በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

የሳሙና ታሪካዊ አመጣጥ

የሳሙና ታሪካዊ አመጣጥ

የሳሙና ታሪካዊ አመጣጥ

የሳሙናን ያህል በሁሉም ቦታ የሚገኙና ጠቃሚ የሆኑ ምርቶች ብዙ አይደሉም። ከሕፃንነታችን ጀምሮ በሕይወት ዘመናችን ሁሉ በየዕለቱ በሳሙና እንጠቀማለን። ሳሙና ለመጀመሪያ ጊዜ የተሠራበት ትክክለኛ ጊዜ ባይታወቅም የቅንጦት ዕቃ መሆኑ ቀርቶ ቀስ በቀስ የዕለታዊ ፍላጎታችን ክፍል ሆኗል።

በ19ኛው መቶ ዘመን የኖሩ አንድ የኬሚስትሪ ባለሞያ አንድ አገር የሚጠቀምበት ሳሙና ብዛት የሕዝቡን ብልጽግናና ሥልጣኔ ለመገምገም የሚያስችል ትክክለኛ መመዘኛ እንደሆነ ተናግረው ነበር። ዛሬ ሳሙና ለንጽሕና እንዲሁም ጤንነትን ለመጠበቅ መሠረታዊ ነገር እንደሆነ ተደርጎ ይቆጠራል። ይህ አስፈላጊ ምርት የዕለት ተዕለት ሕይወታችን ክፍል ለመሆን የበቃው እንዴት ነው?

በጥንት ዘመናት

ከክርስቶስ ልደት በፊት በነበሩት ዘመናት ሳሙና የግል ንጽሕናን ለመጠበቅ ይውል እንደነበረ የሚጠቁም ማስረጃ የለም። በእርግጥ የአማርኛው መጽሐፍ ቅዱስ በኤርምያስ 2:22 ላይ “በልዩ ቅጠል ብትታጠቢ፣ ብዙ ሳሙና ብትጠቀሚም” ይላል። ሆኖም እዚህ ላይ የተገለጸው “ሳሙና፣” ዛሬ እኛ የምናውቀውን በዱቄት መልክም ሆነ በደረቁ አሊያም በሌላ መልክ የተዘጋጀ ሳሙና የሚያመለክት መሆኑን እንድንጠራጠር የሚያደርጉን ምክንያቶች አሉ። እዚህ ላይ የተገለጸው፣ ዛሬ ከምንጠቀምበት ሳሙና ፈጽሞ የተለየ ከአልካላይን የተዘጋጀ ማጽጃ ሳይሆን አይቀርም።

ግሪኮች በኋላ ላይ ደግሞ ሮማውያን ሰውነታቸውን ለመታጠብ ሽቶ የተቀላቀለባቸው ዘይቶችን የመጠቀም ልማድ ነበራቸው። ሳሙና መሥራት የተማሩት ኬልት ከሚባሉት ሕዝቦች ሊሆን ይችላል። በመጀመሪያው መቶ ዘመን ይኖር የነበረው ሮማዊው ጸሐፊ ታላቁ ፕሊኒ ናቹራል ሂስትሪ በተባለው መጽሐፉ ላይ ሳይፖ የተባለውን የፈረንሳይኛ ቃል የተጠቀመ ሲሆን እንደ እንግሊዝኛ፣ ጀርመንኛ፣ ፖርቹጋል፣ ሮማንያና ስፓንኛ ያሉት ቋንቋዎች “ሳሙና” ለሚለው ቃል የራሳቸውን መጠሪያ ያገኙት ከዚህ እንደሆነ ይነገራል።

ከዚያ በኋላ በነበሩት ዘመናት ሳሙና ጥቅም ላይ ስለ መዋሉ ተጠቅሶ የምናገኘው ነገር በጣም ጥቂት ነው፤ በመካከለኛው መቶ ዘመን ግን ኢጣሊያ፣ ስፔይንና ፈረንሳይ ሳሙና ማምረት ጀመሩ። ያም ሆኖ ብዛት ያለው ሳሙና ለማምረት ጥረት ቢደረግም የአውሮፓ የሳሙና ፍጆታ በጣም ጥቂት ነበር። እንዲያውም በ1672 አንድ የጀርመን ሰው ለአንዲት እመቤት መልካም ምኞቱን ለመግለጽ የታሸገ የኢጣሊያ ሳሙና በስጦታ መልክ ሲልክ ይህን ያልተለመደ ዕቃ እንዴት እንደምትጠቀምበት የሚገልጽ ዝርዝር መመሪያ አብሮ መላክ እንደሚያስፈልግ ተሰምቶት ነበር!

ቀደም ባሉት ዘመናት የነበረው የሳሙና አመራረት

ስለ ሳሙና አሠራር የሚገልጸው የመጀመሪያው ዝርዝር መመሪያ የተገኘው በ12ኛው መቶ ዘመን በተዘጋጀ ሳሙና የሚሠራበትን ምስጢር በሚገልጽ መዝገብ ላይ ነው። ዓመታት እያለፉ ቢሄዱም ሳሙና የሚቀመምበት መሠረታዊ አሠራር አልተቀየረም። ከተለያዩ ነገሮች የተገኙ ዘይቶችና ቅባቶች አልካላይን ከተባለ የሚያሟሟ ኬሚካል ጋር ሲፈሉ ድፍድፍ ወይም ያልተጣራ ሳሙና ይወጣል። ይህ ለውጥ የሚካሄድበት ሂደት ሰፖነፊኬሽን በመባል ይጠራል።

የሳሙና ጥራት በተሠራበት ጥሬ ዕቃ ዓይነት ላይ የተመካ እንደሆነ ግልጽ ነው። ጥንት ሳሙና ሲሠራ ጥቅም ላይ የሚውሉት ጥሬ ዕቃዎች ከተቃጠለ እንጨት የተወሰደ አመድና ስብ ነበሩ፤ የመጀመሪያዎቹ የዩናይትድ ስቴትስ ሰፋሪዎች በእነዚህ ጥሬ ዕቃዎች በመጠቀም ቡናማ መልክ ያለውና ወፈር ያለ ፈሳሽ ሳሙና አዘጋጅተው ይጠቀሙበት ነበር። በወቅቱ ሳሙናም ሆነ ሻማ ለመሥራት የሚውለው ዋነኛው ንጥረ ነገር የቀለጠ የበጎችና የከብቶች ሞራ ሲሆን ብዙውን ጊዜ ነጋዴዎች ሻማና ሳሙና በመሥራት ይሸጡ ነበር። ሳሙናውን አፍልተው ሊያወጡት ሲሉ ጨው መጨመራቸው ደረቅ ያለና በቀላሉ ከቦታ ቦታ ለማጓጓዝ የሚያመች ሳሙና መሥራት አስችሏቸዋል፤ ከዚያም መልካም መዓዛ እንዲኖረው እንደ ላቬንደር፣ ዊንተርግሪን ወይም ካራዌ ያሉ እፅዋትን ይጨምሩበታል።

በደቡባዊ አውሮፓ የሚመረተው ሳሙና በአብዛኛው ከወይራ ዘይት የሚዘጋጅ ነበር። በሌላ በኩል ደግሞ ቀዝቃዛ የአየር ንብረት ባለባቸው ቦታዎች የሚኖሩ ሳሙና አምራቾች በሞራ መጠቀማቸውን የቀጠሉ ሲሆን አንዳንዶች ደግሞ የዓሣ ዘይትን ለጥሬ ዕቃነት ማዋል ጀመሩ። በዚህ መንገድ የሚሠራው ሳሙና ለልብስ ማጠቢያነት ቢያገለግልም ሰውነትን ለመታጠብ ግን አይመረጥም ነበር! ሆኖም ሳሙና ለመሥራት የሚያገለግለው ንጥረ ነገር ስብና ዘይት ብቻ አልነበረም።

ሳሙናን በብዛት ማምረት ተጀመረ

ለበርካታ ዘመናት፣ ሳሙና ለመሥራት የሚያገለግለው አልካላይን የተባለው ንጥረ ነገር የሚዘጋጀው በባሕር ውስጥ የሚበቅሉ እፅዋትን ጨምሮ ከሌሎች የተመረጡ ተክሎች አመድ ነበር። ስፔይን ውስጥ ሳልትዎርት የተባለውን ተክል በማቃጠል ባሪላ ተብሎ የሚጠራ የአልካላይን አመድ ይሠራ ነበር። ይህንን አመድ ቤት ውስጥ ከተዘጋጀ የወይራ ዘይት ጋር በመቀላቀል ካስቲል የሚባል ከፍተኛ ጥራት ያለው ነጭ ሳሙና ማምረት ተችሏል።

በ18ኛው መቶ ዘመን ሳሙና፣ ጠርሙስና ባሩድ ለማምረት የሚውለው ፖታሽ የተባለው ንጥረ ነገር በዓለም ዙሪያ ተፈላጊነቱ እየጨመረ መጣ። * በ1790 አካባቢ ኒኮላ ለብላን የተባለ ፈረንሳዊ የቀዶ ሕክምናና የኬሚስትሪ ባለሞያ አልካላይን የተባለውን ንጥረ ነገር ከጨው መሥራት የሚቻልበትን መንገድ አገኘ። ቆየት ብሎም ሌሎች የኬሚስትሪ ባለሞያዎች በውኃ የተበጠበጠ ጨው በመጠቀም ኮስቲክ ሶዳ (ሶድየም ሃይድሮክሳይድ) የተባለውን ንጥረ ነገር ማምረት ቻሉ። እነዚህ ግኝቶች ሳሙናን በኢንዱስትሪ ደረጃ ማምረት የሚቻልበትን መንገድ ጠርገዋል።

ሳሙና ስመ ገናና ሆነ

የ19ኛው መቶ ዘመን መገባደጃ ሰዎችን ስለ ጤናና ንጽሕና ለማስተማር ጥረት የተደረገበት ታላቅ የለውጥ ወቅት ነበር። ያም ሆኖ ግን በጊዜው የነበረው ሳሙና ቡናማ መልክ ያለውና በአብዛኛው ደስ የማይል ከመሆኑም በላይ አልካላይን የተባለው ንጥረ ነገር በደንብ ስለማይጣራ ሰውነትን ይቆጠቁጥ ነበር። ይህ ዓይነቱ ሳሙና የሚዘጋጀው በቤት ውስጥ ንጥረ ነገሮቹን በትላልቅ ድስቶች በማፍላት ነው። ሳሙናው ለሕዝብ የሚሸጠው ተቆራርጦ በሚዛን እየተመዘነ ሲሆን ማን እንዳመረተው የሚገልጽ ምንም ነገር አልነበረውም።

አንዳንዱ ሳሙና በቀላሉ አረፋ ቢያወጣም ከተጠቀሙበት በኋላ እጅ ላይ የሚቀር ቅባት ያለው ከመሆኑም በላይ እያደር መጥፎ ጠረን ያመጣል። በመሆኑም አምራቾች የሸማቹን ፍላጎት ለማርካት የሚያደርጉትን ጥረት በማሳደግ ሳሙናው የሚያጥወለውል ጠረኑ ቀርቶ ደስ የሚል የሎሚ መዓዛ እንዲኖረው የሚያደርጉ እንደ ሲትሮኔላ ያሉ ቅጠላ ቅጠሎችን መጨመር ጀመሩ።

የሳሙናን ጥራት ለማሳደግ ተጨማሪ ማሻሻያዎች እየተደረጉ ነበር። ከአትክልት ዘይት የሚሠሩ ሳሙናዎች ከሌሎቹ የሚበልጡባቸው ጥሩ ጎኖች ስላሏቸው ተወዳጅ እየሆኑ መጡ። በመጓጓዣ ረገድ የተደረገው ለውጥም የሳሙና አምራቾች ከፍተኛ ጥራት ያላቸው ጥሬ ዕቃዎችን በብዛትና በቀላሉ ማግኘት እንዲችሉ መንገድ ከፈተላቸው። ምዕራብ አፍሪካ ከዘምባባ ፍሬ የሚገኝ ዘይት ምንጭ ነበረች፤ ከፍሬው የሚወሰደው ፈካ ያለ ቀለም ያለውና ቅቤ የሚመስል ንጥረ ነገር ደግሞ ሳሙናና መዋቢያዎችን ለመሥራት የሚውል ዋነኛ ጥሬ ዕቃ ሆነ። ከፓስፊክ ደሴቶች ኮፕራ የተባለ የደረቀ ኮኮናት ይመጣ የነበረ ሲሆን ከዚህም የኮኮናት ዘይት ይመረታል። ርቀው ከሚገኙ የተለያዩ አገሮች በሚመጡ ጥሬ ዕቃዎች በመጠቀም የሚመረተው ሳሙና ቀስ በቀስ ታዋቂና ተወዳጅ እየሆነ መጣ።

አምራቾች፣ ሰዎች በተፈጥሯቸው ንጽሕናቸውን የመጠበቅ ፍላጎት እንዳላቸው ያውቃሉ፤ ሳሙና ለንጽሕና በጣም አስፈላጊ መሆኑን ለሸማቾች ማሳመን ያስፈልጋል። በመሆኑም ማስታወቂያ የሚያዘጋጁ ሰዎች ምርቶቻቸው የሚያስገኙትን ውጤት እንደ ማር፣ ፀሐይና በረዶ ከመሳሰሉት ነገሮች ጋር አያይዘው ማስተዋወቅ ጀመሩ። ሌሎች ደግሞ ሳሙና የጽዳትና የሥልጣኔ መገለጫ እንደሆነ አድርገው ለማስተዋወቅ ታዋቂ የሥነ ጥበብ ሥራዎችን ይጠቀሙ ነበር። በ19ኛው መቶ ዘመን መባቻ ላይ ሳሙና በዓለም ዙሪያ ተፈላጊነት ያለው ምርት ሆነ። ይህም የማስታወቂያው ሥራ እንዲጧጧፍ አደረገ። በ1894 ሳሙናን የሚያስተዋውቁ አርማዎች በኒው ዚላንድ የፖስታ ቴምብሮች ላይ እንኳ ሳይቀር ይለጠፉ ጀመር። በዚህ ወቅት ሳሙና ስመ ገናና ሆኖ ነበር።

ዘመናዊው አመራረት

ቀደም ባሉት ዘመናት ሳሙና የሚሠራው ጥሬ ዕቃዎቹን በትላልቅ ድስቶች ውስጥ በማፍላት ሲሆን አንድ ልምድ ያለው ሰው ሳሙናውን በማማሰል ጥራቱን ይከታተል ነበር። ሳሙናውን በማማሰያው ጠቀስ አድርጎ በመመልከት ጥሬ ዕቃዎቹን ወይም ሂደቱን ማሻሻል ያስፈልግ እንደሆነ ይወስናል።

በዛሬው ጊዜ ሳሙና ሲመረት በሦስት መሠረታዊ ሂደቶች ያልፋል። የመጀመሪያው ሰፖነፊኬሽን የሚባለውና የተለያዩ ዘይቶችን ወይም ስቦችን ከአልካላይን ጋር በማፍላት የተጣራ ሳሙና እና ግሊሰሮል የሚባል ንጥረ ነገር የሚወጣበት ሂደት ነው፤ ከዚህ ውህድ 30 በመቶ ያህሉ ውኃ ነው። አልፎ አልፎ ይህ ሂደት ጥሬ ዕቃዎቹን በትልቅ ድስት በማፍላት የሚካሄድ ቢሆንም አብዛኞቹ ዘመናዊ ሳሙና አምራቾች ሰፖነፊኬሽን የሚባለውን ሂደት የሚያከናውኑት በኮምፒውተር በመታገዝ ነው። በሁለተኛው ደረጃ ላይ የተጣራው ሳሙና በሙቀትና በአየር ይደርቅና 12 በመቶ ብቻ የውኃ ይዘት ኖሮት በትናንሹ እንዲድበለበል ይደረጋል። ሦስተኛውና የመጨረሻው ሂደት ሳሙናውን የማጠናቀቁ ሥራ ነው። በትንንሹ የተድበለበለው ሳሙና መልካም መዓዛ እንዲኖረውና ከሌሎች የሳሙና ምርቶች የተለየ እንዲሆን ሽቶ፣ ቀለምና ሌሎች ንጥረ ነገሮች ይጨመሩበትና ወጥ ሆኖ ይወጣል። ከዚያም የተለያየ ቅርጽ እንዲይዝ በሳሙና መዳመጫ ውስጥ ያልፋል። ዛሬ ዛሬ ሸማቾች ቤት ውስጥ የሚጠቀሙባቸው ሳሙናዎች የፍራፍሬና የእፅዋት መዓዛ እንዲኖራቸው ይፈልጋሉ፤ ይህም በሳሙና መጠቀምን መንፈስን የሚያድስ “ተፈጥሯዊ” ነገር እንዲሆን አድርጎታል!

ሳሙና የሚቀመምበትን መንገድ በተመለከተ ያለው ግንዛቤ ከማደጉም በላይ የሚመረትበትን መንገድ በተመለከተ በርካታ ለውጦች ቢካሄዱም በቤት ውስጥ በእጅ የሚሠራው ሳሙና አሁንም ቢሆን ተወዳጅነቱ አልቀነሰም። ሳሙና ለንጽሕናና ለጤና በጣም አስፈላጊ መሆኑን የማይቀበል ሰው የለም። ያም ሆኖ ግን በሥነ ምግባርና በመንፈሳዊ ሁኔታ የቆሸሸ መሆኑ በሚታወቀው በዚህ ዘመን፣ በአካላዊ ሁኔታ ይበልጥ ንጽሕናን መጠበቅ የሚቻል መሆኑ አስገራሚ ነው። ሆኖም ውጫዊ ንጽሕና ይበልጥ ዋጋማ የሚሆነው ውስጣችንም ንጹሕ ሲሆን ነው።

[የግርጌ ማስታወሻ]

^ አን.14 አልካላይን የተባለው ኬሚካል ውኃው ተንኖ እስኪያልቅ ድረስ ከተንተከተከ በኋላ የሚቀረው ነገር ፖታሽ ይባላል። ፖታሹ ቆሻሻው ሙሉ በሙሉ እስኪወገድ ድረስ በእሳት ሲቃጠል ፐርል አሽ በመባል የሚጠራ ነጭ አመድ ይቀራል።

[በገጽ 28 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

ጥንት በሰሜን አሜሪካ ሳሙና ሲሠራ

[በገጽ 29 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

ጥሬ ዕቃዎቹን በማፍላት ሳሙና የሚመረትበት ጥንታዊ ዘዴ

[በገጽ 29 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

“በብልስ” የተባለው የሰር ጆን ኤቭሪት ሚሌ ሥዕል የሳሙና ማስታወቂያ ለመሥራት ውሎ ነበር

[በገጽ 29 ላይ የሚገኝ የሥዕል ምንጭ]

ከላይ:- Victoria & Albert Museum, London/Art Resource, NY; ከታች:- © Jeff Greenberg/Index Stock Imagery