በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

አትክልቶችን መንከባከብ ለጤንነት ይጠቅማል

አትክልቶችን መንከባከብ ለጤንነት ይጠቅማል

አትክልቶችን መንከባከብ ለጤንነት ይጠቅማል

አትክልቶችን መንከባከብ ያስደስትሃል? ከዚህ የትርፍ ጊዜ ማሳለፊያህ የምታገኘው ደስታ ብቻ አይደለም። የለንደኑ ኢንዲፔንደንት ጋዜጣ እንዳሰፈረው ተመራማሪዎች “አትክልት መንከባከብ ጤንነትህን ለመጠበቅ፣ ውጥረትን ለማርገብ፣ የደም ግፊትን ለመቀነስ አልፎ ተርፎም ረዥም ዕድሜ ለመኖር እንደሚረዳ” አረጋግጠዋል።

ጌይ ሰርች የተባሉ ደራሲ “በሥራ ተጠምደን ውለን ድክም ብሎን ቤታችን ከገባን በኋላ በአትክልት ቦታችን ውስጥ የተወሰነ ጊዜ ማሳለፍ ትልቅ እፎይታ ያስገኛል” በማለት ተናግረዋል። አትክልቶችን መንከባከብ እርካታና ደስታ ከማስገኘቱም በላይ ስፖርት ከመሥራት በተሻለ መልኩ ሰውነታችን እንዲንቀሳቀስ ያደርጋል። እንዴት? ሰርች እንደሚሉት ከሆነ “እንደ መቆፈርና አፈር ማለስለስ የመሳሰሉት ረጋ ያሉ ግሩም እንቅስቃሴዎች ብስክሌት ከመንዳት ይልቅ ብዙ ካሎሪ እንዲቃጠል ያደርጋሉ።”

የአትክልት ሥፍራን መንከባከብ በተለይ በዕድሜ ለገፉት ትልቅ ጠቀሜታ አለው። አዳዲስ ተክሎች የሚያድጉበትን ወይም እምቡጥ የሚያወጡበትን ጊዜ መጠባበቃቸው የወደፊቱ ጊዜ ብሩህ ሆኖ እንዲታያቸው ያደርጋል። በተጨማሪም፣ የሮያል ሆርቲካልቸር ሶሳይቲ ባልደረባ የሆኑ ብሪጂድ ቦርድመን የተባሉ አንዲት ሐኪም የዕድሜ መግፋት ለሚያስከትለው “ሕመምና የተስፋ መቁረጥ ስሜት የአትክልት ቦታ ፍቱን መድኃኒት ነው” ሲሉ ተናግረዋል። በዕድሜ የገፉ ሰዎች ከጊዜ ወደ ጊዜ የሌሎች ጥገኛ እየሆኑ መሄዳቸው የተስፋ መቁረጥ ስሜት እንዲሰማቸው ያደርጋል። ዶክተር ቦርድመን እንዳመለከቱት ከሆነ “የሚተከለውን ነገር፣ የአትክልት ቦታውን ዲዛይንና የእንክብካቤውን ዓይነት ራሳችን መወሰናችን ሌሎች ነገሮችን የመቆጣጠር አልፎ ተርፎም ለሌሎች ነገሮች እንክብካቤ የማድረግ ተፈጥሯዊ ፍላጎታችንን ያረካልናል።”

ከአእምሮ ጤና ጋር በተያያዙ ችግሮች የሚሠቃዩ ሰዎች ብዙውን ጊዜ ውብና ሰላማዊ በሆነ አካባቢ መሥራታቸው ዘና ያለ ስሜት እንዲኖራቸው ያደርጋል። ከዚህም በላይ አበቦችን ወይም ለመብልነት የሚውሉ አትክልቶችን በማልማት ሌሎችን መርዳት መቻላቸው የመተማመን መንፈስ እንዲሰማቸውና ለራሳቸው ጥሩ ግምት እንዲኖራቸው ይረዳቸዋል።

ይሁን እንጂ ልምላሜ የተላበሱ ሥፍራዎች የሚጠቅሙት አልሚዎቹን ብቻ አይደለም። የቴክሳስ ዩኒቨርሲቲ ባልደረባ የሆኑት ፕሮፌሰር ሮጀር ኦልሪክ የውጥረት መንስኤዎችን ለማወቅ በተወሰኑ ሰዎች ላይ ጥናት አካሂደው ነበር። በውጤቱም ልምላሜ ወደተላበሱና በዛፎች ወደተከበቡ ቦታዎች የተወሰዱት ሰዎች ከሌሎቹ ይልቅ ቶሎ እንደተሻላቸው የልብ ምታቸውንና የደም ግፊታቸውን በመለካት ተገነዘቡ። በሌላ ተመሳሳይ ጥናት ማረጋገጥ እንደተቻለው በሆስፒታል ቀዶ ሕክምና ከተደረገላቸው በኋላ በማገገም ላይ የሚገኙ በሽተኞች ዛፎችን መመልከት በሚያስችል ክፍል ውስጥ መተኛታቸው ጠቅሟቸዋል። ሰዎቹ ከሌሎች ታማሚዎች ይልቅ “በቶሎ ማገገምና ሳይዘገዩ ወደ ቤታቸው መሄድ ችለዋል፤ ከዚህም በላይ ጥቂት የሕመም ማስታገሻ የተጠቀሙ ሲሆን ያን ያህልም ሲያማርሩ አልተሰሙም።”