በክርስቶስ ስም ደም ማፍሰስ
በክርስቶስ ስም ደም ማፍሰስ
ሜክሲኮ የሚገኘው የንቁ! ዘጋቢ እንደጻፈው
“በቅዳሴ ወቅት፣ ቄሶች ከመስበኪያው ሰገነት ላይ ሆነው ‘የቅድስት እናት ቤተ ክርስቲያን ልጆች ውጊያውን ተቀላቀሉ! መንግሥት ቤተ ክርስቲያንን ለመቆጣጠር እየጣረ ነው!’ በማለት ይጮኻሉ።”—ፔድሮ ሮሳልስ ባርጋስ፣ የዓይን ምሥክር
ሃይማኖተኛ ሰዎች እምነታቸውን ላለማስደፈር መሣሪያ የሚያነሱት ለምንድን ነው? ሰዎች ሃይማኖታቸውን ከጥቃት ለመጠበቅ ዓመጽ ውስጥ መግባታቸው ምን ሊያስከትል ይችላል? ተቃውሞ ካስነሱ በኋላ ክሪስቴሮ ማለትም የክርስቶስ ወታደር የሚል ስም በተሰጣቸው የሜክሲኮ ዓማጺያን ላይ የደረሰው ሁኔታ ለእነዚህ ጥያቄዎች መልስ እንድናገኝ ይረዳናል።
ኢንሳይክሎፒዲያ ኢስፓኒካ “ክሪስቴሮ በ1926 ሃይማኖታዊ ማዕከሎችንና ሕንጻዎችን እንደ መዝጋት ያሉ አንዳንድ እርምጃዎችን በወሰዱት በፕሬዚዳንት ፕሉታርኮ ኤሊያስ ካሊየስ ላይ ላመጹ ሜክሲካውያን ካቶሊኮች የተሰጠ ስም ነው” ብሏል። በመጀመሪያ ለዓማጺያኑ ክሪስቴሮ የሚለውን ስም ያወጣላቸው መንግሥት ነው፤ ምክንያቱም “ንጉሡ ክርስቶስ ለዘላለም ይኑር!” የሚል መፈክር ያሰሙ ነበር። ይሁን እንጂ የግጭቱ መንስኤ ከዚህ ያለፈ ነገር ነበረው።
የግጭቱ መንስኤ
መጀመሪያ በ1850ዎቹ ዓመታት የወጣው የተሐድሶ ሕግ ከጊዜ በኋላ በ1917 ጸደቀ። ከሕጉ ዓላማዎች ውስጥ “የቤተ ክርስቲያንን የማይንቀሳቀስ ንብረት መውረስ” የሚለው ይገኝበታል። (ኢስቶርያ ዴ ሜሂኮ) መንግሥት ይህን ሕግ ያወጣው የካቶሊክ ቤተ ክርስቲያን የምታከማቸውን ሀብትና መሬት ለመገደብ ነበር። ሕጎቹ ገና ከመጽደቃቸው የቀሳውስቱ አካል ጠንካራ ተቃውሞ ማስነሳት ጀመረ። መንግሥትም የተወሰኑ ቄሶችን በቁጥጥር ሥር በማዋል የአጸፋ እርምጃ ወሰደ።
የሜክሲኮ አብዮት (1910-1920) አንዱ ዓላማ ለድሃው ኅብረተሰብ መሬት ማከፋፈል ነበር። ስለዚህ አዲሱ ሕግ ታልሞ የወጣው ሰፋፊ የመሬት ይዞታ ካላቸው የመሬት ከበርቴዎች ላይ መሬት እየወረሱ ለድሃው ማከፋፈል በሚል ዓላማ የነበረ ሲሆን ይህም አሠራር አግራሪያን ሪፎርም ይባላል። በጥቅሉ ሲታይ ቄሶች ይህን ሁኔታ ለማደናቀፍ ፈልገው ነበር። ምክንያቱም አዲሱ ሕግ ሰፋፊ ርስት የያዙትንና በሌሎች ዘንድ ከፍተኛ ተደማጭነት የነበራቸውን ቄሶች ይነካ ነበር። ቤተ ክርስቲያን መሬት የማከፋፈሉን ሐሳብ እንደማትቃወም ብትናገርም እርሷ የነደፈችው ዕቅድ መንግሥት ካቀደው የሚለይ ነበር።
ሆኖም አንዳንድ ሰዎች ቤተ ክርስቲያን ጥብቅና የቆመችው ሀብታም ቀሳውስትን ጨምሮ ሰፋፊ መሬት ለነበራቸው ባለርስቶች ብቻ እንደሆነ ተሰምቷቸው ነበር። በሌላ በኩል ደግሞ መሬት ለድሃው መከፋፈል አለበት የሚለውን ሐሳብ የሚደግፉ አግራሪያን በመባል የሚታወቁ አንዳንድ ቄሶች ነበሩ። ቤተ ክርስቲያን ውስጥ የተፈጠረው ግጭት ያስከተለው ነገር ቢኖር በቤተ ክርስቲያንና በመንግሥት መካከል የነበረውን ልዩነት ማስፋት ብቻ ነው።
የሜክሲኮ ሪፑብሊክ ፕሬዚዳንት ሆነው የተሾሙት ፕሉታርኮ ኤሊያስ ካሊየስ በ1925 መጀመሪያዎቹ ላይ ከቤተ ክርስቲያን ጋር ግንኙነት ያላቸውን የአዲሱን ሕገ መንግሥት
አንቀጾች በጥብቅ ማስፈጸም ጀመሩ። ለምሳሌ ያህል፣ ከውጪ አገር የመጡ ብዙ የካቶሊክ ቄሶችን ከሜክሲኮ አባረሩ። በተጨማሪም የሜክሲኮው ሊቀ ጳጳስ ፀረ-ቀሳውስት የሆኑ አንዳንድ የሕገ መንግሥቱ አንቀጾች እንዲወገዱ ቀሳውስት ትግል እንደሚያደርጉ በማወጃቸው ወደ ወኅኒ እንዲወርዱ አደረጉ። የቤተ ክርስቲያን ንብረት የሆኑ አንዳንድ ሕንጻዎችም ተወረሱ። ብዙ ሰዎች የዚህ ሁሉ እርምጃ ዓላማ ሜክሲካውያን የሚመጸውቱት በጣም በርካታ ገንዘብ ወደ ሮም እንዳይላክ ለማገድ እንደሆነ ተሰምቷቸው ነበር።በሐምሌ 1926 የሜክሲኮ ጳጳሳት በቤተ ክርስቲያናት ውስጥ የአምልኮ ሥርዓት እንዳይከናወን ትእዛዝ አስተላለፉ። መንግሥት ደግሞ ይህን እርምጃ ሕዝቡ በመንግሥት ላይ እንዲያምጽ ተብሎ የተጠነሰሰ ፖለቲካዊ ሴራ እንደሆነ ቆጥሮታል። ያም ሆነ ይህ የአምልኮ ሥርዓት እንዳይፈጸም እገዳ መጣሉ አስከፊ ለሆነው ለክሪስቴሮ ዓመጽ መቀጣጠል ምክንያት ሆኗል።
ጦርነቱ ፈነዳ
በሺህ የሚቆጠሩ ካቶሊኮች በቀሳውስቶቻቸው ግፊት ሃይማኖታቸውን ላለማስደፈር መዋጋት ጀመሩ። ወደ ውጊያም የወጡት የጓዴሎፕዋን ድንግል ምስል እንደ ሰንደቅ ዓላማ አንግበው ነበር። አንዳንድ ክሪስቴሮዎች ሥልጣን ያላቸው ቀሳውስት ለቤተ ክርስቲያኒቱ ደኅንነት ይቆማሉ ብለው አስበው ነበር፤ ሆኖም አብዛኞቹ ጳጳሳትና ቀሳውስት መንግሥት እርምጃ እንዳይወስድባቸው በመፍራት በግጭቱ ላይ ከመሳተፍ ወደኋላ ብለዋል። ከዚህ ይልቅ ተራው ኅብረተሰብ አሰቃቂውን ሃይማኖታዊ ዓመጽ ሲቀላቀል ብዙዎቹ ቀሳውስት ከትግሉ ራሳቸውን አግልለው በሀብታም ቤተሰቦች ቤት ውስጥ ተሸሸጉ።
ይሁን እንጂ አንዳንድ ቀሳውስት ከሁለቱ ጎራዎች ውስጥ በአንዱ ላይ ተሰልፈው ነበር። ዘ ክሪስትያዳ (የክሪስቴሮዎች ጦርነት፣ ጥራዝ 1) የተባለው መጽሐፍ እንደተናገረው 100 የሚያህሉ የካቶሊክ ቄሶች የክሪስቴሮን ንቅናቄ ሲቃወሙ 40 የሚያህሉት ደግሞ የትጥቅ ትግሉን ደግፈው ነበር። በተጨማሪም ሌሎች አምስት ቄሶች በውጊያው ላይ ቀጥተኛ ተሳትፎ ነበራቸው።
የተቀሰቀሰው ዓመጽ አሳዛኝ ውጤት አስከትሏል። በብዙ ቦታዎች ላይ ከባድ ድህነት ተከስቶ ነበር። ከዚህም በላይ ክሪስቴሮዎች ብዛት ያላቸውን ወጣት ወንዶች እያፈሱ ወደ ውጊያው ይወስዱ እንደነበር ዘገባዎች ያሳያሉ። ክሪስቴሮዎችም ሆኑ የመንግሥት ወታደሮች በየጊዜው ወደ አንዳንድ ቤተሰቦች እየሄዱ ምግብ እንዲሰጧቸው ያስገድዷቸው እንደነበርም ሪፖርቶች ይጠቁማሉ። በተጨማሪም ሁለቱም ወገኖች አስገድደው ይደፍሩና ሰዎችን ይገድሉ እንደነበር የሚናገሩ ሪፖርቶች አሉ።
ክሪስቴሮዎችም ሆኑ የመንግሥት ወታደሮች በግጭቱ ውስጥ ምንም ተሳትፎ የሌላቸውን በርካታ ሰላማዊ ሰዎች መገደል ጨምሮ ለተፈጸመው አሰቃቂ ድርጊት ተጠያቂ ናቸው። ከጊዜ በኋላ ከገለልተኛ ምንጭ የተገኙ አኃዞች እንደሚያሳዩት ሦስት ዓመት በፈጀው የትጥቅ ትግል ቢያንስ 70,000 ሰዎች ተገድለዋል።
ውጊያው ቆመ
የካቶሊክ ቤተ ክርስቲያን እና መንግሥት በ1929 ስምምነት ካደረጉ በኋላ በመካከላቸው የነበረው ጥላቻ የበረደ ሲሆን ውጊያውም ነሐሴ ወር ላይ ቆመ። ይሁን እንጂ የክሪስቴሮ ተዋጊዎች በስምምነቱ ላይ ያልተካተቱ ከመሆኑም በላይ ብዙዎች በአምላክ ተሹማለች ብለው የሚያስቧት ቤተ ክርስቲያን ጠላቷ ለሆነው ለመንግሥት መንበርከኳ ግራ አጋብቷቸዋል። ክሪስቴሮዎች ሁኔታው ቅር ቢያሰኛቸውም የቤተ ክህነትን መመሪያ ተቀብለው እጅ በመስጠት ወደየቤታቸው መመለስ ጀመሩ። መንግሥት ብዙ ነገሮችን በትዕግሥት ለማለፍ ቃል የገባ ሲሆን ቅዳሴም እንደገና እንዲጀመር ፈቅዷል። ይሁን እንጂ በሃይማኖቶች ላይ ገደብ የሚያበጁት ሕግጋት አልተቀየሩም ነበር።
ይህን ዓመጽ የካቶሊክ እምነት ተከታይ የሆኑ አንዳንድ ሰዎች ቤተ ክርስቲያን የተሐድሶው ሕግ ከመውጣቱ በፊት የነበራትን ኃይል መልሳ እንድትጨብጥ ለማስቻል ባደረጉት ጥረት እንደተቀሰቀሰ የሚያስቡ ወገኖች አሉ። እንዲህ ያለ ጦርነት ቢነሳም ሕጉ ሃይማኖታዊ ድርጅቶችን የሚመለከት ሕግ እስከጸደቀበት እስከ 1992 ድረስ ተግባራዊ ሲሆን ቆይቷል። አሁንም ድረስ ቢሆን የሃይማኖት ድርጅቶችን የመጠራጠር ስሜት ይታያል። ቄሶችና ሃይማኖታዊ አገልጋዮች በፖለቲካ እንዳይካፈሉ አሁንም እንደተከለከሉ ናቸው። ሃይማኖታዊ ድርጅቶች ይዞታ እንዲኖራቸው የሚፈቀድ ቢሆንም እንኳ ከ1992 በፊት የተወረሱት የቤተ ክርስቲያን ንብረቶች የመንግሥት እንደሆኑ ቀጥለዋል። ያም ሆኖ ሕጉ በሜክሲኮ ያሉ ብዙ ቄሶች በፖለቲካ ጉዳዮች እንዳይሳተፉ አላገዳቸውም።
የተገኘው ውጤት ምንድን ነው?
ክሪስቴሮዎች እምነታቸውን ላለማስደፈር ውጊያ መክፈታቸው ዘላቂ ጥቅም አምጥቶላቸዋል? ከብጥብጡ የተረፈችው ማሪያ ባላዴስ “ያ ሁሉ እልቂት በከንቱ እንደሆነ ይሰማኛል። ምንም እርባና አልነበረውም” ብላለች። በመግቢያው ላይ የተጠቀሰው ፔድሮ ሮሳልስ ባርጋስ ስለ ጦርነቱ አስከፊ ውጤት ሲናገር እንዲህ ብሏል:- “ሰዎች የእምነት ባልንጀሮቻቸውን ሳይቀር ይገድሉ ነበር። የሙት ልጅ ለመሆን የበቃሁትም በዚሁ ምክንያት ነው፤ አባቴን ገድለውብኛል።”
የክሪስቴሮ ዓመጽ ያስከተለው አሳዛኝ ውጤት ከዚያ በኋላ በሰሜናዊው አየርላንድና በቀድሞዋ ዩጎዝላቪያ እንደተነሱት ያሉ ሃይማኖታዊ ግጭቶች እንዳይቀሰቀሱ ትምህርት ሊሆን አልቻለም። እንዲህ ዓይነቱ አሳዛኝ ሁኔታ እንዳይከሰት ማድረግ የሚቻለው ክርስቶስ ያቋቋመውን ንጹሕ ሃይማኖት በሥራ ላይ በማዋል ብቻ ነው። ኢየሱስ ፖለቲካ ውስጥ እንዳይገቡ ማለትም ‘የዓለም ክፍል እንዳይሆኑ’ ደቀ መዛሙርቱን አዟቸዋል። (ዮሐንስ 17:16፤ 18:36) ሐዋርያው ጴጥሮስ ጌታውን በኃይል ለማስጣል በሞከረ ጊዜ ኢየሱስ “በል ሰይፍህን ወደ ሰገባው መልስ፤ ሰይፍን የሚመዝዙ ሁሉ በሰይፍ ይጠፋሉ” ብሎታል።—ማቴዎስ 26:52
ክርስቲያኖች ሲጨቆኑ ምን ያደርጋሉ?
ይህ ማለት ታዲያ እውነተኛ ክርስቲያኖች የአምልኮ ነፃነታቸው ሲነካ ምንም ማድረግ የለባቸውም ማለት ነው? እንደዚህ አይደለም። በአንደኛው መቶ ዘመን የነበሩ ክርስቲያኖች ስደት ሲደርስባቸው በወቅቱ የነበረውን ሕጋዊ መንገድ ተጠቅመው ብዙ ጊዜ መከላከያ ያቀርቡ ነበር። ጉዳያቸውን ይዘው ፍርድ ቤት ይቀርቡ ነበር። አንዳንድ ጊዜ የታሰሩ ቢሆንም እምነታቸውን አልካዱም፤ የፖለቲካ ገለልተኝነታቸውንም አላላሉም።—የሐዋርያት ሥራ 5:27-42
የጥንት ክርስቲያኖች ሃይማኖታዊ መብታቸውን ለማስጠበቅ ብለው ጦርነት ውስጥ የገቡበት ጊዜ የለም። እውነተኛ ክርስቲያኖች የእምነት ባልንጀራቸውን ይቅርና ሌላ ሃይማኖት ያለውን የማንኛውንም ሰው ሕይወት እንኳ ፈጽሞ አያጠፉም። ከዚህ ይልቅ ጌታቸው “እርስ በርሳችሁ ብትዋደዱ፣ ሰዎች ሁሉ የእኔ ደቀ መዛሙርት እንደሆናችሁ በዚህ ያውቃሉ” በማለት የሰጣቸውን ትምህርት አጥብቀው ይከተላሉ።—ዮሐንስ 13:35
[በገጽ 14 ላይ የሚገኝ ሥዕል]
በሁለት የክሪስቴሮ ተዋጊዎች የታጀበ አንድ ቄስ
[ምንጭ]
© (Inventory image number: 422036) SINAFO-Fototeca Nacional
[በገጽ 15 ላይ የሚገኝ ሥዕል]
ፕሬዚዳንት ፕሉታርኮ ኤሊያስ ካሊየስ
[ምንጭ]
© (Inventory image number: 66027) SINAFO-Fototeca Nacional
[በገጽ 15 ላይ የሚገኝ ሥዕል]
አንዳንድ የክሪስቴሮ መሪዎች
[ምንጭ]
© (Inventory image number: 451110) SINAFO-Fototeca Nacional