በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

ምንጊዜም ተወዳጅ የሆነው ቀይ ሽንኩርት

ምንጊዜም ተወዳጅ የሆነው ቀይ ሽንኩርት

ምንጊዜም ተወዳጅ የሆነው ቀይ ሽንኩርት

በሜክሲኮ የሚገኘው የንቁ! ዘጋቢ እንደጻፈው

ሽንኩርት በሌለበት ወጥ ቤት ውስጥ ሁሉ ነገር ተሟልቷል ለማለት ይቻላል? ይህ ሁለገብ አትክልት ከሞላ ጎደል ማንኛውንም ምግብ ለመሥራት ይጠቅማል። ለምሳሌ ያህል፣ የተለያየ ዓይነት ሾርባና ሰላጣ እንዲሁም ዋና ዋና ምግቦችን ለማዘጋጀትና መድኃኒቶችን ለመቀመም ያገለግላል። ቀይ ሽንኩርት በያዘው ኬሚካል ምክንያት ሊያስለቅሰንም ይችላል።

የሚያምር አበባ ካላቸው ዕፅዋት ወገን የሚመደቡት የተለያዩ የቀይ ሽንኩርት ዝርያዎች ለምግብነትና ለመድኃኒት ቅመማ ከማገልገላቸውም በተጨማሪ ውብ የአበባ ምርት ያስገኛሉ። ሆኖም በዓለም ዙሪያ በሰዎች ሁሉ ቤት የማይጠፋው ወፍራም ልጣጭና ከመሬት በታች የሚበቅል እምቡጥ ያለው የሽንኩርት ራስ ነው ለማለት ይቻላል።

ሽንኩርት ሰዎች ከጥንት ጀምረው ሲያለሟቸው ከነበሩት ተክሎች አንዱ ነው። ከክርስቶስ ልደት በፊት በ1513 ገደማ እስራኤላውያን ግብፅ ውስጥ በባርነት ሳሉ ይበሏቸው የነበሩት የሽንኩርት ዓይነቶች እንዳማሯቸው ከሚናገረው የመጽሐፍ ቅዱስ ዘገባ እንደምንረዳው በዚያን ጊዜ ቀይ ሽንኩርት በሰፊው ጥቅም ላይ ይውል ነበር።—ዘኍልቍ 11:5 የ1954 ትርጉም

ይሁን እንጂ ቀይ ሽንኩርት በዓለም ዙሪያ በብዙዎች ዘንድ እንዲወደድ የሚያደርግ ጣዕም እንዲኖረው ያስቻለው ምንድን ነው? እንዲሰነፍጥና የተለየ ሽታ እንዲኖረው ያስቻለው በውስጡ የያዘው ድኝ እንደሆነ ጥርጥር የለውም። በሚላጥበት ወይም በሚከተፍበት ጊዜ የሚያስለቅሰው በድኙ ውስጥ ያለው አሲድ የሚፈጥረው ንጥረ ነገር ነው።

ከጣፋጭነት የላቀ ጠቀሜታ አለው

ቀይ ሽንኩርት የሰው ልጆችን ጤና በመጠበቅ በኩል ትልቅ ሚና ይጫወታል። እንደ ካልሲየም፣ ፎስፈረስና አስኮርቢክ አሲድ ወይም ቫይታሚን ሲ ያሉ ንጥረ ነገሮችን ይዟል። ሆኖም ከረጅም ጊዜ በፊት ጀምሮ ቀይ ሽንኩርት በተለይ በመድኃኒትነቱ ትልቅ ቦታ ሲሰጠው ቆይቷል። አሁንም ቢሆን ጉንፋንን፣ የጉሮሮ እብጠትን፣ የደም ሥሮች መጥበብ በሽታን (አተሮስክለሮሲስ)፣ ወደ ልብ ጡንቻዎች የሚዘዋወረው ደም መጠን እንዲቀንስ የሚያደርግ (ኮሮናሪ) የልብ በሽታን፣ የስኳር በሽታንና አስምን ጨምሮ በርካታ ሕመሞችን ለማከም ይረዳል። እንዲሁም ቀይ ሽንኩርት ቁስለትን፣ ኮሌስትሮልን፣ የሰውነት መቆጣትን፣ የደም መርጋትንና ካንሰርን የመከላከል ዓይነተኛ ባሕርይ አለው።

የተለያየ ቀለም ያላቸው የቀይ ሽንኩርት ዓይነቶች አሉ፤ እነርሱም ነጭ፣ ቢጫ፣ ቡናማ፣ አረንጓዴ፣ ቀይና የወይን ጠጅ ናቸው። ቀይ ሽንኩርትን ጥሬውን፣ ቅቅሉን፣ ተዘጋጅቶ የታሸገውን፣ በሰላጣ መልክ የተሠራውን፣ የደረቀውን፣ የተፈጨውን ወይም ጎረድ ጎረድ ተደርጎ የተከተፈውን ልትመገበው ትችላለህ። ቀይ ሽንኩርት ቢያስለቅስህም እንኳ ድንቅ አትክልት አይደለም?