ቻት ሩም ካለው አደጋ መጠበቅ የምችለው እንዴት ነው?
የወጣቶች ጥያቄ . . .
ቻት ሩም ካለው አደጋ መጠበቅ የምችለው እንዴት ነው?
“በቀን በቀን ለሦስት ወይም ለአራት ሰዓት ያህል በቻት ሩም ከሰዎች ጋር እነጋገራለሁ። አንዳንድ ጊዜ ደግሞ ያለማቋረጥ ለስድስትና ለሰባት ሰዓት ያህል አወራለሁ።”—ሆሴ *
ከማናውቃቸው ሰዎች ጋር በምንገናኝበት በማንኛውም አካባቢ አደጋ ሊያጋጥመን እንደሚችለው ሁሉ በቻት ሩምም (በኢንተርኔት አማካኝነት መልእክት በመጻጻፍ በቀጥታ የሚነጋገሩበት ፕሮግራም ነው) አደጋ ሊያጋጥመን ስለሚችል ጥንቃቄ ማድረግ ያስፈልገናል። ለምሳሌ ያህል አንድ ትልቅ ከተማ ብትጎበኝ አደገኛ አካባቢዎችን በማወቅና ወደ እነዚህ ቦታዎች ከመሄድ በመታቀብ ሕይወትህን ለአደጋ የሚያጋልጡ ነገሮችን ለመቀነስ ትጥራለህ።
ቻት ሩም ውስጥ በምትገባበትም ጊዜ ሁኔታው ተመሳሳይ ነው። በጥቅምት 2005 ንቁ! መጽሔት ላይ ቻት ሩሞች የሚያስከትሏቸው ሁለት አደጋዎች ተብራርተው ነበር፤ በዚያ እትም ላይ ከወሲብ ጥቃት ፈጻሚዎች ጋር የመገናኘት አጋጣሚ እንዳለና ሐቅ ያልሆነ ነገር ለመናገር ልትፈተን እንደምትችል ተገልጿል። ሊታሰብባቸው የሚገቡ ሌሎች አደጋዎችም አሉ። በመጀመሪያ ግን ቻት ሩሞች በምን መልኩ እንደሚዘጋጁ እንመልከት።
የሚዘጋጁት በዓላማ ነው
ብዙውን ጊዜ ቻት ሩሞች ተመሳሳይ ስሜት ያላቸውን ሰዎች ሊማርክ በሚችል መንገድ በርዕስ በርዕሱ ይዘጋጃሉ። አንዳንዶቹ የተዘጋጁት አንድ ዓይነት ስፖርት ወይም የትርፍ ጊዜ ማሳለፊያ አፍቃሪ ለሆኑ ሰዎች ታስበው ይሆናል። ሌሎቹ ደግሞ አንድን የቴሌቪዥን ፕሮግራም በተመለከተ ውይይት ለማድረግ የተከፈቱ ሊሆኑ ይችላሉ። የአንድ ሃይማኖት አባላት የሆኑ ሰዎች ሐሳብ ለሐሳብ እንዲለዋወጡ የተዘጋጁ ቻት ሩሞችም አሉ።
የይሖዋ ምሥክር ከሆንክ ለማወቅ ካለህ ጉጉት የተነሳ በዓለም ዙሪያ ከሚገኙ ወጣት የሆኑ የእምነት አጋሮችህ መካከል ጓደኞች ለማግኘት ይረዳል የሚባልለትን ቻት ሩም ትቃኝ ይሆናል። እምነትህን ከሚጋሩ ወጣቶች መካከል ጓደኛ ለማግኘት መሞከርህ መልካም ነገር ነው። ይሁንና እንዲህ ያሉት ቻት ሩሞች በክርስቲያኖች ላይ ስውር የሆነ አደጋ ያስከትላሉ። አደጋው ምንድን ነው?
አቋምህን ሊያበላሽብህ ይችላል
ታይለር የተባለ አንድ ወጣት እንዲህ ብሏል:- “ሁሉም የይሖዋ ምሥክር ናቸው ብዬ ካሰብኳቸው ሰዎች ጋር በቻት ሩም እነጋገር ነበር። ከጥቂት ጊዜ በኋላ አንዳንዶቹ እምነታችንን ማጣጣል ጀመሩ። ብዙም ሳይቆይ ሰዎቹ ከሃዲዎች እንደሆኑ ግልጽ ሆነልኝ።” እነዚህ ሰዎች የይሖዋ ምሥክር መስለው በመቅረብ የሌሎች ክርስቲያኖችን አቋም ሆነ ብለው ለመሸርሸር የሚሞክሩ ናቸው።
የአምላክ ልጅ ኢየሱስ ክርስቶስ፣ ተከታዮቹ የነበሩ አንዳንድ ሰዎች ጓደኞቻቸውን እንደሚቃወሙ አስጠንቅቆ ነበር። (ማቴዎስ 24:48-51፤ የሐዋርያት ሥራ 20:29, 30) ሐዋርያው ጳውሎስ በዘመኑ የነበሩትን እንዲህ ያሉ ሰዎች ሐሰተኛ ወንድሞች ብሎ ከመጥራቱም በላይ የክርስቲያን ጉባኤ አባላትን ለመጉዳት ‘ሾልከው እንደሚገቡ’ ተናግሯል። (ገላትያ 2:4) የመጽሐፍ ቅዱስ ጸሐፊው ይሁዳ እነዚህ ከሃዲዎች ‘የአምላክን ጸጋ በርኵሰት የመለወጥ’ ዓላማ ይዘው ‘ሾልከው እንደሚገቡ’ ተናግሯል። (ይሁዳ 4) እንዲሁም “ከውኃ በታች እንደ ተሰወሩ ዓለቶች ናቸው” ብሏቸዋል።—ይሁዳ 12 NW
ጳውሎስና ይሁዳ ከሃዲዎች በአብዛኛው የሚጠቀሙበትን የተንኮል ዘዴ ለይተው እንደጠቀሱ ልብ በል። እነዚህ የመጽሐፍ ቅዱስ ጸሐፊዎች ከሃዲዎች ‘ሾልከው የሚገቡት’ የክርስቲያን ጉባኤ አባላትን ሥነ ምግባር የማጉደፍ ዓላማ ይዘው እንደሆነ አስተውለው ነበር። በዛሬው ጊዜ እንዲህ ያሉት ምግባረ ብልሹ ሰዎች መሰሪ ደባቸውን ከግብ ለማድረስ ቻት ሩምን መሣሪያ አድርገው ይጠቀሙበታል። እነዚህ ሐሰተኛ ክርስቲያኖች ልክ ከውኃ በታች እንደተሰወረ ዓለት ወጣት የይሖዋ ምሥክሮችን ለማታለል እውነተኛ ዓላማቸውን ደብቀው አሳቢ መስለው ይቀርባሉ። ይሁንና ግባቸው ምንም ባልጠረጠሩ ክርስቲያኖች ምሳሌያዊ የእምነት መርከብ ላይ አደጋ ማድረስ ነው።—1 ጢሞቴዎስ 1:19, 20
ይህ መጽሔትና የይሖዋ ምሥክሮች ያሳተሟቸው ሌሎች ጽሑፎች ይህንን አደጋ በተመለከተ ተደጋጋሚ ማስጠንቀቂያ ሲሰጡ ቆይተዋል። * ስለዚህ ለይሖዋ ምሥክሮች ተብሎ በተዘጋጀ ቻት ሩም አማካኝነት የምታገኘው ማንኛውም ሰው ከሃዲ ባይሆን እንኳን በመጽሐፍ ቅዱስ ላይ የተመሠረተውን ማስጠንቀቂያ ችላ ያለ ነው። የተሰጣቸውን በመጽሐፍ ቅዱስ ላይ የተመሠረተ መመሪያ የሚያቃልሉ ጓደኞች እንዲኖሩህ በእርግጥ ትፈልጋለህ?—ምሳሌ 3:5, 6፤ 15:5
ከቤተሰብህ ሊያገልህ ይችላል
ቻት ሩም ስትጠቀም ከግምት ውስጥ ልታስገባው የሚያስፈልግህ ሌላው ነገር ደግሞ የሚወስድብህ
ጊዜ ነው። በዚህ ርዕስ መጀመሪያ ላይ የተጠቀሰው ሆሴ “አንዳንድ ጊዜ በቻት ሩም ውይይት ከመጠመዴ የተነሳ ምግብ መብላት እንኳ እረሳለሁ” ብሏል።የሆሴን ያህል በቻት ሩም አልተጠመድህ ይሆናል። ይሁን እንጂ በዚህ መንገድ ለመነጋገር ለሌሎች እንቅስቃሴዎችህ ታውል የነበረውን ጊዜ መቀነስ ያስፈልግሃል። በዋነኝነት የሚነኩት ደግሞ የቤት ሥራህ ወይም በቤት ውስጥ የምታከናውናቸው ነገሮች ላይሆኑ ይችላሉ። ብዙውን ጊዜ በቅድሚያ የምትተወው ነገር ከቤተሰብህ ጋር የምታደርገውን የሐሳብ ግንኙነት ይሆናል። በስፔን የሚኖረው አድሪያን እንዲህ ብሏል:- “ምግብ መብላቴን እንደጨረስኩ ወዲያው እነሳና ቻት ሩም ውስጥ ገብቼ መነጋገር እጀምራለሁ። ቻት ሩም ከቤተሰቦቼ ጋር መነጋገሬን እስከማቆም ድረስ ሱስ ሆኖብኝ ነበር ለማለት ይቻላል።”
በቻት ሩም በመነጋገር ረጅም ጊዜ ማጥፋት በጣም ከሚያስፈልጉህ ሰዎች ራስህን የማግለል ያህል ነው። መጽሐፍ ቅዱስ “መለየት የሚወድድ ምኞቱን ይከተላል፣ መልካሙንም ጥበብ ሁሉ ይቃወማል” በማለት ተገቢ ምክር ይሰጣል። (ምሳሌ 18:1 የ1954 ትርጉም) በብዙ ቻት ሩሞች የምታገኛቸው የማታውቃቸው ሰዎች ጠቃሚ በሆነው የመጽሐፍ ቅዱስ ምክር እንድትመራ ያበረታቱሃል ማለት ዘበት ነው። እንዲያውም የራስ ወዳድነት ፍላጎትህን እንድታሳድድና ክርስቲያናዊ የሥነ ምግባር የአቋም ደረጃዎችን እንድትጥስ ሊያበረታቱህ ይችላሉ።
ቻት ሩምን እንድትወደው ካደረጉህ ነገሮች አንዱ ከቤተሰብህ ጋር ከመነጋገር ይልቅ በኢንተርኔት መነጋገሩ ቀላል መስሎ ስለተሰማህ ይሆናል። የቻት ሩም ጓደኞችህ ስለ አንዳንድ ጉዳዮች ያለህን አመለካከት ለማወቅ ሊጓጉና ስሜታቸውን በግልጽ ሊናገሩ ይችላሉ። በሌላ በኩል ደግሞ የቤተሰብህ አባላት የአንተን ጉዳይ የሚሰሙበት ጊዜ ሊያጡና ስሜታቸውን በግልጽ መናገር ሊከብዳቸው ይችላል።
ይሁንና እንዲህ እያልክ ራስህን ጠይቅ:- ‘የቻት ሩም ጓደኞቼ እውነተኛ ማንነቴን ያውቃሉ? የእኔ ዘላቂ ደኅንነት በእርግጥ ያሳስባቸዋል?’ ከዚህ በተለየ መንገድ የቤተሰብህ አባላት የአንተ ስሜታዊና መንፈሳዊ ጤንነት ያሳስባቸዋል። ወላጆችህ በመጽሐፍ ቅዱስ የአቋም ደረጃዎች ለመመራት የሚጥሩ ከሆነ ከአንተ ጋር የሐሳብ ግንኙነት የማድረግ ልባዊ ፍላጎት ይኖራቸዋል። (ኤፌሶን 6:4) ሐሳብህንና ስሜትህን በአክብሮት የምትገልጽላቸው ከሆነ ፈጽሞ ያልጠበቅከውን የደግነት መልስ ይሰጡህ ይሆናል።—ሉቃስ 11:11-13
ከአደጋ ተጠበቅ
ለምሳሌ ያህል ትምህርት ቤት የሚሰጥህን የቤት ሥራ ለማከናወን የግድ ቻት ሩም መጠቀም ያስፈልግህ ይሆናል። * እንዲህ ከሆነ ከዚህ ቀጥሎ የተጠቀሱትን ቀለል ያሉ ቅድመ ጥንቃቄዎች በማድረግ ቻት ሩም ከሚያስከትለው ወጥመድ መጠበቅ ትችላለህ።
በመጀመሪያ፣ በራስህ ክፍል ውስጥ የሚገኝ ኢንተርኔት የተገጠመለት ኮምፒውተር ከመጠቀም ታቀብ። ራስህ ክፍል ውስጥ በሚገኝ ኢንተርኔት መጠቀም በማታውቀው ከተማ ውስጥ በጨለማ መንገድ ላይ ብቻህን የመጓዝ ያህል ነው፤ እንዲህ ማድረግ ደግሞ ራስን ለችግር ማጋለጥ ነው። ስለዚህ እየተጠቀምህ ያለውን ነገር በቀላሉ ማየት እንዲችሉ ኮምፒውተርህን ሁሉም የቤተሰብ አባላት በሚገቡበት ክፍል ውስጥ አስቀምጠው።
ሁለተኛ፣ የምትጠቀምበትን የኢንተርኔት ድረ ገጽ ለወላጆችህ በማሳየትና በቻት ሩም መነጋገር የፈለግክበትን ምክንያት በመግለጽ ከእነርሱ ጋር ጥሩ የሐሳብ ግንኙነት እንዲኖርህ አድርግ። እንዲሁም ኮምፒውተር የምትጠቀምበትን ሰዓት ርዝመት ወስንና ያወጣኸውን ፕሮግራም በጥብቅ ተከተል።
ሦስተኛ፣ በኢንተርኔት የሚላክልህን መልእክት በማጣራት ፆታዊ ጥቃት እንዳይደርስብህ ሊረዱህ የሚችሉ የኮምፒውተር ፕሮግራሞችን ኮምፒውተርህ ውስጥ አስገባ። በኢንተርኔት እየተጠቀምህ ሳለህ የፆታ ጥያቄ ከቀረበልህ ወዲያውኑ ለወላጆችህ ወይም ለአስተማሪህ አሳውቅ። በአንዳንድ አገሮች፣ አዋቂዎች ለአካለ መጠን አለመድረስህን እያወቁ የፆታ ስሜትን የሚቀሰቅስ መልእክት ወይም ወሲባዊ ምስል የሚልኩልህ ከሆነ ሕገወጥ ድርጊት እንደፈጸሙ ይቆጠራል። እንዲህ የሚያደርጉ ሰዎች ለፖሊስ መከሰስ አለባቸው።
በተጨማሪም በቻት ሩም ለተዋወቅከው ሰው ስምህን፣ አድራሻህን፣ የትምህርት ቤትህን ስምና ስልክ ቁጥርህን አትስጥ። እንዲሁም ፊት ለፊት ለመገናኘት የሚያቀርብልህን ግብዣ ፈጽሞ አትቀበል!
ጠቢቡ ንጉሥ ሰሎሞን የተናገራቸው የሚከተሉት ቃላት ከተጻፉ በሺህ የሚቆጠሩ ዓመታት ያለፉ ቢሆንም ቻት ሩም የሚያስከትለውን አደጋ ጥሩ አድርገው ይገልጻሉ:- “አስተዋይ ሰው አደጋ ሲያይ መጠጊያ ይሻል፤ ብስለት የጐደለው ግን በዚያው ይቀጥላል፤ መከራም ያገኘዋል።”—ምሳሌ 22:3
[የግርጌ ማስታወሻዎች]
^ አን.3 አንዳንዶቹ ስሞች ተቀይረዋል።
^ አን.13 የጥር 2005 ንቁ! መጽሔት ከገጽ 18-21ን ተመልከት።
^ አን.21 የጥር 22, 2000 (እንግሊዝኛ) ንቁ! ገጽ 20ን ተመልከት።
[በገጽ 16 ላይ የሚገኝ ሥዕል]
የምትጠቀምበትን የኢንተርኔት ድረ ገጽ ለወላጆችህ ማሳየቱ ጥበብ ነው