በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

ለድንግል ማርያም ጸሎት ማቅረብ ተገቢ ነው?

ለድንግል ማርያም ጸሎት ማቅረብ ተገቢ ነው?

የመጽሐፍ ቅዱስ አመለካከት

ለድንግል ማርያም ጸሎት ማቅረብ ተገቢ ነው?

ማርያም ስለ ክርስትና አንዳች ነገር በማያውቁ በአብዛኞቹ ሰዎች ዘንድ በደንብ ትታወቃለች። ሁሉን ቻይ የሆነው አምላክ ይህች ወጣት ሴት ኢየሱስን እንድትወልድ በማድረግ የባረካት መሆኑን ቅዱሳን ጽሑፎች ይናገራሉ። ማርያም ኢየሱስን በጸነሰችበት ጊዜ ድንግል የነበረች መሆኗ የኢየሱስን አወላለድ ልዩ ያደርገዋል። አንዳንድ የሕዝበ ክርስትና አብያተ ክርስቲያናት ረዘም ላለ ጊዜ ለማርያም ልዩ የሆነ አምልኮታዊ ክብር ሲሰጡ ኖረዋል። በ431 ከክርስቶስ ልደት በኋላ በኤፌሶን የተካሄደው ጉባኤ ማርያም “የእግዚአብሔር እናት” እንደሆነች ያስታወቀ ሲሆን በዛሬው ጊዜም ብዙ ሰዎች ወደ ማርያም እንዲጸልዩ ተምረዋል። *

የአምልኮታቸው ጉዳይ ከልብ የሚያሳስባቸው ሰዎች ጸሎታቸውን ወደ ትክክለኛው ጸሎት ሰሚ አካል ማቅረብ እንዳለባቸው ያውቃሉ። ታዲያ መጽሐፍ ቅዱስ በዚህ ጉዳይ ላይ ምን ያስተምራል? ክርስቲያኖች ወደ ድንግል ማርያም መጸለይ ይኖርባቸዋል?

‘መጸለይ አስተምረን’

የሉቃስ ወንጌል ዘገባ ከኢየሱስ ደቀ መዛሙርት አንዱ ‘ጌታ ሆይ፤ መጸለይ አስተምረን’ በማለት እንደጠየቀው ዘግቧል። በምላሹም ኢየሱስ “ስትጸልዩ እንዲህ በሉ፤ ‘አባታችን ሆይ፤ ስምህ ይቀደስ።’” እንደዚሁም ኢየሱስ በተራራው ስብከቱ ላይ ተከታዮቹ “በሰማያት የምትኖር አባታችን ሆይ፤ ስምህ ይቀደስ” በማለት እንዲጸልዩ አስተምሯቸዋል።—ሉቃስ 11:1, 2፤ ማቴዎስ 6:9

እዚህ ላይ በቅድሚያ የምንማረው ነገር ቢኖር ጸሎት መቅረብ ያለበት የኢየሱስ አባት ለሆነው ለይሖዋ መሆኑን ነው። በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ ወደ ይሖዋ ካልሆነ በቀር ወደ ሌላ ወደ ማንኛውም አካል መጸለይ እንዳለብን የሚጠቁም ሐሳብ አናገኝም። ይህም ተገቢ ነው፤ ምክንያቱም ሙሴ አሥርቱን ትእዛዛት ሲቀበል ይሖዋ እሱ ብቻ እንዲመለክ የሚፈልግ “ቀናተኛ አምላክ” እንደሆነ ተነግሮታል።—ዘፀአት 20:5

በጸሎት ጊዜ መቁጠሪያ ስለመጠቀም ምን ለማለት ይቻላል?

ወደ ማርያም የሚጸልዩ ብዙ ሰዎች እመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም ሆይ እና አቡነ ዘበሰማያት እንደሚሉት ያሉ ጸሎቶችን በዘልማድ የተወሰነ ቁጥር ያህል መድገም በረከት ያስገኛል የሚል ትምህርት ተሰጥቷቸዋል። በካቶሊኮች ዘንድ “በሠፊው የሚታወቀው የማርያም አምልኮ የሚከናወነው መቁጠሪያን በመጠቀም ነው” በማለት ሲምቦልስ ኦቭ ካቶሊሲዝም የተሰኘው መጽሐፍ ይናገራል። በመቁጠሪያ አማካኝነት የሚካሄደው ጸሎት ለድንግል ማርያም ክብር የሚካሄድ ሃይማኖታዊ ሥርዓት ነው። መቁጠሪያው ጸሎቶቹን ለመቁጠር የሚገለገሉባቸውን በክር ላይ የተሰኩ ዶቃዎች የያዘ ነው። ይኸው መጽሐፍ “በየመሃላቸው በአንድ ለየት ያለ ዶቃ አምስት ቦታ የተከፋፈሉት አሥር አሥር ዶቃዎች ‘እመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም ሆይ’ የሚለውን ጸሎት ሃምሳ ጊዜ፣ ‘አቡነ ዘበሰማያት’ እና ‘ስብሐት ለአብ’ የሚሉትን ጸሎቶች ደግሞ አምስት አምስት ጊዜ ለመድገም ያገለግላሉ” በማለት ይናገራል። ታዲያ አምላክ በመቁጠሪያ አማካኝነት በመድገም የሚቀርበውን እንዲህ ያለ ጸሎት ይሰማል?

እዚህም ላይ ኢየሱስ ለደቀ መዛሙርቱ የሰጣቸው መመሪያዎች ቁርጥ ያለ መልስ ይሰጡናል። ኢየሱስ “ስትጸልዩ፤ ከንቱ ቃላት በመደጋገም ጸሎታቸው የሚሰማላቸው እንደሚመስላቸው አሕዛብ ነገራችሁን አታስረዝሙ” ሲል ተናግሯል። (ማቴዎስ 6:7) ስለዚህ ኢየሱስ ይህንን ጉዳይ ለይቶ በመጥቀስ ተከታዮቹ በጸሎታቸው ላይ የተወሰነ ደንብ ተከትለው እየደጋገሙ የመጸለይን ልማድ እንዲያስወግዱ ነግሯቸዋል።

ይሁን እንጂ አንድ ሰው ‘ኢየሱስ ዛሬ ሰዎች በመቁጠሪያ እየደገሙ ከሚጸልዩአቸው ጸሎቶች አንዱ የሆነውን አቡነ ዘበሰማያት የተሰኘውን ጸሎት ደቀ መዛሙርቱ እየደገሙ እንዲጸልዩ አስተምሯቸው የለም እንዴ?’ ብሎ ይጠይቅ ይሆናል። ኢየሱስ አቡነ ዘበሰማያት ወይም የጌታ ጸሎት በመባል የሚታወቀውን የናሙና ጸሎት እንዳስተማረ የታወቀ ነው። ይሁን እንጂ ጸሎቱን ያስተማራቸው “ከንቱ ቃላት በመደጋገም” እንዳይጸልዩ ካስጠነቀቀ በኋላ መሆኑ ሊስተዋል ይገባዋል። ኢየሱስ የናሙና ጸሎቱን ሲያስተምር በቃል ተሸምድዶ እንዲደገም አስቦ እንዳልነበረ የሚያረጋግጠው ሌላ ነገር ደቀ መዛሙርቱን ጸሎት እንዳስተማረ በሚገልጹት ሁለት ዘገባዎች ላይ የአገላለጽ ልዩነት መኖሩ ነው። (ማቴዎስ 6:9-15፤ ሉቃስ 11:2-4) ኢየሱስ በእነዚህ ጸሎቶች ላይ የገለጻቸው ሐሳቦች ተመሳሳይ ቢሆኑም ቃላቱ ግን የተለያዩ ናቸው። ይህም ኢየሱስ ተከታዮቹ እንዴትና ስለምን ጉዳይ መጸለይ እንደሚችሉ ናሙና ወይም ምሳሌ የሚሆን ጸሎት መስጠቱ ብቻ እንደነበረ እንድንገነዘብ ያደርገናል። ከሁሉም በላይ ደግሞ የኢየሱስ ቃላት ጸሎት መቅረብ ያለበት ለማን እንደሆነ አመልክተዋል።

ማርያምን ማክበር

ቅዱሳን ጽሑፎች ክርስቲያኖች ወደ ማርያም እንዲጸልዩ የማያስተምሩ መሆናቸው ማርያም በአምላክ ዓላማ አፈጻጸም ውስጥ ለተጫወተችው ሚና ሊሰጣት የሚገባውን አክብሮት እንድታጣ አያደርጋትም። በልጅዋ በኩል የሚመጡት በረከቶች ለታዛዥ የሰው ዘሮች ሁሉ ዘላለማዊ ጥቅም ያስገኛሉ። ማርያም ራሷም “ትውልድ ሁሉ ብፅዕት ይሉኛል” በማለት ተናግራለች። ዘመድዋ ኤልሳቤጥም “አንቺ ከሴቶች መካከል የተባረክሽ ነሽ” ብላታለች። በእርግጥም የተባረከች ነች። ማርያም መሲሑን እንድትወልድ መመረጧ ልዩ መብት ነበር።—ሉቃስ 1:42, 48, 49

ይሁን እንጂ በቅዱሳን ጽሑፎች ውስጥ የተባረከች ተብላ የተጠራችው ማርያም ብቻ አይደለችም። ኢያዔል ለጥንቱ የእስራኤል ሕዝብ በዋለችው ውለታ የተነሳ “በድንኳን ከሚኖሩ ሴቶች ሁሉ የተባረከች” እንደሆነች ተነግሮላታል። (መሳፍንት 5:24) ታማኟ ኢያዔል፣ ማርያምና በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ የተጠቀሱ ፈሪሃ አምላክ የነበራቸው ሌሎች ሴቶች የተዉትን አርዓያ መኮረጅ ቢያስፈልገንም ልናመልካቸው ግን አይገባንም።

ማርያም ታማኝ የኢየሱስ ተከታይ ነበረች። ምድራዊ አገልግሎቱን ባከናወነባቸው የተለያዩ ወቅቶችም ሆነ በሞተበት ጊዜ ካጠገቡ አልተለየችም። ከሙታን ከተነሳ በኋላም ከኢየሱስ ወንድሞች ጋር ‘ተግታ ትጸልይ’ ነበር። ይህም ማርያምም በ33 በዋለው የጰንጠቆስጤ ዕለት ከኢየሱስ ደቀ መዛሙርት ጋር በመንፈስ ቅዱስ እንደተቀባችና በሰማይ ከክርስቶስ ጋር የመግዛት ተስፋ ካላቸው የሙሽራይቱ ክፍል አባላት አንዷ እንደሆነች እንድናምን ያደርገናል።—ማቴዎስ 19:28፤ የሐዋርያት ሥራ 1:14፤ 2:1-4፤ ራእይ 21:2, 9

ይሁንና ይህም ቢሆን ወደ ማርያም እንድንጸልይ ምክንያት አይሆነንም። ልባዊ ጸሎት የአምልኮ ክፍል ከመሆኑም በላይ ክርስቲያኖች “በጸሎት ጽኑ” የሚል ማበረታቻ ተሰጥቷቸዋል። (ሮሜ 12:12) ይሁን እንጂ እንዲህ ዓይነቱ አምልኮታዊ ሥርዓት በኢየሱስ ክርስቶስ በኩል ለይሖዋ ብቻ መቅረብ ይኖርበታል።—ማቴዎስ 4:10፤ 1 ጢሞቴዎስ 2:5

[የግርጌ ማስታወሻ]

^ አን.3 ማርያም የእግዚአብሔር እናት ነች የሚለው ሐሳብ ቅዱስ ጽሑፋዊ ባልሆነውና ኢየሱስ እግዚአብሔር ነው በሚለው የሥላሴ መሠረተ ትምህርት ላይ የተመሠረተ ነው።