በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

ተራሮችን ከጥፋት የሚታደጋቸው ማን ይሆን?

ተራሮችን ከጥፋት የሚታደጋቸው ማን ይሆን?

ተራሮችን ከጥፋት የሚታደጋቸው ማን ይሆን?

በኪርጊስታን (ማዕከላዊ እስያ) የምትገኘው ቢሽኬክ ከተማ በ2002 ለአራት ቀናት የቆየውን ዓለም አቀፉን የተራራ የመሪዎች ጉባኤ አስተናግዳለች። ተራሮችን በሚመለከት ጉዳይ ላይ ዓለም አቀፍ ስብሰባ ሲደረግ የመጀመሪያ ነበር። የስብሰባው አዘጋጆች 2002 “የተራሮች አስፈላጊነት እውቅና የሚያገኝበት አዲስ ዘመን መባቻ” እንደሚሆን ተስፋ አድርገው ነበር።

የመሪዎቹ ጉባኤ በአንድ ድምፅ የተራሮች ጥበቃ ጉዳይ ይመለከተኛል ለሚሉ ሁሉ የሚያገለግል መመሪያ የተካተተበትን “የቢሽኬክ የተራራ ፖሊሲ” አጽድቋል። ዋነኛ ዓላማውም “የተራራ ነዋሪዎችን የኑሮ ደረጃ ማሻሻል፣ የተራሮችን ሥነ ምሕዳር መጠበቅና ከተራሮች የሚገኘውን ሀብት በተሻለ ጥበብ መጠቀም ነበር።”

በዚህ ረገድ አንዳንድ መሻሻሎች ታይተዋል። በመላው ዓለም የተዘረጉ የብሔራዊ ፓርክ አውታሮች ልዩ ውበትና የብዝሐ ሕይወት ሀብት ለሚገኝባቸው ቦታዎች ጥበቃ ያደርጋሉ። በብዙ የዓለም ክፍሎች የአካባቢ ጥበቃ ድርጅቶች ይደርስ የነበረውን ውድመት በመግታት ረገድ በተወሰነ ደረጃ ተሳክቶላቸዋል። በኪርጊስታን ተራሮች የተዘረገፈውን የኑክሌር ዝቃጭ ለማስወገድ ቁርጥ ተነሳሽነት መታየቱ የቢሽኬክ የመሪዎች ጉባኤ ያስገኘው አንድ ውጤት ነው። ይህ እጅግ መርዘኛ የሆነ ቆሻሻ በማዕከላዊ እስያ ከሚኖሩ ሕዝቦች መካከል 20 በመቶ የሚሆኑትን የውኃ አቅርቦት አደጋ ላይ ጥሏል።

እንዲያም ሆኖ የዓለምን ተራሮች በመጠበቅ ረገድ ያጋጠመው ችግር ሊበገር የማይችል ሆኗል። ለምሳሌ በ1995 የካናዳ ባለ ሥልጣናት እስካሁን የቆዩትን የብሪቲሽ ኮሎምቢያ ደኖች ለመጠበቅ “የደን አጠቃቀም ሕግ” አውጥተው ነበር። ይሁን እንጂ ከዚያ ወዲህ የተደረገው ክትትል እንዳመለከተው የግንዲላና ጣውላ አምራች ኩባንያዎች በአብዛኛው ሕጉን የጣሱ ሲሆን በጣም ቁልቁለታማ በሆኑ አካባቢዎች የሚገኙ ዛፎችን ጨፍጭፈዋል። የእንጨት ኢንዱስትሪዎች ሕጉ በጣም ጥብቅ ሆኗል ብለው በማማረራቸው በ1997 ላላ እንዲል ተደርጓል።

ለተራሮች ጥበቃ እንቅፋት የሆነው የንግድ ድርጅቶች ፍላጎት ብቻ አይደለም። የቢሽኬኩ ጉባኤ ባወጣው የማጠቃለያ መግለጫ የተራሮችን ሥነ ምሕዳር ከሚሸረሽሩ ምክንያቶች መካከል ጦርነት፣ ድህነትና ረሃብ እንደሚገኙ አስታውቋል። እነዚህ የሥነ ምሕዳር ውድመት መሠረታዊ ምክንያቶች እስኪወገዱ ድረስ ተራሮችም ሆኑ የቀሩት የምድራችን ክፍሎች መጎሳቆላቸው አይቀርም።

አምላክ ለፍጥረቱ ያስባል

ሁኔታው ተስፋ የሚያስቆርጥ ይምሰል እንጂ የተሻለ ጊዜ ይመጣል ብለን ተስፋ የምናደርግበት ምክንያት አለ። ሁሉን የሚችለው አምላክ በፍጥረት ሥራው ላይ የሚደርሰውን ነገር በግዴለሽነት አይመለከትም። መጽሐፍ ቅዱስ “የተራራ ጫፎችም የእርሱ ናቸው” ይላል። (መዝሙር 95:4) በተጨማሪም በተራሮች ለሚኖሩ የእንስሳት ዝርያዎች ያስባል። መዝሙር 50:10, 11 እንደሚለው ይሖዋ “የዱር አራዊት ሁሉ፣ በሺ ተራራዎች ላይ ያለውም እንስሳ የእኔ ነውና። በየተራራው ያለውን ወፍ ሁሉ ዐውቃለሁ፤ በሜዳ የሚገኘው ተንቀሳቃሽ ፍጡር ሁሉ የእኔ ነው” ይላል።

ታዲያ አምላክ በከፍተኛ አደጋ ላይ የሚገኘውን የዓለማችን አካባቢ የሚያድንበት መንገድ አለው? አዎ፣ አለው። አምላክ ‘ፈጽሞ የማይፈርስ መንግሥት እንደመሠረተ’ መጽሐፍ ቅዱስ ይናገራል። (ዳንኤል 2:44) የዚህ ሰማያዊ መንግሥት ገዢ የሆነው ኢየሱስ ክርስቶስ ለምድርና በምድር ላይ ለሚኖሩ የሰው ልጆች ልዩ አሳቢነት አለው። (ምሳሌ 8:31) የእርሱ አገዛዝ በምድር ላይ ሰላም ያሰፍናል፣ ጭቆናንና ብዝበዛን ያስወግዳል፣ በዓለማችን ላይ የደረሰውን ጉዳት በሙሉ ይጠግናል።—ራእይ 11:18

እንዲህ ያለው መፍትሔ እውን ሆኖ ለማየት የምትናፍቅ ከሆነ ‘የአምላክ መንግሥት እንዲመጣ’ ዘወትር እንደምትጸልይ አያጠራጥርም። (ማቴዎስ 6:9, 10) እንዲህ ያለው ጸሎት መልስ ማግኘቱ አይቀርም። የአምላክ መንግሥት በቅርቡ የፍትሕ መጓደልን አስወግዶ በምድር ላይ የደረሰውን ጉስቁልና ሙሉ በሙሉ ይሽራል። ይህ በሚሆንበት ጊዜ ተራሮች በምሳሌያዊ ሁኔታ ‘ደስ ይላቸዋል።’—መዝሙር 98:8 የ1954 ትርጉም