“ነጭ ሽንኩርቱ ትዝ ይለናል!”
“ነጭ ሽንኩርቱ ትዝ ይለናል!”
በዶሚኒካን ሪፑብሊክ የሚገኘው የንቁ! ዘጋቢ እንደጻፈው
ከአገርህ ርቀህ ሳለህ በጣም ቢርብህ ምን ዓይነት ምግብ ለመብላት ትጓጓለህ? የአገርህ ፍራፍሬና አትክልት አሊያም ደግሞ እናትህ የምትሠራው ጣፋጭ የሆነ የሥጋ ወይም የዶሮ ወጥ ሊናፍቅህ ይችላል። ይሁንና ነጭ ሽንኩርት ያምርህ ይሆን?
ከ3,500 ዓመታት ገደማ በፊት እስራኤላውያን በሲና ምድረ በዳ ይጓዙ በነበረበት ወቅት “በግብፅ ያለምንም ዋጋ የበላነው ዓሣ እንዲሁም ዱባው፣ በጢኹ፣ ኵራቱ፣ ነጭ ሽንኩርቱ ትዝ ይለናል” ሲሉ ተናግረዋል። (ዘኍልቁ 11:4, 5) አዎን፣ ነጭ ሽንኩርት ናፍቋቸው ነበር። አይሁዳውያን ነጭ ሽንኩርት በጣም ይወዱ ስለነበር ራሳቸውን ነጭ ሽንኩርት በላተኞች ብለው ይጠሩ እንደነበር ይነገራል።
እስራኤላውያን ነጭ ሽንኩርት እንዲህ ሊወዱ የቻሉት እንዴት ነው? በግብጽ በኖሩባቸው 215 ዓመታት ነጭ ሽንኩርት የምግባቸው አንዱ ክፍል ነበር። የአርኪኦሎጂ ማስረጃ እንደሚያመለክተው ያዕቆብና ቤተሰቡ ወደ ግብጽ ከመጓዛቸው ከረጅም ጊዜ በፊት ግብጻውያን ነጭ ሽንኩርት ያለሙ ነበር። ግሪካዊው ታሪክ ጸሐፊ ሄሮዶተስ የግብጽ ባለ ሥልጣናት ፒራሚድ የሚገነቡላቸውን ባሪያዎች ለመቀለብ ከፍተኛ መጠን ያለው ቀይ ሽንኩርት፣ ፍጁልና ነጭ ሽንኩርት ገዝተው እንደነበረ ዘግቧል። ነጭ ሽንኩርት በብዛት የሚጨመርበት ይህ ምግብ ለሠራተኞቹ ጉልበትና ብርታት ይጨምር የነበረ ይመስላል። ግብጻውያን ፈርዖን ቱታንካሜንን በቀበሩበት ጊዜ ነጭ ሽንኩርትን ጨምሮ ከፍተኛ ዋጋ ያላቸውን በርካታ ነገሮች መቃብሩ ውስጥ አስቀምጠው ነበር። እርግጥ፣ ነጭ ሽንኩርት ለሙታን ምንም የሚሰጠው ጠቀሜታ ባይኖርም ለሕያዋን ግን እጅግ ጠቃሚ ሆኖ ተገኝቷል።
ኃይለኛ መድኃኒት
ሐኪሞች ነጭ ሽንኩርትን ለሕክምና መጠቀም ከጀመሩ በርካታ ዘመናት ተቆጥረዋል። ከብዙ መቶ ዘመናት በፊት ሂፖክረቲዝ እና ዳይስኮርዲዝ የተባሉት ግሪካውያን ሐኪሞች ነጭ ሽንኩርትን ከምግብ አለመፈጨት ጋር ለተያያዙ ችግሮች፣ ለሥጋ ደዌ፣ ለካንሰር፣ ለቁስል፣ ለኢንፌክሽንና ለልብ ሕመም ያዙ ነበር። በ19ኛው መቶ ዘመን ፈረንሳዊው ኬሚስት ሉዊ ፓስተር በነጭ ሽንኩርት ላይ ጥናት በማካሄድ ጀርሞችንና ባክቴሪያዎችን የመግደል ባሕርይ እንዳለው ገለጸ። በ20ኛው መቶ ዘመን አፍሪካ ውስጥ አልበርት ሽዋይትሰር የተባለ ዝነኛ ሚስዮናዊና ሐኪም በአሜባ ምክንያት የሚመጣን ተቅማጥና ሌሎች በሽታዎችን ለማከም በነጭ ሽንኩርት ይጠቀም ነበር። የሩስያ ወታደራዊ ሐኪሞች በሁለተኛው የዓለም ጦርነት ወቅት የዘመናዊ መድኃኒቶች እጥረት ሲያጋጥማቸው የቆሰሉ ወታደሮችን ለማከም የተጠቀሙት በነጭ ሽንኩርት ነበር። በዚህም ምክንያት ነጭ ሽንኩርት የሩስያ ፔኒሲሊን ተብሎ ሊጠራ ችሏል። በቅርቡ ሳይንቲስቶች ነጭ ሽንኩርት ከደም ዝውውር ሥርዓት ጋር በተያያዘ በሚያበረክተው አስተዋጽኦ ላይ ጥናት አካሂደዋል።
በመሆኑም ነጭ ሽንኩርት በምግብነትም ሆነ በመድኃኒትነት ረገድ ያለው ጠቀሜታ እጅግ የጎላ ከመሆኑም በላይ ሽታውና ጣዕሙ በዓይነቱ እጅግ የተለየ ነው። ነጭ ሽንኩርት መጀመሪያ የተገኘው የት ነው? አንዳንድ የስነ ዕፅዋት ሊቃውንት ነጭ ሽንኩርት በመጀመሪያ የተገኘው በማዕከላዊ እስያ እንደሆነና ከዚያ ተነስቶ በመላው ዓለም እንደተሰራጨ ያምናሉ። ነጭ ሽንኩርት እጅግ ተወዳጅ የሆነበትን በምዕራባዊ ንፍቀ ክበብ የሚገኝ አንድ ውብ ሥፍራ እስቲ እንቃኝ።
በኮንስታንሳ ነጭ ሽንኩርት ማልማት
በዶሚኒካን ሪፑብሊክ የሚገኘው የኮንስታንሳ ሸለቆ የአየር ንብረቱ ወይና ደጋ ነው። በተራሮች የተከበበው ይህ ሸለቆ ለም አፈር ያለውና ዝናብ እንደ ልብ የሚያገኝ ሥፍራ ነው። ኮንስታንሳ ነጭ ሽንኩርት ለማልማት እጅግ ተስማሚ የሆነ ቦታ ነው።
በመስከረምና በጥቅምት ወራት በኮንስታንሳ የሚኖሩ ገበሬዎች የእርሻ መሬታቸውን መንጥረው በማረስ አንድ ሜትር ስፋት ባላቸው የአፈር ቁልሎች የተከፋፈሉ ጥልቀት ያላቸው ፈሮች ያወጣሉ። በእያንዳንዱ የአፈር ቁልል ላይ ደግሞ ነጭ ሽንኩርት የሚተክሉባቸውን ብዙም ጥልቀት የሌላቸው ከሦስት እስከ አራት የሚደርሱ ፈሮች ያወጣሉ። በዚህ መካከል ሌሎች ሠራተኞች የነጭ ሽንኩርት ራሶችን ይፈለፍላሉ። ከዚያም የተፈለፈለውን ነጭ ሽንኩርት ውኃ ውስጥ ለ30 ደቂቃ ከዘፈዘፉ በኋላ በአፈሩ ቁልል ላይ በሚገኙት ፈሮች ላይ ይተክሉታል። ሽንኩርቱ ተስማሚ በሆነው የዶሚኒካን የክረምት ወቅት ያድጋል።
መጋቢትና ሚያዝያ ላይ ምርቱ መሰብሰብ ይጀምራል።
ሠራተኞቹ የደረሱትን የነጭ ሽንኩርት ተክሎች እየነቀሉ ለአምስት ለስድስት ቀናት እዚያው እርሻው ላይ ይተዉአቸዋል። ከዚያም ነጭ ሽንኩርቱን በመሰብሰብ ሥሩንና አናቱን እየቆረጡ ንጹሕ የሆኑትን የነጭ ሽንኩርት ራሶች ክሪባስ ተብለው በሚጠሩ ክፍት ማጠራቀሚያዎች ውስጥ ያስቀምጧቸዋል። የሰበሰቡት ነጭ ሽንኩርት ሳይበላሽ ደርቆ እንዲቆይ ለማድረግ ሲሉ በነጭ ሽንኩርት የተሞሉትን ክሪባሶች አንድ ቀን ሙሉ ፀሐይ ላይ ያውሏቸዋል። ከዚያ በኋላ ለገበያ ይቀርባል።ጥቂት ነጭ ሽንኩርት፣ ኃይለኛ ጠረን
ጣፋጭ የሆነ ወጥ ወይም ሰላጣ ለመብላት በምትዘጋጅበት ጊዜ ምግቡ ነጭ ሽንኩርት ያለው ከሆነ አፍንጫህ ወዲያውኑ ይነግርሃል። ይሁን እንጂ የነጭ ሽንኩርት ራስ ከመላጡና ከመከተፉ በፊት ምንም ዓይነት ጠረን የማይኖረው ለምንድን ነው? ነጭ ሽንኩርት እስኪቆረጥ፣ እስኪጨፈለቅ አለዚያም እስኪደቆስ ድረስ ምንም ዓይነት ንክኪ ሳይፈጥሩ ተነጣጥለው የሚቆዩ ኃይለኛ ኬሚካሎች አሉት። ነጭ ሽንኩርት በምትከትፍበት ጊዜ አሊኔስ የተባለ ኤንዛይም አሊን ከተባለ ንጥረ ነገር ጋር ንክኪ ይፈጥራል። ወዲያውኑ ኬሚካላዊ ለውጥ ይፈጠርና የነጭ ሽንኩርትን ጠረንና ጣዕም የሚያመነጨው አሊሲን የተባለ ውሁድ ይፈጠራል።
ገና የተላጠ ነጭ ሽንኩርት በምታኝክበት ጊዜ አሊሲኑ አፍህ ውስጥ የፈነዳ ያህል ይሆናል። ወደድከውም አልወደድከው የነጭ ሽንኩርቱ ሽታ አካባቢህን ሁሉ ያውደዋል። ትንፋሽህ ላይ የሚኖረውን ጠረን ማጥፋት የምትችልበት መንገድ ይኖራል? ሽታውን ለማጥፋት ፓርስሊ (የስጎ ቅጠል) ወይም ቅርንፉድ ታኝክ ይሆናል።
ይሁንና ትንፋሽህ ላይ የሚኖረው የነጭ ሽንኩርት ሽታ በአብዛኛው የሚመጣው ከሳንባዎችህ ነው። ነጭ ሽንኩርት በምትበላበት ጊዜ የተመገብከው ምግብ የሚፈጭባቸው የሰውነትህ ክፍሎች ደምህ ውስጥ እንዲገባ ያደርጉታል፤ ከዚያም በደም አማካኝነት ወደ ሳንባዎችህ ይገባል። ወደ ውጭ በምትተነፍስበት ጊዜ ይህ ኃይለኛ ሽታ በትንፋሽህ አማካኝነት ይወጣል። ስለዚህ የአፍን ጠረን ለመለወጥ ተብለው የሚዘጋጁ ፈሳሾችም ሆኑ ፓርስሊ የነጭ ሽንኩርትን ሽታ ሊያስወግዱ አይችሉም። ለዚህ ችግር የማያዳግም መፍትሔ ሊሆን የሚችል ነገር ይኖራል? እንደ እውነቱ ከሆነ የለም። ይሁንና አብረውህ ያሉ ሰዎች ሁሉ ነጭ ሽንኩርት እንዲበሉ ካደረግክ ምናልባት ሽታውን ልብ የሚል አይኖር ይሆናል!
በብዙ አገሮች ነጭ ሽንኩርት የሌለበት ምግብ መብላት የማይታሰብ ነገር ነው። ነጭ ሽንኩርት በመጠኑ በሚበላባቸው አካባቢዎችም እንኳ ብዙ የነጭ ሽንኩርት በላተኞች ጥቅሙ ከጉዳቱ በእጅጉ እንደሚያመዝን ያምናሉ።
[በገጽ 29 ላይ የሚገኝ ሥዕል]
ከተሰበሰበ በኋላ በመድረቅ ላይ ያለ ነጭ ሽንኩርት
[በገጽ 29 ላይ የሚገኝ ሥዕል]
የኮንስታንሳ ሸለቆ
[በገጽ 29 ላይ የሚገኝ ሥዕል]
ነጭ ሽንኩርት ከመፈጨቱ በፊት የማይሸተው ለምንድን ነው?