በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

አንድ ቢሊዮን ሰዎችን ለመመገብ የሚደረግ ሙከራ

አንድ ቢሊዮን ሰዎችን ለመመገብ የሚደረግ ሙከራ

አንድ ቢሊዮን ሰዎችን ለመመገብ የሚደረግ ሙከራ

በየዕለቱ አንድ ቢሊዮን የሚያህሉ ሰዎች ረሃባቸውን ለማስታገስ ያህል እንኳ የሚበቃ ምግብ አያገኙም። የተባበሩት መንግሥታት እንደሚለው ከሆነ ግን እንዲህ ዓይነቱ አስከፊ ሁኔታ መኖር አልነበረበትም።

“ቀዳሚው እርምጃችሁ የከፋ ድህነትን ማስወገድ እንደሆነ ተናግራችሁ ነበር።” የዓለማችን ታላላቅ ሰዎች በታደሙበት መስከረም 8, 2000 በተካሄደ ዓለም አቀፍ ስብሰባ ላይ ይህን የተናገሩት የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ዋና ጸሐፊ የሆኑት ኮፊ አናን ነበሩ። በዚህ ዓለም አቀፍ ስብሰባ ላይ የተገኙ በርካታ የአገር መሪዎች በዓለም የሚታየውን ድህነት አስመልክቶ ያላቸውን አስተያየት በግልጽ ተናግረዋል። የብራዚሉ ምክትል ፕሬዚዳንት “የከፋ ድህነት ለመላው የሰው ዘር ታላቅ ውርደት ነው” ሲሉ ተናግረዋል። የእንግሊዙ ጠቅላይ ሚኒስትር ደግሞ “ያደጉት አገሮች ከአፍሪካ ጋር በተያያዘ ያስመዘገቡት መጥፎ ታሪክ ሥልጣኔያችንን ለውርደትና ለእፍረት ዳርጎታል” በማለት ከዚያም ያለፈ ነገር ሲናገሩ ተደምጠዋል።

እነዚህ ሁለት ተናጋሪዎች መንግሥታት የተራቡ ሰዎችን ለመመገብ ማድረግ የሚችሉትን ባለማድረጋቸው የተነሳ አሳፋሪ ሁኔታ ውስጥ እንደገቡ ግልጽ አድርገዋል። የስብሰባው ተሳታፊዎች በመላው ምድር ላይ የሚኖሩ ሰዎችን ሕይወት ለማሻሻል ያላቸውን ቁርጠኝነት ለማሳየት ባለ ስምንት ነጥብ የአቋም መግለጫ አስተላልፈዋል። ከነጥቦቹ መካከል የሚከተሉት ይገኙበታል:- “ከቢሊዮን የሚበልጡ ሰዎች ከሚገኙበት አሳፋሪና የሰውን ክብር ከሚነካ አስከፊ ድህነት ወንዶችን፣ ሴቶችንና ሕፃናትን ነፃ ለማውጣት አቅማችን የፈቀደውን ጥረት ሁሉ እናደርጋለን። . . . በተጨማሪም በ2015 ከአንድ ዶላር ያነሰ የዕለት ገቢ ያላቸውንና በረሃብ አለንጋ እየተገረፉ ያሉትን ሰዎች ቁጥር በግማሽ ለመቀነስ ቆርጠን ተነስተናል።”

ከመስከረም 2000 ወዲህ ይህን ታላቅ ዓላማ ለማሳካት ምን ተግባራዊ እርምጃዎች ተወስደዋል?

ከቃል ይልቅ ተግባር የጎላ ድምፅ አለው

በ2003፣ የዓለም ኢኮኖሚ ፎረም የተሰኘ ድርጅት በተባበሩት መንግሥታት ዓመታዊ ስብሰባ ላይ የጸደቁትን ዕቅዶች ለማሳካት ምን ጥረት እንደተደረገ መገምገም ጀምሮ ነበር። ጥር 15, 2004 የወጣው ይፋዊ ሪፖርት “የወጡት ግቦች ጥሩ ቢሆኑም ዓለም አስፈላጊውን እርምጃ ሳይወስድ ቀርቷል።” ረሃብን አስመልክቶ ሪፖርቱ “ችግሩ በዓለማችን ላይ የምግብ እጥረት መኖሩ አይደለም፤ ለእያንዳንዱ ሰው የሚበቃ ምግብ አለ። ችግር የሆነው ይህን እህልና የተመጣጠነ ምግብ ገንዘብ የሌላቸው ሰዎች ሊያገኙ አለመቻላቸው ነው” ሲል ገልጿል።

ዓለም አቀፉን የድህነት ችግር አስመልክቶ ሪፖርቱ እንዲህ ብሏል:- “ለታየው ቸልተኝነት ዋናውን ኃላፊነት የሚወስዱት ሃብታምም ሆኑ ድሃ መንግሥታት ናቸው። ይሁንና በሃብታም አገራት የተነደፈው ዓለም አቀፉ የኢኮኖሚ ፖሊሲ በአመዛኙ በድሆቹ ላይ ጎጂ ተጽዕኖ ያሳድራል። ሃብታም አገሮች ባዶ የተስፋ ቃል ከመስጠት ሌላ ሥርዓቱን ለማሻሻል ወይም የድሃ አገሮችን እድገት ለማፋጠን ያደረጉት እርዳታ እዚህ ግባ የሚባል አይደለም።” ፖለቲከኞቹ እንዲህ ያለ ወቀሳ ሲሰነዘርባቸው ተገቢውን እርምጃ ከመውሰድ ይልቅ ሙግት መግጠማቸውን ገፍተውበታል፤ መንግሥታትም ቢሆኑ ሁኔታዎችን የራሳቸውን ጥቅም ብቻ ለማሳካት ይጠቀሙባቸዋል። በዚህ መሐል የዓለማችን ድሆች ባዶ ሆዳቸውን ያድራሉ።

ዓለም አቀፉ የኢኮኖሚ ፎረም “ከጽኑ ፍላጎት ወደ ድርጊት መሸጋገር” በሚል ርዕስ ባዘጋጀው ጽሑፍ ላይ “ዓለም አቀፍ የንግድ ፖሊሲዎች ካልተቀየሩ፣ ረሃብን በማጥፋት ላይ ያነጣጠሩ ብሔራዊ ፖሊሲዎች ካልተቀረጹ እንዲሁም ውጤታማ የሆኑ ማኅበረሰባዊ ጥረቶች ካልታከሉበት በብዙ አካባቢዎች የሚኖሩ ሰዎች ይበልጥ አስከፊ ለሆነ ረሃብ መጋለጣቸው አይቀሬ ነው” ሲል ገልጿል። ታዲያ የተሻለ ፖሊሲ መንደፍና ይበልጥ “ውጤታማ የሆኑ ማኅበረሰባዊ ጥረቶች” እንዲደረጉ ማስተባበር ያለበት ማን ነው? የጠቅላላውን የሰው ዘር ሁኔታ እናሻሽላለን ሲሉ በ2000 ላይ በይፋ ቃል የገቡት መንግሥታት መሆናቸው የሚያሻማ አይደለም።

የገቡትን ቃል ለመጀመሪያ ጊዜ ሳያከብሩ መቅረት ቃል የተገባላቸውን ያሳዝን ይሆናል፤ በተደጋጋሚ ጊዜ ቃል እየገቡ ሳይፈጽሙ መቅረት ግን ተዓማኒነትን ያሳጣል። የዓለም መንግሥታትም ድሆችን ለመንከባከብ የገቡትን ቃል ሳይፈጽሙ በመቅረታቸው አመኔታን አጥተዋል። በካሪቢያን በምትገኝ ድሃ አገር ውስጥ የምትኖር አንዲት የአምስት ልጆች እናት ቤተሰቧን የምትመግበው በቀን አንድ ጊዜ ብቻ ነው። ይህቺ እናት “የሚያሳስበኝ የምንበላውን የማግኘታችን ጉዳይ ነው፤ ማንም ሥልጣን ላይ ቢቀመጥ ግድ አይሰጠኝም፤ ምክንያቱም ሥልጣን ላይ ከወጡት ውስጥ አንዳቸውም ቢሆን የፈየዱልን ነገር የለም” ስትል ተናግራለች።

የመጽሐፍ ቅዱስ ጸሐፊ የሆነው ኤርምያስ “እግዚአብሔር ሆይ፤ የሰው ሕይወት በራሱ እጅ እንዳልሆነች፣ አካሄዱንም በራሱ አቃንቶ ሊመራ እንደማይችል ዐውቃለሁ” ሲል ተናግሯል። (ኤርምያስ 10:23) ሰብዓዊ መንግሥታት የድሆችን ችግር ማስወገድ አለመቻላቸው የዚህን የመጽሐፍ ቅዱስ አባባል እውነተኝነት ያረጋግጣል።

ሆኖም የሰዎችን ችግር ለማስወገድ ኃይሉም ሆነ ፍላጎቱ ያለው አንድ ገዥ አለ። መጽሐፍ ቅዱስ የዚህን ገዥ ማንነት ይናገራል። ይህ ገዥ ሥልጣን ሲረከብ ማንም ሰው ዳግመኛ አይራብም።

ተስፋ ሰጪ ሁኔታ

“የሁሉ ዐይን አንተን በተስፋ ይጠብቃል፤ አንተም ምግባቸውን በወቅቱ ትሰጣቸዋለህ።” (መዝሙር 145:15) የሰው ልጆች የሚያስፈልጋቸውን ምግብ ለመስጠቱ ጉዳይ ትኩረት እንደሚሰጥ የተነገረለት ማን ነው? ፈጣሪያችን የሆነው ይሖዋ አምላክ ነው። ምንም እንኳ የሰው ልጆች በድርቅና በሌሎች ችግሮች ሳቢያ ለብዙ ሺህ ዓመታት የተሰቃዩ ቢሆንም ይሖዋ ለሰዎች ማሰቡን አላቆመም። ይሖዋ ሰብዓዊ መንግሥታት ያጋጠማቸውን ውድቀት ተመልክቷል፣ በቅርቡም እነዚህን መንግሥታት በራሱ አገዛዝ እንደሚተካቸው አስተማማኝ የሆነው ቃሉ መጽሐፍ ቅዱስ ይገልጻል።

ይሖዋ “እኔ ግን በተቀደሰው ተራራዬ፣ በጽዮን ላይ የራሴን ንጉሥ ሾምሁ” ብሏል። (መዝሙር 2:6) የአጽናፈ ዓለሙ የመጨረሻ ባለ ሥልጣን እንዲህ ብሎ ማወጁ ተስፋ ለማድረግ ምክንያት ይሆነናል። ሰብዓዊ ባለ ሥልጣናት ተገዢዎቻቸውን መርዳት ባይችሉም ንጉሥ እንዲሆን በአምላክ የተሾመው ኢየሱስ ክርስቶስ ግን በምድር ላይ የሚኖሩ ችግረኞች አይተው የማያውቁትን ጥቅሞች እንዲያገኙ ያደርጋል።

በዚህ ንጉሥ አማካኝነት ይሖዋ የተራቡትን ሁሉ ይመግባል። ኢሳይያስ 25:6 አምላክ “ለሕዝብ ሁሉ ታላቅ የምግብ ግብዣ” እንዳዘጋጀ ይናገራል። በክርስቶስ በሚመራው በአምላክ መንግሥት አገዛዝ ሥር በየትኛውም አካባቢ የሚኖሩ ሰዎች በተመጣጠነ ምግብ እጥረት በፍጹም አይጠቁም። ይሖዋን አስመልክቶ መጽሐፍ ቅዱስ “አንተ እጅህን ትዘረጋለህ፤ የሕያዋን ፍጥረታትንም ሁሉ ፍላጎት ታረካለህ” ሲል ይናገራል።—መዝሙር 145:16

[በገጽ 13 ላይ የሚገኝ የተቀነጨበ ሐሳብ]

“ያደጉት አገሮች ከአፍሪካ ጋር በተያያዘ ያስመዘገቡት መጥፎ ታሪክ ሥልጣኔያችንን ለውርደትና ለእፍረት ዳርጎታል።”—የእንግሊዙ ጠቅላይ ሚኒስትር፣ ቶኒ ብሌየር

[በገጽ 12 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

ኢትዮጵያ:- በዚህች አገር 13 ሚሊዮን የሚያህሉ ሰዎች ሕልውና የተመካው በእርዳታ እህል ላይ ሲሆን ከላይ የሚታየው ልጅ ከእነዚህ ውስጥ አንዱ ነው

[በገጽ 12 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

ሕንድ:- እነዚህ ተማሪዎች ምግብ የሚታደላቸው በትምህርት ቤት ውስጥ ነው

[በገጽ 12 ላይ የሚገኙ የሥዕል ምንጮች]

ከላይ:- © Sven Torfinn/Panos Pictures; ከታች:- © Sean Sprague/Panos Pictures