በድንገት ከሥራ መባረር!
በድንገት ከሥራ መባረር!
“ከሥራ ስባረር አንድ ሰው ባልዲ ሙሉ ቀዝቃዛ ውኃ የከለበሰብኝ ያህል ነበር የተሰማኝ። ለራሴ የነበረኝ አክብሮት ክፉኛ አሽቆለቆለ።”—ቶኒ፣ ጀርመን
“አንድ ትልቅ ድንጋይ ራሴ ላይ የተጫነብኝ መሰለኝ። ነጠላ እናት በመሆኔ ሁለቱን ልጆቼን ምን እንደማበላቸውና ወጪዎቼን እንዴት መሸፈን እንደምችል ግራ ገባኝ።”—ሜሪ፣ ሕንድ
“ከሥራ ስባረር በጣም ተስፋ ቆርጬ የነበረ ሲሆን ሌላ ሥራ የማግኘቱም ጉዳይ አስጨንቆኝ ነበር።”—ሃይሜ፣ ሜክሲኮ
በዓለም ዙሪያ የሚገኙ በሚሊዮን የሚቆጠሩ ሰዎች ቶኒ፣ ሜሪና ሃይሜ ያጋጠማቸው ዓይነት አስቸጋሪ ሁኔታ ይደርስባቸዋል። አሁን ወዳለንበት መቶ ዘመን ልንገባ አካባቢ በአውሮፓና በመካከለኛው እስያ ከሚገኘው አጠቃላይ የሠራተኛ ኃይል ውስጥ ወደ 10 በመቶ የሚጠጋው ማለትም 23 ሚሊዮን ገደማ የሚሆነው ሥራ አጥ ነበር። በማደግ ላይ ባሉ አንዳንድ አገሮች ከሚገኘው ሠራተኛ ኃይል ውስጥ ሩብ ያህሉ ሥራ የለውም። በዩናይትድ ስቴትስ “ባለፉት 28 ወራት ውስጥ ወደ 2.6 ሚሊዮን የሚጠጉ የሥራ መስኮች ጨርሶ ጠፍተዋል” በማለት ዘ ኒው ዮርክ ታይምስ በሐምሌ 2003 ላይ ዘግቧል።
በበርካታ አገሮች ውስጥ ሥራ ማግኘት አስቸጋሪ እንዲሆን የሚያደርጉ ብዙ መሰናክሎች ያጋጥማሉ። ለምሳሌ ያህል በየዓመቱ በርካታ የከፍተኛ ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤቶችና የኮሌጅ ምሩቃን ከሥራ ፈላጊዎች ቡድን ጋር ይቀላቀላሉ። ከዚህም በላይ አንድ ሰው ዲግሪ መያዙ ወይም ልዩ ሥልጠና ማግኘቱ በመረጠው ሙያ ሥራ ለማግኘት ዋስትና አይሆነውም። በዚህ ምክንያት ሰዎች በሥራ ዘመናቸው ለበርካታ ጊዜያት ሥራቸውን ሲቀያይሩ መመልከት የተለመደ ነው። እንዲያውም አንዳንዶቹ ከነአካቴው ሙያቸውን መቀየር ይኖርባቸዋል።
ሥራ አጥ ከሆንክ ሥራ የማግኘት አጋጣሚህን ከፍ ማድረግ የምትችለው እንዴት ነው? እንዲሁም ሥራ ካገኘህ በኋላ እንዳትፈናቀል ምን ማድረግ ትችላለህ?