በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

‘ብቻውን እውነተኛ አምላክ’ የሆነው ማን ነው?

‘ብቻውን እውነተኛ አምላክ’ የሆነው ማን ነው?

‘ብቻውን እውነተኛ አምላክ’ የሆነው ማን ነው?

ኢየሱስ አባት ብሎ ወደጠራው አምላክ በተደጋጋሚ ጊዜያት የጸለየ ሲሆን ሌሎችም እንዲሁ እንዲያደርጉ አስተምሯል። (ማቴዎስ 6:9-11፤ ሉቃስ 11:1, 2) ከመሞቱ ጥቂት ሰዓታት ቀደም ብሎ ከሐዋርያቱ ጋር ሆኖ ባቀረበው ጸሎት ላይ “አባት ሆይ! እነሆ ሰዓቱ ደርሶአል፥ ልጅህ እንዲያከብርህ፥ ልጅህን አክብረው። የዘላለም ሕይወትም፥ ብቻህን እውነተኛ አምላክ የሆንከውን አንተንና የላክኸውን ኢየሱስ ክርስቶስን ማወቅ ነው” በማለት ተማጽኗል።—ዮሐንስ 17:1, 3 የ1980 ትርጉም

ኢየሱስ ጸሎቱን ያቀረበው “ብቻህን እውነተኛ አምላክ” ብሎ ለጠራው አካል እንደሆነ ልብ በል። ቀጥሎም “እንግዲህ አባት ሆይ፤ ዓለም ሳይፈጠር ከአንተ ጋር በነበረኝ ክብር በአንተ ዘንድ አክብረኝ” በማለት እግዚአብሔር የበላይ እንደሆነ ጠቁሟል። (ዮሐንስ 17:5) ኢየሱስ እዚህ ላይ በአምላክ ዘንድ ለመከበር በጸሎት እየጠየቀ እርሱ ራሱ እንዴት ‘ብቸኛው እውነተኛ አምላክ’ ሊሆን ይችላል? እስቲ ይህን ጉዳይ እንመርምር።

ኢየሱስ በሰማይ ያለው ቦታ

ኢየሱስ ይህንን ጸሎት ካቀረበ ከጥቂት ሰዓታት በኋላ ተገደለ። ይሁን እንጂ ሞቶ የቆየው ለጥቂት ቀናት ማለትም ከዓርብ ከሰዓት በኋላ እስከ እሁድ ጠዋት ብቻ ነበር። (ማቴዎስ 27:57 እስከ 28:6) ሐዋርያው ጴጥሮስ “ይህን ኢየሱስ፣ እግዚአብሔር ከሞት አስነሣው፤ እኛም ሁላችን ለዚህ ነገር ምስክሮች ነን” በማለት ዘግቧል። (የሐዋርያት ሥራ 2:31, 32) ኢየሱስ ራሱን ከሞት ማስነሳት ይችላል? አይችልም። ምክንያቱም መጽሐፍ ቅዱስ ሙታን “ምንም አያውቁም” ይላል። (መክብብ 9:5) ስለዚህ ልጁን ኢየሱስን ከሞት ያስነሳው ‘ብቻውን እውነተኛ አምላክ የሆነው’ በሰማይ የሚኖረው አባቱ ነው።—የሐዋርያት ሥራ 2:32፤ 10:40

ይህ ከሆነ ከጥቂት ጊዜ በኋላ፣ የኢየሱስ ደቀ መዝሙር የነበረው እስጢፋኖስ በሃይማኖታዊ አሳዳጆች ተገደለ። እነዚህ ሰዎች ሊወግሩት ሲሉ እስጢፋኖስ ራእይ ተመልክቶ ነበር። “እነሆ፤ ሰማያት ተከፍተው፣ የሰው ልጅም በእግዚአብሔር ቀኝ ቆሞ አያለሁ” በማለት ተናግሯል። (የሐዋርያት ሥራ 7:56) እዚህ ላይ እስጢፋኖስ፣ “የሰው ልጅ” የተባለው ኢየሱስ ልክ ወደ ምድር ከመምጣቱ በፊት ‘በአምላክ ዘንድ’ እንደነበረው በሰማይ “በእግዚአብሔር ቀኝ ቆሞ” የይሖዋን ዓላማ ሲያስፈጽም ተመልክቶታል።—ዮሐንስ 17:5

እስጢፋኖስ ከተገደለ በኋላ ኢየሱስ፣ በይበልጥ ጳውሎስ በሚለው ሮማዊ ስሙ ለሚታወቀው ለሳውል በተአምር ተገለጠለት። (የሐዋርያት ሥራ 9:3-6) ጳውሎስ በአቴና፣ ግሪክ ሳለ ‘ዓለምንና በውስጡ ያለውን ሁሉ ስለ ፈጠረው አምላክ’ ተናግሮ ነበር። አክሎም ይህ ‘ብቸኛው እውነተኛ አምላክ’ “በመረጠው ሰው አማካይነት በዓለም ላይ በጽድቅ የሚፈርድበትን ቀን ወስኖአልና፤ እርሱንም ከሙታን በማስነሣቱ ለሰዎች ሁሉ ይህን አረጋግጦአል” ብሏል። (የሐዋርያት ሥራ 17:24, 31) ሐዋርያው ጳውሎስ እዚህ ላይ አምላክ በድጋሚ በሰማይ ሕይወት የሰጠውን ኢየሱስን “ሰው” በማለት ከእግዚአብሔር አሳንሶ ገልጾታል።

ሐዋርያው ዮሐንስም ኢየሱስን ከእግዚአብሔር ያነሰ እንደሆነ አድርጎ ገልጾታል። ወንጌሉን የጻፈው አንባቢዎች “ኢየሱስ እርሱ ክርስቶስ፣ የእግዚአብሔርም ልጅ እንደ ሆነ” እንዲያምኑ መሆኑን ተናግሯል፤ ዮሐንስ በዚህ ጥቅስ ላይ ኢየሱስን እግዚአብሔር እንዳላለው ልብ ማለት ይገባል። (ዮሐንስ 20:31) እንዲሁም ዮሐንስ ከሰማይ ባየው ራእይ ላይ “በግ” ተመልክቶ የነበረ ሲሆን እርሱ በጻፈው ወንጌል ውስጥ ኢየሱስ በግ ተብሎ ተገልጿል። (ዮሐንስ 1:29) በጉ፣ ዮሐንስ ‘ከምድር የተዋጁ [ወይም ከሞት የተነሱ]’ ብሎ ከገለጻቸው 144,000 ሰዎች ጋር ቆሟል። እነዚህ 144,000 ሰዎች የበጉ ‘ስምና የአባቱ ስም በግምባራቸው ላይ እንደተጻፈባቸው’ ዮሐንስ ተናግሯል።—ራእይ 14:1, 3

“በጉ” እና “አባቱ” አንድ ሊሆኑ ይችላሉ? ሊሆኑ እንደማይችሉ ግልጽ ነው። በመጽሐፍ ቅዱስ የተገለጹት የተለያዩ አካላት እንደሆኑ ተደርጎ ነው። ሌላው ቀርቶ ስማቸው እንኳን የተለያየ ነው።

የበጉ ስም እና የአባቱ ስም

ቀደም ብለን እንዳየነው የእግዚአብሔር ልጅ ለሆነው ለበጉ፣ ኢየሱስ የሚል ስም ተሰጥቶታል። (ሉቃስ 1:30-32) የአባቱስ ስም ማን ነው? በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ ስሙ በሺህ በሚቆጠሩ ቦታዎች ላይ ይገኛል። ለምሳሌ ያህል ዘፀአት 6:3 (የ1879 ትርጉም) እንዲህ ይላል:- “ለአብርሃምም: ለይስሐቅም: ለያዕቆብም: ሁሉን: እንደሚችል: አምላክ (ኤልሸደይ): ተገለጥሁ: በስሜም: እግዚእ (ይሖዋ): አልታወቅሁላቸውም።” የሚያሳዝነው በበርካታ የመጽሐፍ ቅዱስ ትርጉሞች ላይ ይሖዋ የሚለው የአምላክ ስም “ጌታ፣” “እግዚአብሔር” እና “አምላክ” በሚሉት ቃላት ተተክቷል። ሆኖም ብዙ የመጽሐፍ ቅዱስ ትርጉሞች መለኮታዊውን ስም በትክክለኛው ቦታ ላይ መልሰው አስገብተውታል።

በእንግሊዝኛ ቋንቋ የተዘጋጀው አሜሪካን ስታንዳርድ ቨርሽን (1901)፣ ይሖዋ የሚለውን የአምላክ ስም በትክክለኛ ቦታው ላይ መልሶ በማስፈር በኩል ዓይነተኛ ምሳሌ ተደርጎ ሊጠቀስ የሚችል የመጽሐፍ ቅዱስ ትርጉም ነው። ይህ መጽሐፍ ቅዱስ በመቅድሙ ላይ እንዲህ ይላል:- “ተርጓሚዎቹ ጉዳዩን በጥንቃቄ ካገናዘቡ በኋላ፣ ‘መለኮታዊው ስም በጣም ቅዱስ በመሆኑ ምክንያት መጠራት አይገባውም’ የሚለው የአይሁዳውያን አጉል እምነት በእንግሊዝኛውም ሆነ በሌላ በማንኛውም የብሉይ ኪዳን ትርጉም ላይ ተጽዕኖ ማሳደር እንደማይገባው በሙሉ ድምፅ አጽድቀዋል፤ ይህ አጉል እምነት የዘመናችን ሚስዮናውያን ባዘጋጇቸው በርካታ ትርጉሞች ላይ ተጽዕኖ አለማድረጉ የሚያስደስት ነው።” *

የሥላሴ ትምህርት የመነጨው ከየት ነው?

ይሖዋና ኢየሱስ አንድ አምላክ ናቸው ስለሚለው የሥላሴ ትምህርትስ ምን ለማለት ይቻላል? ዘ ሊቪንግ ፑልፒት የተባለው መጽሔት በሚያዝያ-ሰኔ 1999 እትሙ ላይ እንደሚከተለው በማለት ለሥላሴ ፍቺ ሰጥቷል:- “አንድ እግዚአብሔርና አብ፣ አንድ ጌታ ኢየሱስ ክርስቶስ እንዲሁም አንድ መንፈስ ቅዱስ አለ፤ እነዚህ ሦስት ‘አካላት’ . . . በባሕርይ አንድ ናቸው፤ . . . ሁሉም ተመሳሳይ ተፈጥሯዊ ሁኔታ ያላቸው እኩል እግዚአብሔር ናቸው፤ ሆኖም አንዱ ከሌላው የተለዩና በየግል ባሕርያቸው የሚታወቁ ናቸው።” *

ይህ የተወሳሰበ የሥላሴ ትምህርት የመነጨው ከየት ነው? ክርስቺያን ሴንቸሪ የተባለው መጽሔት በግንቦት 20-27, 1998 እትሙ፣ አንድ ፓስተር ሥላሴ “የኢየሱስ ትምህርት ሳይሆን የቤተ ክርስቲያን ትምህርት” ነው ብለው እንደተናገሩ ጠቅሷል። ኢየሱስ ስለ ሥላሴ አላስተማረም። ይሁንና ይህ ሐሳብ እርሱ ካስተማራቸው ሌሎች ትምህርቶች ጋር ይስማማል?

አብ ከወልድ ይበልጣል

ኢየሱስ ደቀ መዛሙርቱ “በሰማያት የምትኖር አባታችን ሆይ፤ ስምህ ይቀደስ” ብለው እንዲጸልዩ አስተምሯቸዋል። ይሖዋ የሚል ስም ያለው በሰማይ የሚኖረው አባታችን ከልጁ የሚበልጥ እንደሆነ በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ ተገልጿል። ለምሳሌ ያህል ይሖዋ “ከዘላለም እስከ ዘላለም” ነው። ኢየሱስ ግን “ከፍጥረት ሁሉ በፊት በኵር” እንደሆነ መጽሐፍ ቅዱስ ይናገራል። ይሖዋ ከኢየሱስ የመብለጡን ሐቅ ኢየሱስ ራሱ ‘አብ ከእኔ ይበልጣል’ በማለት አስተምሯል። (ማቴዎስ 6:9፤ መዝሙር 90:1, 2፤ ቈላስይስ 1:15፤ ዮሐንስ 14:28) የሥላሴ መሠረተ ትምህርት እንደሚለው ግን አብና ወልድ “እኩል እግዚአብሔር” ናቸው።

አብ የወልድ የበላይና ራሱን የቻለ አካል ያለው የመሆኑ እውነታ ኢየሱስ ባቀረባቸው ጸሎቶች ላይ በግልጽ ተቀምጧል። ለምሳሌ ያህል ከመገደሉ በፊት “አባት ሆይ፤ ፈቃድህ ከሆነ፣ ይህችን ጽዋ ከእኔ ውሰድ፤ ነገር ግን የእኔ ፈቃድ ሳይሆን የአንተ ፈቃድ ይፈጸም” በማለት ያቀረበውን ጸሎት መጥቀስ ይቻላል። (ሉቃስ 22:42) የሥላሴ መሠረተ ትምህርት እንደሚለው እግዚአብሔርና ኢየሱስ “በባሕርይ አንድ” ከሆኑ የኢየሱስ ፈቃድ ወይም ፍላጎት እንዴት ከአብ ፈቃድ ሊለይ ይችላል?—ዕብራውያን 5:7, 8፤ 9:24

ከዚህም በላይ ይሖዋና ኢየሱስ አንድ ከሆኑ አንዳቸው የሚያውቁትን ነገር እንዴት ሌላው ላያውቅ ይችላል? ለምሳሌ ያህል ኢየሱስ ስለ ዓለም መጨረሻ ሲናገር “ነገር ግን ስለዚያች ቀን ወይም ስለዚያችም ሰዓት ከአብ በቀር፣ የሰማይ መላእክትም ቢሆኑ፣ ወልድም ቢሆን፣ ማንም አያውቅም” ብሏል።—ማርቆስ 13:32

ሥላሴና ቤተ ክርስቲያን

ኢየሱስም ሆነ የቀድሞ ክርስቲያኖች ስለ ሥላሴ አላስተማሩም። ቀደም ሲል እንደተጠቀሰው ሥላሴ “የቤተ ክርስቲያን ትምህርት ነው።” ዘ ሊቪንግ ፑልፒት መጽሔት ሥላሴን በተመለከተ ባወጣው የ1999 እትሙ ላይ “ሁሉም ሰው የሥላሴን መሠረተ ትምህርት የክርስትና መንፈሳዊ ትምህርት አድርጎ የሚገምትበት ጊዜ ሳይኖር አይቀርም” ብሏል። ይሁን እንጂ ትምህርቱ “መጽሐፍ ቅዱሳዊ” እንዳልሆነም አክሎ ተናግሯል።

ኒው ካቶሊክ ኢንሳይክሎፒዲያ (1967) ስለ ሥላሴ ሰፊ ማብራሪያ ከሰጠ በኋላ እንዲህ በማለት እውነታውን ይገልጻል:- “የሥላሴ ቀኖና ከሥር መሠረቱ ሲታይ በ4ኛው መቶ ዘመን መጨረሻ ላይ የተፈጠረ ትምህርት ነው። . . . ‘አንድ አምላክ በሦስት አካላት’ የሚለው ድንጋጌ ጠንካራ መሠረት ያገኘውና በክርስትና ሕይወት ብሎም ሃይማኖታዊ እምነት ውስጥ ሙሉ በሙሉ የተዋሃደው ከ4ኛው መቶ ዘመን በኋላ ነበር።”

ስዊዘርላንድ የሚገኘው የበርን ዩኒቨርሲቲ ፕሮፌሰር የሆኑት ማርቲን ቨርነ እንደሚከተለው ብለዋል:- “በማንኛውም የአዲስ ኪዳን ክፍል ውስጥ ኢየሱስ ሰው ስለመሆኑም ሆነ ስለ መሲሕነቱ በተነገረበት ቦታ ላይ ከእግዚአብሔር አብ ጋር ያለው ዝምድና የተገለጸበት መንገድ፣ ያለምንም ጥርጥር የበታች እንደሆነ ለመረዳት ያስችላል።” ኢየሱስና የጥንት ክርስቲያኖች ያምኑት የነበረው ነገር፣ ዛሬ አብያተ ክርስቲያናት ስለ ሥላሴ ከሚያስተምሩት ትምህርት ፈጽሞ የተለየ እንደሆነ በግልጽ ለማየት ይቻላል። ታዲያ ይህ ትምህርት የመነጨው ከየት ነው?

የሥላሴ እምነት ጥንታዊ መነሻ

መጽሐፍ ቅዱስ አስታሮት፣ ሚልኮም፣ ካሞሽና ሞሎክ የሚባሉትን ጨምሮ ሰዎች ያመልኳቸው ስለነበሩ በርካታ ወንድና ሴት አማልክት ይጠቅሳል። (1 ነገሥት 11:1, 2, 5, 7) የሚገርመው ደግሞ ጥንት የነበሩ በርካታ እስራኤላውያን በአንድ ወቅት በኣል እውነተኛ አምላክ ነው ብለው ያምኑ ነበር። ስለዚህ የይሖዋ ነቢይ የነበረው ኤልያስ “እግዚአብሔር አምላክ ከሆነ እግዚአብሔርን ተከተሉ፤ በኣል አምላክ ከሆነም በኣልን ተከተሉ” በማለት ሕዝቡ እውነቱን አውቆ ምርጫ እንዲያደርግ ጠይቆ ነበር።—1 ነገሥት 18:21

በተጨማሪም ኢየሱስ ከመወለዱ በፊት በሦስት በሦስት የተደራጁ ወይም በሦስትነት የተጣመሩ አረማውያን አማልክትን ማምለክ የተለመደ ነበር። የታሪክ ምሑር የሆኑት ዊል ዱራንት “የመለኰታዊ ሥላሴ ሐሳብ የመነጨው ከግብፅ ነው” ብለዋል። ጄምስ ሃስቲንግ፣ በኢንሳይክሎፒዲያ ኦቭ ሪሊጅን ኤንድ ኤቲክስ ላይ እንዲህ ብለው ጽፈዋል:- “ለምሳሌ በሕንዳውያን ሃይማኖት ውስጥ ብራህማ፣ ሲቫ እና ቪሽኑ የተባሉ የሦስት አማልክት ጥምረት አለ፤ በግብፃውያን ሃይማኖት ደግሞ ኦሳይረስ፣ አይሲስ እና ሆረስ የተባሉ የሦስት አማልክት ጥምረት እናገኛለን።”

ስለዚህ በርካታ አማልክት አሉ ማለት ነው። የጥንት ክርስቲያኖች ይህን ያምኑ ነበር? ኢየሱስንስ እንደ ሁሉን ቻይ አምላክ አድርገው ይመለከቱት ነበር?

[የግርጌ ማስታወሻዎች]

^ አን.12 በገጽ 31 ላይ የሚገኘውን “በአምላክ ስም መጠቀም ይገባናል?” የሚለውን ርዕስ ተመልከት።

^ አን.14 ኢየሱስ ከሞተ ከጥቂት መቶ ዓመታት በኋላ የተዘጋጀው የአትናቴዎስ ድንጋጌ ለሥላሴ እንዲህ የሚል ፍቺ ሰጥቶ ነበር:- “አብ እግዚአብሔር ነው፣ ወልድ እግዚአብሔር ነው፣ መንፈስ ቅዱስም እግዚአብሔር ነው። ይሁንና ሦስት አምላኮች ሳይሆኑ አንድ አምላክ ነው።”

[በገጽ 7 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

ግብፅ

ሆረስ፣ ኦሳይረስና አይሲስ የተባሉ ሦስት ጣምራ አማልክት፣ ከክርስቶስ ልደት በፊት በ2ኛው ሺህ ዓመት

[በገጽ 7 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

ፓልሚራ፣ ሶርያ

የጨረቃ አምላክ፣ የሰማያት ጌታና የፀሐይ አምላክ የተባሉ ሦስት ጣምራ አማልክት፣ አንደኛው ክፍለ ዘመን

[በገጽ 7 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

ሕንድ

አንድነት በሦስትነት ያለው የሂንዱ አምላክ፣ ከክርስቶስ ልደት በኋላ ሰባተኛው ክፍለ ዘመን ገደማ

[በገጽ 7 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

ኖርዌይ

ሥላሴ (አብ፣ ወልድና መንፈስ ቅዱስ) ከክርስቶስ ልደት በኋላ 13ኛው ክፍለ ዘመን ገደማ

[በገጽ 7 ላይ የሚገኝ የሥዕል ምንጭ]

ከላይ ያሉት ሁለት ፎቶዎች:- Musée du Louvre, Paris