በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

መጽሐፍ ቅዱስ ሴቶች ዝቅ ተደርገው መታየት እንዳለባቸው ያስተምራል?

መጽሐፍ ቅዱስ ሴቶች ዝቅ ተደርገው መታየት እንዳለባቸው ያስተምራል?

መጽሐፍ ቅዱስ አመለካከት

መጽሐፍ ቅዱስ ሴቶች ዝቅ ተደርገው መታየት እንዳለባቸው ያስተምራል?

በሦስተኛው መቶ ዘመን ይኖር የነበረው የሃይማኖት ምሑር ተርቱሊያን በአንድ ጽሑፉ ላይ ሴቶች “የዲያብሎስ መግቢያ” እንደሆኑ ገልጿል። ሌሎች ደግሞ ሴቶች ከወንዶች ያነሱ እንደሆኑ ለመግለጽ በመጽሐፍ ቅዱስ ተጠቅመዋል። በመሆኑም ብዙ ሰዎች መጽሐፍ ቅዱስ በሴቶች ላይ አድልዎ እንደሚፈጽም ይሰማቸዋል።

በ19ኛው መቶ ዘመን በዩናይትድ ስቴትስ የሴቶች መብት ተሟጋች የነበሩት ኤሊዛቤት ካዲ ስታንተን “ሴቶች የእኩልነት መብት እንዳያገኙ ትልቅ እንቅፋት የሆኑት መጽሐፍ ቅዱስና አብያተ ክርስቲያናት ናቸው” በማለት አስተያየታቸውን ገልጸዋል። ስታንተን የመጀመሪያዎቹን የመጽሐፍ ቅዱስ አምስት መጻሕፍት አስመልክተው “ሴቶች በሁሉም ነገር ተረግጠው እንዲገዙና እንዲናቁ የሚያስተምሩ እንደነዚህ ያሉ መጻሕፍት በፍጹም አይቼ አላውቅም” በማለት ተናግረዋል።

በዛሬው ጊዜ እንዲህ ዓይነት የተጋነነ አስተሳሰብ ያላቸው ሰዎች ብዙ ባይሆኑም አብዛኞቹ ግን አንዳንድ የመጽሐፍ ቅዱስ ክፍሎች ወንዶች በሴቶች ላይ አድልዎ መፈጸማቸውን እንደሚደግፉ ይሰማቸዋል። ታዲያ ይህ ዓይነቱ መደምደሚያ ትክክል ነው ለማለት ይቻላል?

የዕብራይስጥ ቅዱሳን ጽሑፎች ለሴቶች ያላቸው አመለካከት

መጽሐፍ ቅዱስ “ፍላጐትሽም ወደ ባልሽ ይሆናል፤ እርሱም የበላይሽ ይሆናል” በማለት ይናገራል። (ዘፍጥረት 3:16) ተቺዎች ይህ አባባል አምላክ ለሔዋን ያለውን አመለካከት የሚያሳይ እንደሆነና ወንዶች ሴቶችን ዝቅ አድርገው መመልከታቸውን እንደሚደግፈው ይጠቁማል ብለው ይናገራሉ። ሆኖም ይህ ሐሳብ የአምላክን ዓላማ የሚገልጽ ሳይሆን የእርሱን ሉዓላዊነት መቃወምና ኃጢአት መሥራት ያስከተለውን አሳዛኝ ውጤት የሚያሳይ ነው። በሴቶች ላይ የሚፈጸም ጥቃት የአምላክ ፈቃድ ሳይሆን የሰው ልጆች ፍጹም አለመሆን ያስከተለው መዘዝ ነው። በበርካታ ባሕሎች ውስጥ የሚገኙ ባሎች ሚስቶቻቸውን በኃይልና በጭካኔ ይይዟቸዋል። ሆኖም ይህ የአምላክ ዓላማ አልነበረም።

አዳምም ሆነ ሔዋን የተፈጠሩት በአምላክ አምሳል ነው። ከዚህም በተጨማሪ እንዲዋለዱ፣ ምድርን እንዲሞሏትና እንዲገዟት አምላክ መመሪያ የሰጣቸው ለሁለቱም ነው። የአምላክ ዓላማ አንድ ላይ ተባብረው እንዲሠሩ ነበር። (ዘፍጥረት 1:27, 28) በዚያን ጊዜ አንዳቸው ሌላውን አይጨቁኑም ነበር። በዘፍጥረት 1:31 ላይ “እግዚአብሔርም ያደረገውን ሁሉ አየ፤ እነሆም፣ እጅግ መልካም ነበረ” ይላል።

አንዳንድ ጊዜ የመጽሐፍ ቅዱስ ዘገባዎች በአንድ ጉዳይ ላይ የአምላክን አመለካከት ሳይገልጹ እንዲሁ ታሪካዊ ክንውኖችን ብቻ የያዙ ሊሆኑ ይችላሉ። ሎጥ ሴት ልጆቹን ለሰዶም ሰዎች ለመስጠት ማሰቡን የሚናገረው ዘገባ በሥነ ምግባር ረገድ ተቀባይነት ይኑረው አይኑረው ወይም አምላክ የሎጥን ድርጊት እንዳወገዘው የሚገልጽ ነገር የለም። *ዘፍጥረት 19:6-8

እንዲያውም አምላክ ሁሉንም ዓይነት ግፍና በደል ይጠላል። (ዘፀአት 22:22፤ ዘዳግም 27:19፤ ኢሳይያስ 10:1, 2) የሙሴ ሕግ አስገድዶ መድፈርንና ዝሙት አዳሪነትን ያወግዛል። (ዘሌዋውያን 19:29፤ ዘዳግም 22:23-29) ምንዝር ክልክል የነበረ ሲሆን ድርጊቱን የፈጸሙ ሁለቱም ወገኖች በሞት ይቀጡ ነበር። (ዘሌዋውያን 20:10) ሕጉ በሴቶች ላይ አድልዎ ከመፈጸም ይልቅ ከፍ ተደርገው እንዲታዩ ከማድረጉም በላይ በዙሪያቸው ባሉት ብሔራት ዘንድ ተስፋፍቶ ከነበረው ግፍ ይጠብቃቸው ነበር። በዚያን ጊዜ አንዲት ባለሙያ አይሁዳዊት ሚስት እጅግ የተከበረችና የተወደደች ነበረች። (ምሳሌ 31:10, 28-30) እስራኤላውያን፣ ሴቶችን እንዲያከብሩ የተሰጣቸውን ሕግ አለመታዘዛቸው የአምላክ ፈቃድ ሳይሆን የራሳቸው ስህተት ነበር። (ዘዳግም 32:5) በመጨረሻም አምላክ ዓይን ላወጣ ዓመጸኝነታቸው በጠቅላላ ብሔሩ ላይ በመፍረድ ቀጥቷቸዋል።

ለራስነት ሥርዓት ተገዢ መሆን ሴቶችን ዝቅ ያደርጋቸዋል?

ማንኛውም ማኅበረሰብ በተገቢው ሁኔታ ሊሠራ የሚችለው ሥርዓት ሲኖር ብቻ ነው። ለዚህ ደግሞ ሥልጣን ያለው አስተዳዳሪ ያስፈልጋል። ባለ ሥልጣን ከሌለ ግን ትርምስ ይፈጠራል። መጽሐፍ ቅዱስ “እግዚአብሔር የሰላም አምላክ እንጂ የሁከት አምላክ አይደለም” ይላል።—1 ቆሮንቶስ 14:33

ሐዋርያው ጳውሎስ በቤተሰብ ውስጥ ስላለው የራስነት ዝግጅት ሲናገር “የወንድ ሁሉ ራስ ክርስቶስ ነው፤ የሴትም ራስ ወንድ ነው፤ የክርስቶስም ራስ እግዚአብሔር ነው” ብሏል። (1 ቆሮንቶስ 11:3) ከአምላክ በስተቀር ሁሉም አካል ለበላይ ባለ ሥልጣን ይገዛል። ታዲያ ኢየሱስ ራስ ያለው መሆኑ መድልዎ ተደርጎበታል ማለት ነው? በፍጹም! በቅዱሳን ጽሑፎች መሠረት ወንዶች በጉባኤና በቤተሰባቸው ውስጥ የመሪነት ቦታ እንዲይዙ መደረጋቸው ሴቶች መድልዎ ተደርጎባቸዋል ማለት አይደለም። ጥሩ ቤተሰብም ሆነ ጉባኤ እንዲኖር በአክብሮትና በፍቅር ተነሳስተው የየራሳቸውን ድርሻ የሚወጡ ወንዶችና ሴቶች ያስፈልጋሉ።—ኤፌሶን 5:21-25, 28, 29, 33

ኢየሱስ፣ ሴቶችን ሁልጊዜ በአክብሮት ይመለከታቸው ነበር። ፈሪሳውያን የሚያስተምሯቸውን፣ ሴቶችን ዝቅ የሚያደርጉ ሕግጋትና ወጎችን አልተከተለም። አይሁዳዊ ካልሆኑ ሴቶች ጋር ይነጋገር ነበር። (ማቴዎስ 15:22-28፤ ዮሐንስ 4:7-9) ሴቶችን አስተምሯል። (ሉቃስ 10:38-42) ሴቶች ቸል እንዳይባሉ የሚያሳስቡ መሠረታዊ ሥርዓቶችን በማስተማር ጥበቃ አድርጎላቸዋል። (ማርቆስ 10:11, 12) ምናልባትም ኢየሱስ በነበረበት ዘመን ካደረጋቸው ነገሮች ሁሉ ጎልቶ የሚታየው የለውጥ እርምጃ ሴቶችን የቅርብ ወዳጆቹ እንዲሆኑ ማድረጉ ነው። (ሉቃስ 8:1-3) የአምላክ ባሕርያት ነጸብራቅ የሆነው ኢየሱስ ሁለቱም ፆታዎች በአምላክ ዓይን እኩል መሆናቸውን አሳይቷል። እንዲያውም ከጥንት ክርስቲያኖች መካከል ወንዶችም ሆኑ ሴቶች የመንፈስ ቅዱስን ስጦታ ተቀብለዋል። (የሐዋርያት ሥራ 2:1-4, 17, 18) ከክርስቶስ ጋር ነገሥታትና ካህናት ሆነው የተቀቡ ሰዎች ትንሣኤ አግኝተው ወደ ሰማይ ካረጉ በኋላ የፆታ ልዩነት አይኖርም። (ገላትያ 3:28) የመጽሐፍ ቅዱስ ባለቤት የሆነው ይሖዋ ሴቶችን ዝቅ አድርጎ አይመለከትም።

[የግርጌ ማስታወሻ]

[በገጽ 16 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

ኢየሱስ በዚያን ጊዜ ከነበሩት ከአብዛኞቹ ሰዎች በተለየ መልኩ ለሴቶች አክብሮት ነበረው