በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

ከዓለም አካባቢ

ከዓለም አካባቢ

ከዓለም አካባቢ

የከተሞች ሙቀት መጨመር በእጽዋት እድገት ላይ ተጽዕኖ ያሳድራል

በምሥራቃዊ ሰሜን አሜሪካ ላይ የተደረገ የሳተላይት ክትትል እንዳመለከተው ከከተሞች የሚወጣው ሙቀት በእጽዋት እድገት ላይ ተጽዕኖ ሳያሳድር እንዳልቀረ በሳይንስ ኒውስ ላይ የወጣ አንድ ዘገባ ይገልጻል። ዘገባው በከተሞች ውስጥ የሚገኙ እጽዋት ቀደም ብለው በፀደይ ወራት መጀመሪያ ላይ ያቆጠቁጡና እስከ በልግ ወራት መገባደጃ ድረስ ቅጠላቸው ሳይረግፍ እንደሚቆይ ያመለክታል። በአቅራቢያቸው ባሉ ገጠራማ አካባቢዎች ግን ሁኔታው እንደዚህ አይደለም። ሳይንስ ኒውስ እንደሚለው የከተሞች ሙቀት በአንድ የአምስት ወራት ጊዜ ውስጥ ከከተሞች 10 ኪሎ ሜትር ርቀው ከሚገኙ ገጠራማ አካባቢዎች በ2.28 ዲግሪ ሴንቲግሬድ በልጦ ተገኝቷል። በሰሜናዊ ፍሎሪዳና በደቡባዊ ካናዳ መካከል ቢያንስ 70 የሚያክሉ እያንዳንዳቸው ከ10 ካሬ ኪሎ ሜትር የሚበልጥ ስፋት ያላቸው ከተሞች አሉ። “ይህ መረጃ እንደሚያመለክተው ከተሞቹ በአካባቢው የሙቀት መጠን ላይ ተጽዕኖ አሳድረዋል” ይላል ሳይንስ ኒውስ።

የእንስሳት ጓደኝነት

ገበሬዎችና ከብት አርቢዎች ለብዙ ዘመናት ሲጠረጥሩት የነበረ ነገር ሲሆን አሁን ግን አንያ ቫስላፍስኪ የተባሉት ባዮሎጂስት ባደረጉት ሳይንሳዊ ጥናት ከብቶች በመንጎቻቸው ውስጥ ከሚገኙ ሌሎች ከብቶች ጋር የተለየ ጓደኝነት ሊመሠርቱ እንደሚችሉ አረጋግጠዋል። ቫስላፍስኪ ፈረሶች፣ አህዮች፣ ላሞችና በጎች በሚያርፉበት ጊዜ ተጠጋግተው በመተኛት፣ እርስ በርስ በመነካካት ወይም በሚመገቡበት ጊዜ መኗቸውን በማካፈል ወይም እርስ በርስ በመላላስ ጓደኝነታቸውን ያሳያሉ። ለምሳሌ በጎች ከሌላ እንስሳ ጋር የተጣሉ ጓደኞቻቸውን ራስ ያሻሻሉ። እንዲህ ማድረጋቸው በጎቹን የሚያረጋጋቸውና የሚያጽናናቸው ይመስላል ሲል ዲ ሳይት የተባለው የጀርመንኛ ጋዜጣ ገልጿል። አህዮች አብዛኛውን ጊዜ ከአንድ ጓደኛ በላይ የማይዙ ሲሆን ይህ ወዳጅነታቸው ግን እስከ ዕድሜ ልክ ይዘልቃል። ይሁን እንጂ ተመራማሪዎቹ ለእንስሳቱ ሰብዓዊ ባሕርይ እንዳይሰጡ ስለሚጠነቀቁ እንዲህ ያለው ማኅበራዊ ትስስር ስላለው ባሕርይም ሆነ ውጤት ግምታዊ አስተያየት ከመስጠት ተቆጥበዋል።

በላቲን አሜሪካ የደኖች መመናመን

የተባበሩት መንግሥታት የአካባቢ ፕሮግራም ያወጣው ሪፖርት በላቲን አሜሪካ በ13 ዓመት ጊዜ ውስጥ 50 ሚሊዮን ሄክታር ስፋት ያለው ወይም መላውን መካከለኛ አሜሪካ የሚያክል ስፋት ያለው ደን እንደተመነጠረ ይገልጻል። በብራዚል 23 ሚሊዮን ሄክታር፣ በሜክሲኮ 6.3 ሚሊዮን ሄክታር ስፋት ያለው ደን ከመውደሙም በላይ በሜክሲኮ 400,000 ሄክታር ስፋት ያለው የእርሻ መሬት ተሸርሽሮ ከአገልግሎት ውጭ ሆኗል። ሃይቲ፣ ኤል ሳልቫዶርና የሴንት ሉሲያ ደሴት በዚሁ ጊዜ ውስጥ ከደናቸው ከ46 እስከ 49 በመቶ የሚሆነውን አጥተዋል። የሜክሲኮ ራስ ገዝ ብሔራዊ ዩኒቨርሲቲ ሳይንሳዊ መጽሔት የሆነው ኮሞ ቬስ እነዚህ አኃዛዊ መረጃዎች “አስደንጋጭ ናቸው” ካለ በኋላ “በተለይ ከቀን ወደ ቀን በረሃ እየሆነች ከምትሄደው ዓለማችን እየጠፉ የሚገኙትን በሺህ የሚቆጠሩ እጽዋትና እንስሳት ስናስብ ይበልጥ አስደንጋጭ ይሆንብናል” ብሏል።

ክሮኒክ ፋቲግ ሲንድረም በተባለው ሕመም ለሚሰቃዩ ሰዎች አካላዊ እንቅስቃሴ የሚሰጠው ጥቅም

ክሮኒክ ፋቲግ ሲንድረም የተባለውን ሕመም መንስዔም ሆነ መድኃኒት ለማግኘት ሰፊ ጥናትና ምርምር ቢደረግም እስካሁን የሕክምናው ሳይንስ ሊደርስበት አልቻለም። ዘ ሜዲካል ጆርናል ኦቭ አውስትራሊያ ያወጣው ሪፖርት እንደገለጸው “ጥናት ከተደረገባቸው በርካታ ፀረ ቫይረስ፣ የሆርሞን፣ የጭንቀት ተከላካይና የሰውነት መከላከያ ቀስቃሽ መድኃኒቶች መካከል ይህ ነው የሚባል ውጤት ያሳየ የለም።” ይሁን እንጂ በእግር እንደመሄድ፣ ብስክሌት እንደመንዳትና ዋና የመሰሉ የአካላዊ እንቅስቃሴ ፕሮግራሞች ከሌሎች ሕክምናዎች የተሻለ ውጤት አስገኝተዋል። አንዳንድ የዚህ በሽታ ተጠቂዎች ብዙ አካላዊ እንቅስቃሴ ማድረግ ሕመማቸውን እንደሚያባብስባቸው ስለተገነዘቡ ከአካላዊ እንቅስቃሴ ይርቃሉ። ይሁን እንጂ ሚዛናዊ መሆን ያስፈልጋል። ሕመማቸውና አቅማቸው ከሚፈቅድላቸው መጠን ሳያልፉ በጥንቃቄ አካላዊ እንቅስቃሴ የሚያደርጉ በጭንቀት ደረጃ፣ በጤነኝነት ስሜት፣ በሥራ ችሎታቸውና በደም ግፊታቸው ረገድ ‘የጎላ መሻሻል’ እንደታየባቸው ዘ ሜዲካል ጆርናል ኦቭ አውስትራሊያ ዘግቧል። “የክሮኒክ ፋቲግ ሲንድረም ሕመምተኞች ዋነኛ የመከላከያና የሕክምና አቅጣጫ ከመጠን ያላለፈ አካላዊ እንቅስቃሴ ማድረግ መሆን ይገባዋል” በማለት ሪፖርቱ ይደመድማል።

ፓንዳዎችና ቀርከሃቸው

የለንደኑ ዘ ዴይሊ ቴሌግራፍ “የቻይናና የዓለም ዱር አራዊት ጥበቃ ድርጅት አርማ የሆነው ትልቁ ፓንዳ የተፈራውን ያክል ቁጥሩ አለመመናመኑን” ገልጿል። በዓለም የዱር አራዊት ጥበቃ ድርጅትና በቻይና መንግሥት የተደረገ አራት ዓመት የፈጀ ጥናት በዱር የሚኖሩ ፓንዳዎች ይገመት እንደነበረው ቁጥራቸው ከ1,000 እስከ 1,100 ብቻ ሳይሆን 1,590 እንደሚደርስ አረጋግጧል። ይህ ይበልጥ ትክክል የሆነ አኃዝ የተገኘው ቆጠራው የተካሄደባቸውን አካባቢዎች ትክክለኛ ካርታ ለማንሳት የሚያስችል ዘመናዊ ቴክኖሎጂ በመጠቀም ነው። የዚህ ቆጠራ ውጤት ለዱር አራዊት ጥበቃ ባለሞያዎች መልካም ዜና ቢሆንም በእንግሊዝ አገር በካምብሪጅ የሚገኘው የዓለም ጥበቃ ክትትል ማዕከል የትልቁ ፓንዳ ዋነኛ ምግብ የሆነው የቀርከሃ ተክል በደን መጨፍጨፍ ምክንያት የውድመት አደጋ እንደተደቀነበት አስጠንቅቋል። ቀርከሃዎች በደን መመናመን የሚጠቁበት ዋነኛ ምክንያት “የቀርከሃ ዝርያ ያላቸው የተለያዩ የቀርከሃ ዓይነቶች ከ20 እስከ 100 ዓመት በሚደርስ ጊዜ ውስጥ በአንድ ጊዜ አብበው በአንድ ጊዜ የሚሞቱ መሆናቸው ነው” ሲል የለንደኑ ዘ ጋርዲያን ዘግቧል።

ቢንቢ አባራሪ ጭሶች

በእስያ ሰዎች በሰፊው የሚገለገሉባቸው የቢንቢ ማባረሪያ ጭሶች በተለይ ለልጆች አደገኛ ሊሆኑ እንደሚችሉ የሕንዱ ዳውን ቱ ኧርዝ መጽሔት ዘግቧል። በአንደኛው ጥናት በዮናይትድ ስቴትስ የካሊፎርኒያ ዩኒቨርሲቲ ሳይንቲስቶች ቀስ በቀስ የሚናኘው የቢንቢ ማባረሪያ ጭስ በአካባቢው ያሉትን ሰዎች የሳንባ ካንሰር ለሚያመጡ መርዞች ያጋልጣል። በማደግ ላይ ባሉ አገሮች የሚኖሩ ሰዎች በትናንሽ ጎጆአቸው ውስጥ የቢንቢ ማባረሪያ ጭሶችን ያጨሳሉ። “በተጨማሪም ሰዎቹ በሚተኙበት ጊዜ መስኮታቸውን ይዘጋሉ” ሲሉ የጥናቱ አዘጋጆች ገልጸዋል። ሁለተኛው የማሌዥያና የዩናይትድ ስቴትስ ሳይንቲስቶች ያደረጉት ጥናት ሲሆን በዚህ ጥናታቸው ለስምንት ሰዓት የሚጨስ አንድ የቢንቢ ማባረሪያ ጥቅልል “ከ75 እስከ 137 ሲጋራዎች የሚያወጡትን ያህል መርዛማ ቅንጣቶች እንደሚያወጣ” አረጋግጠዋል። ባለሞያዎቹ እንደ ኒም ዛፍ ካሉ እጽዋት የሚሠሩ የቢንቢ ማባረሪያዎችን በአማራጭነት ያቀርባሉ። “እነዚህ አማራጮች ውጤታማና በጤና ላይ ጉዳት የማያስከትሉ ከመሆናቸውም በላይ ኪስ የሚያራቁቱ አይደሉም” በማለት ሪፖርቱ ገልጿል።

የፊልሞች ደረጃ አሰጣጥ ማሽቆልቆል

“የዛሬዎቹ ፊልሞች ከአሥር ዓመት በፊት ተመሳሳይ ደረጃ ከተሰጣቸው ፊልሞች የበለጠ አሰቃቂ ትርዒት፣ ወሲብና ጸያፍ ነገር የሚታይባቸው ናቸው።” ከዚህ ድምዳሜ የደረሱት በሃርቫርድ ዩኒቨርሲቲ የሕዝብ ጤና አጠባበቅ ተመራማሪዎች የአንዳንድ አገሮችን የፊልም ደረጃ አሰጣጥ ከመረመሩ በኋላ ነው። ጥናቱ ከ1992 እስከ 2003 ባሉት ዓመታት ለፊልሞች በተሰጠው ደረጃና በፊልሞቹ ይዘት መካከል ያለውን ዝምድና መዝኗል። የጥናቱ ውጤት ዕድሜን መሠረት ያደረጉ የፊልም ደረጃ አሰጣጦች ይበልጥ ልል እየሆኑ እንደመጡ አመልክቷል። ተመራማሪዎቹ “ወላጆች ተስማሚ የሆኑ ፊልሞችን ከልጆቻቸው ጋር ሆነው ለልጆቻቸው የመምረጥ፣ ፊልሞቹ የሚያሳድሩትን መጥፎ ተጽዕኖ ለመቋቋምም ሆነ በጎ ተጽዕኖዎችን ለማጠናከር መልእክቶቻቸውን ከልጆቻቸው ጋር የመወያየት ኃላፊነት አለባቸው” ሲሉ ደምድመዋል።