በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

ብዙዎች በፍርሃት የሚኖሩት ለምንድን ነው?

ብዙዎች በፍርሃት የሚኖሩት ለምንድን ነው?

ብዙዎች በፍርሃት የሚኖሩት ለምንድን ነው?

መላው የሰው ዘር በፍርሃት መንፈስ ተውጧል። ይህ መንፈስ በዓይን ሊታይ አይችልም፤ ይሁንና ሳይታወቅ ሁሉንም ሰው ሲያጠቃ ይስተዋላል። እንዲህ ያለውን ሁኔታ የፈጠረው ምንድን ነው? አንዳንድ ሰዎች ከቤታቸው ሲወጡ ፍርሃት የሚሰማቸው ለምንድን ነው? ብዙዎች የሥራ ቦታቸው ስጋት የሚፈጥርባቸው ለምንድን ነው? በርካታ ሰዎች የልጆቻቸው ደኅንነት የሚያሳስባቸው ለምንድን ነው? ሰዎች በገዛ ቤታቸው እንዲፈሩ የሚያደርጓቸው የትኞቹ አደጋዎች ናቸው?

ለፍርሃት መንስኤ የሚሆኑ በርካታ ምክንያቶች እንዳሉ የታወቀ ነው፤ ይሁንና ሰዎችን ሁልጊዜ ሊያስፈሯቸው የሚችሉ አራት አደገኛ ሁኔታዎችን እንመለከታለን። እነርሱም በከተሞች የሚፈጸም ዓመጽ፣ ጾታዊ ትንኮሳ፣ ተገድዶ መደፈርና ቤት ውስጥ የሚፈጸም ድብደባ ናቸው። እስቲ መጀመሪያ በከተሞች ስለሚፈጸም ዓመጽ እንመልከት። በአሁኑ ጊዜ ከዓለማችን ሕዝብ ግማሽ ያህሉ የሚኖረው በከተሞች በመሆኑ ስለዚህ ጉዳት ማንሳቱ ተገቢ ነው።

በከተሞች ውስጥ ያለው አደገኛ ሁኔታ

ድሮ ድሮ ከተሞች ይገነቡ የነበረው ለጥበቃ ተብሎ ሳይሆን አይቀርም፤ አሁን ግን ብዙ ሰዎች ከተሞችን የሚያዩአቸው የአደጋ ቀጠናዎች እንደሆኑ አድርገው ነው። በአንድ ወቅት እንደ ከለላ ይቆጠሩ የነበሩ ቦታዎች አሁን አስፈሪ ስፍራዎች ሆነዋል። በመሃል ከተሞች ውስጥ ያለው ጭንቅንቅ ለወሮበሎች ምቹ ሁኔታ ፈጥሮላቸዋል፤ ከዚህም በላይ ድህነት ባጠቃቸው፣ ጥቂት የመንገድ መብራት ባላቸውና የፖሊሶች ቁጥር አነስተኛ በሆነባቸው አንዳንድ ከተሞች ውስጥ መግባት በጣም አደገኛ ነው።

በርካታ ሰዎች ግድያ ይፈጸምባቸዋል፤ ስለዚህ ሰዎች የሚፈሩበት በቂ ምክንያት አላቸው። በዓለም ዙሪያ በየዓመቱ 1.6 ሚሊዮን ሰዎች በወንጀለኞች እንደሚገደሉ የዓለም ጤና ድርጅት ያወጣው ዘገባ ያሳያል። በአፍሪካ ከሚገኙት 100,000 ሰዎች መካከል በአማካይ 60.9 የሚሆኑት በሰው እጅ እንደሚገደሉ ይገመታል።

ሰላማዊ እንደሆኑ ይታሰቡ የነበሩ በርካታ ሰዎች፣ ቦታዎችና ድርጅቶች አሁን ለደኅንነት አስጊ ተደርገው ይታያሉ። ለምሳሌ ያህል ብዙ የመጫወቻ ስፍራዎች፣ ትምህርት ቤቶችና ሱቆች ከባድ ወንጀል ከሚፈጸምባቸው ቦታዎች ይፈረጃሉ። አንዳንድ ጊዜ ደግሞ ለሰዎች ደኅንነት መቆም የሚገባቸው የሃይማኖት መሪዎች፣ የማኅበራዊ ጉዳይ ሠራተኞችና አስተማሪዎች የተጣለባቸውን አደራ በልተው ከእነርሱ የማይጠበቅ አድራጎት ሲፈጽሙ ይታያሉ። ከእነዚህ ሰዎች መካከል አንዳንዶቹ በልጆች ላይ የሚፈጽሙት ግፍ ወላጆች ልጆቻቸውን ለሌሎች አደራ ሰጥተው መሄድ እንዲከብዳቸው አድርጓል። የፖሊሶች ሥራ ሰዎችን መጠበቅ እንደሆነ የታወቀ ነው፤ ይሁንና በአንዳንድ ከተሞች ውስጥ ያሉ ፖሊሶች ብልሹ የሆነ ምግባር ሲፈጽሙና ሥልጣናቸውን አላግባብ ሲጠቀሙ ማየት የተለመደ ነገር እየሆነ መጥቷል። “በጸጥታ” ኃይሎች ረገድ ያለውንም ሁኔታ ተመልከት፤ በአንዳንድ አገሮች በተቀሰቀሱ የእርስ በርስ ጦርነቶች ወቅት ሰዎች ዘመድ ወዳጆቻቸው በወታደሮች ተወስደው ደብዛቸው መጥፋቱ የማይሽር ጠባሳ ጥሎባቸዋል። በመሆኑም በብዙ የዓለማችን ክፍሎች ፖሊሶችና ወታደሮች የሰው ልጆች የሚሰማቸው ፍርሃት እንዲቀንስ አስተዋጽኦ ከማድረግ ይልቅ አባብሰውታል።

ሲትዝንስ ኦቭ ፊር—ኧርባን ቫየለንስ ኢን ላቲን አሜሪካ የተባለው መጽሐፍ እንዲህ ብሏል:- “በደቡብ አሜሪካ አገሮች ዋና ከተሞች ውስጥ ያሉ ነዋሪዎች በምድር ላይ አሉ የሚባሉ አንዳንድ አደገኛ ሁኔታዎች በሰፈኑባቸው ቦታዎች ውስጥ በፍርሃት ተሸማቅቀው ይኖራሉ። በዚህ በጣም ሰፊ በሆነ ክልል በየዓመቱ ወደ 140 ሺህ የሚጠጉ ሰዎች በሰው ይገደላሉ፤ እንዲሁም ከሦስት ነዋሪዎች አንዱ በቀጥታም ሆነ በተዘዋዋሪ የወንጀል ሰለባ ሆኗል።” በሌሎች የዓለም ክፍሎችም በየጊዜው ፖለቲካዊ ተቃውሞዎች የሚቀሰቀሱት በዋና ከተሞች ውስጥ ነው። እንዲህ ያሉት ተቃውሞዎች ተባብሰው ዓመጽ በሚነሳበት ጊዜ በርካታ ግለሰቦች አጋጣሚውን ተጠቅመው ሱቆችን ይዘርፋሉ። በዚህ ጊዜ በከተማ ውስጥ የሚሠሩ ነጋዴዎች በቁጣ ገንፍሎ በወጣው ሕዝብ እጅ ሊወድቁ ይችላሉ።

በብዙ አገሮች ውስጥ በሀብታሞችና በድሆች መካከል ያለው የኑሮ ልዩነት እጅግ በጣም እየሰፋ መምጣቱ ብዙዎች አምቀው የኖሩትን ብስጭት እንዲያወጡ ያደርጋቸዋል። መሠረታዊ ፍላጎታቸውን እንደተነፈጉ የሚሰማቸው ሰዎች በአካባቢያቸው የሚገኙትን ጥሩ ኑሮ ያላቸው ነዋሪዎች ይዘርፋሉ። በአንዳንድ ከተሞች ውስጥ እንዲህ ያለ ነገር እስካሁን ባይከሰትም፣ ሁኔታውን መቼ እንደሚፈነዳ ባይታወቅም እንኳ ሰዓቱን ጠብቆ መፈንዳቱ ከማይቀር ቦምብ ጋር ማመሳሰል ይቻላል።

የዘራፊዎችና የአብዮተኞች እንቅስቃሴ ከፈጠረው ስጋት በተጨማሪ በዓለም ላይ ፍርሃት እንዲነግሥ ያደረጉ ሌሎች ምክንያቶችም አሉ።

የጾታ ትንኮሳ የፈጠረው ፍርሃት

ፉጨት፣ ጸያፍ አነጋገርና ለወሲብ በመመኘት መመልከት በየዕለቱ በሚሊዮን የሚቆጠሩ ሴቶችን የሚያስደነግጡ ነገሮች ናቸው። ኤዥያ ዊክ የተባለ መጽሔት እንዲህ ይላል:- “ጥናቶች እንደሚያሳዩት ከአራት ጃፓናውያን ሴቶች መካከል አንዷ በአደባባይ ጾታዊ ጥቃት ተፈጽሞባታል፤ ከጥቃቶቹም መካከል 90 በመቶዎቹ የተከሰቱት በባቡር ውስጥ ነው። . . . ጥቃት ከደረሰባቸው ውስጥ በሆነ መንገድ የመከላከል እርምጃ የወሰዱት 2 በመቶዎቹ ብቻ ናቸው። ብዙዎቹ ጥቃት ፈጻሚዎቹን እንዳይቃወሙ ያደረጋቸው ዋነኛ ምክንያት ሰዎቹን መፍራታቸው እንደሆነ ተናግረዋል።”

በሕንድም በሴቶች ላይ የሚፈጸመው ጾታዊ ትንኮሳ በአስደንጋጭ ሁኔታ ጨምሯል። በዚያ አገር የምትገኝ ጋዜጠኛ “አንዲት ሴት ከቤቷ በምትወጣበት ጊዜ ሁሉ ትፈራለች። በረገጠችው ቦታ አሳፋሪ የሆኑ ንግግሮችና የብልግና ቃላት እየሰነዘሩ የሚሳለቁባት ሰዎች ያጋጥሟታል” በማለት ተናግራለች። በአንጻራዊ ሁኔታ ሰላማዊ የሆኑ መንገዶች እንዳሉት ነዋሪዎቹ ከሚናገሩለት አንድ የሕንድ ከተማ የሚከተለው ዘገባ ወጥቷል:- “[የዚህ ከተማ] ችግር ያለው መንገድ ላይ ሳይሆን ቢሮዎች ውስጥ ነው። . . . ጥናት ከተደረገባቸው ሴቶች ውስጥ 35 በመቶዎቹ በሥራ ቦታቸው ጾታዊ ትንኮሳ እንዳጋጠማቸው ተናግረዋል። . . . ሃምሳ ሁለት በመቶዎቹ በሥራ ቦታቸው ጾታዊ ትንኮሳ እንዳይፈጸምባቸው በመፍራት ከሴቶች ጋር [ብቻ] የሚያገናኟቸውን . . . ዝቅተኛ ክፍያ ያላቸውን ሥራዎች መሥራት እንደሚመርጡ ተናግረዋል።”

አስገድዶ የመድፈር ወንጀል የፈጠረው ፍርሃት

ሴቶች ክብራቸውን ከመገፈፍ የበለጠ የሚያስፈራቸው ሌላ ነገር አለ። አንዳንድ ጊዜ ጾታዊ ጥቃት ተገድዶ የመደፈር አደጋ እንዳለ የሚያመላክት ነው። ሴቶች ተገድዶ መደፈርን ከግድያ እንኳን ይበልጥ የሚፈሩት ወንጀል እንደሆነ ይታወቃል። አንዲት ሴት ተገድዶ መደፈር ያጋጥመኝ ይሆናል ብላ በምትፈራበት ቦታ ሳታስበው ልትገኝና የማታውቀውን ወይም ደግሞ የማታምነውን ሰው ታይ ይሆናል። ‘ምን ያደርግ ይሆን? ወዴት መሮጥ እችላለሁ? መጮህ ይኖርብኛል?’ በማለት በጭንቀት ሁኔታውን ለመገምገም ስትሞክር የልቧ ምት ይጨምራል። ሴቶች እንዲህ ያለው ክስተት በተደጋጋሚ የሚያጋጥማቸው ከሆነ ቀስ በቀስ ጤንነታቸው እየተቃወሰ ይሄዳል። ብዙዎች ይህን የመሰለ ፍርሃት ስላለባቸው በከተሞች አካባቢ መኖር ወይም ወደ ከተማ መሄድ አይፈልጉም።

ዘ ፊሜል ፊር የተባለው መጽሐፍ እንዲህ ይላል:- “ፍርሃት፣ ስጋትና ጭንቀት በከተሞች የሚኖሩ የበርካታ ሴቶች የዕለት ተዕለት ገጠመኞች ናቸው። ሴቶች ያለባቸው ተገድዶ የመደፈር ፍርሃት ሁልጊዜ ጥቃቱን ለመከላከል መዘጋጀት እንዲሁም ንቁና ጥንቁቅ መሆን እንዳለባቸው እንዲሰማቸው ያደርጋል፤ ይህ ስሜት ደግሞ በተለይ ማታ ላይ በቅርብ ርቀት ከኋላዋ የሚመጣ ሰው ሲኖር በጭንቀት እንድትወጠር ያደርጋታል። ሴቶች እንዲህ ካለው ስሜት ሙሉ በሙሉ ነጻ መሆን አይችሉም።”

በብዙ ሴቶች ላይ የዓመጽ ድርጊት ይፈጸምባቸዋል። የዓመጽ ፍርሃት ያለባቸው ግን ሁሉም ሴቶች ናቸው ለማለት ይቻላል። የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ያሳተመው ዘ ስቴት ኦቭ ዎርልድ ፖፑሌሽን 2000 የተባለ ጽሑፍ እንደሚከተለው ይላል:- “በመላው ዓለም ቢያንስ ከሦስት ሴቶች አንዷ ተደብድባለች፣ የጾታ ግንኙነት እንድትፈጽም ተገድዳለች ወይም በሌላ መንገድ ጥቃት ተፈጽሞባታል፤ በአብዛኛው እነዚህ ድርጊቶች የተፈጸሙባት በምታውቃቸው ሰዎች ነው።” የፍርሃት መንፈስ ከላይ ከተጠቀሱት ቦታዎች ሌላ በየት ይገኛል? ሰዎች በገዛ ቤታቸው ውስጥ ሆነው መፍራታቸው ምን ያህል ተስፋፍቷል?

ቤት ውስጥ የሚፈጸምን ጥቃት መፍራት

ሌላ ሰው ሳያውቅ ሚስቶችን እየደበደቡ መግዛት በዓለም ዙሪያ የሚፈጸም ከባድ ሕገወጥ ድርጊት ነው፤ ይህ ድርጊት በበርካታ አገሮች እንደ ወንጀል መቆጠር የጀመረው ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ነው። በሕንድ አገር የወጣ አንድ ዘገባ እንዳሳየው “ቢያንስ ቢያንስ 45 በመቶ የሚሆኑት ሕንዳውያን ሴቶች ባሎቻቸው በጥፊ ወይም በካልቾ መትተዋቸዋል አሊያም ደብድበዋቸዋል።” በትዳር ጓደኛ የሚፈጸም በደል ጤንነትን አደጋ ላይ የሚጥል ከባድ የዓለማችን ችግር ነው። የዩናይትድ ስቴትስ ፌደራል የምርመራ ቢሮ ከ15 እስከ 44 ባለው የዕድሜ ክልል ውስጥ የሚገኙ ሴቶችን አስመልክቶ ሲዘግብ የመኪና አደጋ ከሚደርስባቸው፣ በወንበዴዎች ጥቃት ከሚሰነዘርባቸውና ተገድደው ከሚደፈሩት ይልቅ በቤት ውስጥ በሚፈጸምባቸው ድብደባ የሚጎዱት እንደሚበልጡ ገልጿል። ስለዚህ በቤት ውስጥ የሚፈጸም ጥቃት በጥፊ እስከመመታታት ከሚያደርስ አልፎ አልፎ ከሚፈጠር አለመግባባት ይበልጥ አደገኛ ነው። ብዙ ሴቶች በቤታቸው ውስጥ ጉዳት እንዳይደርስባቸውና እንዳይሞቱ ይፈራሉ። በካናዳ የተደረገ ብሔራዊ ጥናት በቤት ውስጥ በሚፈጸምባቸው ጥቃት ከሚሰቃዩት ሦስት ሴቶች አንዷ አንዳንድ ጊዜ ለሕይወቷ እንደምትሰጋ ያሳያል። በዩናይትድ ስቴትስ የሚገኙ ሁለት ተመራማሪዎች “ቤት ለሴቶች እጅግ በጣም አደገኛ የሆነ እንዲሁም የጭካኔና የማሠቃየት ተግባር በተደጋጋሚ የሚፈጸምበት ቦታ ነው” የሚል ድምዳሜ ላይ ደርሰዋል።

በጣም በርካታ ሴቶች እንዲህ ካለው አደገኛ ሁኔታ ውስጥ እንዳይወጡ ጠፍሮ የያዛቸው ምንድን ነው? ብዙ ሰዎች ‘ለምን እርዳታ አይጠይቁም? ወይም ለምን ቤቱን ጥለው አይወጡም?’ የሚል ጥያቄ ያነሳሉ። በአብዛኛው የእነዚህ ጥያቄዎች መልስ ስለሚፈሩ ነው የሚል ይሆናል። በቤት ውስጥ የሚፈጸም ጥቃት ዋነኛ መገለጫው ፍርሃት ነው ተብሎ ይነገራል። መጥፎ የሆኑ ወንዶች ሚስቶቻቸውን ደብድበው ለሌላ ሰው እንዳይናገሩ ለማድረግ የሚጠቀሙበት ዓይነተኛው መንገድ እንደሚገድሏቸው ማስፈራራት ነው። ድብደባ የሚፈጸምባት ሚስት ደፍራ እርዳታ ብትጠይቅ እንኳን እንዳሰበችው ላታገኝ ትችላለች። ምክንያቱም ሰዎች፣ ሌላ ዓይነት ግፍ የሚጠሉትም ጭምር ባሎች በሚስቶቻቸው ላይ የሚፈጽሙትን በደል አቅልሎ የማየት፣ ችላ የማለት ወይም ተገቢ እንደሆነ አድርጎ የመመልከት ዝንባሌ አላቸው። በተጨማሪም ሚስቱን የሚበድል ባል ምናልባት በውጪ ሰዎች ዘንድ የሚወደድ ጠባይ ይኖረው ይሆናል። ብዙውን ጊዜ ጓደኞቹ ሚስቱን ይደበድባል ብለው ማመን ይከብዳቸዋል። በደል የሚፈጸምባቸው በርካታ ሚስቶች የሚያምናቸው ስለማይኖርና መሄጃ ስለሚያጡ ሁልጊዜ እንደፈሩ ከመኖር ውጪ ምንም አማራጭ እንደሌላቸው ይሰማቸዋል።

አንዳንድ ሚስቶች በሚደርስባቸው ድብደባ ምክንያት ቤታቸውን ለቀው ቢወጡ እንኳ ባሎቻቸው ይከታተሏቸዋል። በሰሜን አሜሪካ በሉዊዚያና ግዛት በሚገኙ ከአንድ ሺህ በሚበልጡ ሴቶች ላይ በቅርቡ የተደረገ ጥናት እንዳሳየው ከእነዚህ ሴቶች ውስጥ 15 በመቶ የሚሆኑት ባሎቻቸው ክትትል አድርገው ጥቃት እንደፈጸሙባቸው ሪፖርት አድርገዋል። ምን ያህል እንደሚፈሩ አስበው። አንድ ያስፈራራህ የነበረ ሰው በሄድክበት ቦታ ሁሉ አይጠፋም። ይደውልልሃል፣ ይከተልሃል፣ ይመለከትሃል እንዲሁም ከገባህበት እስክትወጣ ይጠብቅሃል። ምናልባትም አንዱን የቤት እንስሳህን ይገድልብሃል። ይህ ለማስፈራራት የሚደረግ ጥረት ነው!

እንዲህ ዓይነት ፍርሃት የለብህ ይሆናል። ይሁንና ፍርሃት በየዕለቱ በምታደርጋቸው ነገሮች ላይ ምን ያህል ተጽዕኖ ያደርግብሃል?

ፍርሃት በእንቅስቃሴህ ላይ ተጽዕኖ ያደርጋል?

ፍርሃት በነገሠበት ዓለም ውስጥ ስለምንኖር በየዕለቱ ከምናደርጋቸው ውሳኔዎች ምን ያህሎቹን ከፍርሃት ተነሳስተን እንደምንወስናቸው ላንገነዘብ እንችላለን። ፍርሃት በእንቅስቃሴህ ላይ ምን ያህል ተጽዕኖ አድርጓል?

የወንጀል ፍርሃት አንተን ወይም የቤተሰብህን አባላት አምሽታችሁ ወደ ቤት እንዳትገቡ አድርጓችኋል? ፍርሃት በሕዝብ መጓጓዣ እንዳትጠቀም አድርጎሃል? ራቅ ያለ ቦታ እየተመላለሱ መሥራት አደገኛ መሆኑ በሥራ ምርጫህ ላይ ተጽዕኖ አድርጎብሃል? ባልደረቦችህን ወይም ደግሞ በሥራ የምትገናኛቸውን ሰዎች መፍራትህ ሥራ እንድትቀይር አድርጎሃል? ፍርሃት ከማኅበራዊ ኑሮ ወይም ከመዝናኛ ጋር በተያያዘ ያደረገብህ ተጽዕኖ አለ? ሰክረው ወይም ተሰብስበው የሚረብሹ ሰዎችን መፍራትህ ወደ አንዳንድ ስፖርትና ሙዚቃ ማሳያ ቦታዎች ከመሄድ እንድትታቀብ አድርጎህ ይሆን? ፍርሃት በትምህርት ቤት በምታደርገው ነገር ላይ ተጽዕኖ አሳድሯል? በርካታ ወላጆች ልጆቻቸው ዱርዬ እንዳይሆኑ ያላቸው ፍርሃት በትምህርት ቤት ምርጫቸው ላይ ተጽዕኖ ያደርጋል፤ እንዲሁም ልጆቻቸው በእግር ወይም በሕዝብ መጓጓዣ ወደ ቤት መመለስ ሲችሉ ወላጆች በመኪና የሚመልሱበት ምክንያት ፍርሃት ነው።

በእርግጥም የሰው ልጅ የሚኖረው ፍርሃት በነገሠበት ዓለም ውስጥ ነው። የዓመጽ ፍርሃት በአብዛኛው የሰው ልጅ ታሪክ ወቅት የነበረ ችግር ነው። ይህ ሁኔታ ይለወጣል ብለን መጠበቅ እንችላለን? ከፍርሃት ነጻ መውጣት እንዲያው ሕልም ብቻ ነው? ወይስ ማንም ሰው መጥፎ ነገር ይደርስብኛል ብሎ የማይፈራበት ጊዜ እንደሚመጣ መጠበቅ የምንችልበት አጥጋቢ ምክንያት አለ?