በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

ተራሮች አለ እነርሱ መኖር የማንችለው ለምንድን ነው?

ተራሮች አለ እነርሱ መኖር የማንችለው ለምንድን ነው?

ተራሮች አለ እነርሱ መኖር የማንችለው ለምንድን ነው?

“ወደ ተራሮች ውጣና የሚሉህን አዳምጥ። የፀሐይ ብርሃን ወደ ዛፎች ጠልቆ እንደሚገባ የተፈጥሮ ሰላም ወደ ውስጥህ ሰርጎ ሲገባ ይሰማሃል። የሚያስጨንቁህ ነገሮች እንደ ደረቀ የዛፍ ቅጠል ከላይህ ሲረግፉ ነፋሳቱ መላ ሰውነትህን ያድሱልሃል፤ ሞገዶቹም ብርታት ይሰጡሃል።”—ጆን ሚውር፣ አሜሪካዊ ደራሲና የሥነ ተፈጥሮ ተመራማሪ

ን ሚውር ተራሮች ሰዎችን የመቀስቀስና ስሜታቸውን የማነሳሳት ኃይል እንዳላቸው የተገነዘበው ከአንድ መቶ ዓመት በፊት ነበር። ግርማ ሞገሳቸው አድናቆት ያሳድርብናል፤ በውስጣቸው የሚገኙት የዱር ፍጥረታት ልባችንን በደስታ ይሞሉታል እንዲሁም ሰላማዊነታቸውም ያዝናናናል። በተራሮች ውብ ትዕይንት ለመደሰትና መንፈሳቸውን ለማደስ በየዓመቱ በሚሊዮኖች የሚቆጠሩ ሰዎች ወደ ተራሮች ይጎርፋሉ። የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት የአካባቢ ፕሮግራም ዳይሬክተር የሆኑት ክላውስ ቶፕፈር “ተራሮች ለበርካታ ዘመናት የተለያዩ ማኅበረሰቦችንና ባሕሎችን መንፈስ የሚያድሱና የሚያስደንቁ ሆነው ኖረዋል” ሲሉ ተናግረዋል።

ይሁን እንጂ የተራሮች ሁኔታ አሳሳቢ መሆኑ አልቀረም። በቀደሙት ዘመናት ሰው ዝር የማይልባቸው አካባቢዎች ስለነበሩ ምንም ዓይነት ጉስቁልና ሳይደርስባቸው ኖረው ነበር። አሁን ግን ትልቅ አደጋ ተደቅኖባቸዋል። “በእርሻ መሬትና እንደ መንገድ ባሉት የልማት አውታሮች መስፋፋት እንዲሁም በሌሎች አዳዲስ ተጽዕኖዎች ምክንያት እነዚህ ጠፍ አካባቢዎች በመጥፋት ላይ ይገኛሉ” ሲል አንድ በቅርቡ የወጣ የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት መግለጫ አስታውቋል።

ተራራማ አካባቢዎች የሚሸፍኑት የዓለም ክፍል በጣም ሰፊ ነው። ከዓለም ሕዝብ መካከል ከግማሽ የሚበልጠው ኑሮው የተመካው ከተራሮች በሚያገኘው ነገር ነው። በተጨማሪም ተራሮች በሚሊዮን ለሚቆጠሩ ሰዎች በመኖሪያነት ያገለግላሉ። ተራሮች ከተንጣለለ ለምለም መስክ በስተ ጀርባ ሆነው ዓይን ከመማረክ የበለጠ አገልግሎት አላቸው። ለሰው ልጅ ደኅንነት ከሚያበረክቱት አስተዋጽኦ አንዳንዶቹን እስቲ እንመልከት።

ተራሮች በጣም አስፈላጊ የሆኑት ለምንድን ነው?

የውኃ ማከማቻ ናቸው። ትላልቆቹ ወንዞቻችንና በየግድቦቻችን የተከማቸው ውኃ የሚመነጩት ከተራሮች ነው። በሰሜን አሜሪካ በታላቁ የኮሎራዶ ወንዝና በሪዮ ግራንዴ ወንዝ የሚፈሰው ውኃ ሙሉ በሙሉ ሮኪ ማውንቴንስ ከሚባሉት የተራራ ሰንሰለቶች የሚመነጭ ነው። ከጠቅላላው የዓለም ሕዝብ ከግማሽ በላይ የሚሆነው የሚኖረው በደቡባዊና ምሥራቃዊ እስያ ነው። ከእነዚህ ሕዝቦች የአብዛኞቹ ኑሮ የተመካው በሂማሊያ፣ በካራኮራም፣ በፓሚርስ እና በቲቤት ግዙፍ የተራራ ሰንሰለቶች አካባቢ በሚወርደው ዝናብ ላይ ነው።

“የዓለማችን የውኃ ጋኖች የሆኑት ተራሮች በምድር ላይ ለሚገኘው ሕይወትና በሁሉም የዓለም ክፍሎች ለሚኖሩ ሰዎች ደኅንነት እጅግ አስፈላጊ ናቸው” የሚሉት ቶፕፈር በመቀጠል “በረጃጅሞቹ ተራሮች ጫፍ ላይ የሚደርሰው ነገር ሁሉ በቆላማ አካባቢዎች፣ በወንዞችና በውቅያኖሶች ውስጥ ሳይቀር በሚኖረው ሕይወት ላይ ተጽዕኖ ያሳድራል” በማለት አስረድተዋል። በብዙ አገሮች ተራሮች በክረምት ወራት የሚፈጠረውን በረዶ አዝለው ካቆዩ በኋላ በፀደይና በበጋ ወራት ቀስ በቀስ ይለቁታል። በበረሃማ የዓለም ክፍሎች የሚካሄዱ የመስኖ እርሻዎች በአብዛኛው የሚመኩት ራቅ ካሉ ተራራማ አካባቢዎች ቀልጠው በሚወርዱ በረዶዎች ነው። በብዙ ተራሮች ላይ በደን የተሸፈኑ ሸለቋማ አካባቢዎች ስለሚኖሩ እነዚህ ደኖች ከላይ የሚወርደውን ዝናብ ልክ እንደ ስፖንጅ መጥጠው ካቆዩ በኋላ ቀስ በቀስ ወደ ወንዞች እንዲፈስ ስለሚያደርጉ አውዳሚ የሆነ ጎርፍ እንዳይፈጠር ይከላከላሉ።

የዱር አራዊትና የብዝሐ ሕይወት መኖሪያ። ተራሮች ከሰዎች መኖሪያ አካባቢ ርቀው የሚገኙ በመሆናቸውና ለእርሻ ሥራም የማያመቹ በመሆናቸው የሰው ልጅ ጣልቃ ገብነት አይበዛባቸውም። በዚህ ምክንያት ተራራማ በሆኑ አካባቢዎች ረባዳ ከሆኑት አካባቢዎች የጠፉ የእንስሳትና የእጽዋት ዝርያዎች ይገኛሉ። ለምሳሌ በማሌዥያ የሚገኘው ተራራማው ኪናባሉ ብሔራዊ ፓርክ በስፋቱ ከኒው ዮርክ ከተማ የሚያንስ ሲሆን በውስጡ 4,500 የእጽዋት ዝርያዎች ይገኛሉ። በመላው ዩናይትድ ስቴትስ ከሚገኙት የእጽዋት ዝርያዎች አንድ አራተኛ የሚሆኑት ዝርያዎች በዚህ ብሔራዊ ፓርክ ውስጥ ይገኛሉ ማለት ነው። የቻይናው ጃይንት ፓንዳ፣ የአንዲሱ ኮንዶር እንዲሁም የማዕከላዊው እስያ ስኖው ሌፐርድ መኖሪያቸው ተራራ ነው። ሌሎቹም ይጠፋሉ ተብለው የሚሰጋላቸው ቁጥር ስፍር የሌላቸው ዝርያዎች የሚገኙት በተራራማ አካባቢዎች ነው።

ናሽናል ጂኦግራፊክ መጽሔት እንደሚለው “እስካሁን ከሚታወቁት የየብስ እጽዋትና የጀርባ አጥንት ያላቸው እንስሳት ዝርያዎች መካከል ከአንድ ሦስተኛ በላይ የሚሆኑት የምድራችን ሁለት መቶኛ በሚሆን አካባቢ ተወስነው እንደሚኖሩ” የሥነ ምሕዳር ሊቃውንት ይገምታሉ። እጅግ በጣም ብዙ የሆኑ ዝርያዎች ሰው ባልደረሰባቸው ጥቂት ቦታዎች ታጭቀው ይኖራሉ። እነዚህ ቦታዎች በአብዛኛው የሚገኙት በተራራማ አካባቢዎች ሲሆን ሁላችንም በውስጣቸው ካለው ብዝሐ ሕይወት ተጠቃሚዎች ሆነናል። ለብዙ ሕዝቦች ቀለብ ከሚሆኑ አዝርዕት መካከል አንዳንዶቹ በተራራማ አካባቢዎች ከሚበቅሉ የዱር እጽዋት የተገኙ ናቸው። በቆሎ ከሜክሲኮ ደጋ አካባቢዎች፣ ድንችና ቲማቲም ከፔሩ የአንዲስ ተራሮች እንዲሁም ስንዴ ከኮከሰስ ተራሮች የተገኙ ናቸው።

መዝናኛና ውበት። በተጨማሪም ተራሮች የተፈጥሮ ውበት መጠበቂያዎች ናቸው። ትንፋሽ ቀጥ የሚያደርጉ ፏፏቴዎች፣ የሚያማምሩ ሐይቆችና በውበታቸው ከፍተኛ አድናቆት ያተረፉ ውብ አካባቢዎች የሚገኙት በተራራማ አካባቢዎች ነው። ከዓለም ጥብቅ ክልሎች ከአንድ ሦስተኛ የሚበልጡት በተራራማ አካባቢዎች የሚገኙ መሆናቸው አያስደንቅም። እንዲሁም የቱሪስት ማዘውተሪያ አካባቢዎች ሆነዋል።

ራቅ ብለው የሚገኙ ብሔራዊ ፓርኮች ሳይቀሩ ከመላው ዓለም በሚመጡ በሚሊዮን የሚቆጠሩ ቱሪስቶች ይጎበኛሉ። በሰሜን አሜሪካ በከፍታው አንደኛ የሆነውን ማውንት ማከንሊን ለማየት በአላስካ ወደሚገኘው ደናሊ ብሔራዊ ፓርክ በርካታ አገር ጎብኚዎች ከመላው ዓለም ይመጣሉ። ታላላቆቹን የኪሊማንጃሮና የሜሩ ተራሮች ወይም በእነዚህ ሁለት ተራሮች መካከል የሚሰማራውን የዱር አራዊት መንጋ ለማየት ታላቁን ስምጥ ሸለቆ የሚጎበኙ ሰዎች በጣም ብዙ ናቸው። ምንም እንኳ በቂ ቁጥጥር ያልተደረገበት የቱሪስቶች ፍልሰት በቀላሉ ሊጎዳ በሚችለው ሥነ ምሕዳር ላይ አደጋ ሊያስከትል ቢችልም በርካታ የተራራማ አካባቢ ማኅበረሰቦች ከቱሪስቶቹ ፍልሰት ተጠቃሚዎች ሆነዋል።

በተራራማ አካባቢዎች ተጠብቆ የኖረ እውቀት

ባለፉት መቶ ዘመናት በተራራማ አካባቢዎች የሚኖሩ ሰዎች የመኖሪያ አካባቢያቸው አመቺ ባይሆንም እንዴት ኑሯቸውን አሸንፈው እንደሚኖሩ ተምረዋል። የተራራ ነዋሪዎች መሬታቸው ከሁለት ሺህ ዓመት ግብርና በኋላ እንኳን ለምነቱን እንዳያጣ ያስቻለ እርከን ሠርተዋል። የደጋ አካባቢዎችን ተቋቁመው ሊኖሩ የሚችሉ እንደ ላማና ያክ ያሉትን የዱር እንስሳት አላምደው የቤት እንስሳት አድረገዋል። የተራራ ነዋሪዎች ያካበቱት ባሕላዊ እውቀት ለሁላችንም ኑሮ አስፈላጊ የሆኑትን ተራሮች ጠብቆ ለማቆየት እጅግ አስፈላጊ ሊሆን ይችላል።

የወርልድ ዋች ኢንስቲትዩት ባልደረባ የሆኑት አለን ቴን ደርኒንግ “በሁሉም ክፍለ ዓለማት ሥልጣኔ ያልደረሰባቸው ሰፊ አካባቢዎች የሚጠበቁት በአካባቢው ነዋሪዎች ብቻ ነው። እነዚህ ሰዎች የዘመናዊ ሳይንስ ቤተ መጻሕፍት እንኳን ሊተካከሉ የማይችሉት የእውቀት ክምችት አላቸው” ብለዋል። ይህ የእውቀት ክምችትም ቢሆን እንደ ሌሎቹ የተራራማ አካባቢ ሀብቶች ጥበቃ ሊደረግለት ይገባል።

የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት የአካባቢ ጥበቃ ፕሮግራም 2002ን ዓለም አቀፍ የተራሮች ዓመት ሲል ሰይሞታል። የዚህ ፕሮግራም አደራጆች የሰው ልጅ ሕልውና ምን ያህል በተራሮች ላይ የተመካ መሆኑን ለማስገንዘብ “ሁላችንም የተራራ ሰዎች ነን” የሚል መፈክር አውጥተዋል። የዓለም ተራሮች እንዴት ያለ ችግር እንደተደቀነባቸውና እነርሱንም ለመጠበቅ የሚያስችል መፍትሔ መፈለግ አስፈላጊ እንደሆነ ለማስገንዘብ ጥረዋል።

ጉዳዩ ይህን ያህል አሳሳቢ እንደሆነ ተደርጎ መታየቱ በእርግጥም ተገቢ ነው። በኪርጊስታን በተደረገው የቢሽኬክ 2002 የዓለም ተራሮች የመሪዎች ስብሰባ ላይ ዋነኛው ተናጋሪ “ተራሮች የበርካታ የተፈጥሮ ሀብት ምንጮች እንደሆኑ ተደርገው ቢታዩም ለእነዚህ አካባቢዎች ነዋሪዎችና ለሥነ ምሕዳራቸው ዘላቂነት በቂ ትኩረት አይሰጥም” ብለዋል።

የዓለም ተራራማ አካባቢዎችም ሆኑ በዚያ የሚኖሩ ሰዎች ከሚያጋጥሟቸው ችግሮች አንዳንዶቹ ምንድን ናቸው? እነዚህስ ችግሮች ሁላችንንም የሚነኩት እንዴት ነው?