በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

የተሻለ ነገር አግኝተናል

የተሻለ ነገር አግኝተናል

የተሻለ ነገር አግኝተናል

ፍራንሲስ ዴል ሮዛርዮ ዴ ፓዬስ እንደተናገረችው

በ1988 እኔና ወንድሞቼ ከሌሎች የሙዚቃ ቡድኖች ጋር ሆነን በኒው ዮርክ ሲቲ ማዲሰን ስኩዌር ጋርደን በሺዎች በሚቆጠሩ ተመልካቾች ፊት የሙዚቃ ዝግጅታችንን አቀረብን። እኔ ዳንሰኛ ሆኜ የሠራሁበት የሙዚቃ ቡድናችንም ሞቅ ያለ አቀባበል ተደረገለት። ለዚህ ስኬት የበቃነው አባታችን ከልጅነታችን አንስቶ ባደረገልን ጥረት ነው።

ሙዚቀኛ የነበረው አባቴ ሰባቱ ታላላቅ ወንድሞቼ የሙዚቃ ተሰጥኦ እንዳላቸው ሲገነዘብ የራሳቸው ባንድ እንዲያቋቁሙ ሲል ቤታችንን ሸጦ የሚያስፈልጓቸውን የሙዚቃ መሣሪያዎች ገዛላቸው። የተወለድኩት ከጥቂት ዓመታት ቀደም ብሎ ማለትም በ1966 ስለነበር በዚያን ጊዜ ገና ትንሽ ልጅ ነበርኩ። በወቅቱ ቤተሰባችን የሚኖረው ዶሚኒካን ሪፑብሊክ ውስጥ በምትገኝ ኢጉዌይ በምትባል ከተማ ነበር።

በ1978 በኢጉዌይ ከተማ አዳራሽ ወንድሞቼ የሙዚቃ ሥራዎቻቸውን ለመጀመሪያ ጊዜ ለሕዝብ አቀረቡ። ቆየት ብለው ደግሞ ወደ ዋና ከተማው ሳንቶ ዶሚንጎ በመሄድ ዝግጅታቸውን አሳዩ። የራሳቸው ፈጠራ በሆነ አዲስ የሙዚቃ ስልት ሜሬንጌን መዝፈናቸውና መጫወታቸው በብዙዎች ዘንድ ተወዳጅነት አተረፈላቸው። * የሙዚቃ ቡድናቸውም ሎስ ኤርማኖስ ሮዛርዮ (ወንድማማቾቹ ሮዛሪዮዎች) በመባል ይታወቅ ጀመር።

እኔም ታዋቂ ዳንሰኛ የመሆን ሕልም ስለነበረኝ ከወንድሞቼ ጋር የመሥራት ፍላጎት አደረብኝ። በአንድ ግብዣ ላይ የቡድኑ መሪ የነበረው ፔፔ የተባለው ታላቅ ወንድሜ “ፍራንሲስ ከእህቶቼ መካከል የመጨረሻዋ ስትሆን ግሩም ዳንሰኛም ነች” ሲል እንድደንስ ጋበዘኝ። በሥፍራው የነበሩት ታዳሚዎች በአደናነሴ በጣም ተደነቁ። እኔም አጋጣሚውን ተጠቅሜ በቡድኑ ውስጥ ተወዛዋዥ መሆን እንደምፈልግ ለፔፔ ነገርኩት። በመሆኑም በ16 ዓመቴ ሎስ ኤርማኖስ ሮዛርዮ በሚያቀርባቸው የሙዚቃ ዝግጅቶች ሁሉ ላይ ተሳታፊ መሆን ጀመርኩ።

በዚህ ሙያ ያገኘሁት ስኬት

ከዚያ በፊት ባሉት የሜሬንጌ ቡድኖች ውስጥ ሴቶች በድምጻዊነት ይሠሩ የነበረ ቢሆንም በወንድ ሙዚቀኞች ታጅበው በሕዝብ ፊት ሲደንሱ ማየት የተለመደ አልነበረም። ከሜሬንጌ ስልታችን ጋር የሚሄድ አዲስ ውዝዋዜ ካቀነባበርኩ በኋላ እያንዳንዱን እንቅስቃሴ ለሌሎች ተወዛዋዦች አስጠናሁ። የእኔ ዳንስ በብዙዎች ዘንድ ታዋቂነትን አተረፈ፤ አ ሎ ፍራንሲስ ሮዛርዮ (የፍራንሲስ ሮማሪዮ ዳንስ) የሚል ስያሜም ተሰጠው።

በግጥሙ ውስጥ “ኢ አኦራ ቶዶ ኤል ሙንዶ ኮሞ ፍራንሲስ ሮዛርዮ” (አሁን ሁላችንም ልክ እንደ ፍራንሲስ ሮዛርዮ እንደንስ) የሚል ስንኝ ያለው “ኩማንዲ” የሚባል በሜሬንጌ ስልት የተቀነባበረ ዘፈን ነበረን። ይህ ከተባለ በኋላ ሰዎች ልክ እንደ እኔ ለመደነስ ይሞክራሉ። አንዳንዴም መደነሳቸውን አቁመው ወለሉ ላይ በመቀመጥ እኔን ይመለከቱ ነበር። የኋላ ኋላ ፖስተር ላይ የእኔን ፎቶ ብቻ በማውጣት የቡድናችንን የሙዚቃ ዝግጅቶች ማስተዋወቅ ተጀመረ። ማንም ሰው የእኔን ፎቶ ብቻ አይቶ ሎስ ኤርማኖስ ሮዛርዮ የሙዚቃ ትርኢት እንዳለው ማወቅ ይችል ነበር።

ከወንድሞቼ ጋር መሥራት ከጀመርኩ በኋላ ፓዬስ የሚባል የቤተሰብ ስም ያላቸውን ሦስት ወንድማማቾች ጨምሮ ሌሎች ሙዚቀኞችም ወደ ቡድናችን ተቀላቀሉ። ከወንድማማቾቹ መካከል አንዱ ትራንፔት ተጫዋቹ ሮቤርቶ ሲሆን በኋላ ላይ ባለቤቴ ሆነ። እነዚህ ወንድማማቾችም ቡድናችን የሚያገኘው ስኬት ተቋዳሽ ሆኑ። ሎስ ኤርማኖስ ሮዛርዮ የሙዚቃ ዝግጅቱን እንዲያሳይ ከሳንቶ ዶሚንጎ የቴሌቪዥን ማሰራጫ እንዲሁም ከሌሎች አገሮች የተለያዩ ግብዣዎች ይጎርፉለት ጀመር።

በ1988 በአሜሪካና በካናዳ በመዘዋወር ዝግጅታችንን አቀረብን። ከዚህ ውስጥ ቀደም ሲል የጠቀስኩት በማዲሰን ስኩዌር ጋርደን ያሳየነው የሙዚቃ ትርኢት ይገኝበታል። በጣም ታዋቂ የሆኑ የሜሬንጌ ቡድኖች ተሳታፊ በሆኑበት በዚህ ትርኢት ላይ የሙዚቃ ቡድናችን ሰፊ ተቀባይነት አገኘ። ከዚያ በኋላ የሙዚቃ ትርኢት አዘጋጆች ባንዳችን ሁልጊዜ ትርኢቱን በዝግጅቱ መደምደሚያ ላይ እንዲያቀርብ ያደርጉ ጀመር። አደናነሴ ከመቼውም ጊዜ ይበልጥ ትኩረት እያገኘና የሎስ ኤርማኖስ ሮዛርዮ አድናቂዎችም እየተበራከቱ ሄዱ። የዘፈን ቅጂ ሽያጫችንም በፍጥነት አደገ።

በወቅቱ እስከ ኮሎምቢያ፣ ኢኳዶር፣ ፓናማ፣ ፖርቶ ሪኮ፣ ኩራሳኦ፣ ስፔን፣ ጀርመንና ሌሎች ብዙ አገሮች ድረስ እየተጓዝን የሙዚቃ ዝግጅቶቻችንን አሳይተናል። ብዙም ሳይቆይ የሙዚቃ ቡድናችን በላቲኑ ዓለም እጅግ ታላቅ አድናቆት ለማትረፍ ቻለ። ዳንስ፣ መድረክ፣ የመድረክ አልባሳት እንዲሁም መኳኳያዎች በሕይወቴ ውስጥ ትልቁን ሥፍራ ያዙ።

ነጠላ ሳለሁ ብዙ ጊዜ ‘ዳንስ የማይወድ ሰው ቢያፈቅረኝ ዳንስ ከማቆሜ በፊት ከእሱ ጋር ያለኝን ግንኙነት አቆማለሁ’ በማለት እናገር ነበር። ይሁንና በሕይወቴ ውስጥ ቅድሚያ ልሰጣቸው ስለሚገቡ ነገሮች ያለኝ አመለካከት በሚቀየርበት ዋዜማ ላይ ነበርኩ።

ለመንፈሳዊ ነገሮች ዓይኖቼ ተገለጡ

ይህ ለውጥ የጀመረው በ1991 የካናሪ ደሴቶችን በመጎብኘት ላይ ሳለን ነበር። እኔና ሮቤርቶ ከተጋባን ብዙ አልቆየንም። የቡድኑ አባልና የሮቤርቶ ታላቅ ወንድም የነበረው ፍሬዲ ከይሖዋ ምሥክሮች ጋር ማጥናት ጀምሮ ስለነበር ጽሑፎቻቸው ከእጁ አይለዩም ነበር።

አንድ ቀን በምድር ላይ በገነት ለዘላለም መኖር ትችላለህ የሚል ርዕስ ያለው መጽሐፍ በፍሬዲ ክፍል ውስጥ ተቀምጦ አየሁ፤ መጽሐፉንም ማንበብ ጀመርኩ። በዚህ ጊዜ “ሲኦል ምን ዓይነት ቦታ ነው?” የሚለው ምዕራፍ ትኩረቴን ሳበው። ምክንያቱም እናቴ ክፉ የሠሩ ሰዎች በሲኦል ውስጥ ይቃጠላሉ ትል ስለነበር እኔም ወደዚያው እንዳልሄድ ፍርሃቱ ነበረብኝ።

ከጥቂት ሳምንታት በኋላ በዚያው በካናሪ ደሴቶች ውስጥ ሳለን አስወረደኝ። ሆስፒታል ሲወስዱኝም እስካገግም ድረስ ለማንበብ ስላሰብኩ ሮቤርቶ ከፍሬዲ ጠይቆ በክፍሉ ውስጥ ያየሁትን መጽሐፍ እንዲያመጣልኝ ነገርኩት። መጽሐፉን እጅግ ወደድኩት። በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ የተገለጸው ሲኦል የሰው ልጆች መቃብር እንደሆነና አምላክ የሰው ልጆችን ለማሠቃየት በጭራሽ አስቦ እንደማያውቅ እንዲሁም ሌሎች ነገሮችን ተገነዘብኩ። (ኤርምያስ 7:31) መጽሐፍ ቅዱስ ሙታን አንዳች እንደማያውቁ መናገሩ እጅግ አስገረመኝ።—መክብብ 9:5, 10

ወደ ዶሚኒካን ሪፑብሊክ ስንመለስ ፍሬዲ አንድ የይሖዋ ምሥክር እንዲያነጋግረን አደረገ። እርሱም ገነት በሆነች ምድር ላይ ስለምናገኘው ዘላለማዊ ሕይወት የሚገልጸውን የመጽሐፍ ቅዱስ ተስፋ ነገረን፤ ይህም የባለቤቴን የማወቅ ፍላጎት ቀሰቀሰው። (መዝሙር 37:29፤ ሉቃስ 23:43) በመሆኑም መጽሐፍ ቅዱስ እንዲያስጠናን ጠየቅነው።

የባሕርይና የአመለካከት ለውጥ አደረግሁ

የመጽሐፍ ቅዱስ እውቀቴ ይበልጥ እያደገ ሲሄድ እጅግ እወደው ስለነበረው ሥራዬ ያለኝ አመለካከት የዚያኑ ያህል ተለወጠ። የመጽሐፍ ቅዱስ መሠረታዊ ሥርዓቶች አስተሳሰቤን ይቀርጹት ጀመር። (ሮሜ 12:2) ‘በዚህ ሁሉ ሕዝብ ፊት እንዲህ ባለ ሁኔታ እንዴት እደንሳለሁ? እኔ የምፈልገው ይህን አይደለም’ እያልኩ ራሴን እጠይቅ ነበር። “እባክህ ከዚህ ሁኔታ ውስጥ አውጣኝ” ስል ወደ አምላክ ጸለይኩ። ስለሁኔታው ለባለቤቴ በነገርኩት ጊዜ እሱም ተመሳሳይ ስሜት ተሰምቶት ኖሮ “ትንሽ ታገሽ የኔ ፍቅር፤ ቡድኑን መጀመሪያ አንቺ ትለቂያለሽ እኔ ደግሞ እከተልሻለሁ” ሲል አጽናናኝ።

ከጥቂት ጊዜ በኋላ በድጋሚ ጸነስኩ፤ ያለሁበት ሁኔታ እንደ ልብ ለመደነስ ስለማያስችለኝ አጋጣሚውን በመጠቀም በመንግሥት አዳራሽ በሚደረጉት ክርስቲያናዊ ስብሰባዎቸ ላይ አዘውትሬ መገኘት ጀመርኩ። ይህ እኔንም ሆነ በስብሰባዎች ላይ መገኘት ጀምሮ የነበረውን ሮቤርቶን አጠነከረን። በተጨማሪም ከይሖዋ ሕዝቦች ጋር አብሮ የመሰብሰቡን አስፈላጊነት ከፍ አድርገን እንድንመለከተው አደረገን። በመጽሐፍ ቅዱስ እውነት እያደግን ለመሄድ በክርስቲያናዊ ስብሰባዎች ላይ የሚሰጡት ትምህርቶችና ማበረታቻዎች እንደሚያስፈልጉን ተገነዘብን። (ዕብራውያን 10:24, 25) እኔና ሮቤርቶ ለሥራ ጉዳይ ከዶሚኒካን ሪፑብሊክ ውጪ በምንሄድበት ጊዜ እንኳ የመንግሥት አዳራሾችን ፈልገን በስብሰባዎች ላይ እንገኝ ነበር።

ልጅ ከወለድኩ በኋላ ወደ ሥራዬ ተመለስኩ፤ ያም ሆኖ ልቤ በሥራው ላይ አልነበረም። መለወጤ በግልጽ ይታይ ስለነበር ጋዜጠኞች ይነቅፉኝ ጀመር። እንዲሁም ብዙውን ጊዜ “ለምን እንደ በፊቱ አትደንሺም?” የሚል ጥያቄ ይቀርብልኝ ነበር። እኔም ወንድሞቼ ላይ ችግር እንዳልፈጥር ስለ ሰጋሁ ይሖዋ መውጫውን እንዲያሳየኝ ሳላቋርጥ ጸለይኩ። ከቡድኑ ባለቤቶች ውስጥ አንዷ ስለነበርኩ ከወንድሞቼ ጋር መጋጨት ፈጽሞ አልፈለግሁም ነበር።

አሁንም ዳግመኛ ስጸንስ፣ ከወንድማችን ከፔፔ ሞት በኋላ ቡድኑን በኃላፊነት ለተረከበው ለራፋ ከልጆቼ ጋር በርከት ያለ ጊዜ ማሳለፍ ስለምፈልግ ሥራውን መልቀቄን ነገርኩት። እርሱም ጥሩ ነው ብዬ ያሰብኩትን እንዳደርግ ነገረኝ። ከወንድሞቼ ውስጥ ማንም መጽሐፍ ቅዱስ ማጥናቴን የተቃወመ አልነበረም። ለዚህም እጅግ አመስጋኝ ነኝ።

በአዲስ ሕይወት ይሖዋን ማገልገል

በቡድኑ ውስጥ ለአሥር ዓመታት ካገለገልኩ በኋላ በ1993 የዳንሰኝነት ሥራዬን አቁሜ ያለ አንዳች ገደብ ራሴን ለይሖዋ ወሰንኩ። ከዚያም የአምላክ መንግሥት ምሥራች አስፋፊ ሆንኩና ሮቤርቶ ቡድኑን ከለቀቀ በኋላ ሁለታችንም በ1994 ተጠመቅን። (ማቴዎስ 24:14) ማንዌል ፔሬስ የተባለ አንድ የቡድኑን አባል ጨምሮ የሮቤርቶ ወንድሞች የሆኑት ፍሬዲና ሁልዮም የይሖዋ ምሥክሮች ሆኑ። አሁንም ይሖዋን በታማኝነት በማገልገል ላይ ይገኛሉ።

የመዝናኛውን የሥራ መስክ እጅግ እወደው ስለነበር በርካታ ሰዎች ለምን ለቅቄ እንደወጣሁ ግራ ይገባቸው ነበር። አንዳንዶቹ በአገራችን ያለ አንድ በጣም ታዋቂ የቴሌቪዥን ፕሮግራም አዘጋጅ የገለጸው ዓይነት ስሜት ነበራቸው። አዘጋጁ “እንደ ሌሎቹ አርቲስቶች ሁሉ እሷም ሁኔታዎቿ ተሻሽለው ዳግመኛ ወደ ቡድኑ ትመለሳለች” ሲል ተንብዮ ነበር። ሆኖም ፈጽሞ እንደዚያ አልሆነም። ከዚህ ይልቅ ባለኝ አቅም ሁሉ ሙሉ በሙሉ ይሖዋን ለማገልገል ቆርጬ ተነሳሁ።

በአሁኑ ወቅት ካቲ፣ ሮቤርቶና ኦቤድ የተባሉ ሦስት ልጆች አሉን። ልጆቻችንን በሕይወት ውስጥ ከፍተኛ ቦታ ሊይዝ የሚገባው መንፈሳዊ ነገር እንጂ ቁሳዊ ሀብት እንዳልሆነ እንዲገነዘቡ ለማስተማር ጥረናል። በዓለም አሳሳች ተጽዕኖ ሥር እንዳይወድቁ ለማስጠንቀቅና በሕይወታቸው ውስጥ የሚያስፈልጋቸውን ምክር ለመስጠት የሚያስችል ጥሩ ተሞክሮ አለን። ሳምንታዊው የቤተሰብ ጥናታችንም ከጊዜ ወደ ጊዜ ቤተሰቦች እየፈራረሱ በሄዱበት በዚህ ዓለም አንድነታችንን ጠብቀን እንድንኖር በእጅጉ ረድቶናል።

ለልጆቻችን ይሖዋ ሊታመኑበት የሚገባ ሕያው አካል ሆኖ እንዲታያቸው ለማስተማር ጥረት አድርገናል። (ምሳሌ 3:5, 6፤ ዕብራውያን 11:27) በስብሰባዎች ላይ መገኘትና መሳተፍ ያለው አስፈላጊነት እንዲታያቸው ለማድረግ ጥረናል። ልጆቻችን ከመጽሐፍ ቅዱስ እውነት ጋር በሚስማማ መንገድ ሲያድጉ መመልከት ለኛ በዋጋ ሊተመን የማይችል ስጦታ ነው። ላለፉት ሁለት ዓመታት ረዳት አቅኚ በመሆን አገልግያለሁ። (ረዳት አቅኚ የይሖዋ ምሥክሮች በመጽሐፍ ቅዱስ ላይ የተመሠረተ እምነታቸውን ለሌሎች ለማካፈል ሲሉ በወር ከ50 ሰዓት በላይ የሚያሳልፉ ሰዎችን ለማመልከት የሚጠቀሙበት አጠራር ነው።) ባለቤቴም ለዓመታት የጉባኤ ሽማግሌ ሆኖ በማገልገል ላይ ይገኛል።

ሜሬንጌ አሁንም ቢሆን ግሩም እንቅስቃሴ ያለው የሙዚቃ ስልት እንደሆነ ይሰማኛል። የሚያሳዝነው ግን፣ በዛሬው ጊዜ ታዋቂነት ያገኙት ብዙዎቹ የሜሬንጌ ስልቶች ከበፊቶቹ በጣም የተለዩ ናቸው። በአጠቃላይ የበፊቶቹ ጥሩዎች ነበሩ፤ አሁን ግን ተቀባይነት ያለው የሜሬንጌ ሙዚቃ ማግኘት እጅግ ጠንቃቃ መራጭ መሆንን ይጠይቃል።

ይሖዋን ማገልገልን የመሰለ ነገር የለም

ዓለም ብዙ ነገሮችን ያቀርብልናል፤ ይሁንና አንድ ሰው ከእነዚህ ነገሮች በስተ ጀርባ ያለው ምን እንደሆነ አሻግሮ ማየት ይኖርበታል። ይህ በተለይ ላይ ላዩን ሲታይ ማራኪና ምንም ጉዳት የሌለው በሚመስለው በሙዚቃው ኢንዱስትሪ ረገድ እውነታነት አለው። ሆኖም ነገሩ እንደሚታየው አይደለም። በሙዚቃው ኢንዱስትሪ የተሰማሩ ብዙ ሰዎች አደንዛዥ ዕፅ የሚወስዱ ሲሆን በሥነ ምግባር ብልግና ውስጥም ተዘፍቀዋል። በሙዚቃ ዝግጅቶች ውስጥ መካፈል አንድን ሰው ለምንም ነገር ደንታ ከሌላቸውና ለጊዜው ብቻ መኖር ከሚፈልጉ ሰዎች ጋር ጓደኝነት እንዲመሠርት ያደርገዋል።—1 ቆሮንቶስ 15:33

ማንኛውም ሰው ሊያደርገው የሚገባው ከሁሉ የላቀ ነገር ይሖዋን ማገልገል እንደሆነ ተረድተናል። አንድ ትልቅ ትርኢት አቅርበን ወደ ሆቴላችን በተመለስንበት ወቅት የተሰማኝን የባዶነት ስሜት መቼም አልረሳውም። እንደዚያ የተሰማኝ በጣም ያስፈልገን የነበረውን መንፈሳዊ ፍላጎታችንን ማሟላት ባለመቻላችን መሆኑ አሁን ገብቶኛል።—ማቴዎስ 5:3

አሁን ሕይወታችን ይበልጥ ያተኮረው ፈጣሪያችንን በማስደሰቱ ላይ ነው፤ ይህ በተለይ ምሥራቹን የመስበኩንና የማስተማሩን ሥራ ይመለከታል። (ማቴዎስ 24:14፤ የሐዋርያት ሥራ 20:35) እንዲህ ማድረጋችን ደስተኛና እርካታ ያለው ቤተሰብ ያስገኝልናል። ከአምላክ ሕዝቦች መካከል በመሆናችንና እንደኛው በአምላክ አዲስ ዓለም ውስጥ የዘላለም ሕይወት የመውረስ አስደናቂ ተስፋ ያላቸው እውነተኛ ወዳጆችን በማፍራታችን ምስጋናችን ላቅ ያለ ነው።—ማርቆስ 10:29, 30፤ 2 ጴጥሮስ 3:13፤ ራእይ 21:3, 4

የመዝናኛው ዓለም ጠቀም ያለ ገንዘብ ያስገኝልን ነበር። ሆኖም አምላካችንን ይሖዋን ማወቅ ከማንኛውም ቁሳዊ ብልጽግና ጋር ፈጽሞ ሊወዳደር የማይችል መንፈሳዊ ሀብት አስገኝቶልናል። በእርሱ እንድንታመን ግብዣ የሚያቀርብልንን ዓላማ ያለውን ደስተኛ አምላክ ማገልገል በመቻላችን ደስታችን ወደር የለውም! (መዝሙር 37:3) ከዝና እና ከቁሳዊ ሀብት እጅግ የሚልቅ ነገር እንዳገኘን ፍጹም እርግጠኞች ነን፤ እንዲሁም እኛም ሆንን ቤተሰባችን ፈቃዱን በማድረግ ለዘላለም እንቀጥል ዘንድ ይሖዋ እንዲረዳን እንጸልያለን።

[የግርጌ ማስታወሻ]

^ አን.5 ሜሬንጌ ፈጣን ምት ያለው የዳንስ ሙዚቃ ነው። ቀደም ሲል ሜሬንጌን የሚጫወቱት አኮርዲዮን፣ ጉዊሮ (ተመቺ ብረት) እና ታምቦራ (በሁለቱም በኩል የምትመታ አነስተኛ ከበሮ) የያዙ ጥቂት ሰዎችን ያቀፉ ባንዶች ነበሩ። ጊዜው እያለፈ ሲሄድ ግን ኦርኬስታስ (ኦርኬስትራ) የሚባሉ ትልልቅ የሙዚቃ ባንዶች በዶሚኒካን ሪፑብሊክ ተቋቋሙ። በአሁን ጊዜ ያሉ ብዙዎቹ የሜሬንጌ ቡድኖች ኦርጋን፣ ሳክስፎን፣ ትራምፔት፣ ኮንጋ ታምቡር እንዲሁም ሌሎች የሙዚቃ መሣሪያዎችን ይጠቀማሉ።

[በገጽ 23 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

ወደ ሙዚቃው ዓለም በገባሁ ሰሞን ከሌሎች የቡድኑ አባላት ጋር

[በገጽ 23 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

በ1990 አካባቢ በኒው ዮርክ ሲቲ ዝግጅታችንን ስናቀርብ

[በገጽ 25 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

ከመንግሥት አዳራሻችን ፊት ለፊት

[በገጽ 25 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

ድራቢው ፎቶ:- የቤተሰብ ጥናት እያደረግን