የዝናብ ውኃ ማቆር—ጥንትና ዛሬ
የዝናብ ውኃ ማቆር—ጥንትና ዛሬ
ሕንድ የሚገኘው የንቁ! ዘጋቢ እንደጻፈው
በፕላኔታችን ላይ የሚገኘው ውኃ ከመሬትና ከባሕር ላይ ተንኖ የመሄድን፣ ደመና የመሥራትንና በዝናብ መልክ የመውረድን የተፈጥሮ ሂደት ተከትሎ ለበርካታ ምዕተ ዓመታት ዑደቱን ጠብቆ ሲሽከረከር ቆይቷል። ይህ ብክነት የሌለበት አሠራር በምድር ላይ ለሚኖሩ ሁሉ በቂ ውኃ እንዲዳረስ ያደርጋል። ታዲያ የሰው ዘር ከፍተኛ የውኃ ችግር የገጠመው ለምንድን ነው? ምን መፍትሄዎችስ አሉ? መልሱን ለማግኘት በሕንድ ያለውን የውኃ ሁኔታ እንመልከት።
ከአንድ ቢሊዮን ሕዝብ በላይ የሚኖርባት ሕንድ የውኃ ሀብቷ መጠን አሳሳቢ ደረጃ ላይ ደርሷል። ሕንድ ውኃ የምታገኘው ከየት ነው? በበልግ ወራት በሂማልያ ተራራ ላይ ያለው ግግር በረዶ ሲቀልጥ በስተ ሰሜን የሚገኙት ወንዞች ይሞላሉ። ሆኖም በአብዛኛው የአገሪቱ ክፍል ደረቁ ምድር የሚርሰው፣ የውኃ ጉድጓዶችና ሐይቆች እንዲሁም አገሪቱን የሚያቆራርጡት ታላላቅ ወንዞች የሚሞሉት ዓመታዊው የዝናብ ወቅት ሲጀምር ነው። ይህ የዝናብ ወቅት ለመተንበይ የሚያስቸግር ከመሆኑም ሌላ አንዳንዶች እንደሚሉት “ከሳተላይት አንስቶ በዓይነታቸው ልዩ እስከሆኑ ኮምፒውተሮች ድረስ በቴክኖሎጂው መስክ ከፍተኛ እድገት ቢደረግም . . . አመጣጡን ለመገመት የሚያዳግትና በጣም ግራ የሚያጋባ ክስተት ነው።”
ትክክለኛው የዝናብ ወቅት የሚቆየው ለሦስት ወይም ለአራት ወራት ቢሆንም ዝናቡ የሚዘንበው ቀጣይነት ባለው ሁኔታ አይደለም። በአብዛኛው ለአጭር ጊዜ በዶፍ መልክ ይወርዳል። ከዚህም የተነሳ ግድቦች በጣም ስለሚሞሉ ውኃውን መልቀቅ ግድ ይሆናል። ወንዞች ሞልተው ስለሚፈስሱ እርሻዎችና መኖሪያ ቤቶች በጎርፍ ይጥለቀለቃሉ። ዘመናዊ ኢንዱስትሪና የከተሞች መቆርቆር ከፍተኛ የደን ጭፍጨፋ ስላስከተሉ ውኃውን በሥራቸው ይዘው ቀስ በቀስ ወደ መሬት እንዲሰርግ የሚያደርጉ በቂ ዛፎች እንዳይኖሩ ምክንያት ሆኗል። ስለዚህም ጎርፉ የአፈሩን የላይኛ ክፍል አጥቦ በመውሰድ መሬቱን አራቁቶታል። ሐይቆችንና ኩሬዎችን ደለል ስለሚሞላቸው መያዝ የሚችሉት የውኃ መጠን ይቀንሳል። በዚህም ምክንያት ከፍተኛ መጠን ያለው የዝናብ ውኃ ባክኖ ይቀራል።
በመጨረሻም ይህ ኃይለኛ የዝናብ ወቅት ያልፋል። በጋ በሚሆንበት በቀሪው የዓመቱ ክፍል ከፍተኛ ሙቀት ይኖራል። በአጭር ጊዜ ውስጥ መሬቱ ይደርቅና ሜዳው ሁሉ መሰነጣጠቅ ይጀምራል። በኃይል ይፈሱ የነበሩት ወንዞችም መጠናቸው ቀንሶ ጭል ጭል የሚሉ ይሆናሉ። ፏፏቴዎች ይጠፋሉ። በዚህ ወቅት በከርሰ ምድር ውስጥ ከሚገኙት ውኃ አዘል አለቶች ውስጥ ውኃ ለማውጣት ጥልቅ ጉድጓዶች መቆፈር ያስፈልጋል፤ ይህ ደግሞ ውኃ የሚገኝበትን ወለል ይበልጥ እንዲርቅ ያደርገዋል። የዝናቡ መጠን አነስተኛ ሲሆን ድርቅ ይገባል፣ ሰብል ይወድማል፣ ከብቶች ይሞታሉ እንዲሁም በገጠር የሚኖሩ ወደ ከተማ ይፈልሳሉ፤ ይህ ደግሞ በከተማ ያለውን የውኃ ችግር ያባብሰዋል።
በአንድ ወቅት ይህ ችግር አይታወቅም ነበር። በጥንት ዘመን፣ በመላዋ ሕንድ የነበሩ ሰዎች የዝናቡ ወቅት ሲያልፍ በሚደርቁ ወንዞችና ሐይቆች ላይ ብቻ መመካት እንደሌለባቸው ያውቁ ነበር። ዝናብ በሚጥልበት ወቅት ውኃ የሚያጠራቅሙበት ዘዴ አዳብረው የነበረ ሲሆን ከዚያ ውስጥ የተወሰነውን ለጊዜው ለሚያስፈልጋቸው ነገር ከተጠቀሙበት በኋላ የቀረውን ለድርቅ ወቅት ያስቀምጡታል። ይህ ዘዴ የዝናብ ውኃን ማቆር ይባላል።
በዛሬው ጊዜ የዝናብ ውኃን የማቆር አስፈላጊነት
አንድ ሰው ዘመናዊ ቴክኖሎጂን እና ትላልቅ የውኃ ማጠራቀሚያዎችን፣ ግድቦችን እንዲሁም የመስኖ ቦዮችን በሚመለከትበት ወቅት (እነዚህ ሁሉ ሕንድ ውስጥ በብዛት ይገኛሉ) በጥንቱ ዘዴ የዝናብ ውኃ ማጠራቀም አስፈላጊ አይደለም ብሎ ሊያስብ ይችላል። እንዲያውም ሰዎች በየመንደራቸውና በየቤታቸው የቧንቧ ውኃ በማግኘታቸው አብዛኛዎቹ ውኃን የማቆር ዘዴዎች ተትተዋል። ሆኖም አንዳንድ አሳሳቢ ችግሮች ተፈጥረዋል። ባለፉት 50 ዓመታት ሲካሄዱ የቆዩት የውኃ ፕሮጀክቶች በፍጥነት እያደገ የመጣውን ሕዝብ የውኃ ፍጆታም ሆነ በእርሻ ይተዳደር የነበረው ማኅበረሰብ በኢንዱስትሪ መስክ በመሰማራቱ ምክንያት የተፈጠረውን ተጨማሪ የውኃ ፍላጎት ማሟላት አልቻሉም። የአገሪቱን የውኃ ፍላጎት ለማሟላት በቂ የውኃ ክምችት አልነበረም።
አሁን አሁን የአካባቢ ጥበቃ ባለሙያዎችና ጉዳዩ ያሳሰባቸው ባለ ሥልጣናት ሰዎች በግለሰብ ደረጃ ውኃን እንዲያቁሩ ማበረታታት እንዳለባቸው ተሰምቷቸዋል። በመኖሪያ ቤቶች፣ በፋብሪካዎችና በትምህርት ቤቶች እንዲሁም በመጠኑም ቢሆን ውኃ ማጠራቀም በሚቻልባቸው ቦታዎች ሁሉ የዝናብ ውኃ የማቆር አስፈላጊነት እየተበረታታ ነው። እንዲያውም በርካታ ከተሞችና የክልል መንግሥታት አዳዲስ ሕንፃዎች ሲገነቡ የዝናብ ውኃ ማጠራቀሚያ እንዲኖራቸው ያስገድዳሉ!
በሚሊዮን ሊትር የሚገመት የዝናብ ውኃ ወደ ማጠራቀሚያ የሚያስገባ መስመር ስላልተበጀለት ወይ ይተናል አሊያም ወደ ባሕር ይገባል። የዝናብ ውኃን ማቆር
“በዘነበበት ሁሉ ውኃ ማጠራቀም” በሚለው መርህ ላይ የተመረኮዘ ሲሆን ይህም የዝናብ ውኃን በግለሰብ ደረጃ ማቆር ማለት ነው። እንዲሁም ክፍያ የሚጠይቅ በመሆኑ ዝቅተኛ ኑሮ ላለው የኅብረተሰብ ክፍል ከባድ ሸክም ከሚሆነው ከግድብና በቦይ አማካኝነት ከሚገኝ ውኃ በተለየ የዝናብ ውኃ የሚገኘው በነፃ ነው!ለተግባር መነሳሳት
በሕንድ የውኃ ሀብት ጥበቃ የሚያሳስባቸው ብዙ ሰዎች ውኃ በማቆሩ ሥራ ላይ ተሰማርተው ይገኛሉ። አንዳንዶች ዓለም አቀፍ እውቅና በማግኘት እስከ መሸለም ደርሰዋል። ለምሳሌ ራጄንድራ ሲንግ፣ ታዋቂ የሆነው ማግሳይሳይ የተባለ ድርጅት ለማኅበራዊ እድገት አስተዋጽኦ ለሚያደርጉ ሰዎች የሚሰጠውን ሽልማት በ2001 ለመሸለም በቅተዋል። ሲንግ ባቋቋሙት መንግሥታዊ ባልሆነ ድርጅት አማካኝነት በራጃስታን ግዛት ውስጥ በሚገኘው ሕልውናው አደጋ ላይ ወድቆ በነበረው አራቫሪ ወንዝ ላይ የሠሩት ሥራ ወንዙ እንዲያንሰራራ አድርጓል። ራጃስታን ከአገሪቱ ሕዝብ መካከል 8 በመቶ የሚሆነው የሚኖርባት ሆና ሳለ በዚያ የሚገኘው የውኃ ሀብት ግን አንድ በመቶ ብቻ በመሆኑ የተከናወነው ሥራ ወቅታዊና ጠቃሚ ነበር። ከሲንግ ጋር የሚሠሩት ሰዎች በ15 ዓመት ጊዜ ውስጥ ዛፎች በመትከልና ውኃ ለማጠራቀም የሚያገለግሉ በአገሪቱ ጆሃድስ ተብለው የሚጠሩ 3,500 የውኃ ጋኖችን በመገንባት ለመንደሩ ነዋሪዎች እድገት አስተዋጽኦ አበርክተዋል። ሌሎች ደግሞ በብዙኃኑ ዘንድ ታዋቂ ባይሆኑም የሚሠሩት ሥራ የሚያበረክተው አስተዋጽኦ እንዳለ ማወቃቸው እርካታ ስለሚሰጣቸው ውኃ በማቆሩ ሥራ ይካፈላሉ።
የኢንዱስትሪ ባለቤቶች የከተማውን የውኃ አቅርቦት ለመደገፍ የዝናብ ውኃን ማቆር ያለውን ጥቅም ተረድተዋል። በደቡብ ሕንድ፣ ባንግሎር አቅራቢያ የሚገኝ አንድ ፋብሪካ ከጣሪያ ላይ የሚፈሰውን የዝናብ ውኃ ለማጠራቀም የሚያስችል ብዙ ገንዘብ የማይጠይቅ ማጠራቀሚያ ገንብቷል። ከዚህ በፊት መንገድ ላይ ፈስሶና ባክኖ ይቀር የነበረን የዝናብ ውኃ 42,000 ሊትር መያዝ ወደሚችል ገንዳ እንዲገባ ማድረግ ተችሏል። በዝናብ ወቅት የመመገቢያ እቃዎች ለማጠቢያነት እና በፋብሪካው ውስጥ ላለው ካፊቴሪያ አገልግሎት የሚውል በቀን 6,000 ሊትር የዝናብ ውኃ ይጣራል። ለእነዚህ አገልግሎቶች ከከተማው የሚመጣውን የቧንቧ ውኃ አይጠቀሙም።
ምናልባት ‘በገንቦ ውስጥ ያለች የውኃ ጠብታ’ ትል ይሆናል። ሆኖም በዓመት አንድ ጊዜ ብቻ ገንዘብ ገቢ የሚደረግበት የባንክ ሂሳብ አለህ እንበል። ከዚህ ሂሳብ ላይ በየቀኑ ለሚያስፈልግህ ነገር ትንሽ ትንሽ ስታወጣ ቆይተህ ሳታውቀው ካስገባኸው በላይ ወሰድህ። አንድ ቀን የባንኩ ዕዳ እንዳለብህ ተገነዘብክ። ነገር ግን በዓመቱ ውስጥ ለተወሰኑ ወራት የዕለት ወጪህን መሸፈን የሚያስችልህ ከበቂ በላይ ክፍያ ያለው ሥራ ብታገኝ ሂሳብህ የማንሰራራት አጋጣሚ ይኖረዋል። አሁን ይህንኑ ደንብ የውኃ ብክነትን ለመከላከል እንጠቀምበት። ትንሽ ትንሽ ያጠራቀምከውን ውኃ በሚሊዮን ብታባዛው ምን ታገኛለህ? ቀንሰው የነበሩ የውኃ ምንጮች እንደገና ይሞላሉ፣ በከርሰ ምድር ውስጥ የሚገኘው የውኃ ወለል ከፍ ይላል እንዲሁም ውኃ አዘል አለቶች ይሞላሉ። በመሆኑም አጠራቅመኸው ከነበረው የዝናብ ውኃ የምታገኘው “ክፍያ” ሲያቆም ወደነዚህ የውኃ ምንጮች መዞር ትችላለህ። አንድ ነገር አስታውስ፤ ያለው የውኃ መጠን ውስን ስለሆነ ውኃ ከጠፋ የውኃ ዕዳ ውስጥ ልትገባ አትችልም።
ዘላቂው መፍትሄ
ፕላኔታችን ለነዋሪዎቿ የሚያስፈልጋቸውን ሁሉ አሟልታ ይዛለች። ይሁን እንጂ ባለፉት ዘመናት ሁሉ የሰው ስግብግብነትና አርቆ አለማየት በምድር ላይ የሚኖሩ በሚሊዮን የሚቆጠሩ ሰዎች በአስከፊ ሁኔታ ሥር እንዲኖሩ አድርጓል። በቅንነት ጥረት እያደረጉ ያሉ ግለሰቦች ቢኖሩም የሰው ልጆች በተፈጥሮ ላይ የደረሱትን ችግሮች ሙሉ በሙሉ ለመቅረፍ አቅም እንደሌላቸው ግልጽ ነው። ደስ የሚያሰኘው የምድር ፈጣሪ ‘ምድርን ያጠፏትን የሚያጠፋበት ዘመን እንደሚመጣ’ ተስፋ ከመስጠቱም በተጨማሪ የውኃ ዑደትን እንደገና የሚያስተካክል በመሆኑ “ውሃ ከበረሓ ይወጣል፤ ምንጮችም ከምድረ በዳ ይፈልቃሉ።” በእርግጥም “ንዳዳማው ምድር ኲሬ ይሆናል፤ የተጠማው መሬት ውሃ ያመነጫል።” ይህም ከዝናብ ውኃ የምናገኘው አስደሳች ውጤት ነው!—ራእይ 11:18፤ ኢሳይያስ 35:6, 7
[በገጽ 15 ላይ የሚገኝ ሣጥን/ሥዕሎች]
ወደ ጥንቱ የዝናብ ውኃ ማቆሪያ ዘዴ መመለስ
ከጣሪያ የሚወርድ ውኃ:- ቀላልና ብዙ ወጪ የማይጠይቅ። ሾጠጥ ተደርጎ የተሠራ ጣሪያ የዝናብ ውኃ በአሸንዳ በኩል አድርጎ ወደተዘጋጀለት በርሜል እንዲገባ ይረዳዋል። ውኃውን ለማጣራት የሽቦ ማጥለያ፣ አሸዋ፣ ኮረትና ከሰል መጠቀም ይቻላል። ከዚያም መሬት ውስጥ ወደሚገኝ ማጠራቀሚያ ወይም መሬት ላይ ወደተቀመጠ ጋን እንዲገባ ይደረጋል። ውኃውን ከአየር፣ ከፀሐይ ብርሃንና ከቆሻሻ መጠበቅ እንዲቻል ጋኑን መክደን ያስፈልጋል፤ በተጨማሪም አሉም የተባለውን ንጥረ ነገር በመጠቀም አፈርማ ቀለሙን ማጥራትና ባክቴሪያዎች ለመግደል ደግሞ ኬሚካል መጠቀም ይቻላል። ውኃው ለጓሮ አትክልት፣ ለመጸዳጃ ቤትና ለልብስ አጠባ ሊያገለግል ይችላል። ተጨማሪ የማጣራት ሂደት ከተደረገለት ሊጠጣም ይችላል። የተረፈውን ውኃ በጉድጓድ ውስጥ ማጠራቀም ወይም የከርሰ ምድሩ የውኃ ወለል ከፍ እንዲል መሬት ውስጥ ማፍሰስ ይቻላል። በአብዛኛው ከተማ ውስጥ የሚሠራበት ዘዴ ይህ ነው።
ኖላ:- የድንጋይ ግንብ በመገንባት ወራጅ ውኃን መገደብ። ከዚያም ጥላ ሊፈጥሩ የሚችሉ ዛፎችን በመትከል ውኃው እንዳይተን መከላከልና ውኃውን ለማጣራት ደግሞ መድኃኒትነት ያላቸውን ተክሎች በኩሬው ውስጥ መጨመር ነው።
ኩሬ፣ ራፓት:- የዝናብ ውኃን ለማጠራቀም አሸዋማ ወይም ድንጋያማ በሆነ መሬት ላይ ትንሽ ጉድጓድ ወይም ማጠራቀሚያ መገንባት ነው። በዚህ ዘዴ ከተሰበሰበው ውኃ ውስጥ የተወሰነው ጥቅም ላይ ሲውል ቀሪው ደግሞ ወደታች ሰርጎ ከጉድጓድ ውኃ ጋር ይቀላቀላል።
ባንዳረ:- ከምንጭ የሚገኘውን ውኃ ለመሰብሰብ ከመሬት በታች ጋኖችን በመገንባትና በቱቦ አማካኝነት ወደ ውኃ ማጠራቀሚያ ጋን እንዲሄድ በማድረግ ለከተማው አገልግሎት እንዲውል ማድረግ ነው።
ካናት:- የዝናብ ውኃ ለማጠራቀም ከኮረብታማ አካባቢ ቁልቁል የሚወርድበት መንገድ ማዘጋጀት። የዝናብ ውኃው ተሰብስቦ ከመሬት በታች ባሉ ቦዮች አልፎ በስበት አማካኝነት ረጅም ርቀት ከተጓዘ በኋላ ማጠራቀሚያ ጋን ውስጥ ይገባል።
ጥንድ ጋኖች:- ከፍ ብለው የተቀመጡት ጋኖች በአሸንዳ በሚወርደው የዝናብ ውኃ ከሞሉ በኋላ ውኃው ከታች ወደሚገኙ ጋኖች ይፈሳል።
[ምንጭ]
Courtesy: S. Vishwanath, Rainwater Club, Bangalore, India
[በገጽ 13 ላይ የሚገኝ የሥዕል ምንጭ]
UN/DPI Photo by Evan Schneider
[በገጽ 14 ላይ የሚገኝ የሥዕል ምንጭ]
UN/DPI Photo by Evan Schneider