በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

ከሥራ ላለመፈናቀል ምን ማድረግ ትችላለህ?

ከሥራ ላለመፈናቀል ምን ማድረግ ትችላለህ?

ከሥራ ላለመፈናቀል ምን ማድረግ ትችላለህ?

“በሙያው ሥልጡን የሆነውን ሰው አይተሃልን? በነገሥታት ዘንድ ባለሟል ይሆናል።”—ምሳሌ 22:29

ከላይ ያለው ጥቅስ እንደሚያሳየው በሙያቸው ሥልጡን የሆኑ ሠራተኞች ብዙውን ጊዜ ከፍ ያለ ግምት ይሰጣቸዋል። አሠሪዎች ከሠራተኞቻቸው ችሎታዎችና ባሕርያት መካከል የሚማርኳቸው የትኞቹ ናቸው? ሰባት መቶ ተቀጣሪዎች ያሉት የአንድ ድርጅት የሠራተኞች ጉዳይ ኃላፊ የሆኑት ጆርጅ “ጥሩ የሐሳብ ግንኙነት የማድረግ ችሎታ ላለውና ከሌሎች ጋር ተስማምቶ ለሚሠራ ሠራተኛ ትልቅ ግምት እንሰጣለን” በማለት ለንቁ! ዘጋቢ ተናግረዋል። መጽሐፍ ቅዱስ ከሥራ የመፈናቀል አጋጣሚህ እንዲቀንስ የሚረዱህን እነዚህን ችሎታዎች ለማዳበር የሚያስችሉ ተግባራዊ ምክሮች ይዟል። እስቲ ጥቂት ምሳሌዎችን እንመልከት።

ጥሩ የሐሳብ ግንኙነት አድርግ

የመጽሐፍ ቅዱስ ጸሐፊ የሆነው ያዕቆብ የሐሳብ ግንኙነት በማድረግ ረገድ የተዋጣለት ሰው ተግባሩን የሚጀምረው ቃላት ከመሰንዘሩ በፊት እንደሆነ ተናግሯል። አንድ ሰው “ለመስማት የፈጠነ፣ ለመናገር የዘገየ” መሆን እንዳለበት ጽፏል። (ያዕቆብ 1:19) ይህ ምክር ምን ጥቅም አለው? ሰሎሞን “ከማዳመጡ አስቀድሞ የሚመልስ፣ ቂልነትና ዕፍረት ይሆንበታል” ብሏል። (ምሳሌ 18:13) አዎን፣ አሠሪህንና የሥራ ባልደረቦችህን በቅጡ ማዳመጥ አለመግባባት እንዳይፈጠር ይረዳል፤ እንዲሁም አጉል ስህተት ከመፈጸም ይጠብቅሃል።

የምትናገርበት መንገድም እንዲሁ ለውጥ ያመጣል። ሐሳብህን ግልጽ አድርገህና በቂ ድምጽ አውጥተህ የምትናገር ከሆነ የሚያዳምጥህ ሰው ይበልጥ ሊረዳህ ይችላል፤ ይህም የተናገርከውን ጉዳይ ከቁም ነገር እንዲቆጥረው ያደርገዋል። ባለፈው ርዕስ ላይ የተጠቀሱት ብራየን የተባሉት የቅጥር አማካሪ “ሙያዊ ብቃት ጎድሏቸው ሳይሆን ሐሳባቸውን በሚገባ የመግለጽ ችሎታ ስለሚያንሳቸው ምን ያህል ሰዎች ሥራቸውን እንደሚያጡ ብታውቁ ትገረማላችሁ” በማለት አስተያየታቸውን ሰጥተዋል።

ከሌሎች ጋር ተግባብተህ ሥራ

ከሥራ ባልደረቦችህ ጋር ከምታሳልፈው ጊዜ አንጻር እነርሱን በሚገባ እንደምታውቃቸው ምንም ጥርጥር የለውም። በመሆኑም የሚፈጽሙትን ስህተትና ያለባቸውን ጉድለት አንስተህ ለማማት ትፈተን ይሆናል። ይሁንና መጽሐፍ ቅዱስ “በጸጥታ ኑሩ፤ በራሳችሁ ጒዳይ ላይ ብቻ አተኵሩ” የሚል ምክር ይሰጣል። (1 ተሰሎንቄ 4:11) እንዲህ ካደረግክ “በሰው ነገር ጣልቃ ገቢ” ነው የሚል ስም ከማትረፍ ትድናለህ። (1 ጴጥሮስ 4:15) ከሁሉም በላይ ጊዜ ከማባከንና ከሥራ ባልደረቦችህ ጋር አላስፈላጊ ግጭት ከመፍጠር ትጠበቃለህ።

የሆነ ሥራ እንድትሠራ ከተጠየቅህ ኢየሱስ “አንድ ሰው [“አንድ ባለ ሥልጣን፣” NW] አንድ ኪሎ ሜትር ተኩል የሚያህል ርቀት እንድትሄድ ቢያስገድድህ ዕጥፉን መንገድ አብረኸው ሂድ” በማለት የሰጠውን ምክር አስታውስ። (ማቴዎስ 5:41) ኢየሱስ እየተናገረ የነበረው ስለ መንግሥት ባለ ሥልጣን ቢሆንም መሠረታዊ ሥርዓቱ በሥራ ቦታም የሚሠራ ነው። ዕጥፉን መንገድ የሚሄድ ነው ወይም በሌላ አነጋገር ታታሪ ሠራተኛ ነው የሚል ስም ካተረፍክ ከሥራ የመፈናቀል አጋጣሚህ በጣም ሊቀንስ ይችላል። በእርግጥ አሠሪህ እንድታደርግ ሊጠይቅህ የሚችለው እስከተወሰነ ደረጃ ድረስ ብቻ ነው። ኢየሱስ አንድ ሰው “የቄሣርን ለቄሣር፣ የእግዚአብሔርንም ለእግዚአብሔር” መስጠት እንዳለበት ተናግሯል። (ማቴዎስ 22:21) እዚህ ላይ ኢየሱስ ባለ ሥልጣናት ለአምላክ አምልኮ እንደማቅረብ ላሉ ይበልጥ አስፈላጊ የሆኑ ጉዳዮች እንቅፋት እንዲሆኑ ሊፈቀድላቸው እንደማይገባ መመሪያ ሰጥቷል።

ሐቀኛ ሁን

ከ1,400 በሚበልጡ ድርጅቶች ላይ የተደረገ አንድ ጥናት እንደሚያሳየው አብዛኞቹ አሠሪዎች “ሐቀኛና ታማኝ የሆኑ የሥራ አመልካቾችን ከፍ አድርገው ይመለከታሉ።” ታማኝ መሆን ማለት የአሠሪህን ገንዘብ ወይም ዕቃ ከመስረቅ መቆጠብ ማለት ብቻ እንዳልሆነ እሙን ነው። ይህ ጊዜን አለመስረቅንም ይጨምራል። አንድ የሥራና ሠራተኛ አገናኝ ድርጅት ባካሄደው ጥናት አንድ ሠራተኛ በየሳምንቱ በአማካይ 4 ሰዓት ከ15 ደቂቃ የሚያህል ጊዜ እንደሚሰርቅ አረጋግጧል። እነዚህ ሰዎች ጊዜ የሚሰርቁት ልማደኛ አርፋጅ በመሆን፣ ከመውጫ ሰዓታቸው አስቀድመው በመውጣት፣ ከሌሎች ሠራተኞች ጋር በሥራ ሰዓታቸው ማኅበራዊ ጉዳዮችን በማከናወንና በመሳሰሉት መንገዶች ነው።

መጽሐፍ ቅዱስ “ይሰርቅ የነበረ ከእንግዲህ አይስረቅ፤ ነገር ግን ለተቸገሩት የሚያካፍለው ነገር እንዲኖረው በገዛ እጆቹ በጎ የሆነውን እየሠራ ለማግኘት ይድከም” በማለት ይመክራል። (ኤፌሶን 4:28) ከዚህም በላይ የአምላክ ቃል ክርስቲያኖች፣ ባለ ሥልጣናት በማያዩአቸው ጊዜም እንኳን ጠንካራ ሠራተኞች እንዲሆኑ ያበረታታል። ሐዋርያው ጳውሎስ “ሰውን ለማስደሰትና ለታይታ ብላችሁ ሳይሆን በቅን ልብ ጌታን በመፍራት ለምድራዊ ጌቶቻችሁ በሁሉ ነገር ታዘዙ” ብሎ ጽፏል። (ቈላስይስ 3:22) ተቆጣጣሪ በማያየው ጊዜም ጭምር ተግቶ ይሠራል የሚል ስም ካተረፍክ እምነት የሚጣልብህ ሠራተኛ መሆን ትችላለህ።

ምክንያታዊ ሁን

መጽሐፍ ቅዱስ ጊዜያችን አስጨናቂ እንደሚሆን በትክክል ተንብዮአል። (2 ጢሞቴዎስ 3:1) የፖለቲካው እንዲሁም የማኅበራዊው ኑሮ አለመረጋጋትና ነውጥ የኢኮኖሚው ሁኔታ አስተማማኝ እንዳይሆን እንደሚያደርግ የታወቀ ነው። (ማቴዎስ 24:3-8) በመሆኑም ከላይ የተጠቀሱትን ምክሮች በሥራ ላይ ብታውልም እንኳን ምናልባት ከሥራ ልትፈናቀል ትችላለህ።

የሆነ ሆኖ የመጽሐፍ ቅዱስን መመሪያዎች በሥራ ላይ ማዋል ሥራ ከማጣት ጋር በተያያዘ የሚከሰተውን ጭንቀት ለመቀነስ ይረዳል። ኢየሱስ እንዲህ ብሎ ነበር:- “እናንተ እምነት የጐደላችሁ! እግዚአብሔር ዛሬ ታይቶ በነጋታው እሳት ውስጥ የሚጣለውን የሜዳ ሣር ይህን ያህል ካለበሰ እናንተንማ እንዴት አብልጦ አያለብሳችሁ? ስለዚህ፣ ‘ምን እንበላለን? ምን እንጠጣለን? ምንስ እንለብሳለን?’ ብላችሁ አትጨነቁ፤ . . . የሰማዩ አባታችሁም እነዚህ ሁሉ ለእናንተ እንደሚያስፈልጓችሁ ያውቃል።”—ማቴዎስ 6:30-32

በዓለም ዙሪያ እንደሚገኙት በሚሊዮን የሚቆጠሩ ሰዎች ሁሉ ቀደም ሲል የተጠቀሰችው ኤሪካም ከላይ የተጠቀሱትን ቃላት እውነትነት በራሷ ላይ አይታለች። ስሜቷን ጠቅለል አድርጋ በሚከተለው መንገድ ገልጻለች:- “አሁን ያለኝን ሥራ እወደዋለሁ። ይሁን እንጂ ሁኔታዎች ሊለወጡ እንደሚችሉ ከተሞክሮዬ ተመልክቻለሁ። ቢሆንም የመጽሐፍ ቅዱስን መሠረታዊ ሥርዓቶች በሥራ ላይ በማዋልና በይሖዋ በመታመን ሥራ በማይኖረኝ ጊዜ የሚሰማኝን ጭንቀት እንዴት መቀነስ እንደምችልና ባገኘሁት ሥራ የሚሰማኝን እርካታ እንዴት ከፍ ማድረግ እንደምችል ተምሬያለሁ።”

[በገጽ 10 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

በስብሰባዎች ወቅት ትኩረት ሰጥቶ አለማዳመጥ ሥራህን ሊያሳጣህ ይችላል