በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

ከዓለም አካባቢ

ከዓለም አካባቢ

ከዓለም አካባቢ

የቅንጦት ውኃ

ናቱር ኮስሞስ የተባለው የጀርመንኛ መጽሔት “የዘመናችን መለያ ምልክት ሆኗል። ዘናጭ ተማሪዎች ሁልጊዜ የታወቀ መለያ ስም ያለውን ውኃ ይይዛሉ። በኒው ዮርክ ‘ዘናጭ’ ሰዎች የመጠጥ ውኃ በሚሸጥባቸው ቤቶች ይገናኛሉ። አስተናጋጆች ያሰለፉ ባለ አምስት ኮከብ ሆቴሎች የዕድሜ ባለጠጋ የሆኑ የወይን ጠጅ ዓይነቶች ካላቸው ደረጃ የማይተናነስ ክብር የተሰጣቸውን ዓለም አቀፍ የማዕድን ውኃዎች በየዓይነቱ ያቀርባሉ” ይላል። የውኃዎቹ ዋጋ የሚቀመስ አይደለም። “የታወቀ ስም ባለው ኩባንያ የታሸገ የማዕድን ውኃ ይዘው ለመዞር ብዙ ገንዘብ ይከፍላሉ” ይላል ይኸው ጽሑፍ። በአንዳንድ ሆቴሎች የአንድ ሊትር ውኃ ዋጋ እስከ 700 ብር ይደርሳል። የታወቀ ስም ባለው ኩባንያ የታሸገ ውኃ ይዞ መዞር የዘናጭነት ምልክት እንደሆነና ውኃውም ተመራጭ እንደሆነ ተደርጎ ቢታይም ለአንተም ከሁሉ የተሻለው ውኃ ይህ ነው ማለት አይደለም። አንዳንዶቹ የታሸገ ውኃ አምራቾች ምርታቸው የአካል ጥንካሬ፣ ጤንነትና ውበት እንደሚሰጥ ይናገራሉ። ብዙ ባለሞያዎች ግን ከተራው ውኃ የተለየ ምንም ጥቅም አላገኙበትም። ለምሳሌ በጀርመን አገር ያለው የቧንቧ ውኃ ጥራት ከሌላ የዓለም ክፍል አቋርጦ ከሚመጣው የማዕድን ውኃ ያልተናነሰ ጥራት እንዳለው ጽሑፉ ይገልጻል። የቧንቧ ውኃ ደግሞ የፕላስቲክ ጠርሙስም ሆነ በሺህ የሚቆጠር ኪሎ ሜትር መጓጓዝ አያስፈልገውም።

የፈረንሳዮች የአመጋገብ ምሥጢር

የካሊፎርኒያ ዩኒቨርሲቲው በርክሌይ ዌልነስ ሌተር “ፈረንሳዮች ብዙ ቅባትነት ያላቸውን ምግቦች ይበላሉ። ሆኖም ከአሜሪካውያን ይልቅ ቀጭኖች ናቸው፤ በመሆኑም ከልክ በላይ የመወፈር ጉዳይ አያሰጋቸውም። በልብ ሕመም ምክንያት የሚሞቱ ሰዎች ቁጥርም ከአሜሪካ በግማሽ ያነሰ ሲሆን ከማንኛውም [የአውሮፓ ኅብረት] አገርም ዝቅ ያለ ነው” ብሏል። ይህ እንዴት ሊሆን ቻለ? መልሱ ፈረንሳዮች “የሚመገቡት ካሎሪ መጠን ከሌሎቹ ያነሰ ስለሆነ” ሊሆን እንደሚችል ዌልነስ ሌተር ይገልጻል። በፓሪስና በፔንስልቬንያ፣ ዩ ኤስ ኤ በሚገኙ ምግብ ቤቶች የተደረገ ጥናት ለፈረንሳዮች የሚቀርበው ምግብ መጠን ከአሜሪካኖቹ ያነሰ እንደሆነ አመልክቷል። በተጨማሪም የፈረንሳዮች የምግብ አሠራር መመሪያዎች ለየት ይላሉ። ለምሳሌ በፈረንሳይ የምግብ አሠራር መጻሕፍት የሚታዘዘው የሥጋ መጠን አነስተኛ ነው። ጽሑፉ “ምናልባት በጣም አስደናቂ የሆነው ግኝት ፈረንሳዮች የሚቀርብላቸውን በመጠኑ አነስ ያለ ምግብ በልተው ለመጨረስ የሚፈጅባቸው ጊዜ ረዘም ያለ መሆኑ ነው” ይላል። “አንድ ፈረንሳዊ በየቀኑ ምግብ በመብላት የሚያሳልፈው ጊዜ በአማካይ 100 ደቂቃ ሲሆን አሜሪካኖች ግን በ60 ደቂቃ ውስጥ ጎረስ ጎረስ አድርገው ይጨርሳሉ።” ታዲያ መደምደሚያው ምንድን ነው? የምትመገበውን ካሎሪ መጠን ተቆጣጠር። ገንቢ ምግቦችን በልክ ብላ። ምግብህን ቀስ ብለህ አጣጥመህ ብላ። በዛ ያለ ምግብ ከቀረበልህ ለሌላ ሰው አካፍል ወይም አስተርፈህ ቤትህ ውሰድ። እንዲሁም “ቤትህ በመብላት ተደሰት።”

ለመጽሐፎችህ ጥንቃቄ አድርግ

ዲያ ሲዬቴ በተባለው የሜክሲኮ መጽሔት ላይ የወጣ አንድ ጽሑፍ “ከሁሉ የሚከፉት ሁለት የመጻሕፍት ጠላቶች ጊዜና እርጥበት ናቸው” ይላል። መጽሐፎችህ ረዥም ዕድሜ እንዲኖራቸው ከፈለግህ ቢያንስ በዓመት አንድ ጊዜ አቧራቸውን አራግፍላቸው። ይሁን እንጂ በምታራግፍበት ጊዜ አቧራው ወደ ገጾቹ እንዳይገባ መጽሐፉን ጥብቅ አድርገህ መያዝህን አትዘንጋ። እርጥበት የሚበዛበት አካባቢ ከሆነ በእያንዳንዱ ገጽ ላይ ፓውደር ነስንሰህበት ለጥቂት ቀናት ከበድ ያለ ነገር ጭነህበት ከቆየ በኋላ ፓውደሩን በብሩሽ ጠርገህ በማውጣት መጽሐፍህን ከእርጥበት መከላከል ትችላለህ። በእርጥበት ምክንያት ሻጋታ ቢፈጠር ሻጋታውን በምላጭ ቀርፈህ ካነሳህ በኋላ በአልኮል አጽዳው። መጽሐፍ ከመደርደሪያ በምታወጣበት ጊዜ ላይኛውን ጫፍ መሐል ለመሐል ይዘህ አትጎትት። ከሁሉ የሚሻለው ዘዴ መጽሐፉን መሐል ላይ በሁለት ጣቶችህ ይዘህ በግራና በቀኝ ካሉት መጻሕፍት ለማላቀቅ ነቅነቅ ካደረግክ በኋላ ሳብ ማድረግ ነው። በጣም ትላልቅ መጽሐፎች፣ በተለይ አሮጌ ከሆኑ በራሳቸው ክብደት ምክንያት ጉዳት ይደርስባቸዋል። በመጽሐፍ መደርደሪያው ላይ አግድም በማስተኛት በዚህ ምክንያት የሚመጣውን ጉዳት ማስወገድ ይቻላል።

የአሐዳውያን ውድቀት?

“የበርካታ ዓመታት ዕድሜ ካስቆጠሩት [የብሪታንያ] ሃይማኖታዊ ቡድኖች አንዱ . . . በጥፋት ጎዳና ላይ እያሽቆለቆለ የሚገኝ ሲሆን በአሥር በሚቆጠሩ ዓመታት ውስጥ ፈጽሞ ይጠፋል” ይላል የለንደኑ ዘ ታይምስ። በብሪታንያ የሚገኙት የአሐዳውያን እንቅስቃሴ አባላት ከ6,000 አይበልጡም። ከእነዚህ መካከል ግማሽ ያህል የሚሆኑት ዕድሜያቸው ከ65 ዓመት በላይ ነው። ስለ እንቅስቃሴው ከሕልውና ውጭ መሆን የተነበዩት የሃይማኖታዊ ቡድኑ ከፍተኛ አገልጋይ የሆኑት ፒተር ሂውስ ናቸው። ሂውስ በሊቨርፑል የሚገኘውን እጅግ የቆየ ቤተ ክርስቲያን እንደ ምሳሌ በመጥቀስ “ከ1976 ወዲህ አገልጋይ ኖሯቸው የማያውቅ ሲሆን የአሐዳውያን እንቅስቃሴ ፈጽሞ ሞቷል” ብለዋል። “አሐዳውያን” የሚለው ስያሜ በብሪታንያ ሥራ ላይ የዋለው በ1673 እንደሆነ ዘ ታይምስ ይገልጻል። “በእንግሊዝ ቤተ ክርስቲያን ውስጥ በክርስቶስ መለኮትነት ላይ የተነሳው ክርክር ብዙ ችግር ካስከተለ በኋላ የፕሪስቢተሪያን ሃይማኖት ተከታዮች የሆኑ ብዙ እንግሊዛውያን የሥላሴን እምነት ላለመቀበል ሲሉ በ18ኛው መቶ ዘመን አሐዳውያን ሆኑ።” ጋዜጣው በማከል “አሁን ግን ሥላሴያዊ ያልሆነ እምነት መያዝ ሕገ ወጥ መሆኑ ስለቀረና ብዙ አብያተ ክርስቲያናት ብዙ ዘመን ባስቆጠሩ መሠረተ ትምህርቶች ላይ ለየት ያለ አመለካከት ያላቸውን ‘አማኞች’ ችላ ብለው ስለሚያልፉ የአሐዳውያን እንቅስቃሴ አስፈላጊነት እየቀነሰ መጥቷል” ይላል።

ከእርጅና ጋር ተያይዞ የሚመጣ የሰውነት መቀነስ

ሰዎች እያረጁ ሲሄዱ ቁመታቸው ያጥራል። “ምክንያቱ በአብዛኛው ከስበት ኃይል ጋር የተያያዘ ነው” ይላል የአውስትራሊያው ዘ ዴይሊ ቴሌግራፍ። የአንድ ሰው ቁመት በስበት ምክንያት ብዙ ጊዜ ይለዋወጣል። የሰው አካል ሙሉ ቁመቱን የሚይዘው በሚተኛበት ጊዜ ነው። “ሰውነታችን እያረጀ ሲሄድና አቅሙም እየተዳከመ ሲመጣ ግን የቁመቱ መቀነስ ጊዜያዊ መሆኑ እያቆመ ይሄዳል” ይላል ጋዜጣው። ሰዎች እያረጁ ሲሄዱ የጡንቻቸውና የጮማቸው መጠን ይቀንሳል። ይህም የተፈጥሯዊው እርጅና ሂደት አንደኛው ክፍል ሲሆን ለዚህም ምክንያቱ በአብዛኛው በሆርሞኖች ምክንያት የሚከሰት ለውጥ ነው። በተጨማሪም አከርካሪ አጥንት ማርጀትና መኮራመት ስለሚጀምር የአከርካሪያችን ርዝመት በ2.5 ሴንቲ ሜትር ይቀንሳል።” አጥንታችን የሚኮራመተው ኦስትዮፖሮሲስ በሚባለው የአጥንት መሸርሸር ምክንያት ሳይሆን አይቀርም።

ሁለት ቋንቋ ተናጋሪ ልጆችን ማሳደግ

“ልጆች በትዕግሥትና በጥንቃቄ እንዲያድጉ ከተደረገ ከአንድ የበለጠ ቋንቋ ተናጋሪ መሆናቸው ለራሳቸው፣ ለቤተሰባቸውና ለማኅበረሰቡ ትልቅ ጠቀሜታ ሊኖረው ይችላል” ይላል የሜክሲኮ ሲቲው ሚሌኒዮ ጋዜጣ። “ሁለት ቋንቋ የሚናገሩ ልጆች የትምህርት ውጤታቸው አንድ ቋንቋ ብቻ ከሚናገሩ ልጆች የተሻለ እንደሆነ” ጥናቶች አረጋግጠዋል። አንዳንድ ጊዜ ልጆች ሁለቱን ቋንቋዎች ሲደበላልቁና የአንዱን ቋንቋ የአነጋገር ሕግ ከሌላው ጋር ሲያምታቱ ወላጆቻቸው ይጨነቃሉ። “ይሁን እንጂ እነዚህ የሰዋስው ‘ግድፈቶች’ በጣም ጥቃቅን ሲሆኑ በጥቂት ጊዜ ውስጥ ይወጧቸዋል” ይላሉ በልጆች የቋንቋ እድገት ላይ ጥናት ያደረጉት ሳይኮሎጂስት ቶኒ ክላይን። የሁለቱንም ወላጆች ቋንቋ ከተወለዱበት ጊዜ ጀምሮ ቢማሩ ሁለቱም ቋንቋዎች ስለሚቀረጹባቸው ከጊዜ በኋላ ለያይተው መናገር ይችላሉ።