በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

በፍርሃት መኖር

በፍርሃት መኖር

በፍርሃት መኖር

ሮክሳና * በቀን ውስጥ ለተወሰነ ሰዓት ተቀጥራ መሥራት እንደምትፈልግ ለባሏ መንገር ፈራች። በአንድ ወቅት እናቷን ለመጠየቅ የምትሄድበትን የአውቶቡስ መሳፈሪያ ገንዘብ እንዲሰጣት ስትጠይቀው ክፉኛ ስለደበደባት መታከም አስፈልጓት ነበር። ሁልጊዜ የምትኖረው በፍርሃት ነው።

ሮላንዶ ባለቤቱ ማታ ማታ ወደቤት ለመመለስ በሕዝብ መጓጓዣ እንድትጠቀም ፈቅዶ የነበረ ቢሆንም አሁን ግን በመኪና ይዟት መምጣት ጀምሯል። ይህን ያደረገው በአካባቢው በርካታ ወንጀሎች እየተፈጸሙ እንደሆነ ሰምቶ በሰላም የመመለሷ ጉዳይ አሳስቦት ነው።

አይዴ የምትሠራው መሃል ከተማ ነው። አንድ ቀን ወደ ቤት እየተመለሰች ሳለ ሳታስበው ዓመጽ ወደተቀሰቀሰበት የተቃውሞ ሰልፍ መሃል ገባች። በአሁኑ ጊዜ አይዴ በአካባቢዋ ሰላማዊ ሰልፈኞች ሲያልፉ በሰማች ቁጥር ጭንቅ ይላታል። “ፍርሃት ይሰማኛል። ምርጫ አጥቼ ነው እንጂ እዚህ መሥራት አልፈልግም ነበር” በማለት ተናግራለች።

ሮክሳና፣ ሮላንዶና አይዴ የፍርሃት ሰለባ ሆነዋል፤ እነዚህ ሰዎች ፍርሃት የሚሰማቸው ድንገተኛ አደጋ ሲከሰት ብቻ ሳይሆን ሁልጊዜ ነው። በፍርሃት መኖር ግድ የሆነባቸው ሰዎች ኃይላቸው እንደተሟጠጠ ሊሰማቸው ይችላል። ፍርሃት የሚፈልጉትን ነገር እንዳያደርጉ በማገድ ደስታቸውን ይገፍፋቸዋል። ፍርሃት የሰዎችን አስተሳሰብ ሊቆጣጠርና በሌሎች ነገሮች ላይ ማተኮር እንዲያቅታቸው ሊያደርግ ይችላል።

በፍርሃት መኖር ለከፍተኛ ውጥረት ይዳርጋል። ብዙውን ጊዜ የመንፈስ ጭንቀት ሊያስይዝና ጤና ሊያሳጣ ይችላል። “ውጥረት በሽታን የመከላከል አቅም ያሳጣል፤ እንዲሁም በርካታ ሕመሞች እንዲባባሱ ምክንያት ይሆናል” በማለት አንድ የጤና መጽሔት ዘግቧል። “ሰውነት፣ በተለይ ደግሞ ከችግሩ ጋር ተያያዥነት ያላቸው የአካል ክፍሎች ከጊዜ ወደ ጊዜ የመዳከም ምልክት ያሳያሉ። የደም ግፊት መጨመር፣ የልብ ሕመም፣ የኩላሊት በሽታ፣ የጨጓራና የአንጀት መታወክ፣ ቁስለት፣ ራስ ምታት፣ እንቅልፍ ማጣትና የመንፈስ ጭንቀት ሊይዝ ይችላል። ለረጅም ጊዜ የሚዘልቅ ውጥረት ድካም ያስከትላል።”

በዚህ ዘመን ሰዎች በፍርሃት መኖራቸው በጣም የተለመደ ነገር ነው። ሰዎች ያለምንም ፍርሃት ሲኖሩ የምናይበት ጊዜ ይመጣ ይሆን?

[የግርጌ ማስታወሻ]

^ አን.2 አንዳንዶቹ ስሞች ተቀይረዋል።