በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

ሴቶች ውበታቸውን መደበቅ ይኖርባቸዋል?

ሴቶች ውበታቸውን መደበቅ ይኖርባቸዋል?

የመጽሐፍ ቅዱስ አመለካከት

ሴቶች ውበታቸውን መደበቅ ይኖርባቸዋል?

“ሴቶች ፋሽን ይወዳሉ።” ይህን ያሉት በኒው ዮርክ የፋሽን ቴክኖሎጂ ተቋም ውስጥ ልምድ ያላቸው የፋሽን ዲዛይነርና ፕሮፌሰር የሆኑት ዦርዥ ሳይመንተን ናቸው። አክለውም እንዲህ ብለዋል:- “ሴቶች ማንነታቸውን ማሳየት፣ ዝንጥ ብሎ መታየት እንዲሁም ራሳቸውን ማስዋብ ይፈልጋሉ . . . ይህን ማድረግ ለራስህና ከአንተ ጋር ላሉት ሰዎች አክብሮት እንዳለህ የሚያሳይ ይመስለኛል።” አዎን፣ ማጋጌጫዎች ለሴቶች የሴትነታቸው መገለጫ እንደሆኑ፣ ውበት እንደሚጨምሩላቸውና በተወሰነ መጠን በራሳቸው እንዲተማመኑ እንደሚያደርጓቸው ተደርገው መታየት ከጀመሩ ብዙ ዘመናት አልፈዋል።

ሆኖም አንዳንዶች ሃይማኖትን ምክንያት በማድረግ፣ ሴቶች ራሳቸውን ማስዋባቸው ተገቢ እንዳልሆነ ይናገራሉ። በሦስተኛው መቶ ዘመን ከክርስቶስ ልደት በኋላ የኖረው ተርቱሊያን እንዲህ ሲል ጽፏል:- “ቅዱሳት ሴቶች . . . በተፈጥሮ ቆንጆዎች . . . ከሆኑ . . . ራሳቸውን ይበልጥ ማሳመር የለባቸውም፤ ከዚህ ይልቅ ውበታቸውን ለመደበቅ መሞከር አለባቸው።” መኳኳያዎችን በተመለከተ ደግሞ እንዲህ ብሏል:- “ፊታቸውን የተለያዩ ማሳመሪያ ቅባቶች የሚቀቡ፣ ጉንጫቸውን ለማቅላት በቀለም የሚጠቀሙ ወይም ቅንድባቸውን [ኩል በመጠቀም] የሚያስረዝሙ ሴቶች በአምላክ ላይ ኃጢአት ይሠራሉ።” በተጨማሪም “ለጌጣጌጥነት” የሚጠቀሙበትን ወርቅና ብር “የመማረኪያ መሣሪያ” በማለት ገልጾታል።

በዛሬው ጊዜም ሴቶች ማጋጌጫ መጠቀማቸውን አጥብቀው የሚቃወሙ አሉ። እንዲያውም አንዳንድ ሃይማኖቶች አባሎቻቸውን ጌጣጌጦች እንዳይጠቀሙ፣ እንዳይኳኳሉ ወይም ደማቅ ቀለም ያለው ልብስ እንዳይለብሱ ይከለክላሉ። አንዲት ክርስቲያን ሴት ውበቷን መደበቅ ይኖርባታል? ወይስ ራሷን ማስዋብ ትችላለች?

የአምላክ አመለካከት

መጽሐፍ ቅዱስ ስለ ጌጣጌጥና ስለ መኳኳያ አጠቃቀም በዝርዝር ባይናገርም አምላክ እነዚህንም ሆነ ሌላ ዓይነት ማጋጌጫዎችን እንደማያወግዝ በቂ ማስረጃ አለ።

ለምሳሌ ያህል፣ አምላክ ኢየሩሳሌምን የባረከበትን መንገድ ሲገልጽ ከተማዋን በሴት መስሎ “በጌጣጌጥ አንቈጠቈጥሁሽ፤ . . . እጅግ ውብ ሆንሽ” ብሏታል። (ሕዝቅኤል 16:11-13) ይህ ማጋጌጫ ምሳሌያዊ ቢሆንም አንባርን፣ የአንገት ሀብልንና ጉትቻን ይጨምራል። መጽሐፍ ቅዱስ “የጠቢብ ሰው ዘለፋ” ለሚሰማው እንደ ወርቅ ጌጥ እንደሆነ ይገልጻል። (ምሳሌ 25:1, 12) ቅዱሳን ጽሑፎች ጌጣጌጦችን ከጥሩ ነገር ጋር የሚያነጻጽሯቸው መሆኑ ሴቶች ራሳቸውን ለማስዋብ በሚያምሩ ነገሮች መጠቀማቸውን አምላክ እንደማያወግዝ ያሳያል።

ክርስቲያን ሴቶች ራሳቸውን ያስውባሉ

አንዳንድ የመጽሐፍ ቅዱስ ክፍሎች ሴቶች ራሳቸውን ስለ ማስዋባቸው በቀጥታ ይናገራሉ። ሐዋርያው ጳውሎስ “ሴቶች በሚገባ ልብስ . . . ሰውነታቸውን ይሸልሙ” [የ1954 ትርጉም] በማለት ጽፏል። ሴቶች ራሳቸውን “በጨዋነትና ራስን በመግዛት” ሲያስውቡ አምላክን እንደሚፈሩ ያሳያሉ። (1 ጢሞቴዎስ 2:9, 10) ክርስቲያን ሴቶች ጨዋነት በሚንጸባረቅበት ሁኔታ ካጌጡ የአምላክን ትምህርቶችና ጉባኤውን ያስከብራሉ።

አንዳንድ ሰዎች ይኸው ጥቅስ ማጋጌጫን በተመለከተ ሴቶች “በሹሩባ ወይም በዕንቊ ወይም ዋጋቸው ውድ በሆኑ ልብሶች አይሽቀርቀሩ፤ ነገር ግን እግዚአብሔርን እናመልካለን የሚሉ ሴቶች ሊያደርጉ እንደሚገባ በመልካም ተግባር ይዋቡ” ይላል በማለት ተቃውሞ ያሰማሉ። ታዲያ ሴቶች ፀጉራቸውን መሠራት ወይም ጌጣጌጦች ማድረግ የለባቸውም ማለት ነው?

እንዲህ ማለት አይደለም፤ መጽሐፍ ቅዱስ ስለ ማጋጌጫዎች መልካም ነገር ይናገራል። ጳውሎስ መጋጌጥን ከመከልከል ይልቅ በዋነኝነት በክርስቲያናዊ ባሕርያትና በመልካም ተግባራት ራሳቸውን እንዲያስውቡ ሴቶችን አበረታቷል።

ይበልጥ ለውጥ የሚያመጣው አመለካከታችን ነው

ሐዋርያው ጳውሎስ እንዲህ ሲል ጽፏል:- “እርስ በርሳችን፣ አንዱ በሌላው ላይ ከመፍረድ እንቈጠብ፤ በዚህ ፈንታ ግን በወንድምህ መንገድ ላይ የማሰናከያ ድንጋይ ወይም ወጥመድ እንዳታስቀምጥ ቍርጥ ሐሳብ አድርግ።” (ሮሜ 14:13) ይህ ምክር ራሳችንን ለማስጌጥ በምንመርጣቸው ነገሮች ረገድ እንዴት ይሠራል?

በመጀመሪያ ደረጃ ጳውሎስ “እርስ በርሳችን፣ አንዱ በሌላው ላይ ከመፍረድ እንቈጠብ” ሲል ተናግሯል። ‘በወንድሞቻችን መንገድ ላይ የማሰናከያ ድንጋይ እንዳናስቀምጥ’ መጠንቀቅ አለብን። ተቀባይነት አላቸው የሚባሉት አለባበሶች ከአገር አገር እንዲሁም ከባሕል ባሕል ይለያያሉ። በአንድ ወቅት እንዲሁም በተወሰነ አካባቢ ተቀባይነት የነበረው አለባበስ በሌላ ወቅትና አካባቢ ተገቢ እንዳልሆነ ሊቆጠር ይችላል። በባሕላችን ተቀባይነት የሌለው አኗኗር የሚከተሉ ሰዎች እንደሚጠቀሙበት ተደርጎ የሚታየውን ማጋጌጫ በመከተል ሌሎችን ማደናቀፍም ሆነ ማስቀየም አይኖርብንም። ፈሪሃ አምላክ ያላቸው ሴቶች ራሳቸውን እንዲህ ብለው መጠየቃቸው ተገቢ ነው:- የምጠቀምበት ማጋጌጫ በማኅበረሰቡ ዘንድ እንዴት ይታያል? በአለባበሴ ምክንያት የጉባኤው አባላት ይሸማቀቃሉ፣ ግራ ይጋባሉ ወይም ያፍራሉ? አንዲት ክርስቲያን ሴት የመልበስም ሆነ የማጌጥ መብት ቢኖራትም፣ የምትጠቀምበት ማጋጌጫ ሌሎችን የሚያስከፋ ከሆነ መብቷን ትተወዋለች።—1 ቆሮንቶስ 10:23, 24

ከዚህም በተጨማሪ ለራስ ቁመና ከልክ በላይ ትኩረት መስጠት ጤናማ ያልሆነ አመለካከት ወደ ማዳበር ሊመራ ይችላል። በዛሬው ጊዜ በብዙ አገሮች አንዳንድ ሴቶች ጨዋነት በጎደለው መንገድ የሌሎችን ትኩረት ወደ ራሳቸው ለመሳብ በማጋጌጫዎች ይጠቀማሉ። ሆኖም ክርስቲያን ሴቶች ይህን በመሰለው ሁኔታ በማጋጌጫዎች አላግባብ ከመጠቀም ይልቅ ራሳቸውን በመግዛትና በግል ሕይወታቸው በሥነ ምግባር ንጹሖች በመሆን “የእግዚአብሔር ቃል በማንም ዘንድ እንዳይሰደብ” ለማድረግ ይጥራሉ።—ቲቶ 2:4, 5

ፈሪሃ አምላክ ያላቸው ሴቶች ማጋጌጫዎችን ለመጠቀም ቢፈልጉ እንኳ እውነተኛ ቁንጅናቸው “የውስጥ ሰውነት ውበት” መሆን እንዳለበትና ይህም በአስተሳሰባቸውም ሆነ በባሕርያቸው እንደሚንጸባረቅ ይገነዘባሉ። (1 ጴጥሮስ 3:3, 4) በአለባበሷ፣ በመኳኳያ አጠቃቀሟና በአጋጌጧ ረገድ አስተዋይነት የተንጸባረቀበት ምርጫ የምታደርግ ሴት በሌሎች ዘንድ አክብሮት ከማትረፏም በላይ ፈጣሪዋን ታስከብራለች።