በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

አንተስ የትኞቹን ፊልሞች ታያለህ?

አንተስ የትኞቹን ፊልሞች ታያለህ?

አንተስ የትኞቹን ፊልሞች ታያለህ?

ከቅርብ ዓመታት ወዲህ ወሲባዊ ድርጊቶችና አሰቃቂ ትርዒቶች የሚታዩባቸው እንዲሁም ጸያፍ ንግግሮች የሞሉባቸው ፊልሞች እንደ አሸን መፍላታቸው በተመልካቾች ዘንድ የተለያየ ስሜት ፈጥሯል። አንዳንዶች ወሲባዊ ድርጊቶች በፊልም መታየታቸው ፈጽሞ ነውር ነው ሲሉ ሌሎች ደግሞ ምንም ችግር የለውም፣ ይህ ራሱን የቻለ አንድ ኪነ ጥበብ ነው ብለው ይከራከራሉ። አንዳንዶች የዓመጽ ድርጊቶችን በፊልም ማሳየት ፈጽሞ ተገቢ አይደለም ሲሉ ሌሎች ደግሞ ተገቢ ነው ይላሉ። አንዳንዶች የብልግናና የስድብ ቃላት ማሰማት አስጸያፊ ነው ሲሉ በአንጻሩ ደግሞ ሌሎች ይህ የገሃዱ ዓለም እውነታ ነው ይላሉ። በአንዳንዶች ዘንድ ጸያፍ የሆነው አነጋገር በሌሎች ዘንድ ሐሳብን የመግለጽ ነፃነት እንደሆነ ተደርጎ ይታያል። የሁለቱም ወገኖች ክርክር ሲሰማ ከቃላት ስንጠቃ የበለጠ ቁም ነገር ያለው ላይመስል ይችላል።

ይሁን እንጂ የፊልሞች ይዘት እንደተራ የመከራከሪያ ጉዳይ ተደርጎ የሚታይ አይደለም። ወላጆችን ብቻ ሳይሆን የሥነ ምግባር እሴቶችን የሚያከብሩ ሰዎችን በሙሉ ሊያሳስብ የሚገባ ነገር ነው። አንዲት ሴት “ሕሊናዬ ተይ እያለኝ እስቲ ልሞክረው ብዬ ፊልም ቤት ከገባሁ በኋላ በጣም ይከፋኛል። ይህን የመሰለ ቆሻሻ ነገር በሚሠሩት ሰዎችም ሆነ በራሴ አፍራለሁ። ያዋረደኝን ነገር መልሼ እንዳየሁ ይሰማኛል” ብላለች።

መሥፈርቶችን ማስቀመጥ

የፊልሞች ይዘት አሳሳቢ መሆኑ አዲስ ነገር አይደለም። ፊልም መሥራት እንደተጀመረ ወሲባዊ ነገሮችና ወንጀል ነክ ድርጊቶች መታየታቸው ተመልካቾችን ያስቆጣ ነበር። በመሆኑም በ1930ዎቹ ዓመታት በዩናይትድ ስቴትስ በፊልሞች ላይ የሚታዩ ነገሮችን ይዘት በእጅጉ የሚገድብ ሕግ ወጣ።

ዘ ኒው ኢንሳይክሎፒዲያ ብሪታኒካ እንደሚለው ከሆነ “ይህ እጅግ ጨቋኝ የሆነ ሕግ ጤናማ የሆኑ ለአካለ መጠን የደረሱ ሰዎች የሚያደርጓቸውን ነገሮች በአብዛኛው የሚከለክል ነበር። ሕጉ ‘የፍቅር ስሜት’ መታየት እንደሌለበት የሚከለክል ከመሆኑም በላይ ዝሙት፣ ሕገ ወጥ ፍትወት፣ ማሽኮርመምና አስገድዶ መድፈር ለትረካው የግድ አስፈላጊ እስካልሆነና ድርጊቱን የፈጸሙት ሰዎች በፊልሙ መጨረሻ ላይ ቅጣት እንደተሰጣቸው እስካልተገለጸ ድረስ እንደተፈጸመ እንኳን የሚጠቁም ነገር መታየት እንደሌለበት ይናገራል።”

በኃይል ድርጊቶች ረገድም “ለታሪኩ አፈጻጸም የግድ አስፈላጊ ካልሆነ በስተቀር ፊልሞች ዝርዝር የወንጀል አፈጻጸሞችን፣ ሕግ አስከባሪዎች በወንጀለኞች ሲገደሉ የሚያሳዩ ትርዒቶችን፣ የጭካኔ ወይም የግድያ ድርጊቶችን ማሳየት ወይም ራስን የማጥፋት ድርጊቶች ሲፈጸሙ ማሳየት ተከልክለው ነበር። . . . በማንኛውም ሁኔታ ቢሆን የትኛውም የወንጀል ድርጊት እንደ ትክክለኛ ድርጊት ሆኖ መቅረብ አልነበረበትም።” ነገሩን ለማጠቃለል ሕጉ “የተመልካቾችን የሥነ ምግባር ደረጃ ዝቅ የሚያደርግ ፊልም መሠራት እንደሌለበት ይከለክል ነበር።”

ፈጽሞ ከመከልከል ይልቅ ደረጃ ወጣ

በ1950ዎቹ ዓመታት የሆሊዉድ ፊልም አዘጋጆች ዘመን ያለፈበት አሮጌ ሕግ ነው በማለት ሕጉን መተላለፍ ጀመሩ። በመሆኑም በ1968 ሕጉ ተሻረና ደረጃ በሚያወጣ ደንብ ተተካ። * በዚህ የደረጃ አወጣጥ ሥርዓት በፊልሞች ላይ የብልግና ድርጊቶችን በገሐድ ማሳየት የሚቻል ሲሆን ተመልካቾችን ስለ ይዘቱ በቅድሚያ የሚያስጠነቅቅ ምልክት ይደረግበታል። የአሜሪካ ተንቀሳቃሽ ፊልም ማኅበር ፕሬዚዳንት ሆነው ለአርባ ዓመታት ያህል ያገለገሉት ጃክ ቫሌንቲ እንደሚሉት ዓላማው “ወላጆች ልጆቻቸው የትኛውን ፊልም ማየት እንዳለባቸውና እንደሌለባቸው ለመወሰን የሚያስችላቸው የቅድሚያ ማስጠንቀቂያ መስጠት ነው።”

ደረጃ የማውጣት ሥርዓት ሲጀመር መጥፎ ፊልሞችን ገድቦ የያዘው ግድብ ተደረመሰ። ወሲብ፣ የጭካኔ ድርጊትና ጸያፍ ንግግር የሆሊዉድ ፊልሞችን ጽሑፍ አጥለቀለቁ። ለፊልሞች የተሰጠው አዲስ ነፃነት ለቁጥጥር ያስቸገረ ታላቅ ማዕበል ፈጠረ። ያም ቢሆን ተመልካቹ ሕዝብ የቅድሚያ ማስጠንቀቂያ ማግኘት ይችል ነበር። ነገር ግን ደረጃዎቹ ስለ ፊልሙ ማወቅ የሚያስፈልግህን ነገር በሙሉ ያሳውቃሉ?

ደረጃዎች ሊናገሩ የማይችሏቸው ነገሮች

አንዳንዶች ዓመታት እያለፉ ሲሄዱ ደረጃ የማውጣቱ ሥርዓት እጅግ ልል እየሆነ እንደሄደ ይሰማቸዋል። የሐርቫርድ የኅብረተሰብ ጤና አጠባበቅ ትምህርት ቤት ያደረገው ጥናት ይህንን አስተያየት ይደግፋል። ዛሬ ለልጆች ተስማሚ ናቸው የሚባሉ ፊልሞች ከአሥር ዓመት በፊት ከነበሩ ፊልሞች እጅግ የበዛ የብልግናና የጭካኔ ድርጊቶች እንደሚታዩባቸው አረጋግጧል። ጥናቱ በማጠቃለያው “ተመሳሳይ ደረጃ የተሰጣቸው ፊልሞች ሊታዩ በማይገባቸው ትርዒቶች ረገድ በመጠንም ሆነ በዓይነት ይለያያሉ” ብሏል። “ዕድሜን ብቻ መሠረት ያደረገ የደረጃ አወጣጥ ስለሚታዩት የጭካኔና የወሲብ ድርጊቶችም ሆነ ስለሚሰሙት ጸያፍ ንግግሮች እንዲሁም አግባብ ያልሆኑ ሌሎች ድርጊቶች ሁኔታ በቂ መረጃ አይሰጥም።” *

ልጆቻቸውን በግድየለሽነት ወደ ፊልም ቤቶች የሚልኩ ወላጆች በዛሬው ጊዜ ተስማሚ ናቸው የሚባሉትን ፊልሞች ይዘት ላያውቁ ይችላሉ። ለምሳሌ አንድ የፊልም ሐያሲ በዩናይትድ ስቴትስ ወጣቶች እንዲያዩት በተፈቀደ አንድ ፊልም ላይ ስለምትሠራ ዋነኛ ገጸ ባሕርይ የሚከተለውን ብለዋል። “ፈጽሞ ልቅ የሆነች፣ በየቀኑ ለመስከር፣ ዕጽ ያላግባብ ለመውሰድ፣ ቅጥ በሌለው ድግስ ላይ ለመገኘትና ካገኘችው ወንድ ሁሉ ጋር ልቅ ሩካቤ ሥጋ ለመፈጸም ወደኋላ የማትል የ17 ዓመት ልጅ ነች።” እንዲህ ያለው ይዘት አልፎ አልፎ ብቻ የሚታይ አይደለም። እንዲያውም ዘ ዋሽንግተን ፖስት ማጋዚን ለልጆች ተስማሚ ናቸው በተባሉ ፊልሞች ላይ በአፍ ስለሚደረግ ወሲብ ቢጠቀስ “እንደ እንግዳ ነገር” አይታይም ብሏል። ስለዚህ የአንድን ፊልም ይዘት ለመወሰን የተሰጠውን ደረጃ መመልከት ብቻውን በቂ እንደማይሆን ግልጽ ነው። ታዲያ የተሻለ መመሪያ ሊኖር ይችላል?

“ክፋትን ጥሉ”

የፊልሞች ደረጃ አወጣጥ በመጽሐፍ ቅዱስ የሠለጠነ ሕሊና የሚሰጠውን አመራር ሊተካ አይችልም። ክርስቲያኖች የመዝናኛ ምርጫን ጨምሮ ማንኛውንም ነገር በተመለከተ ውሳኔ ሲያደርጉ በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ በመዝሙር 97:10 ላይ የሚገኘውን “ክፋትን ጥሉ” የሚለውን ምክር ለመከተል ይጥራሉ። ክፋትን የሚጠላ ሰው አምላክ በሚጸየፋቸው ነገሮች መዝናናት ስህተት እንደሆነ ይገነዘባል።

በተለይ ወላጆች ልጆቻቸው እንዲመለከቱ በሚፈቅዷቸው ፊልሞች ረገድ ጠንቃቃ መሆን ይገባቸዋል። የተሰጠውን ደረጃ መልከት ማድረግ ብቻ በቂ እንደሆነ ማሰብ ትልቅ ሞኝነት ይሆናል። ለልጅህ ዕድሜ ተስማሚ ነው የሚል ደረጃ የተሰጠው ፊልም በወላጅነትህ የማትደግፈውን አስተሳሰብ የሚያራምድ ሊሆን ይችላል። ይህ ደግሞ ለክርስቲያኖች የሚያስደንቅ ሊሆን አይገባም። ምክንያቱም ዓለም የሚቀበለው አስተሳሰብና ድርጊት ከአምላክ መሥፈርቶች ጋር ይጋጫል። *ኤፌሶን 4:17, 18፤ 1 ዮሐንስ 2:15-17

ይህ ሲባል ግን ሁሉም ፊልሞች መጥፎ ናቸው ማለት አይደለም። ይሁን እንጂ ጥንቃቄ ማድረግ ተገቢ ነው። በዚህ ረገድ የግንቦት 22, 1997 ንቁ! (እንግሊዝኛ) “እያንዳንዱ ግለሰብ ጉዳዩን በጥንቃቄ ማመዛዘንና በአምላክም ሆነ በሰው ፊት ንጹሕ ሕሊና እንዲኖረው የሚያስችለውን ውሳኔ ማድረግ ይኖርበታል” ሲል አስተያየት ሰጥቷል።—1 ቆሮንቶስ 10:31-33

ተስማሚ መዝናኛ ማግኘት

ወላጆች ቤተሰባቸው የሚያየውን ፊልም በሚወስኑበት ጊዜ መራጮች መሆን የሚችሉት እንዴት ነው? በተለያዩ የዓለም ክፍሎች የሚገኙ ወላጆች የሰጧቸውን የሚከተሉትን አስተያየቶች ተመልከት። የእነርሱ አስተያየት ቤተሰብህ ጤናማ የሆነ መዝናኛ እንዲያገኝ በምታደርገው ጥረት ሊያግዝህ ይችላል።—በተጨማሪም “ሌሎች የመዝናኛ ዓይነቶች” የሚለውን ሣጥን ተመልከት።

በስፔይን የሚኖረው ኹዋን እንዲህ ይላል:- “ልጆቻችን ትናንሽ በነበሩበት ጊዜ ፊልም ቤት ሲገቡ ሁሌ እኔ ወይም ባለቤቴ አብረናቸው እንገባ ነበር። ፈጽሞ ብቻቸውን ወይም ከሌሎች ወጣቶች ጋር ሄደው አያውቁም። አሁን ወጣት ከሆኑ ወዲህ ደግሞ ለመጀመሪያ ጊዜ የሚታዩ ፊልሞችን አያዩም። ከዚህ ይልቅ ስለ ፊልሙ የቀረቡ ሂሶችን እስክናነብ ወይም የምናምናቸው ሌሎች ሰዎች የሚሰጡትን አስተያየት እስክንሰማ እንቆያለን። ከዚያም ይህን ፊልም ማየት እንዳለብንና እንደሌለብን በቤተሰብ ሆነን እንወስናለን።”

በደቡብ አፍሪካ የሚኖረው ማርክ ከወጣት ልጁ ጋር በፊልም ቤቶች ስለሚታዩት ፊልሞች በግልጽ ይነጋገራል። ማርክ “እኔና ባለቤቴ ልጃችን ስለ ፊልሙ ያለውን አስተያየት በመጠየቅ ውይይቱን እንጀምራለን” ይላል። አክሎም “ይህም አስተሳሰቡንና የሚያቀርባቸውን ምክንያቶች ለማዳመጥ ያስችለናል። በዚህም የተነሳ ሁላችንም አብረን ልናይ የምንችለውን ፊልም ለመምረጥ እንችላለን” በማለት ተናግሯል።

በብራዚል የሚኖረው ሮዠርዮም ለማየት ያሰቡትን ፊልም ከልጆቹ ጋር ሆኖ ይመዝናል። “የፊልም ገምጋሚዎች የሰጡትን አስተያየት አብሬያቸው አነባለሁ” ይላል። “አብሬያቸው ወደ ቪዲዮ ቤት እሄድና ጥሩ ፊልም እንዳልሆነ የሚጠቁሙ ምልክቶችን ከቪዲዮው ሽፋን ላይ እንዴት ማግኘት እንደሚችሉ አስተምራቸዋለሁ።”

በብሪታንያ የሚኖረው ማቲው ሊያዩ ስለፈለጉት ፊልም ከልጆቹ ጋር መነጋገር ጠቃሚ እንደሆነ አስተውሏል። “ከልጅነታቸው ጀምሮ ቤተሰባችን ሊያይ ስለፈለገው ፊልም በሚደረገው ውይይት ይካፈላሉ። አንድን ፊልም እንደማናይ ከወሰንን እኔና ባለቤቴ በደፈናው መታየት የለበትም ከማለት ይልቅ ምክንያታችንን እናስረዳቸዋለን” ብሏል።

በተጨማሪም አንዳንድ ወላጆች በኢንተርኔት አማካኝነት ስለተለያዩ ፊልሞች ጥናት ማድረጋቸው እንደጠቀማቸው ተናግረዋል። ስለ ፊልሞች ይዘት ዝርዝር ዘገባ የሚያቀርቡ በርካታ የኢንተርኔት ገጾች አሉ። እነዚህን በመጠቀም አንድ ፊልም ምን ዓይነት አስተሳሰብ ወይም ድርጊት እንደሚያራምድ ግልጽ ሥዕል ማግኘት ይቻላል።

የሠለጠነ ሕሊና ያለው ጥቅም

መጽሐፍ ቅዱስ “መልካሙን ከክፉው ለመለየት” የሠለጠነ ልቦና ስላላቸው ሰዎች ይናገራል። (ዕብራውያን 5:14) ስለዚህ የወላጆች ዓላማና ግብ ልጆቻቸው ለራሳቸው ለመወሰን በሚችሉበት ዕድሜ ላይ ሲደርሱ የሚመርጡትን መዝናኛ እንዲወስኑ የሚረዳቸውን መሥፈርት እንዲያገኙ ማስቻል ነው።

በይሖዋ ምሥክሮች መካከል የሚገኙ በርካታ ወጣቶች በዚህ ረገድ ከወላጆቻቸው ግሩም ሥልጠና አግኝተዋል። ለምሳሌ በዩናይትድ ስቴትስ የሚኖሩት ቢልና ቼሪ ከሁለት ወጣት ወንዶች ልጆቻቸው ጋር ፊልም ቤት መግባት ይወዳሉ። ቢል እንዲህ ይላል:- “አይተን ከወጣን በኋላ ፊልሙ ምን ዓይነት የሥነ ምግባር እሴቶችን እንዳስተማረንና ከእነዚህ እሴቶች ጋር እንስማማና አንስማማ እንደሆነ አብረን እንወያያለን።” እርግጥ ቢልና ቼሪ መራጭ መሆን እንደሚያስፈልግ ይገነዘባሉ። ቢል “አስቀድመን ስለፊልሙ እናነባለን። ያልጠበቅነው ተገቢ ያልሆነ ትዕይንት ከመጣ ተነስተን ለመውጣት አናፍርም” ሲል ተናግሯል። ቢልና ቼሪ ልጆቻቸው ውሳኔ በመስጠት ኃላፊነት እንዲካፈሉ በማድረግ ትክክልና ስህተት የሆነውን ነገር የመለየት ችሎታ እንዲያዳብሩ አድርገዋል። ቢል “ሊያዩ በሚመርጧቸው ፊልሞች ረገድ ጥሩ ውሳኔ በማድረግ ላይ ናቸው” በማለት ተናግሯል።

እንደ ቢልና ቼሪ በርካታ ወላጆች ልጆቻቸው በመዝናኛ ረገድ ጥሩውን ከመጥፎው የመለየት ችሎታቸውን እንዲያሠለጥኑ በመርዳት ላይ ናቸው። የፊልሙ ኢንዱስትሪ የሚያመርታቸው አብዛኞቹ ፊልሞች ጥሩ እንዳልሆኑ አይካድም። በሌላ በኩል ደግሞ ክርስቲያኖች በመጽሐፍ ቅዱስ መሠረታዊ ሥርዓቶች የሚመሩ ከሆነ ጤናማ የሆነና መንፈስን የሚያድስ መዝናኛ ማግኘት ይችላሉ።

[የግርጌ ማስታወሻዎች]

^ አን.9 በዓለም ዙሪያ የሚገኙ በርካታ አገሮች አንድ ፊልም ለየትኛው የዕድሜ ክልል የሚስማማ እንደሆነ የሚያሳይ ምልክት የማድረግ ሥርዓት አላቸው።

^ አን.12 ከዚህም በላይ በተለያዩ አገሮች የፊልም ደረጃዎችን ለማውጣት የሚሠራባቸው መሥፈርቶች ሊለያዩ ይችላሉ። በአንድ አገር ወጣቶች ሊያዩት የማይገባ ነው የተባለ ፊልም በሌላ አገር የተፈቀደ ሊሆን ይችላል።

^ አን.16 በተጨማሪም ክርስቲያኖች ለልጆችና ለወጣቶች ተብለው የሚዘጋጁ ፊልሞች የጥንቆላ፣ የመናፍስትነት ወይም ሌላ ዓይነት አጋንንታዊ ገጽታ ያላቸውን ድርጊቶች ሊያካትቱ እንደሚችሉ ልብ ማለት ይኖርባቸዋል።—1 ቆሮንቶስ 10:21

[በገጽ 12 ላይ የሚገኝ ሣጥን/ሥዕሎች]

“በቤተሰብ እንወስናለን”

“ልጅ ሳለሁ በቤተሰብ ሆነን ሲኒማ ቤት የመግባት ልማድ ነበረን። አሁን ግን ትልቅ ልጅ ስለሆንኩ ብቻዬን ገብቼ እንዳይ ተፈቅዶልኛል። ይሁን እንጂ ወላጆቼ ሲኒማ እንድገባ ከመፍቀዳቸው በፊት የፊልሙን ርዕስና ይዘት ማወቅ ይፈልጋሉ። ስለ ፊልሙ ምንም የማያውቁ ከሆነ ከጋዜጣ ላይ ለማንበብ ይሞክራሉ ወይም በቴሌቪዥን የሚቀርበውን የፊልሙን ማስታወቂያ ይመለከታሉ። በኢንተርኔትም ስለ ፊልሙ የተባለ ነገር ካለ ለማየት ጥረት ያደርጋሉ። ፊልሙ ጥሩ እንዳልሆነ ከተሰማቸው ምክንያታቸውን ይገልጹልኛል። እኔም የተሰማኝን እንድገልጽ አጋጣሚውን ይሰጡኛል። ነፃ ውይይት አድርገን በቤተሰብ እንወስናለን።”የ19 ዓመቷ ኤሎዝ፣ ፈረንሳይ

[በገጽ 13 ላይ የሚገኝ ሣጥን/ሥዕል]

በጉዳዩ ላይ ተወያዩ!

“ወላጆች ልጆቻቸውን አንድ ነገር ከልክለው በምትኩ ሌላ ካላዘጋጁ ልጆቹ ያንን የተከለከሉትን ነገር በድብቅ ለማድረግ ሊነሳሱ ይችላሉ። ስለሆነም ልጆች አንድ ጤናማ ያልሆነ መዝናኛ ለመመልከት ጉጉት ሲያድርባቸው አንዳንድ ወላጆች ዝም ብለው አይከለክሏቸውም ወይም አይፈቅዱላቸውም። ከዚህ ይልቅ ሌላ ጊዜ በረጋ መንፈስ መወያየት የሚያስችላቸውን ዝግጅት ያደርጋሉ። ከተወሰኑ ቀናት በኋላ ምንም ሳይቆጡ ልጁ ያንን መዝናኛ ማየቱ ችግር የለውም ብሎ እንዲያስብ ያደረገውን ነገር በመጠየቅ በጉዳዩ ላይ ይወያያሉ። ልጆችን በዚህ መንገድ ሲያወያዩአቸው ብዙውን ጊዜ ከወላጆቻቸው ሐሳብ ጋር ይስማማሉ፤ እንዲያውም ያመሰግናሉ። ከዚያም በወላጆቻቸው እገዛ ቤተሰቡ በአንድነት የሚካፈልበትን ጤናማ መዝናኛ ይመርጣሉ።”ማሳኪ፣ በጃፓን የሚገኝ ተጓዥ የበላይ ተመልካች

[በገጽ 14 ላይ የሚገኝ ሣጥን/ሥዕል]

ሌሎች የመዝናኛ ዓይነቶች

▪ “ልጆች በተፈጥሯቸው ከእኩዮቻቸው ጋር የመሆን ፍላጎት አላቸው። ስለሆነም ሴት ልጃችን ከጥሩ ልጆች ጋር እንድትገጥም ለማድረግ እንጥራለን። በጉባኤያችን ውስጥ ጥሩ ምሳሌ የሚሆኑ ብዙ ልጆች ስላሉ ልጃችን ከእነሱ ጋር እንድትቀራረብ እናበረታታታለን።”ኤሊሳ፣ ጣሊያን

▪ “የልጆቻችንን መዝናኛ ጉዳይ ትኩረት እንሰጠዋለን። ከቤት ወጣ ብሎ በእግር መንሸራሸርን፣ ባርቢኪው ማዘጋጀትን፣ ሽርሽር መሄድንና የተለያየ ዕድሜ ካላቸው ክርስቲያኖች ጋር ተሰባስቦ መጫወትን የመሳሰሉ ጤናማ የመዝናኛ ዝግጅቶችን እናደርግላቸዋለን። በዚህ መንገድ ልጆቻችን መዝናኛ ሲባል ከእኩዮች ጋር ጊዜ ማሳለፍ ብቻ እንዳልሆነ እንዲገነዘቡ እናደርጋለን።”ጆን፣ ብሪታንያ

▪ “ከክርስቲያን ወንድሞች ጋር ተሰባስቦ መጫወት ጥሩ ሆኖ አግኝተነዋል። ልጆቼ እግር ኳስ መጫወት ስለሚወዱ አልፎ አልፎ ከሌሎች ጋር በዚህ ስፖርት የምንካፈልበትን ዝግጅት እናደርጋለን።”ክዋን፣ ስፔይን

▪ “ልጆቻችን የሙዚቃ መሣሪያዎችን እንዲጫወቱ እናበረታታቸዋለን። በተጨማሪም እንደ ቴኒስ፣ መረብ ኳስ፣ ብስክሌት መንዳት፣ ማንበብ እንዲሁም ከጓደኞቻችን ጋር ተሰባስቦ መጫወት በመሳሰሉ መዝናኛዎች አብረናቸው ጊዜ እናሳልፋለን።”ማርክ፣ ብሪታንያ

▪ “ቤተሰባችን ከጓደኞቻችን ጋር ቦሊንግ የሚጫወትበት ፕሮግራም አለው። እንዲሁም በወር አንድ ጊዜ ለየት ያለ ነገር ለማድረግ ጥረት እናደርጋለን። ወላጆች ችግሮች እንዳይከሰቱ ማድረግ የሚችሉበት ቁልፍ የልጆቻቸውን እንቅስቃሴ በትኩረት መከታተል ነው።”ዳኒሎ፣ ፊሊፒንስ

▪ “እንዲሁ ቁጭ ብሎ ፊልም ብቻ ከመመልከት ይልቅ አንዳንድ ነገሮችን በቀጥታ ሄዶ ማየትና የተለያዩ እንቅስቃሴዎችን ማድረግ ይበልጥ አስደሳች ነው። በአካባቢያችን የሚደረጉትን የሥዕል ወይም የመኪና ኤግዚቢሽኖች አሊያም የሙዚቃ ዝግጅቶች ሆነ ብለን እንከታተላለን። እንዲህ ዓይነቶቹ ዝግጅቶች ብዙውን ጊዜ እርስ በርስ መጨዋወትም ያስችላሉ። ከዚህም በላይ መዝናኛ እንዳናበዛም ጥንቃቄ እናደርጋለን። እንዲህ የምናደርገው ጊዜ እንዳናባክን ብቻ ሳይሆን እንዳይሰለቸንና ጣዕሙን እንዳያጣ ነው።”ጁዲት፣ ደቡብ አፍሪካ

▪ “ሌሎች ልጆች የሚያደርጉት ሁሉ ለእኔ ልጆች ትክክል ይሆናል ማለት አይደለም። ስለሆነም ልጆቼ ይህን እንዲገነዘቡ ለመርዳት ጥረት አደርጋለሁ። እንዲሁም እኔና ባለቤቴ ለልጆቻችን ጥሩ መዝናኛ ለማዘጋጀት እንጥራለን። ልጆቻችን ‘የትም አንሄድም? ምንም አናደርግም ማለት ነው?’ ብለው እንዳያማርሩ የተቻለንን ሁሉ እናደርጋለን። በቤተሰብ ሆነን ወደ መናፈሻ ቦታዎች እንሄዳለን፤ እንዲሁም ከሌሎች የጉባኤያችን አባላት ጋር ተሰባስበን ለመጫወት በቤታችን ዝግጅት እናደርጋለን።” *ማሪያ፣ ብራዚል

[የግርጌ ማስታወሻ]

^ አን.47 ማኅበራዊ መዝናኛን በሚመለከት ተጨማሪ መረጃ ለማግኘት ነሐሴ 15, 1992 መጠበቂያ ግንብ ገጽ 15-20ን ተመልከት።

[ምንጭ]

James Hall Museum of Transport, Johannesburg, South Africa

[በገጽ 11 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

ውሳኔ ከማድረግህ በፊት የፊልም ገምጋሚዎች የሚሰጡትን አስተያየት አንብብ

[በገጽ 12, 13 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

ወላጆች ልጆቻችሁ መራጮች እንዲሆኑ አሠልጥኗቸው