በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

የኑሮ ልዩነት—ብቸኛው መፍትሔ ምንድን ነው?

የኑሮ ልዩነት—ብቸኛው መፍትሔ ምንድን ነው?

የኑሮ ልዩነት—ብቸኛው መፍትሔ ምንድን ነው?

በመላው ዓለም በመቶ ሚሊዮን የሚቆጠሩ ሰዎች አስከፊ ከሆነው ድህነት በየዕለቱ ሕይወታቸውን ለመታደግ ይጥራሉ። የሰው ልጅ እንዲህ ዓይነቱን የፍትሕ መዛባት ሙሉ በሙሉ ለማስወገድ ልባዊ ፍላጎት ያለው ጻድቅና የማይጠፋ መንግሥት እንደሚያስፈልገው የተረጋገጠ ነው። እንዲህ ያለው መንግሥት ያሰበውን መልካም እቅድ ከግብ ለማድረስ ኃይል ሊኖረው ይገባል። በእርግጥ የሰው ልጆች እንዲህ ያለውን መንግሥት ሊያቋቁሙ ይችላሉ ብለን መጠበቅ እንችላለን?

መጽሐፍ ቅዱስ “በገዦች አትታመኑ፤ ማዳን በማይችሉ ሥጋ ለባሾችም አትመኩ” ሲል የሚሰጠው ምክር እውነት መሆኑን ታሪክ ያረጋግጣል። (መዝሙር 146:3) በሰብዓዊ መንግሥታት ወይም ገዥዎች መታመን አብዛኛውን ጊዜ ለሐዘን የሚዳርግ ሆኖ አላገኘኸውም? ታዲያ ተስፋችንን በማን ላይ መጣል እንችላለን?

እውነት ነው፣ በሚሊዮን የሚቆጠሩ ሰዎች ፍትሕን የሚያሰፍን ጻድቅ የሆነ መንግሥት እንዲመጣ ሲጸልዩ ቆይተዋል። አንተም ብትሆን ኢየሱስ እንዲህ ሲል ያስተማረውን ጸሎት ጸልየህ ይሆናል:- “በሰማያት የምትኖር አባታችን ሆይ፤ ስምህ ይቀደስ፤ መንግሥትህ ትምጣ፤ ፈቃድህ በሰማይ እንደ ሆነች፣ እንዲሁ በምድር ትሁን። የዕለት እንጀራችንን ዛሬ ስጠን። እኛም ደግሞ የበደሉንን ይቅር እንደምንል፣ በደላችንን ይቅር በለን። ወደ ፈተናም አታግባን ከክፉው አድነን እንጂ።”—ማቴዎስ 6:9-13

ለእኛ በእርግጥ የሚያስፈልገን ይህ ኢየሱስ የጸለየለት መንግሥት ነው? ይህ መንግሥት ጻድቅና የማይጠፋ ነው? ደግሞስ እቅዶቹን ከግብ ለማድረስ የሚያስችል በቂ ኃይል አለው? ምን ጥያቄ አለው! ይህን መንግሥት ያቋቋመው ‘በሰማያት የሚኖረው አባታችን’ “በሚያደርገው ሁሉ ጻድቅ” የሆነ እንዲሁም “ጻድቅና አዳኝ” አምላክ ነው። (ኢሳይያስ 45:21፤ ዳንኤል 9:14) እሱን አስመልክቶ “ዐይኖችህ ክፉውን እንዳያዩ እጅግ ንጹሓን ናቸው” መባሉ ያቋቋመው መንግሥትም እንከን የለሽ እንደሚሆን እንድንተማመን ያደርገናል። (ዕንባቆም 1:13) ከዚህም በላይ ‘እግዚአብሔር ለማንም የማያዳላ ነገር ግን እርሱን የሚፈሩትንና ጽድቅን የሚያደርጉትን ሁሉ ከየትኛውም ወገን ቢሆኑ የሚቀበል’ አምላክ መሆኑ በምድር ላይ ለሚኖር ለማንኛውም ግለሰብ ከልብ እንደሚያስብ ያስገነዝበናል።—የሐዋርያት ሥራ 10:34, 35፤ ሮሜ 2:11

የአምላክ መንግሥት ሥራውን ጀምሯል!

የአምላክ መንግሥት በሰማይ የተቋቋመ አስተዳደር ቢሆንም የአምላክን ዓላማ ከግብ ለማድረስ ትኩረቱን ወደ ምድር አዙሮ አስፈላጊውን እርምጃ ይወስዳል። ይህ እርምጃ ፍጽምና የሚጎድላቸውን ሰብዓዊ መንግሥታት እንከን የለሽ በሆነ መለኮታዊ መስተዳድር መተካትን ይጨምራል። በዳንኤል 2:44 ላይ እንዲህ የሚል ተስፋ ተሰጥቷል:- “በነዚያ ነገሥታት ዘመን፣ የሰማይ አምላክ ፈጽሞ የማይፈርስና ለሌላም ሕዝብ የማይሰጥ መንግሥት ይመሠርታል፤ እነዚያን መንግሥታት ሁሉ ያደቃል፤ እስከ መጨረሻውም ያጠፋቸዋል፤ ይህ መንግሥት ራሱ ግን ለዘላለም ጸንቶ ይኖራል።”

በመጨረሻም፣ መንግሥቱ በሚሰጠው መመሪያ አማካኝነት የአምላክ ፈቃድ በሰማይና በምድር ላይ ይፈጸማል። ይህ መስተዳድር በባለጸጎችና በድህነት በሚማቅቁ ሰዎች መካከል ሰፊ ክፍተት እንዲፈጠር ያደረጉ ምክንያቶችን በሙሉ ጠራርጎ የማስወገድ ችሎታ እንዳለው ማወቃችን እንዴት ያጽናናል! ከዚያ በኋላ ጥቂቶች የሚበለጽጉበትና ብዙኃን በድህነት የሚማቅቁበት ዓለም ፈጽሞ አይኖርም።

የአምላክ መንግሥት እነዚህን ችግሮች ለአንዴና ለመጨረሻ ጊዜ ለማስወገድ ቀደም ሲል እንደተቋቋመ መገንዘባችን ምንኛ ያስደስታል! የመጽሐፍ ቅዱስ የዘመናት ስሌትም ሆነ በዓለም ላይ የተፈጸሙት ክንውኖች በ1914 የአምላክ መንግሥት በሰማይ መቋቋሙን ያመለክታሉ። * ይህ መንግሥት ጽድቅ የሰፈነበትን አዲስ ዓለም መሠረት መገንባት ከጀመረ አንድ መቶ ዓመት ሊሞላው ምንም ያህል አልቀረው።

መንግሥቱ መቋቋሙን የሚገነዘቡና የሚሰጠውን መመሪያ በመከተል ላይ የሚገኙ ሰዎች ከመድሎ የራቁ ናቸው። የይሖዋ ምሥክሮች የስብከቱን ሥራ የሚያከናውኑት በሁሉም አገሮች ነው ለማለት ይቻላል። በእነዚህ አገሮች የሚኖር ማንኛውም ዜጋ ሀብታምም ይሁን ድሃ ዘላለማዊ ሕይወት ማግኘት የሚቻልበትን መንገድ እንዲማር ግብዣ ይቀርብለታል። (ዮሐንስ 17:3) የይሖዋ ምሥክሮች በጉባኤያቸው ውስጥ የአንድን ሰው ችሎታ ወይም ብቃት የሚለኩት በኑሮ ደረጃው አይደለም። ሰዎች የሚመዘኑት ባገኙት ቁሳዊ ብልጽግናም አይደለም። ከዚህ ይልቅ የሚከበሩት በማንነታቸው ነው። ትልቁን ቦታ የሚይዙት ቁሳዊ ነገሮች ሳይሆኑ መንፈሳዊ ጉዳዮች ናቸው።

አንተስ በዚህ ጽድቅ የሰፈነበት መስተዳድር ሥር ለመኖር ምን ማድረግ እንደሚገባህ ለማወቅ ትፈልጋለህ? ከሆነ ዛሬውኑ ምርምር ማድረግህን ጀምር። በሀብት ባልተከፋፈለ ዓለም ውስጥ መኖር የሚያስገኘውን ደስታ እንዴት አሻግረህ መመልከት እንደምትችል ተማር።

[የግርጌ ማስታወሻ]

[በገጽ 8, 9 ላይ የሚገኝ ሣጥን/ሥዕል]

ሀብታምም ሆኑ ድሃ ሁሉም ወንድማማቾች ናቸው

▪ ሁለተኛው የዓለም ጦርነት ሲገባደድ በአውሮፓና በእስያ የሚኖሩ በርካታ የይሖዋ ምሥክሮች የምግብ፣ የልብስና የመጠለያ ችግር አጋጥሟቸው ነበር። በዚህ ጊዜ በሌሎች አገሮች ያሉ የይሖዋ ምሥክሮች በአውሮፓ፣ በፊሊፒንስ እንዲሁም በጃፓን ለሚኖሩት መንፈሳዊ ወንድሞቻቸው በርከት ያለ ልብስና ምግብ ልከዋል። በዩናይትድ ስቴትስና በካናዳ ያሉ ወንድሞች ወደ ሆላንድ፣ ሩማኒያ፣ ቤልጅየም፣ ቼኮዝሎቫኪያ (የአሁኑ ቼክ ሪፑብሊክና ስሎቫኪያ)፣ እንግሊዝ፣ ኦስትሪያ እንዲሁም ጣሊያን የሚላኩ የእርዳታ ቁሳቁሶችን ለግሰዋል።

[ሥዕሎች]

ዩናይትድ ስቴትስ

ስዊዘርላንድ

ጀርመን

▪ በቅርቡ ማለትም በ1994 የበጋ ወራት ከአውሮፓ የተውጣጡ ፈቃደኛ ሠራተኞችን የያዘ አንድ ቡድን በአፍሪካ የሚገኙ ወንድሞችና እህቶችን ለመርዳት በፍጥነት ወደ ስፍራው ተንቀሳቅሶ ነበር። ለሩዋንዳ ስደተኞች በደንብ የተደራጁ መጠለያዎችና የመስክ ሆስፒታሎች ተቋቋሙ። በወቅቱ በሩዋንዳ ከነበሩት የይሖዋ ምሥክሮች ቁጥር ከሦስት እጥፍ በላይ ለሚያህሉ ማለትም ከ7,000 ለሚበልጡ ተጎጂዎች የሚሆኑ በርካታ አልባሳት፣ ብርድ ልብሶች፣ ምግብና መጽሐፍ ቅዱሳዊ ጽሑፎች ወደ ቦታው ተልከዋል።

▪ ከሁለት ዓመት በኋላ ማለትም በ1996 በኮንጎ ዲሞክራቲክ ሪፑብሊክ ምሥራቃዊ ክፍል ጦርነት ተቀሰቀሰ። በዚህም ሳቢያ ሰብሎች ወደሙ፣ የእህል መጋዘኖች ተዘረፉ እንዲሁም የእርዳታ ቁሳቁስ የሚጓጓዝባቸው መንገዶች ተዘጉ። ብዙዎቹ ምግብ የሚያገኙት በቀን አንዴ ብቻ መሆኑ የተመጣጠነ ምግብ እጥረትና በሽታን አስከትሎባቸዋል። በዚህ ጊዜ በአውሮፓ የሚገኙ የይሖዋ ምሥክሮች አፋጣኝ ምላሽ ሰጥተዋል። የሕክምና ዶክተሮችን ያካተተ የይሖዋ ምሥክሮች የእርዳታ ቡድን መድኃኒትና ገንዘብ በመያዝ ስፍራው ደርሷል። ሰኔ 1997 በቤልጅየም፣ በፈረንሳይና በስዊዘርላንድ የሚገኙ የይሖዋ ምሥክሮች 500 ኪሎ ግራም መድኃኒት፣ ከፍተኛ የፕሮቲን መጠን ያለው 10 ቶን ብስኩት፣ 20 ቶን ሌሎች ምግቦች፣ 90 ቶን ልብሶች፣ 18,500 ጥንድ ጫማዎችና 1,000 ብርድ ልብሶች ልከዋል። ይህም በገንዘብ ሲሰላ ወደ 1,000,000 የአሜሪካ ዶላር ይጠጋል።

▪ የይሖዋ ምሥክሮች ከሚሰጡት ቁሳዊ ድጋፍ የበለጠ ትኩረት ያደረጉት ሰዎችን በመንፈሳዊ በመርዳቱ ላይ ነው። ይህንንም ሰዎች የመጽሐፍ ቅዱስ እውነት የሚቀስሙባቸውን የመንግሥት አዳራሾች ለመገንባት ካሳዩት ትጋት በግልጽ መረዳት ይቻላል። በ1997 እንዲህ የሚል ሪፖርት ተደርጓል:- “በሌሎች አገሮች የሚኖሩ ወንድሞች ባደረጉት እርዳታ አማካኝነት [የመጠበቂያ ግንብ] ማኅበር 413 አዳዲስ የመንግሥት አዳራሾችን ለመገንባትና በአራት ወራት ብቻ በ75 አገሮች የሚገኙ 727 አዳራሾችን ደግሞ በተሻሻለ መልክ ለመሥራት የተደረገውን ጥረት ማገዝ አስችሎታል።” በ2003 ደግሞ የሚከተለው ሪፖርት ቀርቦ ነበር:- “የገንዘብ አቅማቸው አነስተኛ በሆኑት የአውሮፓ አካባቢዎች የመንግሥት አዳራሾችን ለመገንባት በተደረገው ዝግጅት ተጠቃሚ ከሆኑት አገሮች መካከል ሩማኒያ ትገኛለች። በዚህች አገር ከሐምሌ 2000 ጀምሮ 124 የመንግሥት አዳራሾች ተገንብተዋል። ለሁሉም የመንግሥት አዳራሾች ማለት ይቻላል ተመሳሳይ ንድፍ የተጠቀመችው ዩክሬን በ2001፣ 61 በ2002 ደግሞ 76 ተጨማሪ አዳራሾችን ገንብታለች። ለመንግሥት አዳራሽ በሚደረገው የገንዘብ መዋጮ አማካኝነት በመቄዶንያ፣ በሩሲያ፣ በሰርቢያና ሞንቴኔግሮ፣ በቡልጋሪያ እንዲሁም በክሮኤሺያ በመቶዎች የሚቆጠሩ የመንግሥት አዳራሾች ተሠርተዋል።”

[ሥዕሎች]

ክሮኤሺያ

ቡልጋሪያ

ሩማኒያ

[በገጽ 7 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

ወላጅ አልባ የሆኑ ሁለት ስደተኛ ሕፃናትን የምትንከባከብ የበጎ ፈቃድ ሠራተኛ

[ምንጭ]

© Liba Taylor/Panos Pictures

[በገጽ 10 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

የይሖዋ ምሥክሮች ተስፋ ያዘለ መልእክት ያሰራጫሉ

[በገጽ 10 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

የአምላክ መንግሥት ድህነትን ያጠፋል