ከዓለም አካባቢ
ከዓለም አካባቢ
ሕፃናት ሙዚቃ መለየት ይችላሉ
“ሕፃናት መናገር ከመጀመራቸው በፊትም እንኳ ሙዚቃ መለየት ይችላሉ” ሲል ሳይንቲፊክ አሜሪካን የተባለው መጽሔት ዘግቧል። ዘገባው እንደሚገልጸው ሕፃናት በሙዚቃ ቃና ላይ የሚታዩ ልዩነቶችንም ሆነ በሙዚቃ ፍጥነትና በሙዚቃ ምት ላይ የሚከሰቱ ለውጦችን የመለየት ችሎታ አላቸው። ከዚህም በተጨማሪ አንድ ሙዚቃ ለየት ባሉ ኖታዎች በሚቀርብበት ጊዜም ይህን ለውጥ ማስተዋል ይችላሉ። የሁለት ወር ሕፃናት እንኳ ሳይቀሩ በጥሩ ሁኔታ ካልተቀናበረ ሙዚቃ ይልቅ በደንብ የተቀናበረን ሙዚቃ መስማት ይመርጣሉ። “በቤልፋስት የሚገኘው የክዊን ዩኒቨርሲቲ ባልደረባ የሆኑት ፒተር ሄፐር ሊወለዱ ሁለት ሳምንት ገደማ የቀራቸው በማኅፀን ውስጥ ያሉ ሕፃናት ከመወለዳቸው በፊት እናቶቻቸው በርከት ላሉ ሳምንታት በየዕለቱ ይሰሙት የነበረውን [የአንድ የታወቀ] የቴሌቪዥን ፕሮግራም ማስተዋወቂያ ሙዚቃ ተሰምቶ ከማያውቅ አዲስ ሙዚቃ መለየት እንደቻሉ አረጋግጠዋል” ሲል ዘገባው ገልጿል።
በመኪና ውስጥ የሚፈጠር ጠብ ለአደጋ ያጋልጣል
የጀርመን ቴክኒካል ሱፐርቪዥን ማኅበር “መኪና ውስጥ የተሳፈሩ ሰዎች በመካከላቸው ጠብ እንዳይፈጠር የተቻላቸውን ሁሉ ጥረት ማድረግ አለባቸው” ሲል ማስጠንቀቂያ መስጠቱን ቤርሊነር ሞርገንፖስት የተባለው ጋዜጣ ዘግቧል። “አሽከርካሪው ሳይታወቀው በኃይል ማሽከርከር ስለሚጀምር አደጋ ሊከሰት የሚችልበት አጋጣሚ ይጨምራል።” በመኪና ውስጥ የተነሣ “ጠብ” በተለይ በመኪናው ውስጥ ለማፈግፈግ የሚያስችል ቦታ ስለማይኖር ወዲያውኑ ሊባባስ ይችላል። ስለዚህ በመኪና ውስጥ የተሳፈሩ ሰዎች ሊያስቆጡና ወደ ጭቅጭቅ ሊመሩ የሚችሉ ርዕሰ ጉዳዮችን ማንሳት አይኖርባቸውም። በመኪናው ውስጥ ያሉት ሁሉ ራሳቸውን የጋራ ግብ ያለው የአንድ ቡድን አባላት እንደሆኑ አድርገው መቁጠር አለባቸው። ጽሑፉ “ከአሽከርካሪው ጎን የሚቀመጠው ሰው ሊሄዱበት የሚገባውን አቅጣጫ በመወሰን፣ ሬዲዮ በመክፈት ወይም ሌሎች አስቸጋሪ ሁኔታዎችን በመወጣት ረገድ እንዴት አስተዋፅኦ ሊያበረክት እንደሚችል ጉዞ ከመጀመራቸው በፊት መታወቅ አለበት” የሚል ምክር ሰጥቷል።
ጥቁር ባሕር እያንሰራራ ነው
አብዛኛውን ጊዜ በተበከለ ውኃ ውስጥ የማይኖሩ እንደ ዶልፊን፣ ሸርጣንና ትናንሽ ዓሣዎች ያሉ ፍጥረታት በአሁኑ ጊዜ በጥቁር ባሕር ውስጥ እየተበራከቱ እንደመጡ ዴሞክራቱችና ኡክሬና የተባለ የዩክሬን ጋዜጣ ገልጿል። በጣም የተበከለ የጥቁር ባሕር ክፍል እንደሆነ ተደርጎ በሚታሰበው የኦዴሳ ወደብም እንኳ ሲ ሆርስ የተባሉ ዓሦች ዳግመኛ እየተባዙ ነው። “በጥቁር ባሕርና በአዞፍ ባሕር ውስጥ ያሉ እንስሳትና ዕፅዋት ለረጅም ጊዜ ከቆየ በሽታ ቀስ በቀስ እያገገሙ ነው” ሲሉ የደቡብ ባሕሮች የሥነ ሕይወት ተቋም የኦዴሳ ቅርንጫፍ ዳይሬክተር የሆኑት ቦሪስ አሌክሳንድሮቭ ተናግረዋል። ይህ ለውጥ ሊታይ የቻለው ለምንድን ነው? ሳይንስ ኒውስ እንዳለው “የኮምዩኒዝም ሥርዓት ሲወድቅ በሩስያ፣ በዩክሬን፣ በሞልዶቫ፣ በሩማንያና በቡልጋሪያ የተከሰተው የኢኮኖሚ ውጥረት ለማዳበሪያ የሚያወጡት ወጪ በእጅጉ እንዲቀንስ ምክንያት ሆኗል። በመሆኑም ወደ ጥቁር ባሕር ይገባ የነበረው በናይትሬት የተበከለ የዝናብ ውኃ በ1990ዎቹ ዓመታት በጣም ቀንሷል።” ጥቅም ላይ የሚውለው ማዳበሪያ መጠን መቀነሱ ለጥቁር ባሕር ያበረከተው አስተዋጽኦ ቢኖርም “የኢኮኖሚ ውድቀት ወይም ደግሞ የግብርናው መስክ መዳከም ሙት የሆኑ [የባሕር] ቀጣናዎችን ለመቆጣጠር ጥሩ ስትራቴጂ አይደለም” ይላል ሳይንስ ኒውስ። በእንግሊዝ በፕሊመዝ ዩኒቨርሲቲ የባሕርና የባሕር ዳርቻዎች ፖሊሲ ፕሮፌሰር የሆኑት ላውረንስ ሚ ሌላ የመፍትሔ ሐሳብ አቅርበዋል። “ወደ ባሕር የሚገባውን ንጥረ ነገር መጠን መወሰን እንድንችል ግብርናችንን ጥበብ በተሞላበት መንገድ እንዴት ማከናወን እንደምንችል መማር ይኖርብናል” ብለዋል።
በቆሻሻ ውኃ የተሞላ መስኖ
“በዓለም ዙሪያ አትራፊ ከሆኑት ሰብሎች መካከል አንድ አሥረኛ የሚሆኑት የሚለሙት በቆሻሻ ውኃ ነው” ሲል ዴር ዥታንዳርት የተባለ አንድ የኦስትሪያ ጋዜጣ ዘግቧል። እንደ ቲማቲምና ኮኮናት ያሉ የተለያዩ ሰብሎች የሚለሙት በዚህ መንገድ ነው። “በቆሻሻ የተሞላው ውኃ በአብዛኛው ምንም ሳይጣራ ከትላልቅ ከተሞች በቀጥታ ወደ መስኖ ቦዮች ይገባል” ይላል ጋዜጣው። የስሪ ላንካ ዓለም አቀፍ የውኃ አያያዝ ተቋም ባልደረባ የሆኑትን ክሪስ ስኮት የተባሉ ባለሙያን በመጥቀስ ጋዜጣው “በከፍተኛ ፍጥነት በማደግ ላይ ባሉ ትላልቅ ከተሞች አቅራቢያ በሚገኙ ብዙ ቦታዎች የውኃ እጥረትን ለማቃለል ያለው ብቸኛ መንገድ ይህ ነው” ሲል ገልጿል። ዘገባው እንደሚጠቁመው በምድር ዙሪያ 20 ሚሊዮን ሄክታር ገደማ የእርሻ መሬት ያለ በመሆኑ ገበሬዎች ከዚህ ሌላ ብዙም አማራጭ የላቸውም፤ ቆሻሻ ውኃን ለመጠቀም የሚገደዱት ማዳበሪያ በነፃ ስለሚያስገኝላቸው ብቻ ሳይሆን ሌላ ውኃ ስለማይገኝ ቢገኝም አቅማቸው ስለማይመጥን ነው።
ሰዎችን በኮንትሮባንድ መሸጥ
“ዓለም አቀፍ የወንጀል ቡድኖች ከአደንዛዥ ዕፅና ከጦር መሣሪያ ንግድ ቀጥሎ በሦስተኝነት ደረጃ ከፍተኛ ገቢ የሚያገኙት ሰዎችን በኮንትሮባንድ በመሸጥ ሲሆን በዚህ ንግድ በዓመት ከ6 ቢሊዮን እስከ 9 ቢሊዮን የሚደርስ ዶላር እንደሚዝቁ ይገመታል” ሲል ዘ ማያሚ ሄራልድ በዓለም አቀፍ እትሙ
ላይ ዘግቧል። በቅርቡ በሜክሲኮ ሲቲ በተካሄደ ጋዜጣዊ መግለጫ ላይ በሰዎች ላይ የሚካሄደውን የኮንትሮባንድ ሽያጭ ለመቆጣጠርና ለመግታት የተቋቋመው የዩናይትድ ስቴትስ የመንግሥት ቢሮ ዳይሬክተር የሆኑት ጆን ሚለር በአንድ ዓመት ውስጥ 17,500 ገደማ የሚሆኑ ሰዎች ወደ ዩናይትድ ስቴትስ በኮንትሮባንድ እንደተሸጡና ከእነዚህ መካከል አንድ ሦስተኛ የሚሆኑት ከሜክሲኮ የመጡ አለዚያም በሜክሲኮ በኩል የገቡ እንደሆኑ ለጋዜጠኞች ገልጸዋል። ሚለር “እየተናገርኩ ያለሁት በሕገ ወጥ መንገድ ወደ አገር ውስጥ ስለገቡ ስደተኞች ሳይሆን በሰዎች ተገድደው ከባርነት በማይለይ ሁኔታ ውስጥ እንዲኖሩ ስለተደረጉ ወንዶች፣ ሴቶችና ሕፃናት ነው” ብለዋል። ለወሲብ መጠቀሚያነትና ለጉልበት ሥራ የሚሸጡ ሰዎች ጉዳይ “በ21ኛው መቶ ዘመን በዋነኝነት ከሚያወዛግቡ የሰብዓዊ መብት ጉዳዮች አንዱ” እንደሆነ ገልጸዋል።ፀሐይና ነፍሰ ጡር እናቶች
“ነፍሰ ጡር ሴቶች ያላቸውን የቫይታሚን ዲ መጠን ለማወቅ በተደረገ ጥናት ከፍተኛ ቁጥር ያላቸው ነፍሰ ጡር እናቶች የዚህ ቫይታሚን እጥረት እንዳለባቸው የተረጋገጠ ሲሆን ይህም በማኅፀናቸው ውስጥ ያሉትን ሕፃናት ለጉዳት ያጋልጣል” ሲል ሰን ሄራልድ የተባለው የአውስትራሊያ ጋዜጣ ዘግቧል። የቫይታሚን ዲ እጥረት ያለባቸው ሕፃናት እግራቸው ሊጣመም፣ በሚጥል በሽታ ሊሠቃዩና ሪኬትስ የተባለው የአጥንት በሽታ ሊይዛቸው ይችላል። ሲድኒ ውስጥ በሚገኘው ሴንት ጆርጅ ሆስፒታል በ1,000 ነፍሰ ጡር ሴቶች ላይ በተካሄደ ጥናት “ነጣ ያለ ቆዳ ካላቸው 10 ሴቶች መካከል አንዷና ጠቆር ያለ ቆዳ ካላቸው አምስት ሴቶች መካከል አንዷ የቫይታሚን ዲ እጥረት እንዳለባቸው ተረጋግጧል።” ለዚህ ችግር መፍትሔው ቀላል ይመስላል። ሰዎች ለሰውነታቸው ከሚያስፈልገው የቫይታሚን ዲ መጠን መካከል 90 በመቶ ገደማ የሚሆነውን የሚያገኙት ቆዳቸው ተስማሚ የሆነ የፀሐይ ብርሃን እንዲያገኝ በማድረግ ነው። “አብዛኞቹ ሴቶች የሚያስፈልጋቸውን ያህል ቫይታሚን ዲ ለማግኘት በቀን ውስጥ ለ10 ደቂቃ ወይም በሳምንት ለአንድ ሰዓት ገደማ ፀሐይ ቢሞቁ [በቂያቸው ነው]” ይላል ጋዜጣው።
ከልክ ባለፈ የአካል ብቃት እንቅስቃሴ ሳቢያ የሚታመሙ ሴቶች
አዘውትረው ከልክ ያለፈ ከባድ የአካል ብቃት እንቅስቃሴ የሚያደርጉ ሴቶች ኦስትዮፖሮሲስ ለተባለ የአጥንት በሽታ፣ ከአመጋገብ ጋር ለተያያዙ ችግሮችና ለወር አበባ ዑደት መስተጓጎል የተጋለጡ እንደሚሆኑ ፎያ የተባለ የብራዚል ጋዜጣ ዘግቧል። በሳኦ ፓውሎ ዩኒቨርሲቲ የአካልና የስፖርት ሕክምና ማዕከል አስተባባሪ የሆኑት ቱሪብዮ ሌይቲ ደ ባሮስ ኔቱ “አንዲት ሴት በሰውነቷ ውስጥ ሊኖር የሚገባው ስብ አንድ ወንድ ሊኖረው ከሚገባው የስብ መጠን በ10 በመቶ የበለጠ መሆን አለበት። በሌላ አነጋገር የሰውነቷ ስብ ከ15 በመቶ ያነሰ መሆን የለበትም” ሲሉ ተናግረዋል። አንዲት ሴት ያላት የስብ መጠን ከዚህ ያነሰ ከሆነ ሰውነቷ የወር አበባዋን የሚቆጣጠሩትን ሆርሞኖች ማመንጨት ሊሳነው የሚችል ከመሆኑም በላይ በአጥንቶቿ ውስጥ የሚኖረው የካልሲየም ክምችት ሊቀንስና ኦስትዮፖሮሲስ ለተባለው በሽታ ልትጋለጥ እንደምትችል ፎያ ገልጿል።