በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

“አምላክ ተብለው የሚጠሩ አማልክት”

“አምላክ ተብለው የሚጠሩ አማልክት”

“አምላክ ተብለው የሚጠሩ አማልክት”

ሐዋርያው ጳውሎስ በልስጥራን የሚኖር አንድ ሽባ ሰው ሲፈውስ ሕዝቡ “አማልክት በሰው ተመስለው ወደ እኛ ወርደዋል!” ብለው ጮኹ። ከዚያም ጳውሎስን ሄርሜን፣ አብሮት የነበረውን በርናባስን ደግሞ ድያ ብለው ሰየሟቸው። (የሐዋርያት ሥራ 14:8-14) የብር አንጥረኛው የኤፌሶኑ ድሜጥሮስ፣ ጳውሎስ በስብከቱ እንዲቀጥል ከተፈቀደለት ‘የታላቂቱ አምላክ የአርጤምስ መቅደስ ምናምን ሆኖ ይቆጠራል’ በማለት አስጠንቅቆ ነበር።—የሐዋርያት ሥራ 19:24-28 የ1954 ትርጉም

በዛሬው ጊዜ አብዛኛው ሕዝብ እንደሚያደርገው ሁሉ በመጀመሪያው መቶ ዘመን የነበሩ ሰዎችም “በሰማይም ሆነ በምድር አምላክ ተብለው የሚጠሩ አማልክት” ያመልኩ ነበር። እንዲያውም ጳውሎስ “ብዙ አማልክትና ብዙ ጌቶች አሉ” ብሎ ነበር። ይሁን እንጂ “ለእኛ ግን አንድ አምላክ አብ አለን” እንዲሁም “አንድ ጌታ ኢየሱስ ክርስቶስ አለን” በማለት ጨምሮ ተናግሯል።—1 ቆሮንቶስ 8:5, 6

ኢየሱስም አምላክ ተብሏል?

ኢየሱስ አምላክ እንደሆነ ፈጽሞ ተናግሮ ባያውቅም ይሖዋ የሾመው ገዥ እንደመሆኑ መጠን በኢሳይያስ ትንቢት ላይ “ኀያል አምላክ” እና “የሰላም ልዑል” ተብሏል። ኢሳይያስ “ለመንግሥቱ ስፋት፣ ለሰላሙም ብዛት ፍጻሜ የለውም” በማለት አክሎ ተናግሯል። (ኢሳይያስ 9:6, 7) ስለዚህ ኢየሱስ “ልዑል” ማለትም የታላቁ ንጉሥ የይሖዋ ልጅ እንደመሆኑ መጠን “ሁሉን የሚችል አምላክ” ያቋቋመው ሰማያዊ መንግሥት ገዥ ሆኖ ያገለግላል።—ዘፀአት 6:3

ይሁንና አንድ ሰው ‘ኢየሱስ “ኀያል አምላክ” ነው ሲባል ምን ማለት ነው? ሐዋርያው ዮሐንስ፣ ኢየሱስ ራሱ እግዚአብሔር እንደሆነ አልተናገረም?’ የሚል ጥያቄ ሊያነሳ ይችላል። ዮሐንስ 1:1 “በመጀመሪያ ቃል ነበረ፤ ቃልም ከእግዚአብሔር ጋር ነበረ፤ ቃልም እግዚአብሔር ነበረ” ይላል። አንዳንዶች በምድር ላይ ሕፃን ሆኖ ተወልዶ ኢየሱስ የተባለው “ቃል” ራሱ ሁሉን የሚችለው አምላክ ነው ብለው ይከራከራሉ። ይህ አባባላቸው እውነት ነው?

“ቃልም እግዚአብሔር ነበረ” የሚለው ሐሳብ ኢየሱስ ራሱ ሁሉን የሚችለው አምላክ እንደሆነ ያሳያል ከተባለ “ቃልም ከእግዚአብሔር ጋር ነበረ” ከሚለው ቀደም ሲል ካለው ሐሳብ ጋር ይጋጫል። ከአንድ ሰው “ጋር” ያለ ግለሰብ ያንኑ ሰው ሊሆን አይችልም። እንዲሁም ይህ የመጽሐፍ ቅዱስ ክፍል በመጀመሪያ የተጻፈው በግሪክኛ ቋንቋ እንደነበር ልብ ማለት ያስፈልጋል። “ቃልም ከእግዚአብሔር ጋር ነበረ” የሚለው ጥቅስ በመጀመሪያ ሲጻፍ “ከእግዚአብሔር” ከሚለው ቃል በፊት፣ ቃሉ ሁሉን ቻይ አምላክን እንደሚያመለክት የሚጠቁም አመልካች መስተኣምር ገብቷል። ይሁንና “ቃልም እግዚአብሔር [a god] ነበረ” በሚለው ዓረፍተ ነገር ውስጥ ከተጠቀሰው “እግዚአብሔር” ከሚለው ቃል በፊት አመልካች መስተኣምር አልገባም። በመሆኑም አንዳንድ የመጽሐፍ ቅዱስ ትርጉሞች ጥቅሱን “ሎጎስም [ቃልም] መለኮት ነበረ” በማለት ተርጉመውታል። (ኤ ኒው ትራንስሌሽን ኦቭ ዘ ባይብል) *

በግሪክኛው ጽሑፍ፣ በዮሐንስ 1:1 ላይ የሚገኘው “እግዚአብሔር” ተብሎ የተተረጎመው “አምላክ [a god]” የሚለው አገላለጽ በሌሎች የመጽሐፍ ቅዱስ ጥቅሶችም ውስጥ ጥቅም ላይ ውሏል። ለምሳሌ ያህል ቀዳማዊ ሄሮድስ አግሪጳ ንግግር ሲያቀርብ ተሰብስቦ ያዳምጥ የነበረው ሕዝብ ‘ይህስ የአምላክ [a god] ድምፅ ነው’ ብሎ ጮኾ ነበር። እንዲሁም ሐዋርያው ጳውሎስ መርዘኛ እባብ ነድፎት እንዳልሞተ የተመለከቱ ሰዎች “ይህስ አምላክ [a god] ነው” ብለዋል። (የሐዋርያት ሥራ 12:22፤ 28:3-6) ቃል እግዚአብሔር ሳይሆን “አምላክ [a god]” መባሉ ከግሪኩ ሰዋስውም ሆነ ከመጽሐፍ ቅዱስ ትምህርት ጋር የሚስማማ ነው።—ዮሐንስ 1:1

እስቲ ዮሐንስ በጻፈው ወንጌል የመጀመሪያ ምዕራፍ ላይ ስለ “ቃል” ምን ብሎ እንደገለጸ ተመልከት። “ቃልም ሥጋ ሆነ፤ በመካከላችንም አደረ፤ እኛም . . . ከአባቱ ዘንድ የመጣውን [የእግዚአብሔርን ሳይሆን] የአንድያ ልጅን ክብር አየን” ብሎ ጽፏል። ስለዚህ ሥጋ የሆነው “ቃል” ኢየሱስ የሚባል ሰው ሆኖ በምድር ላይ ኖሯል፤ ሰዎችም አይተውታል። ዮሐንስ “ከቶውንም እግዚአብሔርን ያየ ማንም የለም” በማለት ስለተናገረ ኢየሱስ ሁሉን ቻይ አምላክ ሊሆን አይችልም።—ዮሐንስ 1:14, 18

‘ታዲያ ቶማስ ከሞት የተነሳውን ኢየሱስን ባየው ጊዜ “ጌታዬ፤ አምላኬም!” ብሎ የጠራው ለምንድን ነው?’ የሚል ጥያቄ ይነሳ ይሆናል። ቀደም ሲል እንደተገለጸው ኢየሱስ መለኮታዊ በመሆኑ አምላክ ሊባል ይችላል፤ ይሁን እንጂ አብ አይደለም። ኢየሱስ ከቶማስ ጋር ከመነጋገሩ በፊት ለመግደላዊት ማርያም “ወደ አባቴና ወደ አባታችሁ፣ ወደ አምላኬና ወደ አምላካችሁ ዐርጋለሁ” ብሎ ነግሯት ነበር። ዮሐንስ ወንጌሉን ለምን ዓላማ እንደጻፈም አስታውስ። ስለ ቶማስ ከተገለጸበት ቦታ ሦስት ቁጥሮች አልፎ፣ ዮሐንስ “ኢየሱስ እርሱ ክርስቶስ፣ የእግዚአብሔርም ልጅ እንደ ሆነ ታምኑ ዘንድ” ብሎ ተናግሯል። እዚህ ላይ ኢየሱስ የእግዚአብሔር ልጅ እንጂ እግዚአብሔር አልተባለም።—ዮሐንስ 20:17, 28, 31

“የዚህ ዓለም አምላክ” ማን ነው?

በዓለማችን በርካታ አማልክት እንዳሉ እሙን ነው። ቀደም ብለን እንደተመለከትነው ከእነዚህ ውስጥ ጥቂቶቹ በመጽሐፍ ቅዱስ ላይ ተጠቅሰዋል። ቢሆንም በጥንት ጊዜ የነበሩ የይሖዋን ኃይል የተመለከቱ ሰዎች በግርምት “አምላክ እግዚአብሔር እርሱ እውነተኛ ነው! እግዚአብሔር እርሱ እውነተኛ አምላክ ነው!” ብለው ነበር። (1 ነገሥት 18:39) ይሁን እንጂ ኃይል ያለው ሌላም አምላክ አለ። መጽሐፍ ቅዱስ “የዚህ ዓለም አምላክ የማያምኑትን ሰዎች ልቡና አሳውሮአል” ይላል።—2 ቆሮንቶስ 4:4

ኢየሱስ ከሞተበት ዕለት ቀደም ብሎ በነበረው ምሽት ይህንን አምላክ “የዚህ ዓለም ገዥ” ብሎ በመጥራት ደቀ መዛሙርቱን ሦስት ጊዜ አስጠንቅቋቸዋል። ኢየሱስ ይህ ኃይለኛ ገዥ ወይም አምላክ “ወደ ውጭ ይጣላል” ብሏል። (ዮሐንስ 12:31፤ 14:30፤ 16:11) ይህ አምላክ ማን ነው? የሚገዛውስ የትኛውን ዓለም ነው?

ከዓመጸኛው መልአክ ከሰይጣን ዲያብሎስ ሌላ ማንም ሊሆን አይችልም። ይህንን እንዴት ማወቅ እንችላለን? ሰይጣን ኢየሱስን በፈተነው ጊዜ “የዓለምንም መንግሥታት ከነክብራቸው አሳየውና፣ ‘ወድቀህ ብትሰግድልኝ ይህን ሁሉ እሰጥሃለሁ’” ብሎት እንደነበር መጽሐፍ ቅዱስ ይናገራል። (ማቴዎስ 4:8, 9) ሰይጣን ለኢየሱስ ለመስጠት ያቀረበው የእርሱ ያልሆነውን ነገር ቢሆን ኖሮ ፈትኖታል ለማለት አይቻልም ነበር። ሐዋርያው ዮሐንስ “መላው ዓለምም በክፉው ሥር እንደ ሆነ እናውቃለን” ብሎ የተናገረው ለዚህ ነው።—1 ዮሐንስ 5:19

ኢየሱስ “የዚህም ዓለም ገዥ . . . ወደ ውጭ ይጣላል” በማለት የገባውን ቃል አስታውስ። (ዮሐንስ 12:31) እንዲያውም ሐዋርያው ዮሐንስ “ዓለምና ምኞቱ ያልፋሉ” በማለት ይህ ዓለም ወይም ሥርዓት ከነገዥው እንደሚወገድ ተንብዮአል። ይሁንና “የእግዚአብሔርን ፈቃድ የሚፈጽም . . . ለዘላለም ይኖራል” በማለትም ጨምሮ ተናግሯል። (1 ዮሐንስ 2:17) አሁን ደግሞ የእውነተኛውን አምላክ ክብራማ ዓላማዎችና ለእኛ የሚያስገኙልንን ጥቅም እንመልከት።

[የግርጌ ማስታወሻ]

^ አን.7 አመልካች መስተኣምርና (ቃልና) ማንነትን ወይም ምንነትን ለይቶ የማያመለክት ቃል ባላቸው እንዲሁም ትልልቅ ፊደላትን (Capital Letters) በሚጠቀሙ አንዳንድ ቋንቋዎች የተተረጎሙ የመጽሐፍ ቅዱስ ትርጉሞች ዮሐንስ 1:1ን እንደሚከተለው በማለት ተርጉመውታል:- “ቃል አምላክ [a god] ነበረ፣” “አምላክ [a god] ቃል ነበረ”። (በጄምስ ኤል ቶመኔክ የተዘጋጀው ዘ ኒው ቴስታመንት፣ በቤንጃሚን ዊልሰን የተዘጋጀው ዚ ኢምፋቲክ ዲያግሎት ኢንተርሊንየር ሪዲንግ)

[በገጽ 8, 9 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

የልስጥራን ነዋሪዎች ጳውሎስንና በርናባስን አማልክት ብለዋቸው ነበር

[በገጽ 8, 9 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

ኢየሱስ ለመግደላዊት ማርያም “ወደ አምላኬና ወደ አምላካችሁ ዐርጋለሁ” ብሏት ነበር