በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

ሠርግ መደገስ ይኖርብናል?

ሠርግ መደገስ ይኖርብናል?

የወጣቶች ጥያቄ . . .

ሠርግ መደገስ ይኖርብናል?

“ለጓደኞቻችንም ሆነ ለዘመዶቻችን ሳንነግራቸው ብቻችንን ሄደን ልንፈራረም እንደምንችል ሐሳቡን መጀመሪያ ያነሳችው እጮኛዬ ሲንዲ ነበረች። በጉዳዩ ላይ ከተነጋገርንበት በኋላ እንዲህ ማድረጉ ጊዜና ጉልበት እንደሚቆጥብ እንዲሁም ውጥረት እንደሚቀንስ ሁለታችንም አመንበት።”—አለን *

ማግባት በሚያስችል ዕድሜ ላይ ከደረሳችሁና የምትወዱት ሰው ካለ፣ ለማንም ሳትናገሩ ብቻችሁን ሄዳችሁ መጋባት ጥሩ አማራጭ ሊመስል ይችላል። በአንዳንድ ሁኔታዎች አንድ ወንድና ሴት ለወላጆቻቸው እንኳ ሳይናገሩ ኮብልለው ለመጋባት ይፈተኑ ይሆናል። ውሳኔ ላይ ለመድረስ የትኞቹ መሠረታዊ ሥርዓቶች ሊረዷችሁ ይችላሉ?

ትልቅ ቦታ ሊሰጠው የሚገባው ባሕሉ ነው?

በአብዛኞቹ ባሕሎች ውስጥ ጋብቻ የተለመደ ነገር ቢሆንም የሠርጉ ሥነ ሥርዓት ግን በጣም ይለያያል። አንድ ክርስቲያን ወንድና ሴት በዋነኝነት ሊያሳስባቸው የሚገባው የሠርጉ ሥነ ሥርዓት የሚፈጸመው በአካባቢው ባሕል መሠረት መሆን አለመሆኑ አይደለም። (ሮሜ 12:2) ከዚህ ይልቅ ሊያሳስባቸው የሚገባው ዋነኛው ጉዳይ በመጠናናት የሚያሳልፉት ጊዜም ሆነ ጋብቻቸው ለይሖዋ አምላክ ክብር የሚያመጣ መሆኑ ነው።—1 ቆሮንቶስ 10:31

ጋብቻ ክቡር የሆነ ዝግጅት እንደመሆኑ መጠን አብዛኞቹ ተጋቢዎች ጉዳዩን በምስጢር ሊይዙት አይፈልጉም። በበርካታ ምዕራባውያን አገሮች ውስጥ የሚገኙ የይሖዋ ምሥክሮች በአካባቢያቸው በሚገኘው የመንግሥት አዳራሽ ውስጥ ለመጋባት ዝግጅት ማድረጋቸው የተለመደ ነው። * ከዚያም ከዘመድ አዝማድና ከጓደኞቻቸው ጋር ለመጫወት ሲሉ ግብዣ ለማድረግ ይፈልጉ ይሆናል። እንደነዚህ ዓይነት ግብዣዎች በጣም ሰፊ መሆን አያስፈልጋቸውም። ሠርግ መደገስ የሚያስጨንቅና ከፍተኛ ወጪ የሚጠይቅ ዝግጅት መሆኑ አይካድም። ለምሳሌ በዩናይትድ ስቴትስ የሠርግ ግብዣዎች ብዙውን ጊዜ በሺህ የሚቆጠሩ ዶላሮች ያስወጣሉ።

ሊጋቡ ያሰቡ አንዳንድ ሰዎች ሠርጉ የሚያስከትለውን ጭንቀትና ወጪ ለመቀነስ ሲሉ ይበልጥ ቀለል ያለ መንገድ መርጠዋል። ሲንዲ እንዲህ ትላለች:- “ሥነ ሥርዓቱ ቀለል ያለና ወጪ ያልበዛበት እንዲሆን ስለፈለግን፣ በባሕሉ መሠረት እንደሚደረገው ዓይነት ሠርግ እንደማንደግስ ለወላጆቻችን ነገርናቸው። ወላጆቼ ሁኔታችንን ግምት ውስጥ በማስገባት ሐሳባችንን የተረዱልን ከመሆኑም በላይ ድጋፋቸው አልተለየንም።” በሌላ በኩል ቀደም ሲል የተጠቀሰው የሲንዲ እጮኛ አለን የሠርጉን እቅድ ለወላጆቹ ሲነግራቸው ውሳኔውን ለመቀበል ከበዳቸው። አለን እንዲህ ይላል:- “ወላጆቼ የሆነ ስህተት እንደሠሩና እንዲህ ዓይነት ውሳኔ ላይ የደረስነው በእነሱ ጥፋት እንደሆነ ተሰማቸው። ሆኖም ምክንያቱ ይህ አልነበረም።”

ወላጆቻችሁ በዚህ ልዩ ቀን የቻሉትን ያህል ብዙ ሰዎች ጠርተው የደስታቸው ተካፋይ እንዲሆኑ ስለሚፈልጉ፣ ቀለል ያለ ሠርግ ለማድረግ ብትወስኑ ሊከፋቸው ይችላል። ሆኖም ቤተሰባችሁ ማግባታችሁን ራሱ እንደሚቃወሙ ስለምታውቁ ለወላጆቻችሁ ሳትናገሩ ለመጋባት አስባችሁ ከሆነስ?

የቤተሰባችሁን ስሜት ግምት ውስጥ አስገቡ

ቤተሰቦቻችሁ እንዳታገቡ የሚከለክሏችሁ ምናልባት ይህን የመሰለ ትልቅ ውሳኔ ለማድረግ ዕድሜያችሁ ገና እንዳልደረሰ ስላሰቡ ይሆናል። እያደጋችሁ ስትሄዱ ምርጫችሁ ሊለወጥ እንዲሁም በትዳር ጓደኛ ምርጫችሁ ትቆጩ ይሆናል ብለው ስለሚፈሩ ነው። በሌላ በኩል ደግሞ ለማግባት ብቁ እንደሆናችሁ ቢሰማቸውም ያፈቀራችሁት ግለሰብ አንዳንድ ጉድለቶች እንዳሉት ተገንዝበው ይሆናል። አሊያም ልታገቡት የመረጣችሁት ግለሰብ ከእናንተ ጋር አንድ ዓይነት እምነት ስለሌለው እንዳታገቡ ሊከለክሏችሁ ይችላሉ።

ወላጆቻችሁ እውነተኛ ክርስቲያኖች ከሆኑ ላቀረቡት ሐሳብ ቅዱስ ጽሑፋዊ ምክንያት ይኖራቸዋል። በመሆኑም ያላቸውን ጥርጣሬ መግለጻቸው ተገቢ ነው። በእርግጥም የተሰማቸውን ጥርጣሬ ካልገለጹላችሁ ይሖዋ ቸልተኛ እንደሆኑና ለልጆቻቸው ፍቅር እንደሌላቸው ወላጆች አድርጎ ይመለከታቸዋል። የእነርሱን ሐሳብ መስማት ጥቅሙ ለራሳችሁ ነው።—ምሳሌ 13:1, 24

በምሳሌ ለማስረዳት ያህል፣ ልብስ ለመግዛት ስትፈልጉ ልብሱ የተስማማችሁ መሆን አለመሆኑን ለማወቅ የአንድ ሰው ሐሳብ መጠየቃችሁ አይቀርም። በሚሰጡት ሐሳብ ሁልጊዜ ትስማማላችሁ ማለት ባይሆንም ልብሱ ለእናንተ የማይሆን ወይም የማያምርባችሁ ከሆነ የቅርብ ጓደኞቻችሁ እንዲነግሯችሁ ትፈልጋላችሁ። ገንዘባችሁ እንዲሁ እንዳይባክን ስለሚረዷችሁ አስተያየታቸውን ትልቅ ቦታ ትሰጡታላችሁ። እንግዲያው ስለ ትዳር ጓደኛ ምርጫችሁ የሚነግሯችሁን ወላጆቻችሁንማ እንዴት አብልጣችሁ ልትሰሟቸው ይገባል! የገዛችሁትን ልብስ የማትፈልጉት ከሆነ በሌላ መቀየር ወይም መጣል የምትችሉ ቢሆንም ከመረጣችሁት የትዳር ጓደኛ ጋር ግን ዕድሜ ልካችሁን አብራችሁ እንድትኖሩ ይሖዋ ይጠብቅባችኋል። (ማቴዎስ 19:5, 6) የመረጣችሁት የትዳር ጓደኛ ከባሕርያችሁና ከመንፈሳዊነታችሁ ጋር የማይስማማ ከሆነ ይህ ጥምረት አንድ የማይስማማ ልብስ ከመልበስ የበለጠ ችግር ይፈጥራል። (ዘፍጥረት 2:18፤ ምሳሌ 21:9) በዚህም ምክንያት እውነተኛ ደስታ ለማግኘት ያላችሁን አጋጣሚ ጭምር ታጣላችሁ።—ምሳሌ 5:18፤ 18:22

እርግጥ አንዳንድ ወላጆች ልጃቸውን እየተቆጣጠሩ ለመኖር ስለሚፈልጉ በራስ ወዳድነት ተነሳስተው ጋብቻውን ይቃወሙ ይሆናል። ሆኖም የወላጆቻችሁ ሐሳብ ራስ ወዳድነት የተንጸባረቀበት ነው ወደሚል መደምደሚያ ከመድረሳችሁና ለመጋባት ከመኮብለላችሁ በፊት በጋብቻው ያልተስማሙበትን ምክንያት ለምን ቆም ብላችሁ አታጤኑም?

መጠንቀቅ አስፈላጊ የሆነበት ምክንያት

እየጎለመሳችሁ ስትሄዱ ምርጫችሁ እየተለወጠ እንደሚሄድ የታወቀ ነው። ሐዋርያው ጳውሎስ “ልጅ ሳለሁ እንደ ልጅ እናገር ነበር፤ እንደ ልጅ አስብ ነበር፤ እንደ ልጅም አሰላ ነበር። ከጐለመስሁ በኋላ ግን የልጅነትን ነገር እርግፍ አድርጌ ትቻለሁ” በማለት ጽፏል። (1 ቆሮንቶስ 13:11) በተመሳሳይም በአሥራዎቹ ዕድሜ ውስጥ እያላችሁ የማረኳችሁ ባሕርያትና እየጎለመሳችሁ ስትሄዱ የሚስቧችሁ ባሕርያት በጣም የተለያዩ መሆናቸው አይቀርም። ስለዚህም መጽሐፍ ቅዱስ የትዳር ጓደኛ እንደመምረጥ ያለ ከባድ እርምጃ ከመውሰዳችሁ በፊት ‘ማግባት ወደሚገባችሁ ዕድሜ’ እስክትደርሱ፣ ማለትም የጾታ ስሜታችሁ የሚያይልበት ጊዜ እስኪያልፍ ድረስ መጠበቁ የተሻለ እንደሆነ ይመክራል።—1 ቆሮንቶስ 7:36 የ1954 ትርጉም

ወላጆቻችሁ የምታፈቅሩት ሰው ጉድለት እንዳለው ቢነግሯችሁስ? ወላጆቻችሁ በሕይወታቸው ባገኙት ተሞክሮ ምክንያት መልካሙን ከክፉው የመለየት ችሎታቸው የተሻለ ሊሆን ይችላል። (ዕብራውያን 5:14) ስለዚህ ልታገቡት ባሰባችሁት ግለሰብ ባሕርይ ላይ እናንተ ልታዩአቸው ያልቻላችኋቸውን ከባድ ድክመቶች ወላጆቻችሁ ሊያስተውሉ ይችላሉ። ጠቢቡ ሰሎሞን “አስቀድሞ ጒዳዩን የሚያሰማ ትክክለኛ ይመስላል፤ ይኸውም ባላንጣው መጥቶ እስከሚመረመር ድረስ ነው” በማለት ያሰፈረውን መሠረታዊ ሥርዓት እንመልከት። (ምሳሌ 18:17) በተመሳሳይም ያፈቀራችሁት ግለሰብ ለእናንተ ትክክለኛ ሰው መሆኑን አሳምኗችሁ ሊሆን ይችላል። ሆኖም ወላጆቻችሁ ‘ከመረመሩት’ በኋላ ልብ ልትሏቸው የሚገቡ አንዳንድ እውነቶችን እንድትመለከቱ ሊያደርጓችሁ ይችላሉ።

ለምሳሌ፣ መጽሐፍ ቅዱስ እውነተኛ ክርስቲያኖች “በጌታ” ብቻ እንዲያገቡ የሚሰጠውን ምክር እንድታስቡበት ጠንከር አድርገው ይመክሯችሁ ይሆናል። (1 ቆሮንቶስ 7:39) ምናልባት አማኝ ያልሆነ ሰው አግብተው በአሁኑ ጊዜ በደስታ ይሖዋን የሚያገለግሉ ክርስቲያኖች እንዳሉ በመናገር ሐሳባቸውን ትቃወሙ ይሆናል። እንዲህ ዓይነት ሁኔታ እንደተከሰተ አይካድም። ሆኖም እንዲህ የመሰሉ አጋጣሚዎች በጣም ጥቂት ናቸው። እምነታችሁን የማይጋራ ሰው ብታገቡ የይሖዋን የሥነ ምግባር መሥፈርቶች ችላ ከማለትም አልፋችሁ ራሳችሁን ለከፋ መንፈሳዊ አደጋ ታጋልጣላችሁ።—2 ቆሮንቶስ 6:14 *

ለማግባት ምክንያት የማይሆኑ ነገሮች

አንዳንድ ወጣቶች የጾታ ብልግና ከፈጸሙ በኋላ ኮብልለው መጋባታቸው ሕሊናቸውን እንደሚያሳርፈው ይሰማቸዋል። ወይም ያልታሰበ እርግዝናን የመሰለ የኃጢአታቸውን ውጤት ይሸፍንልናል ብለው በማሰብ ይጋባሉ።

ኃጢአታችሁን ለመሸፈን ብላችሁ የምታገቡ ከሆነ በስህተታችሁ ላይ ተጨማሪ ስህተት እየሠራችሁ ነው። ሰሎሞን “ኀጢአቱን የሚሰውር አይለማም፤ የሚናዘዝና የሚተወው ግን ምሕረትን ያገኛል” በማለት አስጠንቅቋል። (ምሳሌ 28:13) የሰሎሞን አባትና እናት የሆኑት ዳዊትና ቤርሳቤህ የፈጸሙትን የጾታ ብልግና ለመሸፋፈን ያደረጉት ሙከራ ሞኝነት መሆኑን ተገንዝበዋል። (2 ሳሙኤል 11:2 እስከ 12:25) የሠራችሁትን ኃጢአት ከመሸፋፈን ይልቅ ለወላጆቻችሁና ለጉባኤ ሽማግሌዎች ንገሯቸው። ይህ ድፍረት ቢጠይቅባችሁም ከልባችሁ ከተጸጸታችሁ ይሖዋ ይቅር እንደሚላችሁ እርግጠኛ መሆን ትችላላችሁ። (ኢሳይያስ 1:18) እንደገና ንጹሕ ሕሊና ካገኛችሁ በኋላ ስለትዳር ሚዛናዊ የሆነ ውሳኔ ለማድረግ የተሻለ ሁኔታ ይኖራችኋል።

ለጸጸት የማይዳርግ ውሳኔ

አለን የሠርጉን ቀን መለስ ብሎ ሲያስበው እንዲህ ይላል:- “ሠርጋችን ቀለል ያለ እንዲሆን ያደረግነው ውሳኔ ውጥረታችንን በመጠኑም ቢሆን ቀንሶልናል። የምቆጭበት ብቸኛው ነገር ቤተሰቦቼ ያደረግነውን ውሳኔ እንዲረዱልን አለማድረጌ ነው።”

በእርግጥም የጎለመሱ ተጋቢዎች ሠርጋቸውን በባሕሉ መሠረት ማድረግ አለማድረጋቸው የራሳቸው ምርጫ ነው። ሆኖም ከጋብቻ ጋር የተያያዙ ምንም ዓይነት ውሳኔዎችን ስታደርጉ አትቸኩሉ፣ ከቤተሰቦቻችሁ ጋር ተነጋገሩ እንዲሁም ‘እርምጃችሁን አስተውሉ።’ እንዲህ በማድረግ ለጸጸት ሊዳርጓችሁ የሚችሉ ነገሮችን ትቀንሳላችሁ።—ምሳሌ 14:15

[የግርጌ ማስታወሻዎች]

^ አን.3 ስሞቹ ተቀይረዋል።

^ አን.7 እነዚህ የአምልኮ ቦታዎች ለይሖዋ ምሥክሮች ሠርግ አመቺ ቦታ ናቸው። የሠርግ ሥነ ሥርዓቱ ቀለል ያለ ሲሆን በመጽሐፍ ቅዱስ መሠረታዊ ሥርዓቶች መሠረት ጥሩ ጋብቻ ለመመሥረት የሚያስችል አጠር ያለ ንግግር ይቀርባል። የመንግሥት አዳራሻቸውን ለመጠቀም ክፍያ አይጠየቅም።

^ አን.18 በዚህ ርዕሰ ጉዳይ ላይ ይበልጥ ዝርዝር ማብራሪያ ለማግኘት መጠበቂያ ግንብ ሐምሌ 1, 2004 ገጽ 30-31⁠ን እና ኅዳር 1, 1989 ገጽ 18-22ን (እንግሊዝኛ) ተመልከት።

[በገጽ 20 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

ከጋብቻ ጋር የተያያዙ ምንም ዓይነት ውሳኔዎችን ስታደርጉ ከቤተሰቦቻችሁ ጋር ተነጋገሩ