በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

የዛሬዎቹ ወጣቶች የሚያጋጥሟቸው ጫናዎች

የዛሬዎቹ ወጣቶች የሚያጋጥሟቸው ጫናዎች

የዛሬዎቹ ወጣቶች የሚያጋጥሟቸው ጫናዎች

የጉርምስና ዕድሜ ሁሉ ነገር በተደላደለበት ሁኔታ እንኳን ብዙ ችግሮች የሚፈራረቁበት ወቅት ነው። ወጣቶች ወደ ጉርምስና ዕድሜ ሲጠጉ ቀድሞ የማያውቋቸው ስሜቶች ያስጨንቋቸዋል። ነጋ ጠባ ከመምህሮቻቸውና ከእኩዮቻቸው ጫና ይደርስባቸዋል። ቴሌቪዥን፣ ፊልሞች፣ የሙዚቃው ኢንዱስትሪና ኢንተርኔት ለሚያሳድሩባቸው የማያባራ ተጽዕኖ የተጋለጡ ናቸው። በዚህም ምክንያት አንድ የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ሪፖርት ጉርምስና “በአብዛኛው በውጥረትና በጭንቀት ተለይቶ የሚታወቅ የሽግግር ወቅት” እንደሆነ ገልጿል።

አብዛኛውን ጊዜ ወጣቶች የሚያጋጥማቸውን ውጥረትና ጭንቀት በአግባቡ ለመወጣት የሚያስችል ብስለትና ተሞክሮ በጣም የሚጎድላቸው መሆኑ ያሳዝናል። (ምሳሌ 1:4) ትክክለኛ አመራር ካላገኙ ጉዳት በሚያስከትል ልማድ በቀላሉ ይጠመዳሉ። ለምሳሌ ከላይ የተጠቀሰው የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ሪፖርት “አደንዛዥ ዕፅ መውሰድ የሚጀመረው አብዛኛውን ጊዜ በጉርምስና ዕድሜ እንደሆነ ጥናቶች ያመለክታሉ” ብሏል። እንደ ጠበኝነትና ልቅ ወሲብ ስላሉት አጓጉል ድርጊቶችም ተመሳሳይ ነገር መናገር ይቻላል።

እንደነዚህ ያሉት ሁኔታዎች “ዝቅተኛ ኑሮ ባላቸው” ወይም በአንዳንድ ዘሮች ላይ ብቻ የሚደርሱ ናቸው ብለው ችግሩን ገሸሽ የሚያደርጉ ወላጆች በእጅጉ ተሳስተዋል። በዛሬው ጊዜ ወጣቶችን የሚያጋጥሙ ችግሮች በኢኮኖሚ፣ በማኅበራዊና በዘር ድንበሮች የተገደቡ አይደሉም። ስኮት ዎልተር የተባሉት ደራሲ “‘ወጣት ወንጀለኛ’ የሚባለው ከተናቀ የኅብረተሰቡ ክፍል የመጣ፣ መጥፎ ሠፈር ውስጥ ያደገና በመንግሥት እርዳታ የምትተዳደር ምስኪን እናት ያለችው የ17 ዓመት ወንድ ልጅ ነው ብለህ የምታስብ ከሆነ በጣም ኋላቀር ሆነሃል ማለት ነው” ሲሉ ጽፈዋል። “የዛሬው ወጣት ወንጀለኛ ፈረንጅ አሊያም መካከለኛ ወይም ከፍተኛ የኑሮ ደረጃ ካለው ቤተሰብ የመጣ፣ ከ16 ዓመት በጣም ያነሰ ዕድሜ ያለው እንዲሁም ወንድ ወይም ሴት ሊሆን ይችላል።”

ይሁን እንጂ በርካታ ወጣቶች ለአደጋ የተጋለጡት ለምንድን ነው? በቀደሙት ትውልዶች ውስጥ የነበሩ ወጣቶችም ችግሮችና ፈተናዎች ያጋጥሟቸው አልነበረም? አዎ፣ ያጋጥሟቸው ነበር። ይሁን እንጂ እኛ የምንኖረው መጽሐፍ ቅዱስ “የሚያስጨንቅ ጊዜ” ብሎ በሚጠራው ዘመን ነው። (2 ጢሞቴዎስ 3:1-5) በወጣቶች ላይ ተጽዕኖ የሚያሳድሩ በዚህ የታሪክ ዘመን ብቻ የተከሰቱ ሁኔታዎችና ጫናዎች አሉ። እስቲ አንዳንዶቹን እንመርምር።

በቤተሰብ ኑሮ ውስጥ የታዩ ለውጦች

ለምሳሌ የቤተሰብ ኑሮ ገጽታ እንዴት እንደተለወጠ እንመልከት። ጆርናል ኦቭ ኢንስትራክሽናል ሳይኮሎጂ “በአሜሪካ ከሚኖሩ ልጆች መካከል ከሲሶ የሚበልጡት ገና 18 ዓመት ሳይሞላቸው ወላጆቻቸው ይፋታሉ” ብሏል። ከሌሎች ምዕራባውያን አገሮችም ተመሳሳይ አኃዛዊ መረጃዎች መጥቀስ ይቻላል። ወጣቶች የወላጆቻቸው የጋብቻ ሰንሰለት ሲበጠስ የሚሰማቸውን ከፍተኛ የስሜት ቁስል ለመቋቋም ይገደዳሉ። መጽሔቱ በመቀጠል እንዳለው “በጥቅሉ ሲታይ በቅርብ ጊዜ የቤተሰብ መፍረስ የደረሰባቸው ልጆች፣ ጠንካራ ቤተሰብ ካላቸው አሊያም ረዘም ላለ ጊዜ በአንድ ወላጅ በሚተዳደር ወይም እንጀራ ወላጅ ባለበት ቤተሰብ ውስጥ ካደጉ ልጆች በበለጠ በትምህርት ቤት የሚጠበቅባቸውን ውጤት በማምጣትና ከሌሎች ጋር ተግባብቶ በመኖር ረገድ ችግር ያጋጥማቸዋል። . . . በተጨማሪም የወላጆች ፍቺ በልጁ የባሕርይ እድገትና በራስ የመተማመን ስሜት ላይ ጉዳት ያደርሳል።”

በተጨማሪም ወደ ሥራ ዓለም የሚገቡ ሴቶች ቁጥር እያደገ መምጣቱ በቤተሰብ ሁኔታ ላይ ለውጥ አስከትሏል። በጃፓን በወጣት ወንጀለኞች ላይ የተደረገ አንድ ጥናት በሁለት ወላጆች ገቢ የሚተዳደሩ ቤተሰቦች አንደኛው ወላጅ ቤት ከሚውልባቸው ቤተሰቦች በበለጠ ልጆችን በአግባቡ የማሳደግ ችግር እንደሚያጋጥማቸው ገልጿል።

ብዙ ቤተሰቦች በሁለት ሰው ገቢ ካልተደጎሙ ኑሯቸውን ማሸነፍ እንደሚያቅታቸው የሚካድ ነገር አይደለም። በተጨማሪም ሁለቱም ወላጆች ገቢ የሚያመጡ ከሆነ ልጆች ተንደላቅቀው ሊያድጉ ይችላሉ። ይሁን እንጂ ይህ መጥፎ ጎንም አለው። በሚሊዮን የሚቆጠሩ ልጆች ከትምህርት ቤት ሲመለሱ የሚጠብቃቸው ወና ቤት ነው። ወላጆች ከሥራ የሚመለሱት አብዛኛውን ጊዜ ተዳክመውና በሥራ ቦታ ባጋጠሟቸው ችግሮች ተውጠው ነው። ታዲያ ይህ ምን ያስከትላል? ብዙ ወጣቶች የወላጆቻቸውን ክትትልና እንክብካቤ በበቂ መጠን ሳያገኙ ያድጋሉ። አንድ ወጣት “ቤተሰባችን አብሮ ጊዜ አያሳልፍም” ሲል አማሯል።

ብዙ ታዛቢዎች ይህ አዝማሚያ ለወጣቶች የወደፊት ሕይወት የሚበጅ እንዳልሆነ ይሰማቸዋል። ዶክተር ሮበርት ሾው “ባለፉት 30 ዓመታት እየተስፋፋ የመጣው የልጆች አስተዳደግ ከቤተሰባቸው ጋር ቅርርብ የሌላቸው፣ ድብቅ የሆኑ፣ የመማር ችሎታቸው ደካማ የሆነና ለመቆጣጠር የሚያስቸግሩ ልጆች እንዲበዙ አድርጓል” ብለዋል። “ወላጆች ከልጆቻቸው ጋር ጠንካራ የስሜት መተሳሰር እንዲፈጠር የሚረዱ ነገሮችን ለማድረግ ፋታ እስኪያጡ ድረስ ሥራቸው ላይ ብዙ ጊዜ እንዲያጠፉና ብዙ ገንዘብ እንዲያወጡ የሚገፋፋቸው ፍቅረ ንዋይ የተጠናወተው ማኅበረሰብ በጫነባቸው የባርነት ቀንበር ውስጥ ወድቀዋል።”

በወጣት ልጆች ደኅንነት ላይ የተጋረጠው ሌላ አደጋ ደግሞ ወላጆቻቸው ሥራ ስለሚውሉ ልጆች አብዛኛውን ጊዜ አለተቆጣጣሪ የሚያሳልፉት ሰፊ ጊዜ ያላቸው መሆኑ ነው። በቂ የወላጅ ቁጥጥር አለማግኘት ችግር ይጋብዛል።

ተግሣጽን በተመለከተ ያለው አመለካከት መለወጥ

በተጨማሪም ወላጆች ለልጆቻቸው ስለሚሰጡት ተግሣጽና ቁጥጥር የነበረው አመለካከት እየተለወጠ መምጣቱ በዛሬዎቹ ወጣቶች ላይ ተጽዕኖ አሳድሯል። ዶክተር ሮን ታፈል በግልጽ እንደተናገሩት ብዙ ወላጆች “ሥልጣናቸውን ለሌላ አስረክበዋል።” እንዲህ በሚሆንበት ጊዜ ልጆች ጥሩ ጠባይ እንዲያዳብሩ የሚያስችላቸው ደንብ ወይም መመሪያ ሳያገኙ ያድጋሉ።

በአንዳንድ ሁኔታዎች ወላጆች ራሳቸው በልጅነታቸው የደረሰባቸው መጥፎ ነገር ተጽዕኖ ያሳደረባቸው ይመስላል። የልጆቻቸው ተቆጣጣሪ ሳይሆን የእነሱ ጓደኛ መሆን ይፈልጋሉ። አንዲት እናት “በጣም ልል ነበርኩ” ብላለች። “የእኔ ወላጆች በጣም ጥብቅ ነበሩ። ልጄን እኔ ካደኩበት በተለየ መንገድ ለማሳደግ ፈለግሁ። እንዲህ ማድረጌ ግን ስህተት ነበር።”

አንዳንድ ወላጆች በዚህ ረገድ ምን እስከማድረግ ይደርሳሉ? ዩ ኤስ ኤ ቱዴይ እንዲህ ይላል:- “በኒው ዮርክ፣ በቴክሳስ፣ በፍሎሪዳና በካሊፎርኒያ ከዕፅ ሱሰኝነት እንዲላቀቁ ሕክምና በሚደረግላቸው 600 ወጣቶች ላይ የተደረገ አንድ ጥናት 20 በመቶ የሚሆኑት ልጆች አደገኛ ዕፅ ከወላጆቻቸው ጋር ተጋርተው እንደወሰዱና 5 በመቶ የሚሆኑትን ደግሞ ለመጀመሪያ ጊዜ አደገኛ ዕፅ (አብዛኛውን ጊዜ ማሪዋና) ያቀመሷቸው ወላጆቻቸው እንደሆኑ አሳይቷል።” አንድ ወላጅ እንዲህ ያለውን ኃላፊነት የጎደለው ድርጊት እንዲፈጽም የሚያነሳሳው ምንድን ነው? አንዲት እናት “በቅርብ ልከታተላት በምችልበት በገዛ ቤቴ ብታደርገው እንደሚሻለኝ ነግሬያታለሁ” ብላለች። ሌሎች ደግሞ አብረው ዕፅ መውሰዳቸው ከልጆቻቸው ጋር “ጠንካራ ትስስር” የሚፈጥሩበት አንድ መንገድ ይመስላቸዋል።

ከመገናኛ ብዙኃን የሚደርስባቸው ውርጅብኝ

ከዚህ ሌላ መገናኛ ብዙኃን የሚያሳድሩት ከባድ ተጽዕኖም አለ። ማሪታ ሞል የተባሉ አንድ ተመራማሪ እንደተናገሩት በዩናይትድ ስቴትስ ወጣቶች በአማካይ በቀን አራት ሰዓት ከ48 ደቂቃ ቴሌቪዥን ወይም ኮምፒውተር ላይ ተደቅነው እንደሚያሳልፉ አንድ ጥናት አሳይቷል።

ታዲያ ይህን ማድረጋቸው ምን ጉዳት አለው? ሳይንስ በተባለ መጽሔት ላይ ታትሞ የወጣ አንድ ርዕስ የአሜሪካ የሕክምና ማኅበርን ጨምሮ “ስድስት ታላላቅ የሞያ ማኅበራት በአንዳንድ ልጆች ላይ የሚታየው የጠበኝነትና የኃይለኝነት ባሕርይ” በመገናኛ ብዙኃን ከሚተላለፈው የዓመጽ ድርጊት ጋር ቀጥተኛ ተዛምዶ እንዳለው በአንድ ቃል መስማማታቸውን ዘግቧል። ይኸው መጽሔት “በዚህ ረገድ የመስኩ ባለሙያዎች ያላቸው ግንዛቤ አንድ ዓይነት ቢሆንም ተራው ሕዝብ ግን በመገናኛ ብዙኃን የሚታየው የዓመጽ ድርጊት ማኅበረሰቡን ይበልጥ ጠበኛና ዓመጸኛ እያደረገው እንዳለ ለሚያስገነዝበው ማስጠንቀቂያ ጆሮ የሰጠ አይመስልም” ይላል።

ለምሳሌ የሙዚቃ ፊልሞችን ወይም ክሊፖችን እንውሰድ። ወላጆች አንዳንዶቹ የሙዚቃ ፊልሞች ምን ያህል ወሲባዊ ድርጊቶችን በገሃድ እንደሚያሳዩ ሲመለከቱ ይደነግጣሉ። ታዲያ እንዲህ ያሉት ክሊፖች በወጣቶች ባሕርይ ላይ ተጽዕኖ ያሳድራሉ? አምስት መቶ በሚያክሉ የኮሌጅ ተማሪዎች ላይ የተደረገ አንድ ጥናት እንዳመለከተው “ለጠብ የሚያነሳሱ የሙዚቃ ስንኞች የጠበኝነት ሐሳብና ስሜት እንደሚቀሰቅሱ አረጋግጧል።” አንድ በቅርቡ የተደረገ ሌላ ጥናት እንዳመለከተው “በቡድን የተደራጁ ወረበሎችን ቋንቋ የሚጠቀሙና ወሲብና ዓመጽ የሚያሳዩ የራፕ ሙዚቃ የቪዲዮ ፊልሞችን የሚያዘወትሩ ወጣቶች እነዚህኑ ባሕርያት በተግባር የመፈጸማቸው አጋጣሚ በጣም ከፍተኛ ነው።” በአምስት መቶ ሴት ልጆች ላይ የተደረገው ይህ ጥናት ‘ጋንግስታ’ የሚባሉትን እንዲህ ዓይነት የራፕ ሙዚቃ ፊልሞችን በብዛት የሚመለከቱ ልጆች መምህራቸውን የመማታት፣ የመታሰርና በርካታ የወሲብ ጓደኛ የመያዝ ዕድላቸው ከፍተኛ እንደሆነ አመልክቷል።

ወጣቶችና ኮምፒውተር

ከቅርብ ዓመታት ወዲህ የወጣቶችን አእምሮ በመቅረጽ ረገድ ከፍተኛ ቦታ እየያዘ የመጣው ሌላ ነገር ኮምፒውተር ነው። ፔድያትሪክስ የተባለው መጽሔት እንዲህ ብሏል:- “ከቅርብ ዓመታት ወዲህ የግል መጠቀሚያ የሆኑ ኮምፒውተሮች በበርካታ ቤቶች ውስጥ ይገኛሉ። በዩናይትድ ስቴትስ ከ6 እስከ 17 ዓመት ዕድሜ ያላቸው ልጆች ከሚኖሩባቸው ቤቶች መካከል ሁለት ሦስተኛ የሚሆኑት ኮምፒውተር አላቸው። . . . በቤታቸው ኮምፒውተር ያላቸው ከ3 እስከ 17 ባለው የዕድሜ ክልል ውስጥ የሚገኙ ልጆች ብዛት በ1998 ከነበረው 55 በመቶ አድጎ በ2000 65 በመቶ ደርሷል።” በሌሎች አገሮችም የኮምፒውተር ተጠቃሚዎች ቁጥር አድጓል።

ይሁን እንጂ አንድ ወጣት የኮምፒውተር ተጠቃሚ ለመሆን የግድ እቤቱ ኮምፒውተር እንዲኖረው አያስፈልግም። ስለሆነም አንድ ተመራማሪ “ከአምስት እስከ አሥራ ሰባት ዓመት የዕድሜ ክልል ውስጥ ከሚገኙ ወጣቶች መካከል 90 በመቶ የሚሆኑት የኮምፒውተር ተጠቃሚዎች ሲሆኑ ከእነዚህ መካከል 59 በመቶ የሚሆኑት ደግሞ የኢንተርኔት ተጠቃሚዎች እንደሆኑ” ተናግረዋል። በዚህ ምክንያት ወጣቶች በየትኛውም ዘመን ታይቶ በማይታወቅ መጠን በጣም ብዙ መረጃ የማግኘት አጋጣሚ ተከፍቶላቸዋል። ኃላፊነት ባልጎደለው ሁኔታና በቂ የወላጅ ቁጥጥር እየተደረገበት የሚጠቀሙበት ከሆነ ይህ በራሱ ጥሩ አጋጣሚ ነበር። ይሁን እንጂ በጣም ብዙ ወላጆች ልጆቻቸው አለምንም ገደብ ኮምፒውተር እንዲጠቀሙ ፈቅደዋል።

የኢንተርኔት አጠቃቀምን በተመለከተ በ2001 በተደረገ ጥናት ላይ ተመሥርተው ማሪታ ሞል የተባሉት ተመራማሪ ይህን ሲያረጋግጡ “71 በመቶ የሚሆኑ ወላጆች ስለ ልጃቸው የኢንተርኔት አጠቃቀም ‘በደንብ ወይም በመጠኑ’ እንደሚያውቁ ይሰማቸዋል። ይኸው ጥያቄ ለልጆቹ ሲቀርብ ግን 70 በመቶ የሚሆኑት በኢንተርኔት አማካኝነት ስለሚያደርጓቸው ነገሮች ወላጆቻቸው ‘እምብዛም ወይም ጭራሽ እንደማያውቁ’ ተናግረዋል” በማለት ፊ ዴልታ ካፓን በተባለው መጽሔት ላይ ገልጸዋል። በዚህ ጥናት መሠረት “ከ9 እስከ 10 ዓመት ዕድሜ ክልል ውስጥ ከሚገኙ ልጆች መካከል 30 በመቶ የሚሆኑት የግል ምስጢር የሆነና ለትላልቅ ሰዎች ብቻ የተፈቀዱ ቻት ሩሞችን ከፍተው ተከታትለዋል። ከ11 እስከ 12 ዓመት ከሆናቸው ልጆች መካከል 58 በመቶ፣ ከ13 እስከ 14 ዓመት ከሆናቸው መካከል 70 በመቶ እንዲሁም ከ15 እስከ 17 ዓመት ከሆናቸው መካከል 72 በመቶ የሚሆኑት እንዲህ ስለሚያደርጉ ዕድሜ ከፍ ባለ መጠን ችግሩ እየተባባሰ እንደሚሄድ ተስተውሏል። . . . በቤት ውስጥ የኢንተርኔት አጠቃቀምን በተመለከተ በብሪታንያ የተደረገ ጥናት፣ ከሰባት ወላጆች መካከል አንዱ ልጆቹ በኢንተርኔት ምን እንደሚመለከቱ የሚያውቀው ነገር እንደሌለ አመልክቷል።”

ቁጥጥር ያልተደረገበት የኢንተርኔት አጠቃቀም ልጆችን ለብልግና ሥዕሎች ያጋልጣል። ይሁን እንጂ አደጋው በዚህ ብቻ አያበቃም። ቀደም ሲል የተጠቀሱት ታፈል “ልጆቻችን በትምህርት ቤትና በኢንተርኔት አማካኝነት በርካታ ጓደኞች እያፈሩ ነው። በዚህም ምክንያት አብዛኛውን ጊዜ አይተን ከማናውቃቸው ልጆች ጋር ጊዜ ያሳልፋሉ” ብለዋል።

በእርግጥም የዛሬዎቹ ወጣቶች የቀድሞዎቹ ትውልዶች አጋጥመዋቸው ለማያውቁ ጫናዎችና ችግሮች ተጋልጠዋል። የብዙ ወጣቶች ባሕርይ ግራ የሚያጋባ እየሆነ መምጣቱ ሊያስደንቀን አይገባም። ታዲያ የዛሬዎቹን ወጣቶች ለመርዳት ሊደረግ የሚችል ነገር አለ?

[በገጽ 6 ላይ የሚገኝ የተቀነጨበ ሐሳብ]

“ባለፉት 30 ዓመታት እየተስፋፋ የመጣው የልጆች አስተዳደግ ከቤተሰባቸው ጋር ቅርርብ የሌላቸው፣ ድብቅ የሆኑ፣ የመማር ችሎታቸው ደካማ የሆነና ለመቆጣጠር የሚያስቸግሩ ልጆች እንዲበዙ አድርጓል።”—ዶክተር ሮበርት ሾው

[በገጽ 6, 7 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

ወደ ሥራው ዓለም የሚገቡ ሴቶች ቁጥር እየጨመረ መሄዱ በቤተሰብ ሕይወት ላይ ትልቅ ለውጥ አስከትሏል

[በገጽ 7 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

ክትትል የማይደረግላቸው ወጣቶች በቀላሉ ችግር ውስጥ ይገባሉ

[በገጽ 8 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

ጠበኝነት የሚታይባቸው የሙዚቃ ቪዲዮዎች የጠበኝነት ባሕርይ እንደሚያስከትሉ ተመራማሪዎች አመልክተዋል

[በገጽ 9 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

ልጆችህ በኢንተርኔት ምን እንደሚያዩ ታውቃለህ?