እንደምትወደኝ ለነገረችኝ ልጅ መልስ መስጠት ያለብኝ እንዴት ነው?
የወጣቶች ጥያቄ . . .
እንደምትወደኝ ለነገረችኝ ልጅ መልስ መስጠት ያለብኝ እንዴት ነው?
“ሱዛን እንደምትወደኝ ነገረችኝ፤ ጥያቄው ከእሷ መምጣቱ ለእኔ ምንም ችግር የለውም። እንዲያውም ጥሩ ሆኖልኛል።”—ጄምስ *
“አንድ ወንድ ለአንዲት ሴት የሚያሳየውን ስሜት በተመለከተ ሐቀኛ ካልሆነ ውጤቱ አስከፊ ሊሆን ይችላል።”—ሮቤርቶ
በቅርቡ አንዲት ወጣት ልትጠይቅህ የምትፈልገው ነገር እንዳለ ነገረችህ እንበል። ብዙውን ጊዜ የምትገናኙት ከሌሎች ጓደኞቻችሁ ጋር በብዛት አንድ ላይ ሆናችሁ ቢሆንም ተግባቢና ደስ የምትል ልጅ እንደሆነች ታውቃለህ። ይሁንና የነገረችህ ነገር አስደንግጦሃል። እሷ ከአንተ ጋር የፍቅር ጓደኝነት መመሥረት የምትፈልግ ሲሆን አንተም ተመሳሳይ ስሜት እንዳለህና እንደሌለህ ማወቅ ትፈልጋለች።
ለፍቅር የሚጠይቀው ወንድ ነው እንጂ ሴት መሆን የለባትም የሚል አመለካከት ያለህ ዓይነት ሰው ከሆንክ ነገሩ ፈጽሞ ያልጠበቅከው ሊሆንብህ ይችላል። እርግጥ አብዛኛውን ጊዜ ለፍቅር የሚጠይቀው ወንድ ቢሆንም ይህች ልጅ አንተን በመጠየቋ የጣሰችው ምንም የመጽሐፍ ቅዱስ መመሪያ አለመኖሩን አስታውስ። * ይህን መገንዘብህ ተገቢ ምላሽ እንድትሰጥ ሊረዳህ ይችላል።
አንተም ጉዳዩን ካሰብክበት በኋላ ከተቃራኒ ጾታ ጋር ፍቅር ለመጀመር ዕድሜህ ገና እንደሆነ ልትደመድም ትችላለህ። ወይም ደግሞ በወቅቱ አንተ ለልጅቷ ምንም ዓይነት ስሜት እንደሌለህ ይሰማህ ይሆናል። በተጨማሪም ልጅቷ ወዶኛል ብላ እንድታስብ የሚያደርጋት ነገር አድርገህ ወይም ተናግረህ ሊሆን እንደሚችል በማሰብ የጥፋተኝነት ስሜት ሊሰማህ ይችላል። ታዲያ ምን ማድረግ ይኖርብሃል? በመጀመሪያ ስሜቷን ግምት ውስጥ ማስገባት አለብህ።
ስሜቷን ግምት ውስጥ አስገባ
እንዲህ ባለ ሁኔታ ውስጥ ያለች ወጣት ምን ያህል ጭንቀት እንደምታሳልፍ አስብ። በአንተ ላይ ጥሩ ስሜት ለማሳደር በመጓጓት ስሜቷን አውጥታ ላንተ ለመናገር የምትጠቀምባቸውን ቃላት እየደጋገመች ስትለማመድ ቆይታ ሊሆን ይችላል። ምን መናገርና እንዴት ብላ መናገር እንዳለባት ካሰበች በኋላ ደግሞ ጥያቄዬን ባይቀበልስ የሚል ስሜት ይታገላታል። በመጨረሻ እንደምንም ብላ ያለ የሌለ ድፍረቷን በማሰባሰብና ጭንቀቷን ዋጥ በማድረግ በልቧ ያለውን ነገር ነገረችህ።
እዚህ ሁሉ ችግር ውስጥ ምን አስገባት? ምናልባት የወረት ፍቅር ይዟት ይሆናል። በሌላ በኩል ደግሞ አብዛኞቹ ሰዎች አስተውለውት የማያውቁትን መልካም ጠባይህን በማየት ለአንተ ልዩ አድናቆት አድሮባት ይሆናል። ስለዚህ የምትናገራቸው
ቃላት ከሌላ ሰው ሰምተሃቸው የማታውቃቸውን የምስጋና ቃላት ሊጨምሩ ይችላሉ።ይህን ሁሉ የምንለው በውሳኔህ ላይ ተጽዕኖ ለማሳደር ሳይሆን ውሳኔህን ስታሳውቃት በደግነት መሆን እንዳለበት ለማሳሰብ ነው። ጁሊ የተባለች አንዲት ወጣት “ሰውየው ለሴቲቱ ምንም ስሜት ባይኖረውም እንኳን ከቁም ነገር የሚጥፈው ሰው በመኖሩ ደስ ሊለው ይገባል። ስለዚህ እምቢታውን የሚገልጸው እንዲሁ አፉ እንዳመጣለት ሳይሆን በደግነትና ስሜቷን በማይጎዳ መንገድ መሆን አለበት” በማለት ተናግራለች። እስቲ እምቢታህን “በደግነትና ስሜቷን በማይጎዳ መንገድ” ወይም ሳታስቀይማት ልትገልጽላት ፈልገሃል እንበል።
ከዚህ በፊትም ጥያቄ አቅርባልህ እምቢ ብለሃት ከነበረስ? አሁንስ ልኳን መንገር አለብኝ ብለህ ልታስብ ትችል ይሆናል። ለዚህ ስሜት አትሸነፍ። ምሳሌ 12:18 “ግድ የለሽ ቃል እንደ ሰይፍ ይወጋል፤ የጠቢብ አንደበት ግን ፈውስን ያመጣል” በማለት ይገልጻል። ‘በጠቢብ አንደበት’ መናገር የምትችለው እንዴት ነው?
ስሜቷን ስለገለጸችልህና ለዚህ ቁም ነገር የምትበቃ እንደሆንክ አድርጋ ስለቆጠረችህ ልታመሰግናት ትችላለህ። ሳይታወቅህም እንኳን ቢሆን የተሳሳተ ግምት እንዲያድርባት በማድረግህ ይቅርታ ጠይቃት። አንተ ለእሷ እንዲህ ዓይነት ስሜት እንደሌለህ በግልጽ ሆኖም በደግነት ንገራት። የሰጠሃት ምላሽ ካልገባትና ይበልጥ ፈርጠም ብለህ መናገር የሚያስፈልግህ ከሆነም ሻካራ አነጋገርንና የሚያስከፉ ቃላት ከመጠቀም ተቆጠብ። የተፋጠጥከው በፍቅር ከቆሰለ ስሜቷ ጋር ስለሆነ ትዕግሥተኛ ሁን። ጥያቄውን ያቀረብከው አንተ ብትሆን ኖሮ እምቢታዋን ስሜትህን ሳትጎዳ በደግነት ብትገልጽልህ ደስ አይልህም ነበር?
ሆኖም የተሳሳተ ስሜት እንዲያድርብኝ ያደረግከው ሆን ብለህ ነው ብላ ልትከራከርህ ትችላለች። እንደምታፈቅራት እንዲሰማት ያደረጓትን አንዳንድ ድርጊቶችህን ጠቅሳ ትነግርህ ይሆናል። ‘አበባ የሰጠኸኝን ታስታውሳለህ?’ ወይም ‘ባለፈው ወር አብረን ስንሄድ የነገርከኝ ነገር ታዲያ ምንድን ነው?’ ልትልህ ትችላለች። እንዲህ አድርገህ ከሆነ ራስህን በሐቀኝነት መመርመር ሊኖርብህ ነው።
ሐቁን ተጋፈጥ
የድሮ ዘመን አሳሾች ብዙውን ጊዜ ያገኟቸውን አገሮች ድል አድርገው መያዝና እንደፈለጉ መበዝበዝ እንደሚችሉ ያስቡ እንደነበረ ሁሉ በዛሬው ጊዜም አንዳንድ ወንዶች ሴቶችን እንዳሻቸው ሊጠቀሙባቸው እንደሚችሉ ይሰማቸዋል። ማፍቀር መፈቀሩ ደስ ቢላቸውም የጋብቻ ኃላፊነት ውስጥ መግባት አይፈልጉም። በቃል ኪዳን ሳይታሰሩ እንዲሁ ሴቶችን በመማረክ በስሜታቸው ለመጫወት ይሞክራሉ። እንዲህ ዓይነቱ ወንድ የሴቷን ፍቅር የሚያተርፈው በማታለል ነው። አንድ ክርስቲያን ሽማግሌ “አንዳንድ ወጣት ወንዶች አንዴ ካንዷ ጋር ሌላ ጊዜ ደግሞ ከሌላዋ ጋር ይሆናሉ። በዚህ መንገድ በሴት ስሜት መጫወት ተገቢ አይደለም” ሲል አስተያየት ሰጥቷል። እንዲህ ዓይነቱ ራስ ወዳድነት የሚያስከትለው ውጤት ምንድን ነው?
“ትንታግ ወይም የሚገድል ፍላጻ እንደሚወረውር ዕብድ፣ ‘ቀልዴን እኮ ነው’ እያለ ባልንጀራውን የሚያታልል ሰውም እንደዚሁ ነው።” (ምሳሌ 26:18, 19) አንድ ወንድ በራስ ወዳድነት ተነሳስቶ አንዲትን ሴት ቢቀርብ የኋላ ኋላ ትክክለኛ ውስጣዊ ግፊቱን ትደርስበታለች። ከዚያም፣ ቀጥሎ የቀረበው ተሞክሮ እንደሚያሳየው አታላይነቱ ስሜቷን በእጅጉ ይጎዳዋል።
አንድ ወጣት ከአንዲት ወጣት ጋር ፍቅር መመሥረት
ፈለገ፤ ይሁን እንጂ እሷን የማግባት ፍላጎት አልነበረውም። ጥሩ ጥሩ ምግብ ቤቶች እየወሰደ ይጋብዛታል እንዲሁም የፓርቲ ዝግጅት ወዳለባቸው ቦታዎች ይዟት ይሄዳል። ከእሷ ጋር መሆን ደስ ይለው ነበር፤ እሷም ሊያገባት ያሰበ መስሏት ከእሱ የምታገኘው ትኩረት ያስደስታት ነበር። ሆኖም የእሱ ፍላጎት እንዲሁ ጓደኝነት ብቻ መሆኑን ስታውቅ ስሜቷ በጥልቅ ተጎዳ።አንተም በቀረበችህ ወጣት ላይ ሳታስበውም እንኳን ቢሆን የተሳሳተ ስሜት አሳድረህ ከሆነ ምን ማድረግ ይኖርብሃል? ራስህን ከተወቃሽነት ነፃ ለማድረግና የጉዳዩን አቅጣጫ ለማስለወጥ መሞከሩ ይብሱን ስሜቷን ሊያቆስለው ይችላል። “ኀጢአቱን የሚሰውር አይለማም፤ የሚናዘዝና የሚተወው ግን ምሕረትን ያገኛል” የሚለውን የመጽሐፍ ቅዱስ መሠረታዊ ሥርዓት ልብ በል። (ምሳሌ 28:13) ስለዚህ እውነቱን ተናገር። ለተፈጠረው አለመግባባት ኃላፊነቱን ውሰድ። ሆን ብለህ በስሜቷ ተጫውተህ ከሆነም ከባድ ስህተት መፈጸምህን አምነህ ተቀበል። ከልብ ይቅርታ ጠይቃት።
ይሁን እንጂ ይቅርታ ስለጠየቅህ ብቻ ጉዳዩ በዚያው ያበቃል ብለህ አትጠብቅ። ንዴቷ ለተወሰነ ጊዜ ላይወጣላት ይችላል። ያደረግከውን ነገር ለወላጆቿም ማስረዳት ይኖርብህ ይሆናል። ሌሎች መዘዞችንም መጋፈጥ ሊኖርብህ ይችላል። ገላትያ 6:7 “ሰው የሚዘራውን ያንኑ ያጭዳል” በማለት ይናገራል። ሆኖም ይቅርታ በመጠየቅና ጥፋትህን ለማካካስ የቻልከውን ሁሉ በማድረግ ሰላማዊ ኑሮዋን እንድትቀጥል ልትረዳት ትችላለህ። በሕይወትህ ያጋጠመህ ይህ ሁኔታ ለሌላ ጊዜ በሁሉም የሕይወትህ ዘርፍ ‘ከንፈሮችህ ሽንገላን እንዳይናገሩ’ እንድትጠብቅ ያስተምርሃል።—መዝሙር 34:13
መልስ ከመስጠትህ በፊት በጥሞና አስብ
ነገር ግን ልጅቱን ይበልጥ ለማወቅ የምትፈልግ ከሆነስ? ጉዳዩ ይህ ከሆነ ተቀጣጥሮ መጫወትና ፍቅርን መገላለጽ ለመዝናናት የሚደረጉ ነገሮች እንዳልሆኑ መገንዘብ ይኖርብሃል። ተቀጣጥረው የሚጫወቱ ወንድና ሴት አንዳቸው ለሌላው ያላቸው ስሜት ከጊዜ ወደ ጊዜ እየጠነከረ የሚመጣ ከሆነ በጋብቻ ወደ መተሳሰር እያመሩ መሆናቸውን የሚያመለክት ነገር ነው። ይህ ስሜት ከተጋቡ በኋላም ባልና ሚስት ሆነው እንዲተሳሰሩ ይረዳቸዋል። ታዲያ ይህን ማወቅህ እንዴት ሊነካህ ይገባል?
ስለዚህች ወጣት ካሰብክ በኋላ በብዙ መንገዶች ማራኪ እንደሆነች ትገነዘብ ይሆናል። በሩን ስለከፈተችልህ አንተም ይህ በር እንዳይዘጋ ትፈልግ ይሆናል። ቢሆንም በችኮላ ለጋብቻ ወደ መጠናናት ዘው ብለህ ከመግባት ይልቅ ሁለታችሁም በኋላ አሳዛኝ ሥቃይ ላይ እንዳትወድቁ ለመጠበቅ አሁኑኑ እርምጃዎችን ውሰድ።
አንድ ደረጃ ላይ ስትደርስ ልጅቷን የሚያውቋት ጥቂት ጎልማሳ ግለሰቦችን ማማከር ትፈልግ ይሆናል። እሷም አንተን በተሻለ ሁኔታ እንድታውቅህ ተመሳሳይ ነገር እንድታደርግ ሐሳብ ልታቀርብላት ትችላለህ። እነዚህ የጎለመሱ ሰዎች ስለ ጥሩና ደካማ ጎናችሁ ያላቸውን አስተያየት እንዲነግሯችሁ አንተ ስለ እሷ፣ እሷ ደግሞ ስለ አንተ መጠየቅ ይኖርባችኋል። በተጨማሪም ክርስቲያን ሽማግሌዎች ያላቸውን አስተያየት መጠየቅ ትችላላችሁ። በፍቅር ቀልባችሁን የሳበው ሰው በክርስቲያን ጉባኤ ውስጥ ጥሩ ስም ያለው መሆን አለመሆኑን ማወቅ ተገቢ ነው።
ይሁን እንጂ ‘ሌሎች ሰዎች በእኔ የግል ሕይወት ምን አገባቸው?’ ትል ይሆናል። እውነቱ ግን፣ እንደ ፍቅር ባለው የግል ጉዳይም እንኳን ቢሆን የሌሎችን አስተያየት ማግኘቱ ጥበብ ነው። እንዲያውም ምሳሌ 15:22 ‘ዕቅድ በብዙ አማካሪዎች ይሳካል’ በማለት ስለሚናገር በግል ጉዳይህም ቢሆን ሌሎችን ማማከር መጽሐፍ ቅዱስም የሚደግፈው ነገር ነው። የምታማክራቸው ጎልማሳ ሰዎች ለአንተ ውሳኔ አያደርጉልህም። ይሁን እንጂ የሚሰጡህ ‘ቅን ምክር’ ስለሌላው ሰውም ይሁን ስለራስህ ባሕርይ ለአንተ ያልታዩህ ነገሮች ግልጽ ሆነው እንዲታዩህ ሊያደርግ ይችላል።—ምሳሌ 27:9
በመግቢያችን ላይ የተጠቀሰው ጄምስ ያደረገው ይህንኑ ነበር። ራሱን ችሎ ለብቻው የሚኖር ቢሆንም ስለ ሱዛን ከወላጆቹ ጋር ተነጋገረ። ከዚያም ሊፈጥሩት ስላሰቡት የትዳር ጥምረት ምን አስተያየት እንዳላቸው ለመጠየቅ አንዳቸው ለሌላው የጎለመሱ ሰዎችን ስም ተለዋወጡ። ጄምስና ሱዛን አንዳቸው ስለሌላው ጥሩ አስተያየቶችን ከሰሙ በኋላ ጋብቻ መመሥረት ይችሉ እንደሆነ ለመጠናናት ተቀጣጥረው መጫወት ጀመሩ። አንተም በስሜት ከመጠላለፍህ በፊት ተመሳሳይ አካሄድ ብትከተል በመጨረሻ ስለምታደርገው ውሳኔ ይበልጥ የመተማመን ስሜት ሊኖርህ ይችላል።
ከሁሉ በላይ ወደ ይሖዋ ጸልይ። ተቀጣጥሮ መጫወት ወደ ጋብቻ የሚያደርስ እርምጃ ስለሆነ ከዚህች ወጣት ጋር የወጠንከው ትስስር ወደ ጋብቻ ያደርስ እንደሆነ እንድታስተውል እንዲረዳህ አምላክን ለምነው። ከሁሉ ይበልጥ፣ ሁለታችሁም ወደ እሱ የሚያቀርብ ውሳኔ እንድታደርጉ እንዲረዳችሁ ለምኑት። ለሁለታችሁም እውነተኛ ደስታ የሚያመጣው ይህ ነው።
[የግርጌ ማስታወሻዎች]
^ አን.3 አንዳንዶቹ ስሞች ተቀይረዋል።
^ አን.6 በኅዳር 2004 እና በጥር 2005 በወጡት የንቁ! መጽሔት እትሞች ላይ “የወጣቶች ጥያቄ” በተባለው አምድ ሥር አንዲት ሴት ላፈቀረችው ወንድ እንዴት ስሜቷን ልትገልጽ እንደምትችል የሚጠቁም ሐሳብ ቀርቧል።
[በገጽ 27 ላይ የሚገኝ ሥዕል]
ልጅቷን የማትፈልጋት ከሆነ የተሳሳተ ስሜት እንዳታሳድርባት ተጠንቀቅ