ከዓለም አካባቢ
ከዓለም አካባቢ
በጥንታዊነቱ ከዓለም አንደኛ የሆነ ዩኒቨርሲቲ?
ፖላንዳውያንና ግብጻውያን ባለሙያዎችን ያቀፈ አንድ የአርኪኦሎጂስቶች ቡድን ግብጽ ውስጥ የጥንቱ የእስክንድርያ ዩኒቨርሲቲ የነበረበትን ቦታ አግኝቷል። ሎስ አንጀለስ ታይምስ እንደሚለው ከሆነ ቡድኑ ሁሉም ተመሳሳይ ስፋት ያላቸውና በአንድነት እስከ 5,000 ተማሪዎች ሊይዙ የሚችሉ 13 የትምህርት መስጫ አዳራሾች አግኝቷል። ጋዜጣው እንደሚለው እነዚህ አዳራሾች “በደረጃ የተቀመጡና በክፍሎቹ ሦስት ግድግዳዎች ትይዩ ተደርድረው በስተ መጨረሻ እርስ በርስ በመገናኘት የ‘ሀ’ ቅርጽ የሚፈጥሩ አግዳሚ መቀመጫዎች አሏቸው።” በመካከል ከፍ ብሎ የተቀመጠ የመምህሩ መቀመጫ ሊሆን የሚችል ወንበር አለ። “በመላው የሜዲትራንያን ባሕር አካባቢ፣ በግሪካውያንና ሮማውያን የጥንት ግዛት ይህን የመሰለ የተራቀቀ የትምህርት አዳራሾች ሕንጻ ሲገኝ የመጀመሪያ ጊዜ ነው” ይላሉ የግብጽ የጥንት ቅርሶች ከፍተኛ ጉባኤ ፕሬዚዳንት የሆኑት ዛሂ ሃዋስ። ሃዋስ “ምናልባት በጥንታዊነቱ ከዓለም አንደኛ የሆነ ዩኒቨርሲቲ ሳይሆን አይቀርም” ብለዋል።
የነጭ ሽንኩርት አይስክሬም?
ነጭ ሽንኩርት ለመድኃኒትነት በሚሰጠው ጥቅም የተነሳ መወደስ ከጀመረ ረዥም ዘመን አስቆጥሯል። አሁን በሰሜናዊ ፊሊፒንስ የሚገኘው የማሪያኖ ማርኮስ ስቴት ዩኒቨርሲቲ “ለጤና ይጠቅማል” የተባለ የነጭ ሽንኩርት አይስክሬም እንደሠራ ፊሊፒን ስታር ጋዜጣ ዘግቧል። ይህ አዲስ ምርት ነጭ ሽንኩርት ያስታግሳቸዋል በሚባሉ ሕመሞች ለሚሰቃዩ ሰዎች ይጠቅማል ተብሎ ተስፋ ይደረጋል። ከእነዚህ ሕመሞች መካከል ጉንፋን፣ ትኩሳት፣ የደም ግፊት መብዛት፣ የመተንፈሻ አካላት ችግር፣ ቁርጥማት፣ የእባብ ንክሻ፣ የጥርስ ሕመም፣ ሳንባ ነቀርሳ፣ ሳል፣ ቁስልና ራሰ በራነት ይገኙበታል። ታዲያ እንዴት ነው፣ የነጭ ሽንኩርት አይስክሬም ለመብላት አልጓጓህም?
በአንድ ወቅት ሞቃታማ የአየር ሁኔታ የነበረው አርክቲክ
በሳይቤሪያና በግሪንላንድ መካከል የሚገኘውን የአርክቲክ ውቅያኖስ ወለል እየቆፈረ ሲያጠና የቆየ አንድ ከተለያዩ አገራት የተውጣጣ የሳይንቲስቶች ቡድን ይህ አካባቢ በአንድ ወቅት ሞቃታማ የአየር ሁኔታ እንደነበረው ገልጿል። የአርክቲክን የባሕር ወለል ሲቆፍር የቆየው ይህ ቡድን ሥራውን ያከናወነው በሦስት በረዶ አፍራሽ መሣሪያዎች በመጠቀም ሲሆን ከባሕር ወለል በታች እስከ 400 ሜትር የሚደርስ ጥልቀት ካላቸው ቦታዎች ናሙናዎች ወስዷል። በአንድ ወቅት የውቅያኖሱ ሙቀት እንዳሁኑ ከዜሮ በታች 1.5 ዲግሪ ሴንቲ ግሬድ የደረሰ ሳይሆን 20 ዲግሪ ሴንቲ ግሬድ አካባቢ እንደነበረ በእነዚህ ናሙናዎች ላይ የተገኙ ጥቃቅን የባሕር እጽዋትና እንስሳት ቅሪተ አካሎች ያመለክታሉ። ቢቢሲ የጠቀሳቸው የስቶክሆልም ዩኒቨርሲቲ ባልደረባ የሆኑት ፕሮፌሰር ያን ባክማን “የአርክቲክ ውቅያኖስ ወለል ጥንታዊ ታሪክ በዚህ ቅኝት በተሰበሰቡት አዳዲስ ናሙናዎች መሠረት በአዲስ መልክ ይመረመራል” ብለዋል።
ዲጂታል ሰሌዳ ወደ ትምህርት ቤቶች ገባ
በሜክሲኮ በሚገኙ ከ21,000 የሚበልጡ የአንደኛ ደረጃ ትምህርት ቤቶች ጥቁር ሰሌዳዎች፣ ጠመኔዎችና የጠመኔ ማጥፊያዎች ከኮምፒውተር ጋር በተያያዙ የኤሌክትሮኒክ ሰሌዳዎች በመተካት ላይ እንደሆኑ የሜክሲኮ ሲቲው ኤል ዩኒቨርሳል ዘግቧል። ባሁኑ ጊዜ ሁለት ሜትር ስፋትና አንድ ሜትር ከፍታ ያለው ሰሌዳ አገልግሎት ላይ የዋለው ለአምስተኛና ለስድስተኛ ክፍል ተማሪዎች ነው። ለታሪክ፣ ለሳይንስ፣ ለሂሣብ፣ ለጂኦግራፊና ለሌሎች ትምህርቶች ማስተማሪያነት ሰባት መጻሕፍት በኤሌክትሮኒክ ቅጂዎች ተዘጋጅተዋል። በተጨማሪም በሰሌዳዎቹ ላይ ቪዲዮ ማሳየት ይቻላል። በዚህ የተነሣ በአንዲት መምህርት ክፍል ውስጥ የሚገኙ ተማሪዎች “የቲካልና ፓሌንቼን ፒራሚዶች አይተዋል፣ የማያዎችን ባሕል ተመልክተዋል እንዲሁም ሙዚቃቸውን አዳምጠዋል።” ታዲያ ጥቅሙ ምንድን ነው? መምህሯ “ተማሪዎች የበለጠ ትኩረት ሰጥተው ይማራሉ፣ ተሳትፏቸውም ጨምሯል” ብለዋል።
በዓመት አንድ ሚሊዮን የሚያክሉ ሰዎች ራሳቸውን ይገድላሉ
በመላው ዓለም በአሰቃቂ ሁኔታ ሕይወታቸውን ከሚያጡ ሰዎች መካከል ከግማሽ በላይ የሚሆኑት ራሳቸውን የሚገድሉ ናቸው። በየዓመቱ እስከ አንድ ሚሊዮን የሚደርሱ ሰዎች ራሳቸውን የሚገድሉ ሲሆን ይህ አኃዝ በ2001 በጦርነትና በነፍስ ግድያ ከሞቱ ሰዎች አኃዝ በልጦ ተገኝቷል። አንድ ሰው ራሱን ሲገድል ሌሎች ከ10 እስከ 20 የሚደርሱ ሰዎች ያልተሳካ ራስን የመግደል ሙከራ ያደርጋሉ። ይህን አኃዛዊ መረጃ ያወጣው በስዊዘርላንድ፣ ጄኔቫ የሚገኘው የዓለም ጤና ድርጅት ነው። ይህ ድርጅት እንዳለው አንድ ሰው በሞተ ቁጥር “ስሜታዊ፣ ማኅበራዊና ኢኮኖሚያዊ ቀውስ የሚደርስባቸው በርካታ ቤተሰቦችና ወዳጆች ይኖራሉ።” ሰዎች ራሳቸውን እንዳይገድሉ ከሚረዱ ነገሮች መካከል “ከፍተኛ የሆነ በራስ የመተማመን መንፈስ፣” ከቤተሰቦችና ከወዳጆች የሚገኝ ስሜታዊ ድጋፍ፣ ጠንካራ የቤተሰብ ትስስር ብሎም ሃይማኖተኝነት ወይም መንፈሳዊነት እንደሚገኙበት ሪፖርቱ ገልጿል።
አቧራማ አውሎ ነፋስ የሚያደርሰው ጉዳት
የለንደኑ ዘ ታይምስ መጽሔት በበረሃማ አካባቢዎች ባለሁለት ዲፈረንሽያል መኪናዎች መነዳታቸው “በመላው ዓለም የአቧራማ አውሎ ነፋሶች ብዛት በአሥር እጥፍ እንዲያድግ ያደረገ ሲሆን ይህም በአካባቢያችንና በሰዎች ጤና ላይ ከፍተኛ ጉዳት በማድረስ ላይ ነው” ይላል። ተሽከርካሪዎቹ በጣም ስስ የሆነውን የምድረ በዳውን ገጽ ስለሚጎዱ የአቧራ ቅንጣቶች በነፋስ ተገፍተው ይነሳሉ። የኦክስፎርድ ዩኒቨርሲቲ ባልደረባ የሆኑት ፕሮፌሰር አንድሩ ጉዲ “ባሁኑ ጊዜ በምድረ በዳ አካባቢዎች የሚንቀሳቀሱ በርካታ ተሽከርካሪዎች አሉ” ብለዋል። “በመካከለኛው ምሥራቅ ግመል ይጋልቡ የነበሩ ዘላኖች አሁን መንጎቻቸውን የሚጠብቁት በባለ ሁለት ዲፈረንሽያል መኪኖች ነው።” “አቧራማ አውሎ ነፋሶች” ከምድረ በዳዎች ጠርገው ከሚረጯቸው የአቧራ ቅንጣቶች በተጨማሪ “ከእርሻ ማሳዎችና ከደረቁ የሐይቅ ወለሎች የፀረ አረምና የፀረ ተባይ መድኃኒት ብናኞችን አንስተው ወደ ከባቢ አየር እንዲገቡ ያደርጋሉ” ሲሉ ጉዲ ያስጠነቅቃሉ። ከዚህም ሌላ በነፋስ የሚወሰዱ ቅንጣቶች ከባድ የጤና ችግር ሊያስከትሉ የሚችሉ አለርጂዎችንና ተሕዋስያንን ተሸክመው ያሰራጫሉ። የአካባቢ ደኅንነት ተመራማሪዎች የአፍሪካ አሕጉር በከፊል በ1930ዎቹ ዓመታት በዩናይትድ ስቴትስ በድርቅና መሬቱ ከመጠን በላይ በመታረሱ ምክንያት በፕሬይሪ አካባቢዎች ላይ የደረሰውን ውድመት የመሰለ ጥፋት ሊደርስበት ይችላል ብለው ይሰጋሉ።
ተራራ ወጪዎች ግድየለሽነታቸው ለአደጋ እያጋለጣቸው ነው
በየዓመቱ በመቶ የሚቆጠሩ ሰዎች ተራራ ሊወጡ ሲሞክሩ ይሞታሉ። አንዳንዶቹ የሚሞቱት ድንጋይ ተንዶባቸው ወይም እንደ ልብ ድካም ባሉ ቀድሞ በማያውቋቸው የጤና ችግሮች ምክንያት ነው። ይሁን እንጂ ላይፕሲገር ፎልክጻይቱንግ የተባለው የጀርመን ጋዜጣ ተራራ የሚወጡ ሰዎች ከሚሞቱባቸው ዋነኛ ምክንያቶች አንዱ ግድየለሽነት እንደሆነ ገልጿል። ችግሩ በወጣቶችና ልምድ በሌላቸው ላይ ብቻ የተወሰነ አይደለም። የዘርማት፣ ስዊዘርላንድ የተራራ ወጪ መሪዎች ማኅበር ፕሬዚዳንት የሆኑት ሚጂ ቢነር እንደሚሉት “ልምድ ያላቸውም ሆኑ የሌላቸው፣ አብዛኛውን ጊዜ አደጋ የሚደርስባቸው አቅማቸውን ባለማወቃቸው ወይም የአየሩን ሁኔታም ሆነ ሌሎች ሁኔታዎችን በትኩረት ባለመከታተላቸው የተነሣ ነው።” ተንቀሳቃሽ ስልክ የሚይዙ አንዳንድ ሰዎች ምንም አደጋ ቢደርስባቸው የሚያነሳቸው ሄሊኮፕተር እንደሚኖር በማመን ከልክ በላይ ይዳፈራሉ።
አደገኛ የሆኑ የባሕር ሞገዶች
በመላው ዓለም በአማካይ በየሳምንቱ ሁለት ትላልቅ መርከቦች እንደሚሰጥሙ ተነግሯል። ከ200 ሜትር የበለጠ ርዝመት ያላቸው ነዳጅ ተሸካሚና ኮንቴይነር ጫኝ መርከቦች ሳይቀሩ ሰጥመዋል። ከእነዚህ አደጋዎች መካከል አብዛኞቹ የደረሱት በአደገኛ የባሕር ሞገዶች ምክንያት እንደሆነ ይታመናል። ትላልቅ መርከቦችን ሊያሰምጡ የሚችሉ በጣም ትልቅ ከፍታ ያላቸው ሞገዶች እንደታዩ የሚገልጹ ሪፖርቶች ባሕረኞች የፈጠሯቸው የተጋነኑ ታሪኮች ተደርገው ይወሰዱ ነበር። ይሁን እንጂ የአውሮፓ ኅብረት ያደረገው ጥናት እነዚህ ታሪኮች ትክክለኛ እንደሆኑ አረጋግጧል። በሳተላይት ራዳር መሣሪያዎች አማካኝነት የተደረገው ጥናት በጣም ግዙፍ ሞገዶች መኖራቸውን አመልክቷል። የዚህ ጥናት መሪ የሆኑት ቮልፍጋንግ ሮዘንታል “ማንም ሰው ያስብ ከነበረው የበለጠ ብዙ ትላልቅ የባሕር ሞገዶች መኖራቸው ተረጋግጧል” ማለታቸውን ሱትዶይቸ ጻይቱንግ ዘግቧል። ቡድናቸው በሦስት ሳምንት ጊዜ ውስጥ ቢያንስ አሥር ትላልቅ ሞገዶች አይቷል። እነዚህ ሞገዶች ቀጥ ብለው የሚቆሙ፣ እስከ 40 ሜትር የሚደርስ ከፍታ ያላቸውና መርከቦችን ክፉኛ ሊጎዱ ብሎም ሊያሰጥሙ የሚችሉ ናቸው። ይህን ኃይል ሊቋቋሙ የሚችሉ መርከቦች ብዙ አይደሉም። “አሁን የምናጠናው የሞገዶቹን መነሳት መተንበይ እንችል እንደሆነ ነው” ይላሉ ሮዘንታል።