በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

ከስክሪፕት እስከ ፊልም ማሳያ ሸራ

ከስክሪፕት እስከ ፊልም ማሳያ ሸራ

ከስክሪፕት እስከ ፊልም ማሳያ ሸራ

ባለፉት ጥቂት አሥርተ ዓመታት ሆሊዉድ ዋነኛው የታላላቅ ፊልሞች ምንጭ ሆኖ ቆይቷል። ብዙዎቹ የአሜሪካ ፊልሞች በዩናይትድ ስቴትስ ውስጥ በወጡ በጥቂት ሳምንታት፣ እንዲያውም አንዳንድ ጊዜ በጥቂት ቀናት ውስጥ በሌሎች አገሮች ስለሚወጡ በዩናይትድ ስቴትስ የፊልም ዘርፍ የሚፈጸሙ ክስተቶች በመላው ዓለም ላይ ተጽዕኖ ያሳድራሉ። እንዲያውም አንዳንድ ፊልሞች በአንድ ጊዜ በተለያዩ አገሮች ወጥተዋል። የዋርነር ብራዘርስ የፊልም ኩባንያ የአገር ውስጥ ስርጭት ፕሬዚዳንት የሆኑት ዳን ፌልማን “ዓለም አቀፉ ገበያ በጣም ሞቅ ያለ ከመሆኑም በላይ በከፍተኛ ሁኔታ እያደገ መጥቷል። ስለዚህ ፊልሞችን የምንሠራው ዓለም አቀፋዊ ይዘት እንዳላቸው በማሰብ ነው” ብለዋል። በተለይ በአሁኑ ጊዜ በሆሊዉድ የሚደረገው ነገር በመላው ዓለም የመዝናኛ ኢንዱስትሪ ላይ ተጽዕኖ ያሳድራል። *

ይሁን እንጂ ከፊልም ትርፍ ማግኘት ከውጭ እንደሚታየው ቀላል ነገር አይደለም። ብዙ ፊልሞች የማዘጋጃና የማስተዋወቂያ ወጪያቸውን ለመሸፈን ብቻ ከ100 ሚሊዮን ዶላር በላይ ይፈጃሉ። ይህን ያህል ገቢ ማግኘት አለማግኘታቸው የተመካው ደግሞ ገና ይውደደው ይጥላው በማይታወቀው ተመልካች ላይ ነው። በኤመሪ ዩኒቨርሲቲ የፊልም ጥናቶች ፕሮፌሰር የሆኑት ዴቪድ ኩክ “ተመልካቹ ሕዝብ በሆነ ወቅት ላይ ቀልቡ በምን እንደሚሳብና ምን እንደሚያስደስተው በቅድሚያ ማወቅ አይቻልም” ብለዋል። ታዲያ ፊልም ሠሪዎች ለኪሣራ የመዳረግ ዕድላቸውን የሚቀንሱት እንዴት ነው? የዚህን መልስ ለማወቅ ፊልሞች ስለሚሠሩበት መንገድ ጥቂት መሠረታዊ ነገሮች ማወቅ ያስፈልገናል። *

የቅድመ ዝግጅት ሥራ—መሠረት መጣል

በፊልም ሥራ ሂደት ውስጥ ረዥሙን ጊዜ የሚፈጀውና ከሁሉ ይበልጥ አስፈላጊ የሆነው የቅድመ ዝግጅት ሥራ ነው። ለማንኛውም ትልቅ ፕሮጀክት በቂ ዝግጅት ማድረግ ዋነኛ ቁልፍ ነው። ለቅድመ ዝግጅት ሥራ የሚወጣው እያንዳንዱ ወጪ በፊልም ሥራ ወቅት ከዚያ ብዙ እጥፍ ገንዘብ ያድናል ተብሎ ተስፋ ይደረጋል።

የፊልም ሥራ የሚጀምረው ልብ ወለድ ወይም እውነተኛ በሆነ ታሪክ ላይ ተመሥርቶ ነው። ጸሐፊው ታሪኩን ወደ ስክሪፕት ወይም ወደ ፊልም ጽሑፍነት ይለውጠዋል። ጽሑፉ ወይም የፊልሙ ተውኔት ለፊልሙ ሥራ ተመቻችቶና ተሻሽሎ የመጨረሻ መልኩን ይዞ እስኪቀርብ ድረስ ደጋግሞ መጻፍና ማስተካከል ያስፈልጋል። በዚህ የመጨረሻ ስክሪፕት ውስጥ የፊልሙ ጭውውትና የእንቅስቃሴዎቹ መግለጫ ይሰፍራል። እንደዚሁም ጽሑፉ እንደ ካሜራ አቅጣጫና መሸጋገሪያ ትዕይንቶች ያሉ ቴክኒካዊ ዝርዝር ጉዳዮችን ጭምር ይይዛል።

ይሁን እንጂ አንድ የፊልም ተውኔት ለአዘጋጁ ለሽያጭ የሚቀርበው ገና እዚህ ደረጃ ላይ እንዳለ ነው። * አንድ አዘጋጅ የሚፈልገው የፊልም ተውኔት ምን ዓይነት ነው? አብዛኛውን ጊዜ የበጋ ፊልሞች ዒላማ የሚያደርጉት ከ13 እስከ 19 ዓመት ዕድሜ ክልል ውስጥ የሚገኙ ልጆችንና አንድ የፊልም ሐያሲ “የፖፕኮርን ጭፍራ” ብለው የጠሯቸውን በ20 እና በ25 የዕድሜ ክልል ውስጥ የሚገኙ ወጣቶችን ነው። ስለዚህ አንድ አዘጋጅ የወጣቶችን ቀልብ የሚስብ የፊልም ስክሪፕት ሊመርጥ ይችላል።

ያም ሆኖ በሁሉም የዕድሜ ክልል የሚገኙ ተመልካቾችን የሚስብ ስክሪፕት ይበልጥ ተመራጭ ይሆናል። ለምሳሌ ያህል ትናንሽ ልጆች በቀልድ መጽሐፋቸው ውስጥ በሚያውቁት የታወቀ ገጸ ባሕርይ ላይ የተመሠረተ ፊልም እንደሚያጓጓቸው የታወቀ ነው። እነርሱ ለማየት ሲሄዱ ደግሞ ወላጆቻቸው አብረዋቸው መሄዳቸው አይቀርም። ይሁን እንጂ የፊልም አዘጋጆች የአፍላ ጎረምሶችንና የወጣቶችን ቀልብ የሚማርኩት እንዴት ነው? ሊዛ መንዲ ዘ ዋሽንግተን ፖስት ማጋዚን በተባለው መጽሔት ላይ “ዋናው ቁልፍ ታሪኩን ስሜት ቀስቃሽ ማድረግ ነው” ብለዋል። የብልግና ቃላት በመጨመር፣ አሰቃቂ ትርዒቶችን በማቅረብና ወሲባዊ ድርጊቶችን በዛ አድርጎ በማሳየት “ሁሉም የኅብረተሰብ ክፍል እንዲያየው ከተደረገ የአንድ ፊልም ትርፋማነት ከፍ ሊል ይችላል።”

አንድ አዘጋጅ አንድ የፊልም ጽሑፍ ትርፍ ሊያስገኝ ይችላል ብሎ ካሰበ ሊገዛውና ጥሩ ዝና ያተረፈ ዳይሬክተርና ዝነኛ ተዋንያን ሊቀጥር ይችላል። ፊልሙ በእውቅ ዳይሬክተርና በጣም ዝነኛ በሆነ ተዋናይ መዘጋጀቱ በሚወጣበት ጊዜ ብዙ ተመልካች እንዲያገኝ ያስችለዋል። ከዚህም በተጨማሪ ዝነኛ ሰዎችን መጠቀሙ ገና እዚህ ደረጃ ላይ እያለም እንኳ የፊልሙን ዝግጅት ስፖንሰር የሚያደርጉ ባለሀብቶችን ቀልብ በቀላሉ መሳብ ያስችላል።

ሌላው የቅድመ ዝግጅት ዘርፍ የትርዒቶቹን ቅንብር በንድፍ ማዘጋጀት ነው። የትርዒቶች ቅንብር ንድፍ የፊልሙን የተለያዩ ክፍሎች፣ በተለይም ብዙ እንቅስቃሴ የሚደረግባቸውን ክፍሎች ቅደም ተከተል የሚያሳይ ሥዕል ነው። ይህ ንድፍ ለፊልም አንሺው እንደ መመሪያ ሆኖ ስለሚያገለግለው ፊልሙ በሚቀረጽበት ወቅት ብዙ ጊዜ እንዳይባክንበት ይረዳዋል። የፊልም ዳይሬክተርና የፊልም ተውኔት ጸሐፊ የሆኑት ፍራንክ ዳረቦንት እንደሚሉት “ካሜራውን ከየት አቅጣጫ ባደርገው ይሻላል እያሉ በማሰብ በርካታ ጊዜ ከማባከን የሚከፋ ነገር የለም።”

በቅድመ ዝግጅት ጊዜ የሚደረጉ ሌሎች ነገሮችም አሉ። ለምሳሌ ፊልሙ የሚነሳው የት ቦታ ነው? ረዥም ጉዞ ማድረግ ያስፈልጋል? የመድረክ ገጽ ዝግጅትና ግንባታ ያስፈልጋል? የተለየ ልብስ ያስፈልጋል? ለመብራት፣ ለሜካፕና ለፀጉር ዝግጅት ማን ቢሆን ይሻላል? ልዩ የድምፅና የምስል ቴክኒካዊ ቅንብሩንስ ማን ቢሠራው ይሻላል? ተዋናዮቹን ተክተው አደገኛ የሆኑ ወይም ልዩ ችሎታ የሚጠይቁ እንቅስቃሴዎችን የሚያደርጉ ሰዎችስ ያስፈልጋሉ? እነዚህ ሁሉ ገና ፊልሙ መነሳት ከመጀመሩ በፊት ሊታሰብባቸው ከሚገቡ ነገሮች መካከል ጥቂቶቹ ናቸው። በአንድ ትልቅ ፊልም መጨረሻ ላይ የሚሰፍሩትን ሰዎች ስም ዝርዝር ብትመለከት በፊልሙ ዝግጅት በመቶዎች የሚቆጠሩ ሰዎች እንደተካፈሉ ትገነዘባለህ። በበርካታ ፊልሞች ዝግጅት ላይ የተካፈለ አንድ ቴክኒሽያን “አንድ ትልቅ ፊልም ለማዘጋጀት አንድ ከተማ የሚሞሉ ሰዎች ያስፈልጋሉ” ብሏል።

የፊልም ቀረጻ

ፊልም የመቅረጽ ሥራ ብዙ ጊዜ የሚፈጅ፣ አድካሚና ብዙ ወጪ የሚጠይቅ ሊሆን ይችላል። በእርግጥም በቀረጻ ወቅት የምትባክነው እያንዳንዷ ደቂቃ በሺዎች የሚቆጠር የገንዘብ ኪሣራ ታደርሳለች። አንዳንድ ጊዜ ተዋናዮቹን፣ የቀረጻ ሠራተኞችንና መሣሪያዎችን ራቅ ወዳለ የዓለም ክፍል ማጓጓዝ አስፈላጊ ይሆናል። ሆኖም ቀረጻው የትም ተከናወነ የት በእያንዳንዱ ቀን የሚከናወነው ሥራ በርከት ያለ ገንዘብ ይጠይቃል።

የመብራት ሠራተኞች፣ ፀጉር ሠሪዎችና የሜካፕ ባለሞያዎች ቀድመው የፊልሙ ቀረጻ ሥራ የሚከናወንበት ቦታ መድረስ ይኖርባቸዋል። በእያንዳንዱ የፊልም ቀረጻ ቀን ኮከብ ተዋናዮችን ለቀረጻ ማዘጋጀት በርካታ ሰዓታት ይፈጃል። ከዚህ ሁሉ በኋላ ረጅም ሰዓታት የሚፈጀው አድካሚ የቀረጻ ሥራ ይጀመራል።

ዳይሬክተሩ የእያንዳንዱን ትርዒት ቀረጻ በቅርብ ይቆጣጠራል። በጣም ቀላል ነው የሚባል ትዕይንት እንኳን ሙሉ ቀን ሊፈጅ ይችላል። በአንድ ፊልም ውስጥ ከሚካተቱ ትዕይንቶች አብዛኞቹ በነጠላ ካሜራ የሚቀረጹ በመሆናቸው አንዱን ትዕይንት ከተለያዩ አቅጣጫዎች ደግሞ ደጋግሞ ማንሳት ግድ ይሆናል። በተጨማሪም ቴክኒካዊ ስህተቶችን ለማረም ወይም በጣም የተሻለውን እንቅስቃሴ ለመቅረጽ ሲባል እያንዳንዱ እንቅስቃሴ ተደጋግሞ መሠራት ሊኖርበት ይችላል። ትልቅ ትዕይንት ከሆነ 50 ጊዜ ወይም ከዚያ በላይ ደጋግሞ መቅረጽ ሊያስፈልግ ይችላል! ከዚያም ዳይሬክተሩ አብዛኛውን ጊዜ እያንዳንዱ የቀረጻ ቀን ካለቀ በኋላ የተቀረጸውን ሁሉ በጥንቃቄ ተመልክቶ የትኛው እንደሚጣልና የትኛው እንደሚወሰድ ይወስናል። በአጠቃላይ የፊልም ቀረጻው ሥራ የሳምንታት ወይም የወራት ጊዜ ሊፈጅ ይችላል።

ከቀረጻ በኋላ ማገጣጠም

የቀረጻው ሥራ ከተከናወነ በኋላ የፊልሙ የተለያዩ ክፍሎች አስፈላጊው ማስተካከያ ይደረግባቸውና ተገጣጥመው አንድ ወጥ ፊልም ይሆናሉ። በመጀመሪያ ድምፁ ከፊልሙ ጋር እንዲዋሃድ ይደረጋል። ከዚያም የፊልሙ ኤዲተር ወይም አርታኢ የፊልሙን የተለያዩ ክፍሎች አገጣጥሞ ረቂቅ ፊልም ያዘጋጃል።

በዚህ ደረጃ ላይ እያለ ለየት ያሉ የድምፅና የምስል ቅንብሮች እንዲገቡበት ይደረጋል። እነዚህን የድምፅና የምስል ቅንብሮች ማዘጋጀት በጣም የተወሳሰበ ሥራ ሲሆን አንዳንድ ጊዜ የሚከናወነው በኮምፒውተር በመታገዝ ነው። በዚህ መንገድ በጣም አስደናቂና ሕያው የሆነ ውጤት ማግኘት ይቻላል።

አጃቢ ሙዚቃ የሚጨመረውም በዚህ ድህረ ቀረጻ ሥራ ላይ ሲሆን ይህ የሥራ ክፍል በዛሬዎቹ ፊልሞች ላይ ትልቅ ቦታ እየተሰጠው መጥቷል። ኤድዊን ብላክ ፊልም ስኮር መንዝሊ በተባለው መጽሔት ላይ “ባሁኑ ጊዜ የፊልም ኢንዱስትሪ ለ20 ደቂቃ የሚቆይ ወይም አንድን ልዩ ትዕይንት ለማጀብ ብቻ ሳይሆን አብዛኛውን ጊዜ ከአንድ ሰዓት በላይ የሚቆይ አንድ ወጥ ሙዚቃዊ ቅንብር በመጠየቅ ላይ ነው” ብለዋል።

አንዳንድ ጊዜ አንድ አዲስ ፊልም በፊልሙ ሥራ ባልተካፈሉና የዳይሬክተሩ ጓደኞች ወይም የሥራ ባልደረቦች በሆኑ ተመልካቾች እንዲታይ ይደረጋል። እነዚህ ተመልካቾች በሚሰጡት አስተያየት መሠረት ዳይሬክተሩ አንዳንድ ትዕይንቶች እንደገና እንዲሠሩ ወይም ጨርሶ እንዲወጡ ሊያደርግ ይችላል። እነዚህ ተመልካቾች ባለመቀበላቸው ምክንያት አጨራረሳቸው በሙሉ እንዲለወጥ የተደረጉ ፊልሞች አሉ።

በመጨረሻ ያለቀው ፊልም ለቲያትር ቤቶች ይላካል። ፊልሙ በጣም ተወዳጅ ይሁን ወይም መናኛ አሊያም መካከለኛ የሚታወቀው በዚህ ጊዜ ነው። ይሁን እንጂ የሚደርሰው ኪሣራ የገንዘብ ኪሣራ ብቻ አይደለም። ፊልሞች በተደጋጋሚ ተወዳጅነት ካጡ የተዋናዩ የሥራ ዕድል ወይም የዳይሬክተሩ ስምና ዝና ይበላሻል። ጆን ቦርማን የተባሉት ዳይሬክተር የፊልም ሥራ የጀመሩበትን ጊዜ መለስ ብለው በማስታወስ “በርካታ ጓደኞቼ አንድ ሁለት ጊዜ ሳይሳካላቸው በመቅረቱ ምክንያት ሥራቸውን አቁመዋል። የፊልም ሥራ በጣም ጨካኝ ነው። ለጌቶችህ ገንዘብ ካላስገኘህ ወዲያው ትባረራለህ” ብለዋል።

እርግጥ ነው፣ አብዛኞቹ የፊልም ተመልካቾች ፊልም ቤት ደጃፍ ላይ ቆመው እዚያ የተለጠፉ ፖስተሮችን በሚመለከቱበት ጊዜ የፊልም ሠራተኞች የሚያጋጥማቸውን የሥራ ችግር እንደማያስቡ የታወቀ ነው። ዋነኛ ትኩረታቸው ‘ይህ ፊልም ጥሩ ይሆን? እንዲያው ገንዘቤን ከፍዬ ባየው አያስቆጨኝ ይሆን? ፊልሙ የሚያሰቅቅ ወይም የሚያስጸይፍ ይሆን? ልጆቼ ሊያዩት የሚገባ ፊልም ነው?’ በሚለው ጉዳይ ላይ ነው። አንድን ፊልም ለማየት በምትወስንበት ጊዜ እንደነዚህ ላሉት ጥያቄዎች መልስ ማግኘት የምትችለው እንዴት ነው?

[የግርጌ ማስታወሻዎች]

^ አን.2 የሐርቫርድ የንግድ ሥራ ትምህርት ቤት ፕሮፌሰር የሆኑት አኒታ ኤልበርስ እንደሚሉት ከሆነ “በአሁኑ ጊዜ ከውጭ አገሮች የሚገኘው የቲኬት ሽያጭ ገቢ ከአገር ውስጥ ሽያጭ ከሚገኘው ገቢ የሚበልጥ ቢሆንም አንድ ፊልም በዩናይትድ ስቴትስ ውስጥ የሚኖረው ተቀባይነት በውጭ አገሮች የፊልም ገበያ ላይ ተጽዕኖ ማሳደሩ አልቀረም።”

^ አን.3 የፊልሞች አሠራር ዝርዝር እንደየፊልሙ ሊለያይ ቢችልም እዚህ ላይ የቀረበው አንድ ዓይነት የአሠራር ቅደም ተከተል ነው።

^ አን.7 አንዳንድ ጊዜ ለአዘጋጁ የሚቀርበው የተጠናቀቀ የፊልም ጽሑፍ ወይም ስክሪፕት ሳይሆን አስተዋጽኦው ይሆናል። ታሪኩ ከጣመው ይገዛውና ሙሉው ታሪክ ለፊልም በሚመች መንገድ ይጻፋል።

[በገጽ 6 ላይ የሚገኝ የተቀነጨበ ሐሳብ]

“ተመልካቹ ሕዝብ በሆነ ወቅት ላይ ቀልቡ በምን እንደሚሳብና ምን እንደሚያስደስተው በቅድሚያ ማወቅ አይቻልም።”—ዴቪድ ኩክ፣ የፊልም ጥናቶች ፕሮፌሰር

[በገጽ 6, 7 ላይ የሚገኝ ሣጥን/ሥዕል]

አዳዲስ ፊልሞችን ለሽያጭ ማቅረብ

ፊልሙ ተጠናቋል። በሚሊዮን የሚቆጠሩ ሰዎች እንዲያዩት ዝግጁ ሆኗል። ብዙ ተመልካች ያገኝ ይሆን? የፊልም ነጋዴዎች ምርታቸውን ለማስተዋወቅና ከፍተኛ ገቢ እንዲያስገኝላቸው ለማድረግ ከሚጠቀሙባቸው ዘዴዎች መካከል ጥቂቶቹን እንመልከት።

ወሬ መንዛት:- የተመልካቾችን ጉጉት ለመቀስቀስ ከሚያስችሉ ውጤታማ ዘዴዎች አንዱ ወሬ እንዲናፈስ ማድረግ ነው። አንዳንድ ጊዜ ወሬው መናፈስ የሚጀምረው ፊልሙ ከመውጣቱ ከወራት በፊት ነው። ምናልባት ቀድሞ የወጣ ዝነኛ ፊልም ተከታይ ክፍል እንደሚወጣ ሊነገር ይችላል። በዚያኛው ፊልም ላይ የሠሩ ኮከብ ተዋናዮች በዚህኛውም ላይ ይሠሩ ይሆን? እንደ መጀመሪያው ፊልም ጥሩ ይሆን?

አንዳንድ ጊዜ ወሬ የሚዛመተው በፊልሙ ውስጥ ተካተዋል በሚባሉ አንዳንድ አወዛጋቢ ነገሮች ሊሆን ይችላል። ለምሳሌ የጾታ ብልግናን በገሃድ የሚያሳይ ትዕይንት ያለው የመሆኑ ጉዳይ ሊሆን ይችላል። ትዕይንቱ ያን ያህል አስጸያፊ ነው? ከሚገባው በላይ እርቃን የወጣ ነው? ተቃራኒ አስተያየቶች በይፋ ክርክር በሚደረግባቸው ጊዜ ፊልም ሠሪዎች ዋጋ ያልተከፈለበት ማስታወቂያ ያገኛሉ። አንዳንድ ጊዜ በዚህ መንገድ የተቀጣጠለው ውዝግብ ለፊልሙ የመጀመሪያ እይታ በርካታ ተመልካቾችን ይስባል።

መገናኛ ብዙኃን:- በጣም ከተለመዱት የማስተዋወቂያ ዘዴዎች መካከል ፖስተሮች፣ የጋዜጣና የቴሌቪዥን ማስታወቂያዎች፣ በፊልም ቤቶች በዕለቱ ከሚታየው ፊልም በፊት ተቀንጭበው ለማስተዋወቂያነት የሚታዩ አጫጭር ትርዒቶች እንዲሁም ኮከብ ተዋናዮች መጨረሻ ላይ ስለሠሩት ፊልም የሚሰጧቸው አስተያየቶች ይገኛሉ። በአሁኑ ጊዜ ደግሞ ኢንተርኔት ዋነኛው የፊልም ማስተዋወቂያ መሣሪያ ሆኗል። የፊልም ሐያሲ የሆኑት ስቲቭ ፔርሳል “ዶረቲ [ዘ ዊዛርድ ኦቭ ኦዝ የተባለው ፊልም ተዋናይ] የጫማዋን ተረከዝ ከምታንቀጫቅጭ የኮምፒውተሯን ማውዝ ብታንቀጫቅጭ ኖሮ ስለ ኮከብ የፊልም ተዋናዮች የተለያዩ አሉባልታዎች የሚሰራጩባቸውን፣ ከአዳዲስ ፊልሞች ላይ የተቀነጨቡ ማስተዋወቂያዎች የሚቀርቡባቸውን፣ የፊልም ቤት መግቢያ ቲኬቶችና ፕሮግራሞች የሚቀርቡባቸውን በርካታ የፊልም ድረ ገጾችን ታገኝ ነበር” ብለዋል።

ለሽያጭ የሚቀርቡ ሸቀጦች:- የማስተዋወቂያ ሸቀጦች ለአዳዲስ ፊልሞች የተመልካቾችን ጉጉት ሊቀሰቅሱ ይችላሉ። ለምሳሌ በወጣቶች የቀልድ መጻሕፍት ዝነኛ ገጸ ባሕርይ ላይ የተመሠረተ ፊልም ከሆነ ከፊልሙ ጋር ተያይዘው የምግብ መያዣ ዕቃዎች፣ መጠጫዎች፣ ጌጣጌጦች፣ አልባሳት፣ የቁልፍ መያዣዎች፣ ሰዓቶች፣ መብራቶችና ሌሎች ሸቀጦች ለሽያጭ ይቀርባሉ። “አብዛኛውን ጊዜ ከፊልም ጋር ተዛማጅነት ካላቸው ሸቀጦች መካከል 40 በመቶ የሚሆኑት ፊልሙ ከመውጣቱ በፊት ተሸጠው ያልቃሉ” ሲሉ ጆይ ሲስቶ በአንድ የአሜሪካ የመዝናኛ መጽሔት ላይ ጽፈዋል።

በቤት የሚታዩ ቪዲዮዎች:- በፊልም ቤቶች የቲኬት ሽያጭ በቂ ገቢ ያላገኘ ፊልም በቤት በሚታዩ ቪዲዮ ፊልሞች ሽያጭ ኪሣራውን ሊያካክስ ይችላል። የፊልሞችን ገቢ የሚከታተሉት ብሩስ ናሽ “ከ40 እስከ 50 በመቶ የሚሆነው የፊልሞች ገቢ የሚገኘው በቤት ከሚታዩ የቪዲዮ ፊልሞች ሽያጭ ነው” ብለዋል።

የደረጃ ምደባዎች:- ፊልም ሠሪዎች የደረጃ ምደባዎችን በመጠቀም ገቢያቸውን እንዴት ከፍ እንደሚያደርጉ አውቀዋል። ለምሳሌ አንድ ፊልም ልጆች ሊያዩት የማይገባ ነው የሚል ደረጃ የሚያሰጠው አንድ ትዕይንት እንዲገባበት ሊያደርጉ ይችላሉ። በሌላ በኩል ደግሞ ልጆች እንዲያዩት ለማስቻል ብቻ አንዳንድ ትዕይንቶች ተቆርጠው እንዲወጡ ሊደረግ ይችላል። ሊዛ ሙንዲ በዋሽንግተን ፖስት ማጋዚን ላይ ለልጆች የተፈቀደ ወይም የተከለከለ የሚለው የደረጃ አወጣጥ “ዋነኛ የማስተዋወቂያ መሣሪያ ሆኗል። የፊልም ስቱዲዮዎች ለወጣቶችና ወጣትነት ዕድሜ ላይ ለመድረስ ለሚጓጉ ትናንሽ ልጆች ፊልሙ ጥሩ እንደሆነ መልእክት የሚያስተላልፉበት መሣሪያ አድርገው ይጠቀሙበታል” ሲሉ ጽፈዋል። የደረጃ ምደባዎች “ወላጆችን በማስጠንቀቅና ልጆችን በማጓጓት በመካከላቸው አለመግባባት እንዲባባስ አድርጓል” በማለት ሙንዲ ተናግረዋል።

[በገጽ 8, 9 ላይ የሚገኙ ሥዕል]

ፊልሞች የሚዘጋጁት እንዴት ነው?

ስክሪፕት

የቀረጻ ንድፍ

አልባሳት

ሜካፕ

በተመረጠው ቦታ የቀረጻ ሥራ ሲካሄድ

ለየት ያሉ ቅንብሮች ቀረጻ

የሙዚቃ ቀረጻ

የድምፅ ቅንብር

በኮምፒውተር የሚቀናበር እንቅስቃሴ

ኤዲቲንግ