ስለ ቻት ሩም ማወቅ ያለብኝ ነገር ምንድን ነው?
የወጣቶች ጥያቄ . . .
ስለ ቻት ሩም ማወቅ ያለብኝ ነገር ምንድን ነው?
“አይናፋር ብሆንም እንኳን በኢንተርኔት ቻት ሩም አማካኝነት ፊት ለፊት ቢሆን ከማላናግራቸው ሰዎች ጋር ማውራት እችላለሁ። ስለማንነቴ ምንም አያውቁም።”—ፒተር *
“በቻት ሩም ስታወሩ የፈለጋችሁትን መናገር እንደምትችሉ ይሰማችኋል።”—አቢጌል
ሰዎች በኢንተርኔት አማካኝነት መልእክት በመጻጻፍ በቀጥታ የሚነጋገሩበት መንገድ ቻት ሩም ይባላል። ቻት ሩም፣ የሚላክላቸውን መልእክት ማንበብና መልስ መስጠት ለሚችሉ በርካታ ሰዎች ግልጋሎት ይሰጣል።
በተለይ ወጣት የኢንተርኔት ተጠቃሚዎች የሚወዷቸው አንዳንድ ቻት ሩሞች አሉ። የተለያየ ባሕል ያላቸው በሚሊዮን የሚቆጠሩ ወጣቶች በየዕለቱ ማንኛውንም ጉዳይ የሚመለከቱ ሐሳቦችን በቻት ሩም ይጻጻፋሉ። አሁን አሁን አንዳንድ ትምህርት ቤቶች በዚህ ዓለም አቀፍ የመገናኛ ዘዴ እየተጠቀሙ ነው። ለምሳሌ ያህል በዩናይትድ ስቴትስ የሚገኙ ተማሪዎች አስተማሪዎቻቸው እየተከታተሏቸው በስፔን፣ በእንግሊዝ ወይም በሌላ ቦታ ከሚገኙ ተማሪዎች ጋር ማኅበራዊ ጉዳዮችን አንስተው መነጋገር ይችላሉ። አልፎ ተርፎም ብቃት ካላቸው መሐንዲሶች፣ ቀማሚዎች ወይም ሌሎች ባለሙያዎች ጋር ስለ ክፍል ሥራቸው መነጋገር ይችላሉ።
ቢሆንም በርካታ ሰዎች በቻት ሩም መነጋገር የሚፈልጉት ስለ ትምህርት ጉዳዮች አይደለም። በኢንተርኔት የመጠቀም አጋጣሚ ካለህ ራስህን ከምን አደጋዎች መጠበቅ ይገባሃል?
የወሲብ ጥቃት ፈጻሚዎች ማጥመጃ
አቢጌል እንዲህ ብላለች:- “ከአንዳንድ ሰዎች ጋር በቻት ሩም እየተነጋገርኩ ሳለ አንድ ሰው የማውቃቸው የ14 ዓመት ልጆች እንዳሉ ጠየቀኝ። ከእነርሱ ጋር የፆታ ግንኙነት መፈጸም ፈልጎ ነበር። ለፆታ ግንኙነቱ ገንዘብ ሊከፍላቸው ፈቃደኛ እንደሆነም ነገረኝ።”
ችግር ያጋጠማት አቢጌል ብቻ አይደለችም። አዳኞች ኢንተርኔትን ተጠቅመው የሚፈጥሩት ችግር በጣም ከመስፋፋቱ የተነሳ መንግሥታት ወጣቶች እንዴት ከአደጋ መጠበቅ እንደሚችሉ የሚገልጹ መመሪያዎችን አዘጋጅተዋል። ለምሳሌ ያህል የዩናይትድ ስቴትስ ፌደራል የምርመራ ቢሮ (ኤፍቢአይ) ያሳተመው ጽሑፍ ገና መነጋገር እንደጀመሩ የጾታ ብልግናን በግልጽ ከሚያወሩ ግለሰቦች እንዲጠነቀቁ አሳስቧል። እንዲሁም “አሳቢነት፣ ፍቅርና ደግነት በማሳየት አልፎ ተርፎም ስጦታዎችን በመስጠት ዒላማዎቻቸውን ቀስ በቀስ የሚያታልሉ” ሰዎች እንዳሉ አስጠንቅቋል።
የዩናይትድ ስቴትስ ፌደራል የምርመራ ቢሮ ከእነዚህ ተንኮለኞች መካከል አንዳንዶቹ የሚጠቀሙባቸውን ዘዴዎች እንዲህ በማለት ለይቶ ጠቅሷል:- “ልጆች ችግራቸውን ሲናገሩ ያዳምጧቸዋል፤ አብረዋቸውም ያዝናሉ። በቅርብ የወጣውን ሙዚቃ፣ ልጆቹ ጊዜያቸውን እንዴት ማሳለፍ እንደሚፈልጉና ሌሎች ፍላጎቶቻቸውን በሚገባ ያውቃሉ። እነዚህ ግለሰቦች በኢንተርኔት ውይይት ወቅት ፆታዊ ቃላትንና ይህን የሚመለከቱ ርዕሰ ጉዳዮችን ቀስ በቀስ ጣል በማድረግ የልጆቹ የሀፍረት ስሜት እንዲቀንስ ለማድረግ ይሞክራሉ።”
አደገኛ ሁኔታ የሚፈጥሩት መጥፎ የሆኑ ትልልቅ ሰዎች ብቻ አይደሉም። የመጽሐፍ ቅዱስን የሥነ ምግባር ደረጃዎች ችላ የሚሉ ወይም ጨርሶ የማያከብሩ ወጣቶችንም በተመለከተ ጥንቃቄ አድርግ። ኮዴ የተባለ ወጣት ያጋጠመውን ነገር ተመልከት። ከወጣቶች ጋር በኢንተርኔት እየተነጋገረ ሳለ አንዲት ልጃገረድ እሷና እርሱ ብቻ ሊነጋገሩ ወደሚችሉበት ገጽ ውስጥ እንዲገባ ጋበዘችው። ከዚያም የፆታ ስሜት የሚቀሰቅስ ጥያቄ አቀረበችለት። ኮዴ ራሱን በመቆጣጠር ወዲያውኑ ውይይታቸውን አቋረጠ።
ስለ ፆታ የማወቅ ተፈጥሯዊ ፍላጎት ስላለን ኮዴ የወሰደውን ዓይነት እርምጃ መውሰድ በጣም ሊከብድህ ይችላል። ቀደም ሲል የተጠቀሰው ፒተር እንዲህ በማለት ሐቁን ተናግሯል:- “በኢንተርኔት የሚደረገው ውይይት መልኩን ቀይሮ ፆታዊ ጉዳይ ከተነሳ ንግግሩን ለማቋረጥ የሚያስችል ራስን የመግዛት ባሕርይ አለኝ ብዬ አስብ ነበር። ይሁንና ንግግሩን ሳላቋርጥ ብዙውን ጊዜ ስለ ፆታ ጉዳይ ውይይት አደርግ ነበር። ቆይቶ የጥፋተኝነት ስሜት ይሰማኝ ነበር።” ሆኖም ‘በቻት ሩም ሳወራ እውነተኛ ማንነቴን እስካልገለጽኩ ድረስ ስለ ፆታ ጉዳይ መነጋገሬ ምን አደጋ አለው?’ የሚል ጥያቄ ታነሳ ይሆናል።
በኢንተርኔት ስለ ፆታ ማውራት ጉዳት አለው?
መጽሐፍ ቅዱስ ስለ ፆታ በግልጽ ይናገራል። (ምሳሌ 5:18, 19) ሰዎች በወጣትነታቸው ከፍተኛ የፆታ ፍላጎት እንደሚኖራቸው የተረጋገጠ ነው። ስለዚህ ስለ ፆታ ጉዳይ መነጋገር አለብህ። በዚህ አንገብጋቢ ጉዳይ ረገድ ላሉህ ጥያቄዎች መልስ ማግኘት ይገባሃል። * ይሁን እንጂ የፆታ ጉዳይን በተመለከተ ላሉህ ጥያቄዎች መልስ የምታገኝበት መንገድ በአሁኑና በወደፊቱ ደስታህ ላይ ከፍተኛ ተጽዕኖ ያሳድራል።
በኢንተርኔት አማካኝነት ሌላው ቀርቶ ጓደኞችህ እንደሆኑ ከሚናገሩ ሰዎች ጋር ስለ ፆታ ጉዳይ የምታወራ ከሆነ መጨረሻህ በመጽሐፍ ቅዱስ ላይ እንደተገለጸው አንድ ወጣት ይሆናል። ይህ ወጣት ከጉጉቱ የተነሳ በአንዲት ዝሙት አዳሪ ቤት አካባቢ ያንዣብብ ነበር። መጀመሪያ ላይ ዝም ብላ ታነጋግረው ነበር። በኋላ ላይ ግን ፍላጎቱ በመቀስቀሱ ከእርሷ ጋር መነጋገሩ ብቻ አላረካውም። “ለዕርድ እንደሚነዳ በሬ . . . ሳያንገራግር ተከተላት፤ . . . በራ ወደ ወጥመድ እንደምትገባ ወፍ ሆነ።”—ምሳሌ 7:22, 23
በተመሳሳይ በኢንተርኔት ስለ ፆታ ማውራት በቀላሉ ፍላጎትህን ለማርካት ወደ መመኘት ይመራሃል። በጉርምስና ዕድሜ ላይ የሚገኝ ፊሊፕ የተባለ ወጣት “ከአንድ ሰው ጋር በኢንተርኔት እየተነጋገርኩ እያለ ኮምፒውተሬ ላይ በድንገት የብልግና ሥዕል ብቅ አለ። ምስሉን የላከው እያነጋገርኩት የነበረው ሰው ነው” ብሏል። አንድ ጊዜ የፆታ ብልግናን በገሃድ የሚያሳዩ ነገሮችን የመመልከት ፍላጎት ካደረብህ ምናልባት በአዋቂዎች ቻት ሩም ውስጥ ገብቶ ማየትን የመሳሰሉ ነገሮችን ለማድረግ ትፈተን ይሆናል። * ወሲባዊ ምስሎችን የማየት ሱስ የተጠናወታቸው ብዙ ሰዎች የሥነ ምግባር ብልግና መፈጸማቸውና መዘዙንም ማጨዳቸው አይቀርም።—ገላትያ 6:7, 8
በኢንተርኔት የፆታ ጉዳይ አንስተው ሊያነጋግሩህ የሚፈልጉ ሰዎች ስለ አንተ ደኅንነት ምንም አይገዳቸውም። እነዚህ የማታውቃቸው ሰዎች የሚፈልጉት የብልግና ወሬ እንድታወራና ምናልባትም ሥነ ምግባር የጎደለው ድርጊት እንድትፈጽም በማድረግ ፍላጎታቸውን ማርካት ነው። * ንጉሥ ሰሎሞን ልጁን ፆታዊ ጥቃት ከምትፈጽምበት ሴት ለመጠበቅ ሲል እንዲህ ብሎ ጽፏል:- ‘መንገድህን ከእርሷ አርቅ፤ በደጃፏም አትለፍ፤ ይኸውም ጒብዝናህን ለሌሎች እንዳትሰጥ፣ ባዕዳን በሀብትህ እንዳይፈነጥዙ ነው።’ (ምሳሌ 5:8-10) ከዚህ ምክር በስተ ጀርባ ያለው መመሪያ በሚከተለው መንገድ ሊሠራበት ይችላል:- በአንተ ጉዳት መፈንጠዝ ወይም መርካት ለሚፈልጉ ሰዎች ጉብዝናህን አሊያም ክብርህን ከመስጠት እንድትድን የፆታ ጉዳይ ከሚወራባቸው ቻት ሩሞች ራቅ።
“ግብዞች”
ምናልባት ስለ ፆታ ጉዳይ በኢንተርኔት አላወራም ትል ይሆናል። ሆኖም ቀደም ሲል እንደተጠቀሱት ፒተርና አቢጌል ቻት ሩም ማንነትህን ሳትገልጽና ምንም ሳታፍር ስለ ራስህ መናገር የምትችልበት መንገድ እንደሆነ ሊሰማህ ይችላል። * ዳሩ ግን ጥንቃቄ የሚጠይቅ ሌላም አደጋ አለ።
በቻት ሩም ስምህን መጥቀስ ስለማይጠበቅብህ ሐቅ ያልሆነ ነገር እንድትናገር ልትፈተን ትችላለህ። አቢጌል “ከሰዎች ጋር መነጋገር እጀምርና እነርሱ የሚያስቡት ዓይነት ሰው ሆኜ ለመገኘት እሞክራለሁ” ብላለች። አንተም ልክ እንደ አቢጌል ከአንድ የቻት ሩም ቡድን ጋር ለመመሳሰል ስትል ያልሆንከውን ሆነህ ለመቅረብ ትፈተን ይሆናል። አዳዲስ ጓደኞችን ለማግኘት ካለህ ምኞት የተነሳ እንደ እነርሱ መናገር ወይም እነርሱ የሚወዱትን መውደድ ልትጀምር ትችላለህ። በሌላ በኩል ደግሞ ወላጆችህ ወይም ጓደኞችህ እንደማይቀበሉት የምትገምተውን ሐሳብና ስሜት በቻት ሩም አማካኝነት መግለጽ እንደምትችል ይሰማህ ይሆናል። በዚያም ሆነ በዚህ አንዱን ወይም ሌላውን ወገን ታታልላለህ። በኢንተርኔት ያልሆንከውን ሆነህ ስትቀርብ በቻት ሩም የምታነጋግራቸውን ሰዎች እያታለልክ ነው። በተቃራኒው ደግሞ ለወላጆችህና ለጓደኞችህ ትክክለኛ ስሜትህን እንዲሁም ሐሳብህን ካልገለጽክ እያታለልካቸው ነው።
ቻት ሩም በአንጻራዊ ሁኔታ ሲታይ አዲስ ግኝት ቢሆንም መዋሸትና ማታለል ሰዎች ከተፈጠሩበት ጊዜ ጀምሮ የነበረ ዝንባሌ ነው። አንዳንድ የቻት ሩም ተጠቃሚዎች የሚጠቀሙባቸውን ዘዴዎች የፈጠረው፣ መጽሐፍ ቅዱስ የመጀመሪያው ሐሰተኛ እንደሆነ የሚናገርለት ሰይጣን ዲያብሎስ ነው። ሰይጣን የመጀመሪያውን ሐሰት ከመናገሩ በፊት እውነተኛ ማንነቱን ደብቆ ነበር። (ዘፍጥረት 3:1-5፤ ራእይ 12:9, 10) የንጉሥ ዳዊትን ምሳሌ በመከተል በሐሰተኞች ከመታለል መዳን ትችላለህ። ዳዊት “ከማይረቡ ጋር አልተቀመጥሁም፤ ከግብዞችም ጋር አልተባበርሁም” በማለት ጽፏል።—መዝሙር 26:4
ቀደም ሲል እንደተጠቀሰው አንዳንድ ጊዜ ቻት ሩም ለጠቃሚ ዓላማ ያገለግላል። ቢሆንም ይሖዋን ማስደሰት የሚፈልጉ ወጣቶች ይህንን ዘመናዊ የመገናኛ ዘዴ በሚጠቀሙበት ጊዜ ከፍተኛ ጥንቃቄ ማድረግ ይገባቸዋል። የቤት ሥራ ለመሳሰሉ ጉዳዮች ቻት ሩም መጠቀም የምትፈልግ ከሆነ ወላጆችህ ወይም ብስለት ያለው ሌላ አዋቂ ሰው በውይይትህ ወቅት አብረውህ እንዲሆኑ ጠይቅ። ወደፊት በሚወጣ ርዕስ ላይ ደግሞ ቻት ሩም በምትጠቀምበት ጊዜ ልትጠነቀቅባቸው የሚገቡ ሌሎች ሁለት ምክንያቶች ይብራራሉ። እንዲሁም ጥንቃቄ ብታደርግም እንኳን ሊነሱ የሚችሉትን አንዳንድ ችግሮች እንዴት መቋቋም እንደምትችል እንመለከታለን።
[የግርጌ ማስታወሻዎች]
^ አን.3 አንዳንዶቹ ስሞች ተቀይረዋል።
^ አን.15 ወጣቶች የሚጠይቋቸው ጥያቄዎችና ተግባራዊ መሆን የሚችሉ መልሶች የተባለው መጽሐፍ ከጋብቻ በፊት የፆታ ግንኙነት ስለመፈጸም፣ ስለ ማስተርቤሽንና ስለሌሎች ተመሳሳይ ርዕሰ ጉዳዮች በመጽሐፍ ቅዱስ ላይ የተመሠረቱ ግሩም ምክሮችን ይዟል።
^ አን.17 በንድፈ ሐሳብ ደረጃ በአዋቂዎች ቻት ሩም መጠቀም የሚችሉት ከተወሰነ የዕድሜ ክልል በላይ ያሉ ሰዎች ናቸው። ይህም የሆነበት ምክንያት በአብዛኛው የሚነጋገሩባቸው ርዕሰ ጉዳዮችና የሚላላኳቸው ፎቶዎች ወሲብ ነክ በመሆናቸው ነው። ይሁን እንጂ የዘጠኝ ዓመት ልጆች ሳይቀሩ በአዋቂዎች ቻት ሩም ውስጥ ለመግባት ሲሉ ዕድሜያቸውን እንደሚደብቁ ጥናቶች ያሳያሉ።
^ አን.18 በቻት ሩም የምትነጋገረው ከማን ጋር እንደሆነ ለይተህ ማወቅ ስለማትችል ተቃራኒ ፆታ መስሎ የቀረበህ ሰው ምናልባት ከአንተ ጋር ተመሳሳይ ፆታ ሊኖረው ይችላል።
^ አን.20 ኤ ፓረንትስ ጋይድ ቱ ኢንተርኔት ሴፍቲ የተባለ ጽሑፍ የኢንተርኔት ተጠቃሚዎች በቻት ሩም ለሚያናግሯቸው ሰዎች ስማቸውን፣ አድራሻቸውን ወይም የስልክ ቁጥራቸውን በፍጹም መስጠት እንደሌለባቸው ይመክራል!
[በገጽ 18, 19 ላይ የሚገኝ ሥዕል]
በኢንተርኔት የሚደረግ ውይይት አደገኛ ሊሆን ይችላል