በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

አርማጌዶንን መፍራት ይኖርብሃል?

አርማጌዶንን መፍራት ይኖርብሃል?

የመጽሐፍ ቅዱስ አመለካከት

አርማጌዶንን መፍራት ይኖርብሃል?

“አርማጌዶን” ምንድን ነው? በቀላል አገላለጽ አርማጌዶን የሚለው ቃል የዓለም መሪዎች አምላክንና በኢየሱስ ክርስቶስ የሚመራውን መንግሥቱን በመቃወም የሚሰባሰቡበትን ሁኔታ ያመለክታል። የመጽሐፍ ቅዱስ ክፍል በሆነው በራእይ መጽሐፍ ውስጥ ሐዋርያው ዮሐንስ መንግሥታት አምላክን በመቃወም በምሳሌያዊ አገላለጽ አርማጌዶን በሚባል ሥፍራ እንደተሰባሰቡ በራእይ ተመልክቷል።

“አርማጌዶን” የሚለው ቃል በቅዱሳን ጽሑፎች ውስጥ የሚገኘው አንድ ጊዜ ብቻ ቢሆንም በዘመናችን በአንዳንድ ቋንቋዎች የተለያዩ ነገሮችን ለማመልከት በስፋት ጥቅም ላይ ይውላል። አርማጌዶን የኑክሌር እልቂትንና የኮምፒውተር ቫይረስን ጨምሮ ከፍተኛና አነስተኛ አደጋዎችን ለማመልከት ተሠርቶበታል። ስለ ዓለም መጨረሻ ወይም ስለ አርማጌዶን ዋዜማ የሚገልጹና ተወዳጅነት ያተረፉ በርካታ መጻሕፍት ተዘጋጅተዋል። በዚህ ርዕሰ ጉዳይ ላይ የተጻፈ አንድ ተከታታይ ልብ ወለድ ባለፉት አሥር ዓመታት ውስጥ ከ60 ሚሊዮን በሚበልጡ ቅጂዎች ተሸጧል።

አንዳንድ ሰዎች አርማጌዶንን ይፈሩታል። አሸባሪዎች፣ ጦርነት የሚወዱ አገሮች ወይም ከሰው ቁጥጥር ውጭ የሆኑ አደጋዎች በምድር ላይ ሕይወት ሊኖር ወደማይችልበት ደረጃ የሚያደርስ ዓለም አቀፋዊ እልቂት ሊያስከትሉ እንደሚችሉ ይሰማቸዋል። ሌሎች ደግሞ አምላክ በወሰነው ጊዜ ፕላኔታችንንና በላይዋ ያለውን ነገር ሁሉ በቁጣ እንደሚያጠፋው ያምናሉ። እንደዚህ ያሉ ነገሮችን መጠበቅ በእርግጥም ያስፈራል! ይሁን እንጂ ‘ሁሉን በሚችለው አምላክ ታላቅ ቀን የሚሆነውን ጦርነት’ በሚመለከት ሊኖረን የሚገባው ትክክለኛ ግንዛቤ ምንድን ነው?—ራእይ 16:14, 16

ምድር ትጠፋለች?

በአርማጌዶን የሚጠፉት ሁሉም ሰዎች አይደሉም። ይህን እንዴት እናውቃለን? መጽሐፍ ቅዱስ “ጌታ፣ በእውነት እያመለኩት የሚኖሩትን ከፈተና እንዴት እንደሚያድናቸውና ዐመፀኞችን እየቀጣ ለፍርድ ቀን እንዴት ጠብቆ እንደሚያቈያቸው ያውቃል” በማለት ዋስትና ይሰጠናል። (2 ጴጥሮስ 2:9) እንግዲያውስ አምላክ ተወዳዳሪ የሌለውን ኃይሉን ሙሉ በሙሉ እንደሚቆጣጠረው እርግጠኞች መሆን እንችላለን። አምላክ በአርማጌዶን በቁጣ የሚፈርደው ሉዓላዊነቱን በሚቃወሙ ሰዎች ላይ ብቻ ነው። በዚህ ጦርነት ላይ በስህተት የሚጠፋ ንጹሕ ሰው አይኖርም።—መዝሙር 2:2, 9፤ ዘፍጥረት 18:23, 25

አምላክ ‘ምድርን ያጠፏትን እንደሚያጠፋ’ መጽሐፍ ቅዱስ ይነግረናል። (ራእይ 11:18) እንግዲያውስ የይሖዋ አምላክ ዓላማ ፕላኔታችንን ማጥፋት እንዳልሆነ ግልጽ ነው። በዚህ ፈንታ የእርሱን አገዛዝ የሚቃወመውን ክፉ ሰብዓዊ ኅብረተሰብ ያስወግደዋል። ይህ ጥፋት አምላክ በኖኅ ዘመን ካመጣው የውኃ መጥለቅለቅ ጋር ይመሳሰላል።—ዘፍጥረት 6:11-14፤ 7:1፤ ማቴዎስ 24:37-39

‘የሚያስፈራ ቀን’

እርግጥ ነው፣ ስለ መጪው ጥፋት የሚገልጹት በርካታ የመጽሐፍ ቅዱስ ትንቢቶች የሚያስፈሩ ናቸው። ለምሳሌ ያህል፣ ነቢዩ ኢዩኤል “ታላቁና የሚያስፈራው የእግዚአብሔር ቀን” ምን እንደሚመስል ገልጿል። (ኢዩኤል 2:31) የአምላክ የጦር መሣሪያ ግምጃ ቤት በረዶ፣ ዐመዳይ፣ የመሬት መናወጥ፣ ተዛማች በሽታዎች፣ ዶፍ ዝናብ፣ የእሳትና የድኝ ዝናብ፣ ለሕይወት አስጊ የሆነ ሽብር፣ መብረቅ እንዲሁም ሥጋን የሚያበሰብስ መቅሠፍት እንደያዘ መጽሐፍ ቅዱስ ይናገራል። * (ኢዮብ 38:22, 23፤ ሕዝቅኤል 38:14-23፤ ዕንባቆም 3:10, 11፤ ዘካርያስ 14:12, 13) ከዚህም በላይ መጽሐፍ ቅዱስ በዚህ አስፈሪ ቀን የሚሞቱት ሰዎች ሬሳ ማዳበሪያ እንዲሆን ወይም አእዋፍና ሌሎች እንስሳት እንዲመገቡት ሜዳ ላይ ተጥሎ ምድርን ከዳር እስከ ዳር እንደሚሸፍናት ሥዕላዊ በሆነ መንገድ ይገልጻል። (ኤርምያስ 25:33, 34፤ ሕዝቅኤል 39:17-20) የአምላክ ጠላቶች በዚህ ጦርነት ወቅት ድንጋጤና ፍርሃት ይይዛቸዋል።—ራእይ 6:16, 17

ታዲያ ይህ ማለት ታዛዥ የሆኑ የእውነተኛው አምላክ አገልጋዮች በአርማጌዶን ስለሚፈጸሙት አስደናቂ ሁኔታዎች ፍርሃት ሊያድርባቸው ይገባል ማለት ነው? በጭራሽ፣ ምክንያቱም በምድር ላይ ያሉ የአምላክ አገልጋዮች በዚህ ጦርነት ተካፋይ አይሆኑም። ከዚህም በላይ ይሖዋ ጥበቃ ያደርግላቸዋል። ያም ሆኖ እውነተኛ አምላኪዎች አስፈሪ በሆኑት የአምላክ ኃይል መግለጫዎች መደነቃቸው አይቀርም።—መዝሙር 37:34፤ ምሳሌ 3:25, 26

ይሁን እንጂ ሐዋርያው ዮሐንስ ስለ አርማጌዶን ማስጠንቀቂያ ከመስጠትም በተጨማሪ “የዚህን መጽሐፍ የትንቢት ቃል የሚጠብቅ ብፁዕ [“ደስተኛ፣” NW] ነው” የሚለውን የሚያበረታታ ሐሳብ በመንፈስ አነሳሽነት መጻፉም ልብ ሊባል የሚገባው ቁም ነገር ነው። (ራእይ 1:3፤ 22:7) ታዲያ አንድ ሰው ስለ አርማጌዶን በማሰላሰል ደስተኛ ሊሆን ይችላል? ይህ ሊሆን የሚችለው እንዴት ነው?

አምላክ እርምጃ እንድንወስድ ያቀረበው ጥሪ

አንድ ኃይለኛ ዓውሎ ነፋስ እየተቃረበ ሲመጣ የአካባቢው ባለ ሥልጣናት ሕይወት ለማዳን ማስጠንቀቂያ ይሰጣሉ። ሁሉም ሰው ማስጠንቀቂያውን እንዲሰማ ለማድረግ ሲባል ፖሊሶች ማስጠንቀቂያ የሚሰጡ መሣሪያዎችን ይጠቀማሉ አሊያም በየቤቱ እየሄዱ ይናገራሉ። እንዲህ የሚደረግበት ዓላማ ሕዝብን ማሸበር ሳይሆን ሕይወታቸውን ለማዳን እርምጃ እንዲወስዱ መርዳት ነው። አስተዋይ የሆኑ ግለሰቦች ማስጠንቀቂያውን በጥሩ መንፈስ የሚቀበሉ ሲሆን እርምጃ በመውሰዳቸውም ይደሰታሉ።

በቅርብ ስለሚመጣው የአርማጌዶን “ዓውሎ ነፋስ” የሚገልጸው የማስጠንቀቂያ መልእክትም ከዚህ ጋር ተመሳሳይ ነው። (ምሳሌ 10:25) ይሖዋ በጽሑፍ በሰፈረው ቃሉ ውስጥ ስለዚህ ጦርነት ዝርዝር መረጃ ሰጥቶናል። ፍላጎቱም ሰዎችን ለማሸበር ሳይሆን በቂ ማስጠንቀቂያ ለመስጠትና ሰዎች ንስሐ ገብተው እርሱን ለማገልገል የማያወላውል ጥረት እንዲያደርጉ መርዳት ነው። (ዘካርያስ 2:2, 3፤ 2 ጴጥሮስ 3:9) እንዲህ ዓይነት እርምጃ የሚወስዱ ሰዎች ከጥፋት በመትረፍ ይባረካሉ። ከዚህ ለማየት እንደሚቻለው እየቀረበ ያለውን የአምላክ ጦርነት መፍራት አያስፈልገንም። ከዚህ ይልቅ “የእግዚአብሔርን ስም የሚጠራ ሁሉ፣ እርሱ ይድናል” የሚለውን ተስፋ በማመን መጪውን ጊዜ በልበ ሙሉነት ልንጠባበቅ እንችላለን።—ኢዩኤል 2:32

[የግርጌ ማስታወሻ]

^ አን.10 አንዳንድ የመጽሐፍ ቅዱስ ክፍሎች በምሳሌያዊ አነጋገር ወይም “ምልክት” የተጻፉ መሆናቸው ልብ ሊባል ይገባል። (ራእይ 1:1 NW) በመሆኑም በእነዚህ ትንቢቶች ላይ የተጠቀሱት ነገሮች ምን ያህል ቃል በቃል ጥቅም ላይ እንደሚውሉ በእርግጠኝነት መናገር አንችልም።

[በገጽ 22 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

ኃይለኛ ዓውሎ ነፋስ እየተቃረበ ሲመጣ የአካባቢው ባለ ሥልጣናት ሕይወት ለማዳን ማስጠንቀቂያ ይሰጣሉ

[በገጽ 23 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

ስለ አርማጌዶን የሚገልጸው አምላክ የሰጠው የማስጠንቀቂያ መልእክት ሰዎች ሕይወታቸውን ለማዳን እርምጃ እንዲወስዱ የሚቀርብ ጥሪ ነው