በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

ጥሩ ምሥክርነት የሚሰጡ ወጣቶች

ጥሩ ምሥክርነት የሚሰጡ ወጣቶች

ጥሩ ምሥክርነት የሚሰጡ ወጣቶች

በይሖዋ ምሥክሮች መካከል የሚገኙ በርካታ ወጣቶች በትምህርት ቤትም ሆነ በክርስቲያናዊ አገልግሎት በሚካፈሉበት ጊዜ ስለ እምነታቸው በድፍረት በመመሥከራቸው ጥሩ ውጤት አግኝተዋል። የሚከተሉትን ምሳሌዎች እንመልከት። *

ክርስቲና እንዲህ ትላለች:- “ሦስተኛ ክፍል ሳለሁ አስተማሪያችን ለእያንዳንዳችን ማስታወሻ ደብተር ሰጠችንና በየቀኑ ስለምንሠራው ነገር እንድንጽፍ ነገረችን። አስተማሪዋም የጻፍነውን ሰብስባ ካነበበችው በኋላ አንዳንድ ነገሮችን ጽፋ እንደምትመልስልን ገለጸች። በቲኦክራሲያዊ የአገልግሎት ትምህርት ቤት ስለማቀርበው ክፍል ለመጻፍ ወሰንኩ። አስተማሪዋ በጽሑፉ ስለተደሰተች ክፍሌን ሳቀርብ እንድትሰማ ወደ መንግሥት አዳራሽ ጋበዝኳት። እርሷ ብቻ ሳትሆን የአንደኛ ክፍል አስተማሪዬም አብራት መጣች። ከዚያም አስተማሪዋ፣ ትምህርት ቤት ውስጥ ለተማሪዎቹ ባቀረብኩት ክፍል ምን ያህል እንደተደሰተችበት ነገረቻቸው። እኔም በጣም ተደሰትኩ፤ ታሪኩ ግን በዚህ ብቻ አላበቃም። ከአንድ ዓመት ገደማ በኋላ የይሖዋ ምሥክሮች በሚያደርጉት የወረዳ ስብሰባ ላይ ተሞክሮዬን ስናገር የሦስተኛ ክፍል አስተማሪዬም በስብሰባው ላይ ተገኝታ ነበር። ቆየት ብሎም፣ አቅኚ ከሆነች ጓደኛዬ ጋር ሆነን አስተማሪዬ ጋር ሄድንና ወደ ዘላለም ሕይወት የሚመራ እውቀት የተባለውን መጽሐፍ አበረከትንላት። በአንድ የአውራጃ ስብሰባ ላይም መገኘት ችላለች!”

ሲድኒ የስድስት ዓመት ልጅ እያለች የአምላክን ቃል እውነት፣ ሙታን በምን ሁኔታ ላይ እንደሚገኙና ኢየሱስ ያለውን ቦታ ለክፍል ጓደኞቿ በድፍረት በመናገር ረገድ የተዋጣላት ነበረች። “ቀናተኛና ደፋር የሆነች ትንሽ የአምላክ አገልጋይ” እንደሆነች እናቷ ትናገራለች። ሲድኒ በመጀመሪያው የትምህርት ዓመት መገባደጃ ላይ “ስለ ክፍል ጓደኞቼ በጣም ተጨንቄያለሁ” በማለት በሐዘን ተናገረች። “ስለ ይሖዋ እንዴት መማር ይችላሉ?” ሲድኒ አንድ ሐሳብ መጣላት። በትምህርት ዘመኑ የመጨረሻ ቀን ላይ ለእያንዳንዱ ተማሪ በስጦታ ወረቀት የተጠቀለለ ገጸ በረከት ሰጠች። ስጦታውም የመጽሐፍ ቅዱስ ታሪኮች መማሪያ መጽሐፌ የተባለው ጽሑፍ ሲሆን ሲድኒ በጠቅላላ 26 የሚያህል አበርክታለች፤ ለተማሪዎቹ ስጦታቸውን ቤት ሲደርሱ ከወላጆቻቸው ጋር ሆነው መክፈት እንደሚችሉ ነገረቻቸው። ሲድኒ የክፍል ጓደኞቿን ለእርሷ የተመደቡ የአገልግሎት ክልሏ እንደሆኑ አድርጋ ትመለከታቸዋለች። የክፍል ጓደኞቿ መጽሐፉን ወድደውት እንደሆነ ስልክ በመደወል ጭምር ጠይቃቸዋለች። አንዲት ልጅ መጽሐፉን ሁልጊዜ ማታ ማታ ከእናቷ ጋር እንደምታነበው ነገረቻት።

ኤለን የ15 ዓመት ልጅ በነበረችበት ጊዜ ለታሪክ አስተማሪዋ በርካታ ንቁ! መጽሔቶችን ትሰጠው ነበር። ኤለን እንዲህ ትላለች:- “ንቁ! መጽሔቶቹን በጣም የወደዳቸው ሲሆን መጽሔቶቹን ማንበብ ከጀመረ አሁን ሁለተኛ ዓመቱን ይዟል። በቅርብ የመጽሐፍ ቅዱስ ታሪኮች መማሪያ መጽሐፌ የተባለውን መጽሐፍ ከሰጠሁት በኋላ ሁለቱም ሴት ልጆቹ መጽሐፉን በጣም እንደወደዱት ነገረኝ። ከዚያም ከታላቁ አስተማሪ ተማሩ (እንግሊዝኛ) የተባለውን መጽሐፍ ሰጠሁት። ከጊዜ በኋላ እንዲህ የሚል ካርድ ሰጠኝ:- ‘ለመጽሐፎቹ በጣም አመሰግናለሁ። እኔና ሴቶች ልጆቼ በጣም የሚመስጡ ሆነው አግኝተናቸዋል። እንደ አንቺ አስተዋይና በሙሉ ልቡ የሚሠራ ወጣት ማየት በጣም ደስ ያሰኛል። ከአንቺ እምነት ጋር ሊወዳደር የሚችል ምንም ዓይነት ስጦታ የለም። እኔ ላስተምርሽ ከምችለው ይበልጥ አንቺ አስተምረሽኛል!’ ይህ ተሞክሮ የመጽሐፍ ቅዱስን እውነት ለሰዎች ለማድረስ ስንጥር ምን ያህል እንደሚያደንቁት እንድገነዘብ አስችሎኛል።”

ዳንኤል የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናት ማስጠናት የጀመረው በስድስት ዓመቱ ነበር። “እናቴ የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናት ስታስጠና ከእርሷ ጋር እሄድ የነበረ ቢሆንም እኔ ራሴ አንድ ሰው ማስጠናት ፈለግኩ” ይላል። መጽሐፍ ቅዱሳዊ ጽሑፎችን ያበረከተላቸውን ሚስዝ ራትክሊፍ የሚባሉ አረጋዊት ለማስጠናት መረጠ። እንዲህ አላቸው:- “በጣም የምወደውን የመጽሐፍ ቅዱስ ታሪኮች መማሪያ መጽሐፌ የተባለውን መጽሐፍ እንዲያዩት እፈልጋለሁ፤ በየሳምንቱ እየመጣሁ ለእርስዎ ላነብልዎት እችላለሁ?” ሚስዝ ራትክሊፍ የዳንኤልን ግብዣ ተቀበሉ። የዳንኤል እናት የሆነችው ሎራ እንዲህ ትላለች:- “የዚያኑ ዕለት ከሚስዝ ራትክሊፍ ጋር ጥናት ጀመርን። ዳንኤልና ሚስዝ ራትክሊፍ በየተራ አንቀጹን ካነበቡ በኋላ በታሪኩ መጨረሻ ላይ ከተጠቀሱት ጥቅሶች ዳንኤል የመረጣቸውን እሳቸው እንዲያነቡት ይጠይቃቸው ነበር። ሚስዝ ራትክሊፍ ጋር አብሬው ብሄድም እሳቸው ለመወያየት የሚፈልጉት ከዳንኤል ጋር ብቻ ነበር!” ከጊዜ በኋላ ሚስዝ ራትክሊፍ ከዳንኤል ጋር በምድር ላይ በገነት ለዘላለም መኖር ትችላለህ የተባለውን መጽሐፍ ማጥናት ጀመሩ። በዚህ ጊዜ፣ የዳንኤል ታናሽ እህት የሆነችው ናታሊ ማንበብ ችላ ስለነበር በጥናቱ ላይ መገኘት ጀመረች። ሚስዝ ራትክሊፍ ብዙ ጥያቄዎች ነበሯቸው፤ እንዲያውም አንዳንዶቹ ውስብስብ ነበሩ። ዳንኤልና ናታሊ መጽሐፍ ቅዱሳዊ የውይይት አርዕስት የተባለውን ቡክሌትና ከመጽሐፍ ቅዱስ ጀርባ ያለውን የጥቅሶች ማውጫ በመጠቀም መጽሐፍ ቅዱሳዊ መልሶችን ለመስጠት ችለዋል። ሚስዝ ራትክሊፍ ዕድሜያቸውን በሙሉ የካቶሊክ ሃይማኖት አባል የነበሩ ቢሆኑም በተማሩት ነገር በጣም ተደስተው ነበር። በአንድ ጥናት መጨረሻ ላይ “ምነው ከዓመታት በፊት መጽሐፍ ቅዱስን ማጥናት ጀምሬ በሆነ ኖሮ!” ለማለት ችለዋል። በጣም የሚያሳዝነው በቅርቡ ሚስዝ ራትክሊፍ በ91 ዓመታቸው ሞቱ። መጽሐፍ ቅዱስን በማጥናታቸው በገነቲቱ ምድር ላይ የሞቱት እንደሚነሱ የሚናገረውን ተስፋ ጨምሮ ውድ የሆኑ እውነቶችን ለማወቅ ችለዋል። በአሁኑ ጊዜ ዳንኤል አሥር ዓመቱ ሲሆን ሁለት የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናቶችን ይመራል። ናታሊ ደግሞ ስምንት ዓመቷ ሲሆን እኩያዋ የሆነችን ልጅ ታስጠናለች።

እንደ ክርስቲና፣ ሲድኒ፣ ኤለን፣ ዳንኤልና ናታሊ የመሰሉ ወጣቶች ለክርስቲያን ወላጆቻቸው ደስታ ያመጣሉ። ከሁሉም በላይ የይሖዋን ልብ ያስደስታሉ፣ ይሖዋ ደግሞ እነዚህ ወጣቶች ለስሙ የሚያሳዩትን ፍቅር አይረሳም።—ምሳሌ 27:11፤ ዕብራውያን 6:10

[የግርጌ ማስታወሻ]

^ አን.2 በዚህ ርዕስ ውስጥ የተጠቀሱት ጽሑፎች በሙሉ በይሖዋ ምሥክሮች የተዘጋጁ ናቸው።

[በገጽ 26 ላይ የሚገኙ ሥዕሎች]

ክርስቲና (ከላይ) እና ሲድኒ

[በገጽ 27 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

ዳንኤልና ናታሊ

[በገጽ 27 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

ኤለን