሚያስደስቱኝን ነገሮች ለማድረግ እጥራለሁ። ከእነዚህም ውስጥ ቻይንኛ መማር፣ በአውራጃ ስብሰባዎች ላይ መገኘት እንዲሁም ከቤተሰቦቼና ከጓደኞቼ ጋር ለሽርሽር ወጣ ማለት ይገኙበታል። ኢየሱስ ‘ከእናንተ መካከል ተጨንቆ በዕድሜው ላይ አንዲት ሰዓት መጨመር የሚችል አለን?’ ሲል የተናገራቸውን ቃላት መቼም ቢሆን አልረሳቸውም።”—ማቴዎስ 6:27
አክላም “ሁልጊዜ ተጫዋች ለመሆን እጥራለሁ። ከዶክተሮቹ ጋር እንቀላለዳለን፣ አስቂኝ ፊልሞችን እመለከታለሁ ከዚህም በላይ ከወዳጅ ዘመዶቼ ጋር ዘወትር እገናኛለሁ። አብረዋችሁ የሚስቁ ወዳጆችን ማግኘት ፍቱን መድኃኒት ነው። አንድ ቀን ወደ ቀዶ ሕክምና ክፍል ከመግባቴ በፊት አንዳንድ ጓደኞቼና ዘመዶቼ በዋዜማው ምሽት ያጋጠማቸውን አንድ አስቂኝ ሁኔታ አወጉኝ። በጣም ከመሳቄ የተነሳ ዘና ያለ ስሜት ኖሮኝ ወደ ቀዶ ሕክምና ክፍሉ ገባሁ።”
የተጫዋችነት ባሕርይና አዎንታዊ አመለካከት ማዳበር የጤና ችግሮችን ለመቋቋም እገዛ ሊያበረክት እንደሚችል ለመገንዘብ ኮንቺ የመጀመሪያዋ አይደለችም። ዘመናዊው ሕክምና ተጫዋች መሆን ሕመምንና በሽታን ለመቋቋም ለምናደርገው ትግል ጠቃሚ ድርሻ እንደሚያበረክት ከተገነዘበ ሰንበትበት ብሏል።
ለሰውነትና ለአእምሮ ጤንነት ይጠቅማል
ከላይ የተጠቀሰው አስተሳሰብ አዲስ አይደለም። ንጉሥ ሰሎሞን ከዛሬ 3,000 ዓመት በፊት “ደስተኛ ልብ ጥሩ መድኀኒት ነው” ሲል ጽፎ ነበር። (ምሳሌ 17:22) በተመሳሳይም በ17ኛው ክፍለ ዘመን ይኖር የነበረው ስፔናዊው ደራሲ ሎፕ ደ ቪጋ “ጨዋነት የተላበሱ ቀልዶችን ብንናገር ጤናሞች ሆነን መኖር የምንችል ይመስለኛል” ሲል ጽፏል። ሆኖም አሁን ባለው ውጥረት በተሞላ ዓለም ውስጥ ሰዎች ተጫዋችና ቀልደኛ ከመሆን ይልቅ ዝም ማለት የመረጡ ይመስላል። የምንኖረው ቴክኖሎጂው እጅግ በመጠቀበት ዘመን ውስጥ ሲሆን የተጫዋችነት መንፈስ ደግሞ እየጠፋ መጥቷል። ኤል አርቲ ደ ላ ሪሳ (የሳቅ ጥበብ) የተባለ አንድ የጽሑፍ ሥራ፣ በዘመናዊው ኅብረተሰብ ውስጥ “ሆሞ ሳፒየንስ (ዘመናዊው ሰው) በሆሞ ዲጅታልስ (በኮምፒውተራዊ የሰው ምሥሎች) የተተካ” ይመስላል በማለት ይገልጻል። አንዳንድ ጊዜ ኮምፒውተር ሳቅንና ፈገግታን የመሳሰሉ ባሕርያትን የተካ ይመስላል።
የታመሙ ሰዎች ተጫዋችና ቀልደኛ መሆናቸው ይበልጥ አዎንታዊ የሆነ አስተሳሰብ፣ ስሜትና ባሕርይ እንዲኖራቸው ይረዳቸዋል። የካንሰርና የማስታገሻ መድኃኒቶች ስፔሻሊስት የሆኑት ዶክተር ሂማ ሳንስ-ኦርትስ በቅርብ ባወጡት አንድ ጽሑፍ ላይ እንደገለጹት ተጫዋች መሆን “የመግባባት ችሎታን ይጨምራል፣ የሰውነትን በሽታ የመከላከል አቅም ያጐለብታል፣ ሕመምን ያስታግሳል፣ ጭንቀትን ያስወግዳል፣ የአእምሮንና የጡንቻን ውጥረት ይቀንሳል እንዲሁም የፈጠራ ችሎታን ለማዳበርና ብሩህ ተስፋ ለመያዝ ያስችላል።”
ተጫዋች መሆን ያለው ትልቅ ጠቀሜታ
ቀልደኛ ወይም ተጫዋች መሆን የመፈወስ ኃይል አለው የሚባለው ለምንድን ነው? በጣም አስቸጋሪ ሁኔታ ውስጥ በምንሆንበት ጊዜም እንኳ ነገሮችን አዎንታዊ በሆነ መንገድ እንድንመለከት ስለሚረዳን ነው። ሳንስ-ኦርትስ “በዕለት ተዕለት ሕይወታችን ውስጥ ተጫዋችና ሳቂታ በመሆን ኃይላችንን ማደስ፣ ድካማችንን ማስታገስና ትካዜያችንን ማስወገድ እንችላለን” በማለት ተናግረዋል።
ፈገግ እንድንል ወይም እንድንስቅ የሚያደርጉን ነገሮች እንደየሰዉና እንደየባሕሉ እንደሚለያዩ ግልጽ ነው። ሳንስ-ኦርትስ ሁኔታውን “ውበት እንደ ተመልካቹ እንደሆነ ሁሉ ቀልድም እንዲሁ ነው” በማለት ይገልጻሉ። አስተዳደጋችን ወይም የትምህርት ደረጃችን ምንም ይሁን ምን ተጫዋች መሆናችን ከሌሎች ጋር ለመግባባት እንዲሁም የሚሰማንን ከፍተኛ የመረበሽ፣ የውጥረት ወይም የስጋት ስሜት ለማስወገድ ያስችለናል። ታዲያ ይህን ያህል የሚጠቅመን ከሆነ የተጫዋችነትን ባሕርይ ማዳበር የምንችለው እንዴት ነው?
ልንወስደው የምንችለው የመጀመሪያው እርምጃ፣ በችግራችን ወይም በሕመማችን ላይ ብቻ ማተኮራችንን አቁመን እያንዳንዱ አጋጣሚ ባለው አዎንታዊ ጎን ለመደሰት መሞከር ነው። በተጨማሪም ችግሮቻችንን አጋነን እንድንመለከት የሚያደርጉ የተዛቡ ወይም ሚዛናዊነት የጎደላቸው አመለካከቶችን አስወግደን ምክንያታዊ አስተሳሰብ ለማዳበር ብርቱ ጥረት ማድረግ ይኖርብናል። አንድን ሁኔታ በተለየ መንገድ ለመመልከት በመጣርም የተጫዋችነትን ባሕርይ ማዳበር እንችላለን። ሁልጊዜ ሳቂታዎች ወይም ፈገግታ የማይለየን ላንሆን እንችላለን፤ ሆኖም የአንድን ሁኔታ አስቂኝ ጎን ማየታችን ችግሮችን ለመቋቋም ይረዳናል። ሳንስ-ኦርትስ “ቀልድ ወይም ጨዋታ የሚያሳስበንን ችግር ለጊዜው ቸል ብለን ሁኔታውን ከተለየ አቅጣጫ እንድንመለከትና . . . አዳዲስ የመፍትሄ ሐሳቦችን በማፍለቅ በተሳካ ሁኔታ ችግሩን እንድንወጣ ያስችለናል” በማለት አብራርተዋል።
ቀልደኛ የመሆን ወይም የተጫዋችነት ባሕርይ በሕይወታችን ውስጥ ለሚያጋጥሙን ችግሮች ሁሉ መፍትሄ ነው ማለት አይደለም፤ ያም ሆኖ ግን ችግሮችን ይበልጥ አዎንታዊ አመለካከት ይዘን ምክንያታዊ በሆነ መንገድ እንድንጋፈጥ ይረዳናል። ኮንቺ “መታመም ቀልድ አይደለም፤ ሆኖም ምንጊዜም ተጫዋች ለመሆን ጥረት ማድረግ አለባችሁ። ሕይወቴን በተለያዩ አትክልቶች የተሞላ አንድ የአትክልት ቦታ እንደሆነ አድርጌ እመለከተዋለሁ፤ የሚያሳዝነው ከእነዚህ አትክልቶች አንዱ በሽታዬ ነው። ሆኖም ይህ አትክልት ማለትም ያለብኝ የካንሰር ሕመም ሌሎቹን እንዳይበክል ጥንቃቄ አደርጋለሁ። እርግጥ ነው ያለብኝን የካንሰር በሽታ ሙሉ ለሙሉ አሸንፌዋለሁ ማለት ባልችልም አሁንም ቢሆን በሕይወቴ ደስተኛ ነኝ፤ በጣም አስፈላጊው ነገር ደግሞ ይህ ነው።”
[በገጽ 27 ላይ የሚገኝ ሥዕል]
ኮንቺ ከባለቤቷ ከፊልክስና ከታናሽ እህቷ ከፓይላይ ማበረታቻ ታገኛለች