በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

የአውሮፓ ፍርድ ቤት የአንዲትን እናት መብት አስከበረ

የአውሮፓ ፍርድ ቤት የአንዲትን እናት መብት አስከበረ

የአውሮፓ ፍርድ ቤት የአንዲትን እናት መብት አስከበረ

ፈረንሳይ የሚገኘው የንቁ! ዘጋቢ እንደጻፈው

ኅሣሥ 16, 2003 መቀመጫውን በፈረንሳይ፣ ስትራስቡር ያደረገው የአውሮፓ የሰብዓዊ መብቶች ፍርድ ቤት፣ የፈረንሳይ ፍርድ ቤቶች ሴራፊን ፓላው ማርቲኔዝ በተባለች የይሖዋ ምሥክር ላይ ሃይማኖታዊ መድልዎ በመፈጸማቸው ጥፋተኛ እንደሆኑ ፈረደባቸው።

ሴራፊን ከሁለት ዓመት በፊት ጥሏት ከሄደው ባሏ ጋር ፍቺ እንድትፈጽም በ1996 ተፈቀደላት። ልጆቿን የማሳደጉ ኃላፊነትም ለእርሷ ተሰጥቶ ነበር። ሆኖም ልጆቿ ለሦስት ዓመት ተኩል ያህል ከእርሷ ጋር ይኖሩ የነበረ ቢሆንም በ1997 አባታቸውን ሊጠይቁት ሲሄዱ ወደ እናታቸው እንዳይሄዱ ከለከላቸው። ሴራፊን እንዲህ ብላለች:- “ልጆቼን ከትምህርት ቤት ላመጣ ስሄድ ርዕሰ መምህሩ ፖሊስ ጠራ። ለልጆቼ ስለ እምነቴ እንዳልነግራቸው በማሰብ እንዳያቸው የፈቀዱልኝ በፖሊስ መኮንኖቹ ፊት ነበር። የሚያናግሩኝ ልክ እንደ ወንጀለኛ ነበር። ስለ አምላክም ሆነ ስለ መጽሐፍ ቅዱስ እንደማልነግራቸውና ወደ ክርስቲያናዊ ስብሰባዎች ይዣቸው እንደማልሄድ የሚገልጽ ሰነድ ላይ ከፈረምኩ ልጆቼን መውሰድ እንደምችል ነገሩኝ።”

ሴራፊን ክስ መሠረተች። ነገር ግን በ1998 የኒም ይግባኝ ሰሚ ፍርድ ቤት ልጆቹ ለአባትየው እንዲሰጡ ፈረደ። ፍርድ ቤቱ ይህን ውሳኔ ያስተላለፈው የይሖዋ ምሥክሮች ልጆቻቸውን ያስተምሩታል ብሎ ለሚያምነው ትምህርት ካለው ብርቱ ነቀፌታ የተነሳ ነው። ሴራፊን እንዲህ ትላለች:- “ልጆቼ ጥሩ ክርስቲያኖች ሆነው እንዲያድጉ ይረዳቸዋል ብዬ የምሰጣቸው ትምህርት እነርሱን ለመጉዳት አስቤ ያደረግሁት እንደሆነ ተደርጎ መወቀሴ በጣም ያሳዝናል።”

ኩር ደ ካሴሸን የተባለው የፈረንሳይ ይግባኝ ሰሚ ጠቅላይ ፍርድ ቤት የኒም ይግባኝ ሰሚ ፍርድ ቤት በወሰነው ውሳኔ በመስማማቱ ሴራፊን ጉዳዩን ለአውሮፓ የሰብዓዊ መብቶች ፍርድ ቤት ለማቅረብ ወሰነች። ፍርድ ቤቱ 6 ለ1 በሆነ ድምፅ የሚከተለውን ውሳኔ አስተላለፈ:- “[የፈረንሳይ] ይግባኝ ሰሚ ፍርድ ቤት በከሳሿ ሃይማኖት ምክንያት አድልዎ እንዳደረገ ፍርድ ቤቱ ማስተዋል ችሏል። . . . ይህን ዓይነት አድልዎ ማድረግ ተገቢ አይደለም።” ከዚህም በላይ የፈረንሳይ ፍርድ ቤት ውሳኔውን ያስተላለፈው ተጨባጭ ማስረጃ ኖሮት ወይም ሴራፊን ልጆቿን ለመንከባከብ ባለመቻሏ ምክንያት እንዳልሆነ ጨምሮ ተናግሯል፤ ይህ ጉዳይ አሳሳቢ ቢሆንም ጨርሶ እንዳልተነሳ ከገለጸ በኋላ “ፍርድ ቤቱ ብይን ላይ ለመድረስ በዋነኝነት ያተኮረው በይሖዋ ምሥክሮች” ላይ ብቻ እንደሆነ ተናግሯል። ከዚያም ሴራፊን ሃይማኖታዊ መድልዎ ስለተደረገባት እንዲሁም መብቶቿ ስለተጣሱ የፈረንሳይ መንግሥት ካሳ እንዲከፍላትና ያወጣችውን ወጪ እንዲሸፍንላት ወስኗል።

የአውሮፓ የሰብዓዊ መብቶች ፍርድ ቤት ከዚህ ቀደም ብሎ ሰኔ 1993 ኢንግሪት ሆፍማን የተባለች የይሖዋ ምሥክር በሃይማኖቷ ምክንያት የኦስትሪያ ፍርድ ቤት መድልዎ እንዳደረገባት የሚገልጽ ተመሳሳይ ውሳኔ አድርጎ ነበር። * በፈረንሳይ የሚታተመው ላ ሰሜን ዡሪዲክ የተባለው የሕግ መጽሔት “ለሆፍማን ከተሰጠው ብያኔ ጋር የሚመሳሰለው ይህ ፍርድ፣ በመሠረቱ ቤተሰብ የማስተዳደሩ ኃላፊነት የሚሰጠው ሃይማኖት እየታየ መሆን እንደሌለበት አረጋግጧል” ሲል ጽፏል። የሴራፊን ጠበቃም የሚከተለውን አስተያየት ሰጥተዋል:- “ይህ ውሳኔ መተላለፉ በጣም አስፈላጊ ነው፤ ምክንያቱም ፍርድ ቤቱ ያረቀቀው ሕግ የማይሻር በመሆኑ የይሖዋ ምሥክሮች የሆኑ ወላጆች አድልዎ የሌለበት ፍርድ እንዲያገኙ ያስችላል።”

አሁን በስፔን የምትኖረው ሴራፊን በውሳኔው ምን እንደተሰማት ስትጠየቅ እንዲህ ብላ መልስ ሰጥታለች:- “በጣም ከመደሰቴም በላይ እፎይታ ተሰምቶኛል። በሃይማኖቴ ምክንያት ልጆቼን መነጠቄና ለአምስት ዓመታት እንዳላያቸው መከልከሌ ከባድ ሥቃይ አስከትሎብኝ ነበር፤ ሆኖም የይሖዋ ድጋፍ አልተለየኝም። ውሳኔው የእኔ ዓይነት ሁኔታ ውስጥ የሚገኙትን እንደሚረዳቸው ተስፋ አደርጋለሁ።”

[የግርጌ ማስታወሻ]

^ አን.7 በጥቅምት 8, 1993 ንቁ! (እንግሊዝኛ) መጽሔት ገጽ 15 ላይ የወጣውን “የይሖዋ ምሥክሮች ልጆቻቸውን የማሳደግ መብታቸውን ተከራክረው አስከበሩ” የሚለውን ርዕስ ተመልከት።

[በገጽ 14 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

ሴራፊን