በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

ከዓለም አካባቢ

ከዓለም አካባቢ

ከዓለም አካባቢ

የቪታሚን ኪኒኖችና ካንሰር

በ170,000 ሰዎች ላይ የተካሄዱ የ14 ጥናቶች ውጤት፣ የቪታሚን ኪኒኖች የጉሮሮ፣ የሆድ፣ የጉበት፣ የአንጀትና የጣፊያ ካንሰርን ሊከላከሉ እንደማይችሉ ጠቁሟል። ዶይትቸስ ኤርተስተብላት የተባለው የሕክምና መጽሔት እንዳለው ቤታ ካሮቲን የሚባሉት ኪኒኖች እንዲሁም ቪታሚን ኤ፣ ሲ እና ኢ ምንም ዓይነት ጠቃሚ ውጤት የማያስገኙ ከመሆናቸውም በላይ በካንሰር የመያዝ አጋጣሚን በመጠኑ ሊያሳድጉ ይችላሉ። በዩናይትድ ኪንግደም የካንሰር ምርምር ተቋም ባልደረባ የሆኑት ዶክተር ሪቻርድ ሱሊቫን እንዲህ ብለዋል:- “የሆድ ዕቃ ካንሰርን ለመከላከል የሚረዳ ምንም ዓይነት አቋራጭ መንገድ የለም። በሽታውን ለመከላከል ቪታሚኖችን የምትወስዱ ከሆነ ገንዘባችሁን እያባከናችሁ ነው። በካንሰር የመያዝ አጋጣሚን ለመቀነስ የሚያስችለው ከሁሉ የተሻለው መንገድ ተመጣጣኝ ምግብ መመገብና ከማጨስ መቆጠብ ነው።”

የጀርሞች መኖር ያስጨንቃችኋል?

“ከቤት ውስጥ ጀርሞችን ሙሉ በሙሉ አጠፋለሁ ብሎ ማሰብ የማይመስል ነገር ከመሆኑም ሌላ እንዲያው ከንቱ ልፋት ነው” ሲል ዘ ኒው ዮርክ ታይምስ ላይ የወጣ አንድ ርዕስ ገልጿል። “አብረዋችሁ የሚኖሩ በጣም ያረጁ ወይም በጠና የታመሙ ሰዎች አሊያም አራስ ሕፃናት (ከ6 ወር በታች) ከሌሉ በስተቀር ምግብ የምትሠሩበት አካባቢ፣ የበር እጀታ ወይም ማንኪያ ላይ የሚገኙ በጥቂት መቶዎች የሚቆጠሩ ባክቴሪያዎች” በጤንነታችሁ ላይ “የሚያስከትሉት ጉዳት የለም።” እርግጥ፣ ቶሎ የሚበላሽ ምግብ ለረጅም ሰዓት ከማቀዝቀዣ ውጪ ከተቀመጠ በባክቴሪያ ሊበከልና የምግብ መመረዝ ሊያስከትል ይችላል። ይህ እንዳይሆን እንዲህ ዓይነት ምግቦችን ማቀዝቀዣ ውስጥ ማስቀመጥ ይኖርባችኋል። ከዚህ በተጨማሪ ራሳችሁን ከባክቴሪያ ለመከላከል ፀረ ባክቴሪያ ምርቶችን መጠቀሙ አስፈላጊ አይደለም። “በቀን ውስጥ የተወሰነ ጊዜ እጃችሁን በሳሙናና በውኃ ከታጠባችሁ በቂ ነው” በማለት ጽሑፉ ይገልጻል።

እምነት እያጡ ነው

“አብዛኞቹ ስፔናውያን በሕይወታቸው ውስጥ ከፍተኛ ተጽዕኖ በሚያሳድሩት በአብዛኞቹ ተቋሞች ላይ ያን ያህል እምነት የላቸውም” ሲል በስፔን የሚታተመው ኤል ፓኢስ የተባለው ጋዜጣ ዘግቧል። የማኅበራዊ ጉዳይ ምርምር ማዕከል እንዳለው ቃለ ምልልስ ከተደረገላቸው 2,500 ሰዎች መካከል ከግማሽ የሚበልጡት በመንግሥት ላይ፣ 56.2 በመቶ የሚሆኑት በባንክ ተቋማት ላይ እንዲሁም 57.7 በመቶ የሚሆኑት በንግድ ማኅበራት ላይ እምነት እንደሌላቸው ገልጸዋል። ከአጠቃላዩ ሕዝብ ውስጥ 75 በመቶ የሚሆኑት ካቶሊኮች እንደሆኑ በሚናገሩባት በዚች አገር፣ ከ61 በመቶ በላይ የሚሆኑት ሰዎች “በካቶሊክ ቤተ ክርስቲያን ላይ ያን ያህል እምነት እንደሌላቸው” ገልጸዋል። ዲያሪዮ 16 የተባለ ጋዜጣ ርዕሰ አንቀጽ በዚህ ጉዳይ ላይ ሐሳብ ሲሰጥ “አብዛኞቹ ስፔናውያን ካቶሊኮች እንደሆኑ በእርግጠኝነት ቢያምኑም ከመካከላቸው ብዙዎቹ ሃይማኖቱን በቁም ነገር አይዙትም ወይም ትምህርቶቹን አይቀበሉም” ብሏል።

ማንበብ የማስታወስ ችሎታን ያሳድጋል

የማስታወስ ችሎታችሁን ማሻሻል የምትችሉት እንዴት ነው? የብራዚሉ ፎልያ ኦንላይን የተባለ ጋዜጣ “ተአምር እንዲፈጠር አትጠብቁ” ይላል። “ምሥጢሩ ያለው አእምሯችሁን ማሠራቱ ላይ ነው።” አእምሯችሁን ለማሠራት የሚያገለግለው ከሁሉ የተሻለው ዘዴ ማንበብ ነው። እንዴት? የነርቭ ሐኪም የሆኑት ኢቫን ኢስኪርዶ እንዲህ ይላሉ:- “አንድ ሰው ‘ዛፍ’ የሚለውን ቃል አንብቦ እንደጨረሰ በሕይወት ዘመኑ የሚያውቃቸው የዛፍ ዓይነቶች በሙሉ የሴኮንድ አንድ መቶኛ በሚሆን ጊዜ ውስጥ በአእምሮው ውልብ ይላሉ።” ኢስኪርዶ እንዳሉት “ይህ ሁሉ የሚሆነው ምንም ሳናውቀው ነው።” እንዲህ ዓይነቱ የአእምሮ ስፖርት አንጎላችን እንደ ኦልዛይመርስ ለመሳሰሉ የመርሳት በሽታዎች እንዳይጋለጥ ያደርገዋል የሚል እምነት አላቸው። በብራዚል፣ ሳኦ ፓውሎ በሚገኘው የማስታወስ ችግር የምርምር ማዕከል ባልደረባ የሆኑት የነርቭ ሐኪሙ ቫግነር ጋታስ “የማስታወስ ችሎታችንን ይበልጥ በተጠቀምንበት መጠን በዚያው ልክ ከጉዳት እንጠብቀዋለን” ብለዋል።

በሞባይል መልእክት መላላክ እየተስፋፋ ነው

“በዓለም ዙሪያ በየዓመቱ ከ360 ቢሊዮን በላይ የሚሆኑ መልእክቶች በሞባይል ይላካሉ” ሲል ኢንተርናሽናል ሄራልድ ትሬቢውን ዘግቧል። “ይህም በየቀኑ አንድ ቢሊዮን ገደማ አጫጭር መልእክት መሆኑ ነው።” የአጭር መልእክት አገልግሎት ወይም የኤስ ኤም ኤስ ጠቀሜታ እያደገ መጥቷል። ቁጥራቸው እያደገ የመጣ ኩባንያዎች ሊገዙን ይችላሉ የሚሏቸው ሰዎች ሞባይል ስልክ ላይ የጽሑፍ መልእክት በመላክ ሸቀጦቻቸውን ያስተዋውቃሉ። ለምሳሌ ያህል፣ በአሁኑ ጊዜ ሰዎች የሊቀ ጳጳሱ ጸሎቶች ሞባይል ስልካቸው ላይ እንዲላኩላቸው ከፍለው መጠየቅ ይችላሉ። የኔዘርላንድ ፖሊስ የተሰረቁ ሞባይል ስልኮች ላይ አጭር የጽሑፍ መልእክት በመላክ ስልኩን ለመግዛት ለሚያስቡ ሰዎች የተሰረቀ ዕቃ መሆኑን ማስጠንቀቂያ ይሰጣል። በሌላ በኩል ደግሞ አንድ ወንድ ሚስቱን “ፈትቼሻለሁ” ብሎ ሦስት ጊዜ በይፋ ካሳወቀ ሊፈታት እንደሚችል ሃይማኖታዊ ሕጉ በሚፈቅድባቸው በአንዳንድ አገሮች፣ ሞባይል ስልክ ላይ በሚላክ አጭር መልእክት አማካኝነት መፋታት እንደሚቻል በሕግ ተፈቅዷል።

በኔዘርላንድ ያለው የኢንተርኔት አጠቃቀም

“በ11 እና 12 ዓመት የዕድሜ ክልል ውስጥ ከሚገኙ አምስት ልጆች መካከል አንዱ በኢንተርኔት መልእክት እየተለዋወጠ ሳለ ከማያውቀው ሰው የብልግና መልእክት ደርሶታል” ሲል ኦልኸማን ደኽበልት በተባለው የደች ጋዜጣ ላይ የወጣ አንድ ጥናት ገልጿል። ለ660 ወላጆችና ዕድሜያቸው ከ8 እስከ 12 ዓመት ለሆነ 220 ልጆች በተላከው መጠይቅ መሠረት የኢንተርኔት ተጠቃሚ ከሆኑት ልጆች ውስጥ ከግማሽ በላይ የሚሆኑት አልፎ አልፎ “ደስ የማይል ነገር” ያጋጠማቸው ሲሆን ከዚህም ውስጥ “የሚያናድድ መልእክት (የማይፈለግ ኢ ሜይል)” ወይም እርቃንን የሚያሳዩ ምስሎች አሊያም ሌላ ዓይነት ተገቢ ያልሆነ መረጃ ይገኙበታል። አብዛኞቹ ልጆች ያጋጠማቸውን ነገር ለወላጆቻቸው ተናግረዋል። ከዚህ በተጨማሪ ከ10 ወላጆች መካከል 8 የሚሆኑት ልጆቻቸው ኢንተርኔት መጠቀማቸው የሚያስከትልባቸው ጉዳት እንደሚያሳስባቸው፣ ግማሽ ገደማ የሚሆኑት ልጆቻቸው ኢንተርኔት ሲጠቀሙ በቅርብ የመከታተል ሐሳብ እንዳላቸው፣ 60 በመቶ የሚሆኑት ወላጆች ደግሞ ልጆቻቸውን ለመቆጣጠር እንዲያመቻቸው ኮምፒውተሩን ሳሎን ቤት እንደሚያደርጉት እንዲሁም ልጆች በኢንተርኔት ጨዋታዎች በመጫወት፣ መልእክት በመላክና ሐሳብ በመለዋወጥ በቀን በአማካይ አንድ ሰዓት ገደማ እንደሚያሳልፉ ጥናቱ ገልጿል።

አስበልጠው የሚያዩት ምክር

“ከትላልቅ ኩባንያዎች ዳይሬክተሮች ውስጥ ሁለት ሦስተኛ የሚሆኑት ከሥራ ጋር የተያያዘ ከባድ ችግር በሚያጋጥማቸው ጊዜ አንድ የቦርድ አባል ወይም የሥራ ባልደረባቸው ከሚሰጣቸው ምክር ይልቅ ሚስቶቻቸው የሚነግሯቸውን መቀበል እንደሚመርጡ” የለንደኑ ዘ ታይምስ ገልጿል። ጥናቱን ያካሄደው የምክር አገልግሎት ሰጪ ድርጅት ባለቤት የሆኑት ቦብ አርነልድ፣ የንግድ ድርጅት ኃላፊዎች የሚፈልጉት አማካሪዎቻቸው ችሎታ ያላቸው እንዲሆኑ ብቻ ሳይሆን እምነት የሚጣልባቸው ሆነው እንዲገኙም ነው ብለዋል። “የቦርድ አባላቱ አማካሪዎች በራሳቸው መወሰን የሚችሉ፣ ተጨባጭ ነገር ይዘው የሚናገሩና ልምድ ያላቸው መሆናቸው በጣም አስፈላጊ ነገር ነው” ሲሉ ገልጸዋል፤ ሆኖም ከሁሉም በላይ አስፈላጊ የሆነው እምነት የሚጣልበት ሰው ማግኘት ስለሆነ ሚስቶች ከማንም በላይ ተመራጭ ናቸው።

የቼክ አገልግሎት በቅርቡ ያከትማል

“በአንድ ትውልድ ጊዜ ውስጥ ቼኮች ከአገልግሎት ውጪ የሚሆኑ ይመስላል” ሲል ዩ ኤስ ኒውስ ኤንድ ወርልድ ሪፖርት ተናግሯል። “በብድር ካርድ ግዢ መፈጸም፣ በቀጥታ ከባንክ ሒሳብ ላይ መክፈል እና በኮምፒውተር አማካኝነት የባንክ አገልግሎት መጠቀምን የመሳሰሉ ርካሽና ፈጣን የሆኑ አማራጭ የክፍያ ዘዴዎች” ከተጀመሩ ወዲህ በቼክ መክፈል በጣም ቀንሷል። ለዚህ አስተዋጽኦ ያደረጉት ሌሎች ነገሮች ደንበኞች ለገዙት ዕቃ በቀጥታ ከባንክ ሒሳባቸው ላይ አበዳሪዎቻቸው ገንዘቡን እንዲወስዱ ፈቃድ መስጠት የሚቻልባቸው የባንክ ሒሳብ ዝውውርና አውቶማቲክ የዕዳ ክፍያ ዝግጅቶች መኖራቸው ነው። የባንክ ተቋማት የወረቀት ቼኮችን ማስቀረት የሌላ ሰው መረጃ በመጠቀም የሚፈጸምን ስርቆት ለመከላከል ያስችላል ብለው ይናገራሉ። ይሁን እንጂ አንዳንድ ደንበኞችና ማጭበርበርን የሚከላከሉ ባለሙያዎች የኤሌክትሮኒክ ቼኮች የሰዎች ነጻነት ይበልጥ እንዲደፈርና የማጭበርበሪያ ዘዴዎች እንዲጨምሩ ያደርጋሉ ሲሉ ስጋታቸውን ገልጸዋል።