በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

ከፍርሃት ነጻ መሆን ይቻላል?

ከፍርሃት ነጻ መሆን ይቻላል?

ከፍርሃት ነጻ መሆን ይቻላል?

በዚህ አደገኛ ዓለም ውስጥ የሚኖር ማንኛውም ሰው ሙሉ በሙሉ ከፍርሃት ነጻ መሆን ይችላል? በጭራሽ! በአምላክ የሚያምኑ ሰዎች እንኳን ለጭንቀት የሚዳርጉ አደገኛ ሁኔታዎች ያጋጥሟቸዋል። ለምሳሌ ያህል በመጀመሪያው መቶ ዘመን በጣም ረጅም ጉዞ አድርጎ የነበረው ሐዋርያው ጳውሎስ ለመርከብ አደጋ፣ ለወንዝ ሙላት አደጋ፣ ለወንበዴዎች አደጋና ለከተማ አደጋ ተጋልጦ እንደነበር ተገልጿል። (2 ቆሮንቶስ 11:25-28) ዛሬም በተመሳሳይ አብዛኞቻችን አደገኛ ሁኔታዎች ያጋጥሙናል።

ይሁንና ጥሩ ጥንቃቄ በማድረግና አደጋ የሚያስከትልብንን ሁኔታ በመቀነስ ጭንቀታችንን ማቃለል እንችል ይሆናል። መጽሐፍ ቅዱስ “አስተዋይ ሰው አደጋ ሲያይ መጠጊያ ይሻል፤ ብስለት የጐደለው ግን በዚያው ይቀጥላል፤ መከራም ያገኘዋል” ይላል። (ምሳሌ 22:3) መውሰድ ከምትችላቸው ጠቃሚ እርምጃዎች መካከል አንዳንዶቹ ምንድን ናቸው?

ጥንቃቄ ማድረግ

የሚገርመው መጽሐፍ ቅዱስ ከተጻፈ ረጅም ጊዜ ያለፈ ቢሆንም ዛሬ ያሉትን ችግሮች ለማስወገድ የሚረዱ ብዙ ጠቃሚ መመሪያዎችን ይዟል። ለምሳሌ ያህል እንዲህ የሚል ሐሳብ እናገኛለን:- “የጠቢብ ሰው ዐይኖች ያሉት በራሱ ውስጥ ነው፤ ሞኝ ግን በጨለማ ውስጥ ይራመዳል።” (መክብብ 2:14) በአካባቢህ ያለው ሰው ማን እንደሆነ ማወቅና በተቻለ መጠን በጨለማ ቦታዎች ከመሄድ መቆጠብ ጥበብ ነው። በእግር ወደ ቤት ስትሄድ ቢርቅብህም እንኳን በተቻለ መጠን ጥሩ መብራት ባለበት መንገድ ተጓዝ። መጽሐፍ ቅዱስ “ከአንድ፣ ሁለት መሆን ይሻላል፤ . . . አንድ ሰው ብቸኛውን ቢያጠቃውም፣ ሁለት ከሆኑ ይመክቱታል” በማለት ተጨማሪ ምክር ይሰጣል። (መክብብ 4:9, 12) በአደገኛ አካባቢ የምትኖር ከሆነ ወደ ቤትህ ከሌላ ሰው ጋር የምትሄድበትን መንገድ ማመቻቸት ትችላለህ?

ዘራፊ ቢይዝህ ሕይወት ከንብረት እንደሚበልጥ ማስታወስህ አስተዋይነት ነው። (ማቴዎስ 16:26) በተጨማሪም ተቃውሟቸውን ለመግለጽ የተሰበሰቡ ሰዎች አደገኛ እንደሆኑና ሊያደርጉት የሚችሉትን ነገር መገመት እንደሚያስቸግር መገንዘብ ይገባሃል።—ዘፀአት 23:2

ከሥነ ምግባር ውጪ የሆነ ንግግር በመናገር፣ ጸያፍ ቀልዶች በማውራት ወይም ተገቢ ባልሆነ መንገድ በመነካካት ጾታዊ ትንኮሳ የሚፈጽምብሽን ሰው በጥብቅ መቃወም ይገባሻል። ዮሴፍ ምግባረ ብልሹ የነበረች ሴት በያዘችው ጊዜ እንዳደረገው ከዚያ አካባቢ መሸሽ ሊያስፈልግሽ ይችላል። በዚያን ጊዜ ዮሴፍ ‘ሸሽቶ ከቤት ወጥቶ’ ነበር። (ዘፍጥረት 39:12) መሸሽ የማይቻል ከሆነ “እረፍ!”፣ “አትንካኝ!” ወይም “እንደዚህ ዓይነት ወሬ አልወድም!” ማለት ትችያለሽ። ከተቻለ ጾታዊ ጥቃት መፈጸም ወደተለመደባቸው ቦታዎች ከመሄድ ተቆጠቢ።

በቤት ውስጥ የሚፈጠረውን ፍርሃት መቋቋም

ተደባዳቢ ባል ካለሽ ምን ማድረግ ትችያለሽ? የባልሽ አመል ባልታሰበ ወቅት የአንቺን ወይም የልጆችሽን ጤንነትና ሕይወት አደጋ ላይ ሊጥል እንደሚችል ከተሰማሽ እንዴት ማምለጥ እንደምትችይ እቅድ ማውጣቱ ጥሩ ሊሆን ይችላል። * ያዕቆብ ወንድሙ ዔሳው ክፉ ነገር ሊፈጽምበት ቢሞክር የሚያመልጥበትን ዘዴ በጥንቃቄ አዘጋጅቶ እንደነበር መጽሐፍ ቅዱስ ይገልጻል። በኋላ ላይ ያዕቆብ ያቀደውን ነገር ማድረግ አላስፈለገውም ነበር፤ ቢሆንም ቅድመ ጥንቃቄ አድርጓል። (ዘፍጥረት 32:6-8) ለማምለጥ እቅድ ስታወጪ በድንገት ብትሄጂ ሊቀበልሽ የሚችል ሰው ማዘጋጀትም አለብሽ። ምን እንደምትፈልጊ ቀደም ብለሽ ከሚቀበልሽ ሰው ጋር መነጋገር ትችያለሽ። ጠቃሚ መረጃዎችንና ሌሎች አስፈላጊ ነገሮችን በቀላሉ ሊገኙ በሚችሉበት ቦታ ማስቀመጡ የተሻለ ነው።

ከዚህ በተጨማሪ የትዳር ጓደኛሽ የሚፈጽምብሽን በደል ለሚመለከታቸው ባለ ሥልጣናት ማሳወቅና ጥበቃ እንዲያደርጉልሽ መጠየቅ አንዱ አማራጭ ነው። * መጽሐፍ ቅዱስ ሁሉም ሰው ድርጊቱ የሚያስከትለውን መዘዝ መቀበል እንዳለበት ይናገራል። (ገላትያ 6:7) የመንግሥት ባለ ሥልጣናትንም በተመለከተ “እርሱ ለአንተ መልካሙን ለማድረግ የእግዚአብሔር አገልጋይ ነውና። ነገር ግን ክፉ ብታደርግ ፍራ” ይላል። (ሮሜ 13:4) በቤት ውስጥ የሚፈጸመው ጥቃት በመንገድ ላይ ከሚፈጸመው ወንጀል ተለይቶ አይታይም። አንድን ሰው እየተከታተሉ ማስፈራራትም በበርካታ አገሮች ውስጥ በሕግ የሚያስጠይቅ ወንጀል ነው።

ከላይ ያየናቸውን እርምጃዎች መውሰዱ በተወሰነ መጠንም ቢሆን ፍርሃትን ለመቀነስ ይረዳል። ይሁንና መጽሐፍ ቅዱስ ጠቃሚ ምክሮችን በመስጠት ብቻ አይወሰንም። ይህ መጽሐፍ ራስን ከአደጋ ለመጠበቅ የሚረዳ ምክር ብቻ ሳይሆን አምላክ አሁን ምን እያደረገ እንዳለና ወደፊት ምን እንደሚያደርግ የሚገልጹ መሬት ጠብ የማይሉ ትንቢቶችን ይዟል። መጽሐፍ ቅዱስ በፍርሃት ውስጥ መኖር ግድ ለሆነባቸው ሰዎች ምን ተስፋ ይዟል?

በዓለም ላይ ሰፍኖ የሚገኘው ፍርሃት ምን ትርጉም አለው?

ሐዋርያው ጳውሎስ የጻፈው የሚከተለው ሐሳብ ትልቅ ትርጉም አለው:- “በመጨረሻው ዘመን የሚያስጨንቅ ጊዜ [ይመጣል]። ሰዎች ራሳቸውን የሚወዱ . . .፣ ፍቅር የሌላቸው፣ ለዕርቅ የማይሸነፉ፣ ሐሜተኞች፣ ራሳቸውን የማይገዙ፣ ጨካኞች፣ መልካም የሆነውን የማይወዱ . . . ይሆናሉ።” (2 ጢሞቴዎስ 3:1-3) ይህ ጥቅስ በጣም አስፈሪ ስለሆነ ዘመን የሚናገር ነው።

ኢየሱስ ስለ “ዓለም መጨረሻ” ሲናገር እንዲህ ብሎ ነበር:- “ሕዝብ በሕዝብ ላይ፣ መንግሥትም በመንግሥት ላይ ይነሣል፤ ታላቅ የመሬት መናወጥ ይሆናል፤ ራብና ቸነፈር በተለያየ ስፍራ ይከሠታል፤ አስፈሪ ነገር እንዲሁም ከሰማይ ታላቅ ምልክት ይሆናል።” (ማቴዎስ 24:3, 7, 8፤ ሉቃስ 21:10, 11) ስለዚህ “አስፈሪ ነገር” መመልከታችንም ሆነ ይህ ሁኔታ በየቦታው ፍርሃት እንዲሰፍን ማድረጉ ሊያስገርመን አይገባም። ይሁንና እነዚህ ነገሮች ምን ትርጉም አላቸው?

ኢየሱስ “እነዚህ ነገሮች መፈጸማቸውን ስታዩ፣ የእግዚአብሔር መንግሥት እንደ ቀረበች ዕወቁ” ብሏል። (ሉቃስ 21:31) በዘመናችን አምላክ ከሰማይ ሆኖ የሰው ልጆችን ሁሉ የሚገዛበት መንግሥት እንደሚመጣ መጠበቅ እንችላለን። (ዳንኤል 2:44) በዚያን ጊዜ ሕይወት ምን ይመስላል?

ከፍርሃት ነጻ እንወጣለን!

መጽሐፍ ቅዱስ ጦርነት ተወግዶ ሰላም የሚሰፍንበትና ክፉዎች ጠፍተው ምድር አምላክን በሚወዱ ሰዎች የምትሞላበት ጊዜ እንደሚመጣ ይናገራል። የኢየሱስ ሐዋርያ የነበረው ጴጥሮስ ወደፊት ስለሚመጣው ‘ኃጢአተኞች የሚጠፉበት የፍርድ ቀን’ ተናግሯል። በዚያን ጊዜ በምድር ላይ ‘ጽድቅ ስለሚኖር’ የሚያስፈራ ክፉ ነገር አይገኝም። (2 ጴጥሮስ 3:7, 9, 13) እርስ በርሳቸው በሚዋደዱ ታማኝ ሰዎች መካከል መኖር ምን ያህል እፎይታ እንደሚሰጥ አስበው! ይህ ተስፋ አሁን ላለው አደገኛ ሁኔታ የተለየ አመለካከት እንዲኖረን ይረዳናል። አሁን ያሉት አስጊ ሁኔታዎች ለዘላለም አይቀጥሉም።—መዝሙር 37:9-11

አንድ የይሖዋ ነቢይ በስጋት እየተሠቃዩ ላሉ ሰዎች እንዲህ ብሏል:- “የሚፈራ ልብ ላላቸው እንዲህ በሉ፤ ‘በርቱ፤ አትፍሩ፤ አምላካችሁ ይመጣል፤ ሊበቀል ይመጣል፤ እርሱም ብድራቱን ይዞ፣ ሊያድናችሁ ይመጣል።” (ኢሳይያስ 35:4) ስለዚህ የእውነተኛው አምላክ አገልጋዮች የወደፊቱን ጊዜ በተስፋ ሊጠባበቁ ይችላሉ። (ፊልጵስዩስ 4:6, 7) በፍርሃት መኖር ግድ የሆነባቸው ሰዎች ይሖዋ እርሱን በሚያውቁና ፍቅራዊ ባሕርያቱን በሚያንጸባርቁ ሰዎች ምድርን ለመሙላት የነበረውን የመጀመሪያ ዓላማ እንደሚፈጽም ማወቃቸው በጣም ያጽናናቸዋል።—ዘፍጥረት 1:26-28፤ ኢሳይያስ 11:9

ይሖዋ ለሰው ልጆች ያለውን ፍቅራዊ ዓላማ ከመፈጸም የሚያግደው አንዳች ነገር እንደሌለ እናውቃለን። (ኢሳይያስ 55:10, 11፤ ሮሜ 8:35-39) ይህንን ስንገነዘብ በብዙዎች ዘንድ የሚታወቀው አንድ መዝሙር ለእኛ ልዩ ትርጉም ይኖረዋል። መዝሙሩ እንዲህ ይላል:- “እግዚአብሔር እረኛዬ ነው፤ . . . ነፍሴንም ይመልሳታል። ስለ ስሙም፣ በጽድቅ መንገድ ይመራኛል። በሞት ጥላ ሸለቆ ውስጥ፤ ብሄድ እንኳ፣ አንተ ከእኔ ጋር ስለ ሆንህ፣ ክፉን አልፈራም።” (መዝሙር 23:1-4) ምንም እንኳን ጊዜው የባሰ እያስፈራ ቢሄድም ከፍርሃት ነጻ የሆነው ዓለም እየቀረበ ነው፤ መምጣቱም የማይቀር ነው።

[የግርጌ ማስታወሻዎች]

^ አን.9 ከመጽሐፍ ቅዱስ መመሪያዎች ጋር በሚስማማ መንገድ ከትዳር ጓደኛ መለየት ስለሚቻልባቸው ሁኔታዎች ለማወቅ የመጋቢት 2002 ንቁ! ገጽ 10⁠ን መመልከት ይቻላል።

^ አን.10 በታኅሣሥ 2001 ንቁ! ከገጽ 3-12 እና በሚያዝያ 1998 ንቁ! ከገጽ 3-14 ላይ በቤት ውስጥ ስለሚፈጸም ጥቃት ተጨማሪ ሐሳቦችን መመልከት ይቻላል።

[በገጽ 26-28 ላይ የሚገኙ ሥዕሎች]

አምላክ በቅርቡ ከፍርሃት ነጻ የሆነ ዓለም ያመጣል