በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

ከመጥፎ ልጆች ጋር እንዳልገጥም ምን ማድረግ ይኖርብኛል?

ከመጥፎ ልጆች ጋር እንዳልገጥም ምን ማድረግ ይኖርብኛል?

የወጣቶች ጥያቄ . . .

ከመጥፎ ልጆች ጋር እንዳልገጥም ምን ማድረግ ይኖርብኛል?

“በትምህርት ቤት ውስጥ ከአንዲት ልጅ ጋር መሆን ጀመርኩ። . . . ዕፅ አትወስድም፣ መረን የለቀቁ ጭፈራ ቤቶች አትሄድም ወይም መጥፎ ሥነ ምግባር ያላት ልጅ አይደለችም። ስትሳደብ እንኳ ሰምቻት አላውቅም፤ ደግሞም በጣም ጎበዝ ተማሪ ነች። ሆኖም መጥፎ ጓደኛ ነበረች።”—ቤቨርሊ *

ቤቨርሊ እዚህ መደምደሚያ ላይ ልትደርስ የቻለችው ለምንድን ነው? መለስ ብላ ስታስበው ልጅቷ ጎጂ የሆኑ ነገሮችን እንድታደርግ ተጽዕኖ እንዳደረገችባት ተገንዝባለች። ቤቨርሊ እንዲህ ትላለች:- “ከእሷ ጋር በመግጠሜ መናፍስታዊ መጻሕፍትን ማንበብ የጀመርኩ ከመሆኑም በላይ ከመናፍስትነት ጋር የተያያዘ ታሪክ እስከ መጻፍ ደርሼ ነበር።”

ሜላኒ የተባለች ወጣት ደግሞ እንደ እርሷው ክርስቲያን ነኝ የሚል ሰው ባሳደረባት ግፊት ምክንያት ሥነ ምግባር የጎደለው ድርጊት ፈጽማለች! አንድ ሰው ጥሩ ጓደኛ ሊሆንህ እንደሚችል እንዴት ማወቅ ትችላለህ? ከማያምኑ ጋር መወዳጀት ምንጊዜም ቢሆን አደጋ ያስከትላል? በክርስቲያኖች መካከል የሚመሠረተው ወዳጅነትስ ሁልጊዜ አስተማማኝ ነው ማለት ይቻላል?

በተለይ ደግሞ ከተቃራኒ ጾታ ጋር ስለመወዳጀት ምን ሊባል ይችላል? አንድ ሰው የወደፊት የትዳር ጓደኛችሁ ሊሆን እንደሚችል ካሰባችሁ ግንኙነቱ በጎ ተጽዕኖ የሚያሳድር መሆኑን ማወቅ የምትችሉት እንዴት ነው? እነዚህን ጥያቄዎች በተመለከተ መልስ ማግኘት እንድንችል የመጽሐፍ ቅዱስ መሠረታዊ ሥርዓቶች እንዴት እንደሚረዱን እንመልከት።

ጥሩ ጓደኞች እንዴት ያሉ ናቸው?

ቤቨርሊ፣ አብራት የምትማረው ልጅ የእውነተኛው አምላክ አገልጋይ አለመሆኗ ብቻ ከእሷ ጋር ጓደኝነት ከመመሥረት ወደኋላ እንድትል ሊያደርጋት ይገባ ነበር? እርግጥ እውነተኛ ክርስቲያኖች አንድ ሰው የእምነት ባልንጀራቸው ስላልሆነ ብቻ ጨዋ እንዳልሆነ ወይም ሥነ ምግባር እንደጎደለው አድርገው አያስቡም። ሆኖም የጠበቀ ወዳጅነት በመመሥረት ረገድ እንዲጠነቀቁ የሚያደርጋቸው ምክንያት አለ። ሐዋርያው ጳውሎስ በአንደኛው መቶ ዘመን በቆሮንቶስ ጉባኤ ይገኙ ለነበሩ ክርስቲያኖች “መጥፎ ጓደኝነት መልካሙን ጠባይ ያበላሻል” በማለት ማስጠንቀቂያ ሰጥቷቸዋል። (1 ቆሮንቶስ 15:33) ጳውሎስ ምን ማለቱ ነበር?

የቆሮንቶስ ክርስቲያኖች የግሪክ ፈላስፋ የነበረውን ኤፊቆሮስን ከሚከተሉ ኤፊቆሮሳውያን ጋር ወዳጅነት መሥርተው ሊሆን ይችላል። ኤፊቆሮስ ተከታዮቹ ማስተዋል፣ ድፍረት፣ ራስን መግዛትና ፍትሕን የመሳሰሉ ባሕርያትን እንዲያዳብሩ ያስተምራቸው ነበር። ስውር ከሆኑ መጥፎ ድርጊቶች እንዲርቁም ጭምር ያበረታታቸው ነበር። ታዲያ ጳውሎስ ኤፊቆሮሳውያንንም ሆነ በጉባኤ ውስጥ የሚገኙ የእነርሱ ዓይነት አመለካከት የነበራቸውን ሰዎች ‘መጥፎ ጓደኞች’ ያላቸው ለምንድን ነው?

ኤፊቆሮሳውያን የእውነተኛው አምላክ አገልጋዮች አልነበሩም። በሙታን ትንሣኤ ስለማያምኑ ትኩረታቸው ያረፈው በአሁኑ ዘመን በተቻለ መጠን ተደስቶ በመኖር ላይ ነበር። (የሐዋርያት ሥራ 17: 18, 19, 32) በቆሮንቶስ ጉባኤ ውስጥ የነበሩ አንዳንዶቹ እንዲህ ካሉ ሰዎች ጋር በመወዳጀታቸው ምክንያት በትንሣኤ ላይ የነበራቸውን እምነት ማጣታቸው ምንም አያስደንቅም። ጳውሎስ በ1 ቆሮንቶስ ምዕራፍ 15 ላይ ስለ መጥፎ ጓደኝነት ከማስጠንቀቅም በላይ ለጥንት ክርስቲያኖች የትንሣኤ ተስፋ እውነት መሆኑን ለማሳመን በርካታ የመከራከሪያ ነጥቦች ያቀረበው ለዚህ ነው።

ይህ ታሪክ የሚያስተላልፈው መልእክት ምንድን ነው? አምላካዊ ጎዳና የማይከተሉ ሰዎችም እንኳ ጥሩ ባሕርይ ሊኖራቸው ይችላል። ሆኖም የቅርብ ጓደኛ እንዲሆኑህ ከመረጥካቸው አስተሳሰብህን፣ እምነትህንና ጠባይህን ያበላሹብሃል። በመሆኑም ጳውሎስ ለቆሮንቶስ ክርስቲያኖች በጻፈው ሁለተኛ መልእክቱ ላይ “ከማያምኑ ሰዎች ጋር አግባብ ባልሆነ መንገድ አትጠመዱ” ብሏል።—2 ቆሮንቶስ 6:14-18

የ16 ዓመቱ ፍሬድ የጳውሎስን ቃላት ማዳመጥ ጥበብ እንደሆነ ተገንዝቧል። መጀመሪያ ከትምህርት ሰዓት ውጪ ባለው ጊዜ በማደግ ላይ ወዳለ አገር ሄዶ በዚያ የሚገኙ ልጆችን ለማስተማር በተዘጋጀ ፕሮጀክት ውስጥ ለመሳተፍ ተስማምቶ ነበር። ሆኖም እሱና ሌሎች ተማሪዎች አብረው በሚዘጋጁበት ጊዜ ፍሬድ ሐሳቡን ለወጠ። “ከእነሱ ጋር በጣም ብዙ ጊዜ ማሳለፌ መንፈሳዊነቴን እንደሚጎዳው ተገነዘብኩ” በማለት ተናግሯል። በዚህ ምክንያት ፍሬድ ከፕሮጀክቱ ወጥቶ ችግረኞችን በሌላ መልኩ ለመርዳት ወሰነ።

ከክርስቲያን ባልደረቦቻችን ጋር መወዳጀት

በክርስቲያን ጉባኤ ውስጥ ስላለ ጓደኝነትስ ምን ለማለት ይቻላል? ጳውሎስ ወጣቱን ጢሞቴዎስ እንዲህ በማለት አስጠንቅቆት ነበር:- “በአንድ ትልቅ ቤት ውስጥ የወርቅና የብር ዕቃ ብቻ ሳይሆን፣ የዕንጨትና የሸክላ ዕቃም ይኖራል፤ ከእነዚህ አንዳንዶቹ ለከበረ፣ ሌሎቹም ላልከበረ አገልግሎት ይውላሉ። እንግዲህ ማንም ራሱን ከእነዚህ ከጠቀስኋቸው ነገሮች ቢያነጻ ለክቡር አገልግሎት የሚውል፣ የተቀደሰ፣ ለጌታው የሚጠቅም፣ ለመልካም ሥራም ሁሉ የተሰናዳ ዕቃ ይሆናል።” (2 ጢሞቴዎስ 2:20, 21) እዚህ ላይ ጳውሎስ ነገሩን ከመሸፋፈን ይልቅ በክርስቲያኖች ዘንድ እንኳ ሳይቀር አንዳንዶች የማያስከብር ጠባይ ሊኖራቸው እንደሚችል በግልጽ ተናግሯል። ለጢሞቴዎስም ከእንደነዚህ ዓይነቶቹ መራቅ እንዳለበት በግልጽ ጥብቅ ምክር ሰጥቶታል።

እንዲህ ሲባል ክርስቲያን የእምነት ባልደረቦችህን በጥርጣሬ ዓይን መመልከት አለብህ ማለት ነው? በፍጹም። ወይም ደግሞ ከጓደኞችህ ፍጽምናን ትጠብቃለህ ማለትም አይደለም። (መክብብ 7:16-18) ሆኖም አንድ ወጣት ወደ ክርስቲያን ስብሰባዎች ስለመጣ ወይም በጉባኤ ውስጥ ቅንዓት ያላቸው ወላጆች ስላሉት ብቻ ጥሩ ጓደኛ መሆን ይችላል ማለት አይደለም።

በምሳሌ 20:11 ላይ “ሕፃን እንኳ ጠባዩ ንጹሕና ቅን መሆኑ፣ ከአድራጎቱ ይታወቃል” ይላል። ስለዚህ እንደሚከተለው ብለህ መጠየቅህ ተገቢ ነው:- በሕይወቱ/ቷ ቅድሚያ የሚሰጠው/የምትሰጠው ከይሖዋ ጋር ላለው/ላት ዝምድና ነው? ወይስ “የዓለምን መንፈስ” የሚያንጸባርቅ አስተሳሰብና አዝማሚያ ይታይበታል/ባታል? (1 ቆሮንቶስ 2:12፤ ኤፌሶን 2:2) ከእሷ ወይም ከእሱ ጋር መሆንህ ይሖዋን እንድታመልክ ያበረታታሃል?

ለይሖዋና ለመንፈሳዊ ነገሮች ጥልቅ ፍቅር ያላቸውን ጓደኞች መምረጥህ ችግሮችን እንድታስወግድ ከማድረጉም በላይ አምላክን ማገልገልህን እንድትቀጥል የበለጠ ያጠናክርሃል። ጳውሎስ ለጢሞቴዎስ “በንጹሕ ልብ ጌታን ከሚጠሩት ጋርም ጽድቅን፣ እምነትን፣ ፍቅርንና ሰላምን ተከታተል” ብሎታል።—2 ጢሞቴዎስ 2:22

ከተቃራኒ ጾታ ጋር መወዳጀት

ለጋብቻ የደረሳችሁና ለማግባት የምትፈልጉ ከሆነ ከላይ ያየናቸው መሠረታዊ ሥርዓቶች የትዳር ጓደኛ ምርጫችሁን ሊነኩ እንደሚችሉ በጥሞና አስባችሁበታል? ለማግባት ያሰባችሁት ግለሰብ በብዙ መንገድ ሊስባችሁ ቢችልም አንደኛ ቦታ ሊሰጠው የሚገባው ግን ግለሰቡ ለመንፈሳዊ ነገሮች ያለው አመለካከት ነው።

ስለዚህም መጽሐፍ ቅዱስ “በጌታ” ያልሆነ ጋብቻ ልንፈጽም እንደማይገባን በተደጋጋሚ ጊዜያት ማስጠንቀቂያ ሰጥቷል። (1 ቆሮንቶስ 7:39፤ ዘዳግም 7:3, 4፤ ነህምያ 13:25) እርግጥ ክርስቲያን ያልሆኑ ግለሰቦችም ኃላፊነት የሚሰማቸው፣ ጨዋና አሳቢ ሊሆኑ ይችላሉ። ሆኖም እናንተ የምትፈልጉትን ያህል እንዲህ ዓይነቶቹን ባሕርያት እንድታዳብሩ አይገፋፏችሁም፤ እንዲሁም ዓመታት እያለፉ ሲሄዱ ትዳራችሁ የተሳካ እንዲሆን ጥረት አያደርጉም።

በሌላው በኩል ራሱን ለይሖዋ የወሰነና ለአምላክ ታማኝ የሆነ ሰው፣ በምንም ዓይነት ሁኔታ ሥር ቢሆን ክርስቲያናዊ ባሕርያትን ለማዳበርና እነዚህን ባሕርያት ላለማጣት ጥረት ያደርጋል። ተጋቢዎቹ እርስ በርስ የሚኖራቸውን ፍቅር መጽሐፍ ቅዱስ ከይሖዋ ጋር ካላቸው ጥሩ ዝምድና ጋር አያይዞ እንደሚገልጸው ይገነዘባል። (ኤፌሶን 5:28, 33፤ 1 ጴጥሮስ 3:7) ስለዚህ ሁለቱም የትዳር ጓደኛሞች ይሖዋን የሚወዱ ከሆኑ ይህ አንዳቸው ለሌላው ታማኝ እንዲሆኑ ይገፋፋቸዋል።

ታዲያ ይህ ሲባል የትዳር ጓደኛሞቹ ክርስቲያን መሆናቸው ጋብቻው ስኬታማ እንደሚሆን ዋስትና ይሰጣል ማለት ነው? አይሰጥም። ለምሳሌ ለመንፈሳዊ ነገሮች እምብዛም ፍላጎት የሌለውን ሰው ብታገቡ ውጤቱ ምን ይሆናል? በመንፈሳዊ ደካማ የሆነ ሰው የዚህን ሥርዓት ጭንቀት መቋቋም ስለማይችል ከክርስቲያን ጉባኤ የመውጣት አጋጣሚው ሰፊ ይሆናል። (ፊልጵስዩስ 3:18፤ 1 ዮሐንስ 2:19) የትዳር ጓደኛችሁ “[በ]ዓለም ርኵሰት” ቢማረክ የሚገጥማችሁን ከባድ ሐዘንና በጋብቻችሁ ውስጥ ሊፈጠር የሚችለውን የከረረ አለመግባባት አስቡት።—2 ጴጥሮስ 2:20

ግንኙነቱ ወደ ጋብቻ ከማምራቱ በፊት በሚከተሉት ጥያቄዎች ላይ አስቡባቸው:- ሁኔታው/ዋ መንፈሳዊ ሰው መሆኑን/ኗን ያሳያል? በክርስቲያናዊ አኗኗር ረገድ ጥሩ ምሳሌ ነው/ነች? የመጽሐፍ ቅዱስ እውነት በውስጡ/ጧ ሥር ሰዷል ወይስ በመንፈሳዊ ለማደግ ጊዜ ያስፈልገዋል/ያስፈልጋታል? ሕይወቱን/ቷን የሚመራው ዋነኛ ነገር ለይሖዋ ያለው/ያላት ፍቅር መሆኑን እርግጠኛ ናችሁ? ግለሰቡ መልካም ስም እንዳለው ማወቁም ይረዳል። ዋናው ነጥብ ግን ግለሰቡ ለይሖዋ ያደረና ጥሩ የትዳር ጓደኛ ሊሆን እንደሚችል ልታምኑበት ይገባል።

“ከመጥፎ ሰዎች” ጋር መወዳጀት የሚፈልጉ ግለሰቦች መጀመሪያውኑም ቢሆን መጥፎ ነገሮችን ይኸውም ተገቢ ያልሆኑ መዝናኛዎችንና እንቅስቃሴዎችን የሚወዱ እንደሆኑ አትዘንጉ። በጉባኤ ውስጥ ያሉ ምሳሌ የሚሆኑ ወጣቶች እንዲህ በመሰለው እንቅስቃሴ አይተባበሯችሁም። ስለዚህ ልባችሁን መርምሩ።

ልባችሁ ተግሣጽ የሚያስፈልገው ሆኖ ካገኛችሁት ተስፋ አትቁረጡ። ልብ ሊስተካከል ይችላል። (ምሳሌ 23:12) አስፈላጊ የሆነው ቁም ነገር የምትፈልጉት ምንድን ነው? የሚለው ነው። ጥሩ የሆነውን ነገር ማድረግና መልካም ምግባር ካላቸው ሰዎች ጋር ለመቀራረብ ትፈልጋላችሁ? ይሖዋ ይህን የመሰለውን የልብ ዝንባሌ እንድታዳብሩ ይረዳችኋል። (መዝሙር 97:10) መልካሙን ከክፉው ለመለየት እንድትችሉ የማስተዋል ችሎታችሁን ማሠልጠናችሁ የሚጠቅሟችሁና የሚያንጿችሁን ጓደኞች ለይታችሁ ለማወቅ ቀላል ያደርግላችኋል።—ዕብራውያን 5:14

[የግርጌ ማስታወሻ]

^ አን.3 ስሞቹ ተቀይረዋል።

[በገጽ 13 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

መንፈሳዊ አመለካከት ያላቸው ሰዎች መልካም ጓደኞች ናቸው