በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

ትልቅ ደረጃ ላይ ለመድረስ መመኘት ስህተት ነው?

ትልቅ ደረጃ ላይ ለመድረስ መመኘት ስህተት ነው?

የመጽሐፍ ቅዱስ አመለካከት

ትልቅ ደረጃ ላይ ለመድረስ መመኘት ስህተት ነው?

“ዝነኛ መሆን፣ ሀብት ማካበትም ሆነ ሥልጣን መያዝ ምን ስህተት አለው?” ይህ ጥያቄ የቀረበው አንድ ሃይማኖታዊ ማኅበር “ኤቲካል ዳይለማስ” በሚል ርዕስ ባወጣው ሪፖርት ላይ ነበር። መግለጫው አምላክ ለአብርሃም “ታላቅ ሕዝብ አደርግሃለሁ፤ ደግሞም እባርክሃለሁ፤ ስምህን ገናና አደርገዋለሁ” በማለት የተናገራቸውን ቃላትም ጠቅሷል።—ዘፍጥረት 12:2

ሪፖርቱ “ትልቅ ደረጃ ላይ ለመድረስ የሚደረገው ጥረት ሌሎችን የሚጎዳ መሆን [እንደሌለበት]” ከገለጸ በኋላ “ዓላማዬን ከግብ ለማድረስ እኔው ራሴ ካልታገልኩ ሌላ ማን ይታገልልኛል?” በማለት የተናገሩ አንድ የመጀመሪያው መቶ ዘመን አይሁዳዊ ምሑርን ይጠቅሳል። አክሎም “በሕይወታችን ስኬታማ ለመሆን አቅማችን የሚፈቅደውን ሁሉ ካላደረግን ሌላ ማንም ይህን ሊያደርግልን አይችልም” በማለት ይደመድማል። ትልቅ ደረጃ ላይ የመድረስ ምኞት አምላክን ለማገልገል ለሚፈልጉ ሰዎች የሚያስከትለው ችግር አለ? አቅም የፈቀደውን ሁሉ ለማድረግ መጣር ምን ነገሮችን ያጠቃልላል? ትልቅ ደረጃ ላይ ለመድረስ መመኘት ስህተት ነው? በዚህ ረገድ የመጽሐፍ ቅዱስ አመለካከት ምንድን ነው?

አብርሃም ትልቅ ደረጃ ላይ የመድረስ ምኞት ነበረው?

አብርሃም የላቀ የእምነት ሰው እንደነበረ መጽሐፍ ቅዱስ ይገልጻል። (ዕብራውያን 11:8, 17) አምላክ አብርሃምን ታላቅ ሕዝብ እንደሚያደርገውና ስሙንም ገናና እንደሚያደርገው ቃል ሲገባለት ትልቅ ደረጃ ላይ የመድረስ ምኞት እንዲኖረው ማበረታታቱ አልነበረም። አምላክ ይህን ሲል በአብርሃም በኩል የሰውን ዘር የመባረክ ዓላማ እንዳለው መናገሩ ሲሆን ይህም በሰብዓዊ ሁኔታ ትልቅ ደረጃ ላይ ከመድረስ ይበልጥ ዋጋ ያለው ነገር ነበር።—ገላትያ 3:14

አብርሃም ለአምላክ ያደረ ሰው ሆኖ ለመኖር ሲል በዑር ባለጸጋ ሆኖ በምቾት የመኖር አጋጣሚውን ትቷል። (ዘፍጥረት 11:31) በኋላም ለሰላም ሲል ከአካባቢው ምርጥ የሆነውን ሥፍራ ለወንድሙ ልጅ ለሎጥ አሳልፎ በመስጠት ሥልጣኑንና መብቱን በፈቃደኝነት ለቋል። (ዘፍጥረት 13:8, 9) በመጽሐፍ ቅዱስ ዘገባ ላይ አብርሃም ትልቅ ደረጃ ላይ የመድረስ ምኞት እንደነበረው የተገለጸበት አንድም ቦታ የለም። ከዚህ ይልቅ በአምላክ ዘንድ እንደ እውነተኛ ‘ወዳጅ’ ተደርጎ እንዲወደድ ያደረጉት እምነቱ፣ ታዛዥነቱና ትሕትናው ናቸው።—ኢሳይያስ 41:8

ለማዕረግ፣ ለዝናና ለሥልጣን የተለየ አመለካከት መያዝ

በአማርኛ ትልቅ ደረጃ ላይ የመድረስ ምኞት የሚል ፍቺ የተሰጠው አምቢሽን የተሰኘው የእንግሊዝኛ ቃል በዌብስተርስ መዝገበ ቃላት ላይ “ማዕረግ፣ ዝናና ሥልጣን ለማግኘት መቋመጥ” የሚል ፍቺ ተሰጥቶታል። በጥንት ዘመን የኖረው ንጉሥ ሰሎሞን እጅግ ባለጸጋ የነበረ ከመሆኑም ባሻገር ማዕረግ፣ ዝናና ሥልጣን ነበረው። (መክብብ 2:3-9) ይሁን እንጂ ልብ ሊባል የሚገባው ጉዳይ ሰሎሞን እነዚህን ነገሮች ለማግኘት አልሞ ያልተነሳ መሆኑ ነው። ሰሎሞን ንግሥናውን ሲወርስ አምላክ የፈለገውን ነገር እንዲለምን ግብዣ አቅርቦለት ነበር። ሰሎሞን ታዛዥ ልብና የአምላክን የተመረጠ ሕዝብ መምራት ይችል ዘንድ የሚያስፈልገውን ማስተዋል እንዲሰጠው አምላክን በትሕትና ጠየቀ። (1 ነገሥት 3:5-9) በኋላም ያገኘውን የተሟላ ብልጽግናና ሥልጣን ከዘረዘረ በኋላ ሰሎሞን “ሁሉም ከንቱ፣ ነፋስንም እንደ መከተል ነበር” በማለት ተናግሯል።—መክብብ 2:11

ሰሎሞን ሰዎች አቅማቸው የሚፈቅደውን ሁሉ ለማከናወን ጥረት ስለማድረጋቸውስ የተናገረው ነገር አለ? በተወሰነ መጠን የተናገረው ነገር አለ ለማለት ይቻላል። በሕይወቱ ውስጥ ያጋጠሙትን የተለያዩ ነገሮች ካጤነ በኋላ የደረሰበት ድምዳሜ “እግዚአብሔርን ፍራ፤ ትእዛዛቱንም ጠብቅ፤ ይህ የሰው ሁለንተናዊ ተግባሩ ነውና” የሚል ነበር። (መክብብ 12:13) ሰዎች በሕይወታቸው ውስጥ አቅማቸው የሚፈቅደውን ሁሉ አድርገዋል ማለት የሚቻለው ማዕረግ፣ ሀብት፣ ዝና ወይም ሥልጣን ለማግኘት ሲጥሩ ሳይሆን የአምላክን ፈቃድ ሲፈጽሙ ነው።

ትሕትና ክብር ያስገኛል

እርግጥ ነው፣ አይብዛ እንጂ ለራስ መልካም አመለካከት ማዳበር ምንም ስህተት የለበትም። መጽሐፍ ቅዱስ ባልንጀራችንን እንደራሳችን እንድንወድ ያዘናል። (ማቴዎስ 22:39) ምቾትና ደስታ መፈለግ ተፈጥሯዊ ነገር ነው። ይሁን እንጂ ቅዱሳን ጽሑፎች በትጋት መሥራትን፣ ትሕትናንና አቅምን ማወቅንም ያበረታታሉ። (ምሳሌ 15:33፤ መክብብ 3:13፤ ሚክያስ 6:8 NW) ሐቀኞች የሆኑና እምነት የሚጣልባቸው እንዲሁም ተግተው የሚሠሩ ሰዎች ብዙውን ጊዜ መታወቃቸው ስለማይቀር ጥሩ ሥራ የሚያገኙ ሲሆን አክብሮትም ያተርፋሉ። በእርግጥ ይህን አካሄድ መከተሉ የግል ጥቅም ለማግኘት ሲባል ሌሎችን መጠቀሚያ ለማድረግ ከመሞከር ወይም ሥልጣን ለማግኘት ከሌሎች ጋር ከመፎካከር የተሻለ ነው።

ኢየሱስ ደቀ መዛሙርቱ በሠርግ ድግስ ላይ ለራሳቸው የተመረጠ ቦታ እንዳይፈልጉ አስጠንቅቋቸዋል። እነርሱ በዝቅተኛ ቦታ እንዲቀመጡና ጋባዡ ከፍ ባለው ቦታ እንዲሆኑ እስኪጠይቃቸው እንዲጠብቁ መክሯቸዋል። ኢየሱስ በዚህ ሁኔታ ላይ የሚሠራውን መሠረታዊ ሥርዓት በግልጽ ሲናገር “ራሱን ከፍ ከፍ የሚያደርግ ሁሉ ዝቅ ይላል፤ ራሱንም ዝቅ ዝቅ የሚያደርግ ሁሉ ከፍ ይላል” ብሏል።—ሉቃስ 14:7-11

እውነተኛ ክርስቲያኖች ትልቅ ደረጃ ላይ ለመድረስ አይመኙም

መጽሐፍ ቅዱስ በትዕቢት ተነሳስቶ ትልቅ ደረጃ ላይ ለመድረስ መመኘት ከአለፍጽምና ጋር የተያያዘ እንደሆነ ያመለክታል። (ያዕቆብ 4:5, 6) ሐዋርያው ዮሐንስ በአንድ ወቅት ትልቅ ደረጃ ላይ የመድረስ ምኞት ነበረው። ትልቅ ቦታ ለማግኘት የነበረው ምኞት ከፍተኛ ከመሆኑ የተነሳ ከወንድሙ ጋር በመሆን በመንግሥቱ ውስጥ የተከበረ ቦታ እንዲሰጣቸው ዓይን አውጥተው ኢየሱስን ጠይቀውታል። (ማርቆስ 10:37) በኋላ ግን ዮሐንስ ይህን አመለካከቱን ለውጧል። እንዲያውም በሦስተኛ መልእክቱ ላይ “መሪ መሆን የሚወደው” በማለት የጠራውን ዲዮጥራጢስን አስመልክቶ ተግሣጽ ያዘሉ ኃይለኛ ቃላት ጽፏል። (3 ዮሐንስ 9, 10) በዛሬው ጊዜ ያሉ ክርስቲያኖችም የኢየሱስን ቃላት ተግባራዊ በማድረግ ራሳቸውን ዝቅ የሚያደርጉ ሲሆን ትልቅ ደረጃ ላይ የመድረስ ምኞትን ማስወገድ እንዳለበት የተማረውን የአረጋዊውን የሐዋርያው ዮሐንስን ምሳሌ ይከተላሉ።

እውነታውን ስንመለከት ደግሞ የአንድ ሰው ተሰጥኦ፣ ችሎታ፣ ጥሩ ተግባርና ትጋት የታከለበት ሥራ ግለሰቡ እውቅና ለማግኘቱ ሁልጊዜ ዋስትና እንደማይሆን እንገነዘባለን። እነዚህ ነገሮች አንዳንድ ጊዜ ከሰዎች ዘንድ ሽልማት ሲያስገኙ አንዳንድ ጊዜ ደግሞ አያስገኙም። (ምሳሌ 22:29፤ መክብብ 10:7) አንዳንድ ጊዜ እምብዛም ብቃት የሌላቸው ሰዎች በሥልጣን ቦታ ላይ ሲቀመጡ የበለጠ ችሎታ ያላቸው ችላ ይባላሉ። በዚህ ፍጽምና በጎደለው ዓለም ውስጥ ማዕረግና ሥልጣን የሚያገኙት ሰዎች ከሁሉ የተሻለ ብቃት ያላቸው ላይሆኑ ይችላሉ።

እውነተኛ ክርስቲያኖች ትልቅ ደረጃ ላይ የመድረስን ምኞት በተመለከተ ምን ማድረግ እንዳለባቸው ለመወሰን አይቸገሩም። በመጽሐፍ ቅዱስ የሠለጠነ ኅሊናቸው ይህን ዓይነቱን ምኞት እንዲያስወግዱ ይረዳቸዋል። በማንኛውም ሁኔታ ውስጥ ለአምላክ ክብር ሲሉ የቻሉትን ሁሉ ለማድረግ የሚጣጣሩ ሲሆን ውጤቱንም በእርሱ እጅ ይተዉታል። (1 ቆሮንቶስ 10:31) ክርስቲያኖች አምላክን በመፍራትና ትእዛዛቱን በመጠበቅ አቅማቸው የፈቀደውን ሁሉ ለማድረግ ይጣጣራሉ።

[በገጽ 24, 25 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

አምላክ አብርሃም ትልቅ ደረጃ ላይ የመድረስ ምኞት እንዲኖረው አበረታቶታል?