በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

‘ብቸኛው እውነተኛ አምላክ’ የገባው ቃል

‘ብቸኛው እውነተኛ አምላክ’ የገባው ቃል

‘ብቸኛው እውነተኛ አምላክ’ የገባው ቃል

ይሖዋ አምላክ የመጀመሪያዎቹን ባልና ሚስት ፈጥሮ በምድር ላይ በሚገኝ ዔድን በሚባል የአትክልት ሥፍራ ውስጥ አስቀመጣቸው። እንዲሁም ልጆች እንዲወልዱና ‘ምድርን እንዲገዟት’ አዘዛቸው፤ የቤተሰቡ ቁጥር እያደገ ስለሚሄድ የተሰጣቸው ትእዛዝ መኖሪያቸው የሆነችውን ገነት ማስፋፋትን ይጨምራል። (ዘፍጥረት 1:26-28፤ 2:15) አምላክ የሰው ልጆችን ገነት በሆነች ምድር ላይ እንዲኖሩ ለማድረግ ያወጣው ዓላማ ፍጻሜውን ያገኝ ይሆን?

በእርግጥ ይፈጸማል! የመጽሐፍ ቅዱስ ትንቢት እንደሚገልጸው “[ይሖዋ] ሞትንም ለዘላለም ይውጣል . . . ከፊት ሁሉ እንባን ያብሳል።” ይህ ትንቢት ፍጻሜውን በሚያገኝበት ጊዜ “እንዲህ ይባላል፤ ‘እነሆ፤ አምላካችን ይህ ነው፤ በእርሱ ታመንን፤ እርሱም አዳነን፤ እግዚአብሔር ይህ ነው፤ በእርሱ ታመንን፤ በማዳኑም ደስ ይበለን፤ ሐሤትም እናድርግ’።”—ኢሳይያስ 25:8, 9

የመጨረሻው የመጽሐፍ ቅዱስ ክፍል ሰይጣን የሚገዛው የአሁኑ ዓለም ወይም ሥርዓት ከተወገደ በኋላ በምድር ላይ ምን ዓይነት ሁኔታዎች እንደሚሰፍኑ ይገልጻል። መጽሐፍ ቅዱስ አምላክን በሚወዱ የሰው ልጆች ስለሚዋቀረው “አዲስ ምድር” እንዲህ በማለት ይናገራል:- “የእግዚአብሔር ማደሪያ በሰዎች መካከል ነው፤ እርሱ ከእነርሱ ጋር ይኖራል፤ እነርሱም ሕዝቡ ይሆናሉ፤ እግዚአብሔር ራሱም ከእነርሱ ጋር ይኖራል፤ አምላካቸውም ይሆናል። እንባን ሁሉ ከዐይናቸው ያብሳል፤ ከእንግዲህ ወዲህ ሞት ወይም ሐዘን ወይም ልቅሶ ወይም ሥቃይ አይኖርም።”—ራእይ 21:1-4

እንዴት ያለ ግሩም ተስፋ ነው! ይህን ተስፋ ማመን እንችላለን? የኢየሱስን መሥዋዕታዊ ሞትና ያከናወናቸውን ተአምራት ስናስብ፣ አምላክ ቃል የገባውን ማንኛውንም ነገር እንደሚፈጸም እምነት እንዲኖረን የሚያስችል ጠንካራ መሠረት እናገኛለን።—2 ቆሮንቶስ 1:20

ኢየሱስ ሕይወቱን ቤዛ አድርጎ ሰጥቷል

አዳም በሰይጣን ግፊት በአምላክ ላይ በማመጹና ኃጢአት በመሥራቱ ምክንያት ዘሮቹ በሙሉ ኃጢአቱን ወረሱ። መጽሐፍ ቅዱስ እንዲህ ይላል:- “ኀጢአት በአንድ ሰው በኩል ወደ ዓለም እንደ ገባ ሁሉ፣ ሞትም በኀጢአት በኩል ገብቶአል፤ . . . ሞት ወደ ሰዎች ሁሉ መጣ፤ ምክንያቱም ሁሉም ኀጢአትን ሠርተዋል።” ይሁንና ዘገባው ሲቀጥል “በአንዱ ሰው [ፍጹም ሰው በነበረው በኢየሱስ] መታዘዝ . . . ብዙዎች ጻድቃን ይሆናሉ” ይላል። (ሮሜ 5:12, 19) በዚህ ተከታታይ ርዕስ የመጀመሪያ ክፍል ላይ ኢየሱስ ‘ከሰማይ የሆነው’ “የኋለኛው አዳም” እንደተባለና ሕይወቱን “ለብዙዎች ቤዛ አድርጎ” እንደሰጠ ተገልጿል።—1 ቆሮንቶስ 15:45, 47፤ ማቴዎስ 20:28

በመሆኑም በኢየሱስ የሚያምኑ ሁሉ ‘በቤዛው የኀጢአት ይቅርታ’ እና የዘላለም ሕይወት ማግኘት ይችላሉ። (ኤፌሶን 1:7፤ ዮሐንስ 3:36) ይሖዋ አምላክ የሰውን ዘር ዓለም በጥልቅ የሚያፈቅር ከመሆኑ የተነሳ ልጁን አዳኝ አድርጎ በመስጠቱ በእርግጥም ደስ ሊለን ይገባል! (ሉቃስ 2:10-12፤ ዮሐንስ 3:16) ኢየሱስ በአንደኛው ክፍለ ዘመን ለነበሩ ችግር ላይ የወደቁ ሰዎች ያደረገውን ነገር መመርመራችን ስለ ወደፊቱ ጊዜ ጠለቅ ያለ ግንዛቤ እንዲኖረን ይረዳናል። እንዲሁም ኢየሱስ ምን ያህል አስደናቂ ነገሮችን እንዳደረገ ለማወቅ እንችላለን!

የአዲሱ ዓለም ናሙናዎች

ኢየሱስ ወደ እሱ የመጡትን ሕሙማንና በሽተኞች በሙሉ መፈወስ ችሏል። መፈወስ ያቃተው አንድም ዓይነት ሕመም ወይም የአካል ጉዳት አልነበረም። በተጨማሪም በጥቂት ዓሣና እንጀራ ብቻ በሺዎች የሚቆጠሩ ሰዎችን በተአምር መግቧል፤ ይህንንም በተደጋጋሚ ፈጽሟል።—ማቴዎስ 14:14-22፤ 15:30-38

በአንድ ወቅት ኢየሱስ ዓይነ ስውር ሆኖ የተወለደ አንድ ሰው ማየት እንዲችል አደረገ፤ የሰውየው ጎረቤቶችና የሚያውቁት ሰዎች ተአምር እንደተፈጸመ አመኑ፤ የአይሁድ የሃይማኖት መሪዎች ግን ነገሩን ተጠራጠሩ። ስለዚህ ዓይኑ የበራለት ሰው እንዲህ በማለት አስረዳቸው:- “ዐይነ ስውር ሆኖ የተወለደን ሰው ዐይን የከፈተ አለ ሲባል፣ ዓለም ከተፈጠረ ጀምሮ ማንም ሰምቶ አያውቅም። ይህ ሰው ከእግዚአብሔር ባይሆን ኖሮ ይህን ማድረግ ባልቻለ ነበር።”—ዮሐንስ 9:32, 33

ኢየሱስ አገልግሎቱን በሚያከናውንበት ወቅት፣ በእስር ላይ የነበረው የአክስቱ ልጅ መጥምቁ ዮሐንስ ስለ ኢየሱስ የሚነገሩት ነገሮች እውነት መሆናቸውን ለማረጋገጥ መልእክተኞችን ላከ። መጽሐፍ ቅዱስ “በዚያኑ ጊዜ ኢየሱስ ብዙ ሰዎችን ከበሽታ፣ ከደዌና ከርኩሳን መናፍስት ፈወሳቸው፤ የብዙ ዐይነ ስውራንንም ዐይን አበራ” ይላል። ከዚያም ኢየሱስ ለመልእክተኞቹ እንዲህ አላቸው:- “ያያችሁትንና የሰማችሁትን ለዮሐንስ ንገሩት፤ ዐይነ ስውራን ያያሉ፤ ዐንካሶች በትክክል ይራመዳሉ፤ ለምጻሞች ነጽተዋል፤ ደንቈሮዎች ይሰማሉ፤ ሙታን ተነሥተዋል።”—ሉቃስ 7:18-22

እስቲ አስበው፣ ባለፉት ጊዜያት አንድ ጥሩ ነገር ቢከሰት ያው ሁኔታ በድጋሚ ሊፈጸም እንደሚችል አታምንም? ኢየሱስ ጥቂት ተአምራት በመፈጸም፣ ወደፊት የአምላክ መንግሥት ንጉሥ ሆኖ በሚገዛበት ጊዜ በሰፊው ምን እንደሚያከናውን ናሙና አሳይቷል። ኢየሱስ የፈጸማቸው ተአምራት ከአምላክ ለመላኩና የእርሱ ልጅ ለመሆኑ እንደ ማረጋገጫ ሆነው አገልግለዋል።

የአምላክ መንግሥት በምትገዛበት ጊዜ፣ በትንቢት የተነገሩ አስደናቂ ነገሮች ቃል በቃል ይፈጸማሉ። አስቀድሞ በተተነበየው መሠረት የዕውሮች ዓይን ይገለጣል፣ የደንቆሮዎች ጆሮ ይከፈታል፣ አንካሳ እንደ ሚዳቋ ይዘልላል እንዲሁም የሚታመም ሰው አይኖርም። በመላው ምድር ሰላምና ደኅንነት ይሰፍናል። ሌላው ቀርቶ በአሁኑ ጊዜ አደገኛ የሆኑ እንስሳት እንኳ ከሰዎች ጋር በሰላም ይኖራሉ።—ኢሳይያስ 9:6, 7፤ 11:6-9፤ 33:24፤ 35:5, 6፤ 65:17-25

እንዲህ ያሉ ሁኔታዎች በሰፈኑበት የአምላክ መንግሥት አገዛዝ ሥር ለዘላለም መኖር ትፈልጋለህ? ኢየሱስ ለአባቱ ሲጸልይ “እውነተኛ አምላክ የሆንኸውን አንተንና የላክኸውንም ኢየሱስ ክርስቶስን ያውቁ ዘንድ ይህች የዘላለም ሕይወት ናት” በማለት ማድረግ ስላለብህ ነገር ተናግሯል። (ዮሐንስ 17:3) እንዲህ ያለውን ሕይወት ሰጪ እውቀት ከመቅሰም ምንም ነገር እንዲያግድህ አትፍቀድ።

[በገጽ 10 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

አምላክ ስለ ምድር የገባው ቃል ይህ ነው