በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

ሳይንስና መጽሐፍ ቅዱስ የሕይወትን ትርጉም እንዳገኝ ረድተውኛል

ሳይንስና መጽሐፍ ቅዱስ የሕይወትን ትርጉም እንዳገኝ ረድተውኛል

ሳይንስና መጽሐፍ ቅዱስ የሕይወትን ትርጉም እንዳገኝ ረድተውኛል

በርንት ኦልሽላግል እንደተናገረው

የሕይወትን ትርጉም ለማግኘት 20 ዓመታት ፈጅቶብኛል። በዚህ ረገድ እንዲሳካልኝ የረዱኝ ሳይንስና መጽሐፍ ቅዱስ ናቸው። ሳይንስ ማጥናቴ ሕይወት ትርጉም ሊኖረው ይገባል ብዬ እንዳምን አድርጎኛል፤ መጽሐፍ ቅዱስ ደግሞ ይህን ትርጉም የገለጠልኝ ከመሆኑም በላይ በደንብ እንድረዳው አስችሎኛል።

አንዳንድ ሰዎች ሳይንስና መጽሐፍ ቅዱስ እንደሚጋጩ ሲናገሩ ሰምታችሁ ይሆናል። እኔ ሁለቱንም አጥንቻለሁ፤ ሆኖም በእነዚህ ሰዎች አባባል አልስማማም። ለምን እንደዚህ እንዳልኩ ለማወቅ ትፈልጉ ይሆናል።

በደቡብ ጀርመን በምትገኘው በሽቱትጋርት ከተማ በ1962 ተወለድኩ። አባቴ በማሽን ንድፍ አውጪነት ሥራ ላይ ተሠማርቶ የነበረ ሲሆን እርሱና እናቴ በቤተ ክርስቲያን ውስጥ ንቁ ተሳትፎ ያደርጉ ነበር። በአራት ዓመት የምትበልጠኝ ካሪን የምትባል እህት አለችኝ። ልጅ ሳለሁ አባቴ ሳይንሳዊ ሙከራ እንዳደርግበት ያመጣልኝ መጫወቻ በሕይወቴ ውስጥ ትልቅ መሠረት ጥሎልኛል። በዚህ ስጦታ አማካኝነት ቀላል የሆኑ የኬሚስትሪና የፊዚክስ ሙከራዎችን በመሥራት እጫወት ነበር። አዎን፣ መማር ያስደስተኝ ነበር።

ከጊዜ በኋላ ከዚህ መጫወቻ ወደ ኮምፒውተር ተሸጋገርኩ። ገና በአሥራዎቹ ዕድሜ ውስጥ እያለሁ እንኳ በጣም ምርጥ የሚባለው ኮምፒውተር አንጎላችን መሆኑን ተገንዝቤ ነበር። ይሁን እንጂ ‘አንጎል ሊኖረን የቻለው እንዴት ነው? አንጎልን የሰጠን ማን ነው? የሕይወትስ ትርጉም ምንድን ነው?’ የሚሉት ጥያቄዎች በአእምሮዬ ውስጥ ይጉላሉ ነበር።

ከፍተኛ ትምህርት መከታተል

በ16 ዓመቴ ትምህርቴን ከጨረስኩ በኋላ በአንድ ፎቶ ላብራቶሪ ውስጥ ረዳት ሆኜ በተለማማጅነት መሥራት ጀመርኩ። ትምህርት በጣም ያስደስተኝ ስለነበር ዩኒቨርሲቲ ገብቼ ፊዚክስ የማጥናት ግብ ነበረኝ። ይሁን እንጂ ዩኒቨርሲቲ መግባት በጣም ረጅም ጊዜ ይወስድ ነበር። ለመግባት የሚያስችለኝን ብቃት ለማሟላት ብቻ እንኳ አምስት ዓመታት ፈጅቶብኛል። በ1983 የዩኒቨርሲቲ ትምህርቴን በሽቱትጋርት የጀመርኩ ሲሆን ሙኒክ ሄጄ ጥናቴን ቀጠልኩ። በመጨረሻም በ1993 በኦውግስበርግ ዩኒቨርሲቲ የፊዚክስ ዶክትሬቴን አገኘሁ።

በዩኒቨርሲቲ ያሳለፍኳቸው የመጀመሪያዎቹ ዓመታት ቀላል አልነበሩም። ትምህርት የሚሰጥበት አዳራሽ ብዙውን ጊዜ 250 በሚያህሉ ተማሪዎች ይሞላ ነበር፤ ይሁን እንጂ አብዛኞቹ በጥቂት ወራት ውስጥ አቋርጠው ወጡ። እኔ ግን የጀመርኩትን ለመጨረስ ቆርጬ ነበር። እዚያው ዩኒቨርሲቲ ውስጥ እኖር ስለነበር ተድላ ከሚያሳድዱ ብዙ ተማሪዎች ጋር ገጠምኩ። እንደነዚህ ካሉት ተማሪዎች ጋር መግጠሜ መጥፎ ተጽዕኖ አሳድሮብኝ ነበር። በዚህ ምክንያት መረን ወደ ለቀቁ ጭፈራ ቤቶች መሄድና አደንዛዥ ዕፅ መውሰድ ጀመርኩ።

የሕይወትን ትርጉም ለማወቅ ወደ ሕንድ ሄድኩ

ፊዚክስ በማጥናቴ የአጽናፈ ዓለምን የተፈጥሮ ሕጎች በተመለከተ ጥልቅ እውቀት አግኝቻለሁ። ይዋል ይደር እንጂ ሳይንስ የሕይወትን ትርጉም ይገልጥልኛል የሚል ተስፋ ነበረኝ። ይሁን እንጂ ፊዚክስ የሕይወትን ትርጉም ሊያሳውቀኝ እንደማይችል ተረዳሁ። በ1991 የሩቅ ምሥራቆችን የማሰላሰያ ዘዴ ለመማር ከአንድ ቡድን ጋር ወደ ሕንድ ተጓዝኩ። አገሪቷንም ሆነ ሕዝቦቿን የመመልከት አጋጣሚ በማግኘቴ በእጅጉ ተደስቻለሁ! ሆኖም በሀብታሙና በድሃው መካከል ያለው የኑሮ ልዩነት በጣም አስደነገጠኝ።

ለምሳሌ ያህል፣ ፑን በምትባል ከተማ አቅራቢያ ወደሚኖር አንድ የሂንዱ እምነት አስተማሪ ጋር ሄደን ነበር። ይህ አስተማሪ ‘አንድ ሰው ትክክለኛውን የማሰላሰል ዘዴ መማሩ ሀብታም እንዲሆን ይረዳዋል’ የሚል እምነት ነበረው። እዚህ ሰው ጋር በየቀኑ ማለዳ ላይ እየተነሳን በቡድን ሆነን እናሰላስል ነበር። በተጨማሪም ይህ የሃይማኖት አስተማሪ ባሕላዊ መድኃኒቶችን በከፍተኛ ዋጋ ይሸጥ ነበር። ብዙ ገንዘብ እንደሚያገኝ ከአኗኗሩ መረዳት ይቻላል። በአንጻሩ ግን የዚሁ እምነት አባል የሆኑ ብዙ መነኮሳት በድህነት ተቆራምደው ሲኖሩ ተመልክተናል። ከዚህ የተነሳ ‘ማሰላሰል እነዚህን መነኮሳት ጭምር ለምን ሀብታም አላደረጋቸውም?’ እያልኩ ራሴን እጠይቅ ጀመር። ወደ ሕንድ መሄዴ እነዚህን የመሳሰሉ ሌሎች ብዙ ጥያቄዎችን አስነስቶብኛል።

ከሕንድ ካመጣኋቸው ማስታወሻዎች መካከል ለማሰላሰያነት የሚያገለግል አንድ ደወል ይገኝበታል። ደወሉ በአግባቡ ከተመታ በትክክል እንዳሰላስል የሚረዳኝ የሙዚቃ ቃና እንደሚያመጣልኝ ተነግሮኝ ነበር። ወደ ጀርመን ከተመለስኩ በኋላ ደግሞ የወደፊት ዕጣህን እነግርሃለሁ ይለኝ የነበረ አንድ ሰው የሠራውን የኮከብ ቆጠራ ቻርት ገዛሁ። ይሁን እንጂ ማሰላሰሌ ስለ ሕይወት ትርጉም ያሳወቀኝ አንዳች ነገር አልነበረም። የኮከብ ቆጠራ ቻርቱም ቢሆን ምንም እርባና የሌለው ተራ ወረቀት እንደሆነ ተረዳሁ። ስለዚህ የሕይወትን ትርጉም በተመለከተ ላሉኝ ጥያቄዎች መልስ ሳላገኝ ቀረሁ።

ከመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ መልስ አገኘሁ

በ1993 በሕይወቴ ውስጥ ለውጥ እንዳደርግ የሚያነሳሳ አንድ ያልጠበቅኩት ነገር አጋጠመኝ። በዚህ ወቅት ጥናቴንም ሆነ የምርምር ሥራዬን ጨርሼ በኳንተም ፊዚክስ ላይ የመመረቂያዬን ጽሑፍ እያዘጋጀሁ ነበር። የማስረከቢያው ቀን ከመድረሱ በፊት ጽሑፉን አዘጋጅቼ ለመጨረስ ስል ሁሉን ነገር ትቼ ሌት ተቀን እሠራ ነበር። ይሁን እንጂ አንድ ቀን ከሰዓት በኋላ ድንገት በሬ ተንኳኳ። በሩን ስከፍት ሁለት ሴቶች ቆመው ነበር።

“በመጽሐፍ ቅዱስ መሠረት 1914 ከሌሎቹ ዓመታት የተለየ ዓመት መሆኑን ታውቃለህ?” ብለው ጠየቁኝ። ጥያቄያቸው በጣም አስደነቀኝ። እንደዚህ ዓይነት ነገር ሰምቼ የማላውቅ ከመሆኑም በላይ ስለዚህ ጉዳይ ለማሰብ ጊዜውም አልነበረኝም። ይሁን እንጂ ጥያቄው ትኩረቴን ሳበው። መጽሐፍ ቅዱስ ከብዙ ዓመታት በፊት 1914ን የተለየ ዓመት አድርጎ ገልጾታል ለማለት የቻሉት እንዴት ነው?

“ስለዚህ ጉዳይ ይበልጥ ለማወቅ ትፈልጋለህ?” አሉኝ። ‘ምን እንደሚሉ ብሰማ በንግግራቸው መሃል የሚጋጩ ሐሳቦችን ማግኘቴ አይቀርም’ ብዬ አሰብኩ። ይሁን እንጂ የሚቃረኑ ሐሳቦችን ሳይሆን የመጽሐፍ ቅዱስን ተዓማኒነት የሚያረጋግጥ አሳማኝ ነጥብ አገኘሁ። ወደፊት ምድርን ሁሉ የሚያስተዳድረው የአምላክ መሲሐዊ መንግሥት በ1914 በሰማይ መቋቋሙን መጽሐፍ ቅዱስ በግልጽ እንደሚናገር ተማርኩ። *

እነዚህ ሴቶች የይሖዋ ምሥክሮች ነበሩ፤ ውይይት ካደረግን በኋላ በምድር ላይ በገነት ለዘላለም መኖር ትችላለህ የሚለውን መጽሐፍ ሰጥተውኝ ሄዱ። * መጽሐፉን በጥቂት ቀናት ውስጥ ያነበብኩት ሲሆን በውስጡ ያለው ሁሉ ግልጽና ምክንያታዊ መሆኑን ተረዳሁ። እነዚያ የይሖዋ ምሥክሮች ሰዎች ገነት በሆነች ምድር ላይ ለዘላለም እንዲኖሩ የይሖዋ ፈቃድ እንደሆነ ከመጽሐፍ ቅዱስ አሳዩኝ። መጽሐፍ ቅዱስ በትንቢት እንደሚናገረው ይህ ተስፋ በቅርብ ጊዜ እውን ይሆናል። ስለ ወደፊቱ ጊዜ እንዴት ያለ አስደሳች ተስፋ ተሰጥቷል! ልቤ በተስፋው ስለተነካ ዓይኖቼ እንባ አቀረሩ። ላለፉት 20 ዓመታት ስፈልገው የኖርኩት ነገር ይህ ይሆን?

የመኖሬ ዓላማ ይሖዋ አምላክን ማወቅና በሙሉ ልብ እርሱን ማገልገል እንደሆነ ለመረዳት ጊዜ አልወሰደብኝም። የምማረው ነገር እውነት መሆኑን ስለተረዳሁ ከይሖዋ ምሥክሮች ጋር መጽሐፍ ቅዱስ ማጥናቴን ቀጠልኩ። ለመንፈሳዊ ጉዳዮች ያለኝ ጥማት ፈጽሞ አልረካም ነበር። ከሦስት ወር በኋላ የዶክትሬት መመረቂያዬን ጽሑፍ ሳስረክብ መጽሐፍ ቅዱስን ግማሽ ለግማሽ አንብቤ ነበር።

ከመልስ ያለፈ ነገር አገኘሁ

በግንቦት 1993 የይሖዋ ምሥክሮች ኦውግስበርግ በሚገኘው የመንግሥት አዳራሽ በሚያደርጉት ስብሰባ ላይ ለመጀመሪያ ጊዜ ተገኘሁ። በዚያ የሰማኋቸው ትምህርቶች የእውነትን መልእክት የሚያስተጋቡ ነበሩ። ከዚህም በላይ በይሖዋ ምሥክሮች መካከል ስገኝ ባይተዋርነት አልተሰማኝም። አዲስ ሰው ብሆንም እንኳ ሞቅ ያለ ሰላምታ በመስጠት ጥሩ አቀባበል አድርገውልኛል። አጠገቤ ተቀምጠው የነበሩ አንዲት አረጋዊት እህት የመዝሙር መጽሐፍ ፈልገው አመጡልኝ። በቀጣዮቹ ሳምንታት ደግሞ አንድ የይሖዋ ምሥክርና ልጁ በመኪናቸው ወደ መንግሥት አዳራሽ ይወስዱኝ ነበር። ብዙም ሳይቆይ እነዚህ አዳዲስ ወዳጆቼ ቤታቸው ይጋብዙኝ ጀመር። ከጊዜ በኋላ የሕይወትን ትርጉም በተመለከተ የተማርኩትን ነገር ለሌሎች ማካፈል እንዳለብኝ ተሰማኝ።

ከመጽሐፍ ቅዱስ የተማርኳቸውን ነገሮች በሥራ ላይ እያዋልኩ ስመጣ በሕይወቴ ላይ ለውጥ ማድረግ ጀመርኩ። ለምሳሌ ያህል፣ ከአስማት ጋር የተገናኙ ዕቃዎች ሊኖሩኝ እንደማይገባ ወሰንኩ። ስለዚህ ከኮከብ ቆጠራ ጋር የተያያዙ ነገሮችንም ሆነ የማሰላሰያ ደወሉን ከሕንድ ካመጣኋቸው ሌሎች ሃይማኖታዊ ማስታወሻዎች ጋር አስወገድኳቸው። መጽሐፍ ቅዱስ ማጥናቴን በመቀጠል ራሴን ለአምላክ ወሰንኩ፤ ከዚያም በሰኔ ወር 1994 ሙኒክ ውስጥ ተጠምቄ የይሖዋ ምሥክር ሆንኩ። የሕይወትን ትክክለኛ ትርጉም በደንብ የተረዳሁት በዚህ መንገድ ነበር።

በመስከረም 1995 የይሖዋ ምሥክሮች የሙሉ ጊዜ አገልጋይ ወይም አቅኚ ሆንኩ። ይህም ሲባል ብዙ ጊዜዬን ከሰዎች ጋር ስለ አምላክ ዓላማዎች በመነጋገር አሳልፋለሁ ማለት ነው። ይህን የማደርገው ይሖዋ በሚሰጠው ኃይል በመታመን ነው። ብዙውን ጊዜ በአገልግሎት ላይ ረጅም ሰዓታት አሳልፌ ማታ ወደ ቤት ስገባ ይሖዋን ከማወቄ በፊት ተሰምቶኝ የማያውቅ ከፍተኛ የደስታና የእርካታ ስሜት ይሰማኛል። በጥር 1997 አሁን በምኖርበት ዜልተርስ፣ ጀርመን በሚገኘው የይሖዋ ምሥክሮች ቅርንጫፍ ቢሮ (ቤቴል ይባላል) የሙሉ ጊዜ አገልግሎቴን እንድቀጥል ተጋበዝኩ። ወላጆቼ ብዙ ጊዜ እየመጡ ይጠይቁኛል፤ እምነቴን ባይጋሩም እንኳ ለቤቴል አክብሮት ያላቸው ሲሆን እዚህ በመሆኔ ደስተኞች ናቸው።

ሳይንስና መጽሐፍ ቅዱስ

አንዳንድ ሰዎች፣ ለረጅም ዓመታት ሳይንስ ያጠና ሰው መጽሐፍ ቅዱስን እንዴት ሊያምን ይችላል? ብለው ይጠይቁ ይሆናል። እንደ እውነቱ ከሆነ ሳይንስና መጽሐፍ ቅዱስ እንደሚጋጩ የሚያሳይ ነገር አላገኘሁም። የፊዚክስ ሊቅ እንደመሆኔ መጠን ሕይወት የሚመራባቸውን ሕግጋት አጥንቻለሁ፤ እነዚህ ሕግጋት ከሰው ልጆች አእምሮ እጅግ የላቀ የማሰብ ችሎታ ያለው አካል ለመኖሩ ማስረጃ ይሆናሉ።

ለምሳሌ በፊዚክስ፣ በኬሚስትሪ እና በባዮሎጂ ትምህርቶች ውስጥ ብዙ ንድፈ ሐሳቦች አሉ። እነዚህ ንድፈ ሐሳቦች ቀላል ቢሆኑ እንኳ ከእነርሱ ጋር ተያይዞ የሚመጣው የሒሳብ ቀመር በጣም ውስብስብ ሊሆን ይችላል። ከፍተኛ ችሎታ ያላቸው ሳይንቲስቶች አንድ ዓይነት አዲስ ንድፈ ሐሳብ በሚያወጡበት ጊዜ የኖቤል ተሸላሚዎች ይሆናሉ። ሳይንቲስቶች ለመረዳት ብርቱ ትግል የሚያደርጉለትን አጽናፈ ዓለም የነደፈውና ወደ ሕልውና ያመጣው አካል እጅግ የላቀ ችሎታ እንደሚኖረው ምንም ጥርጥር የለውም!

ብዙ የዝግመተ ለውጥ አራማጆች እንደሚሉት ሕይወት በአጋጣሚ መጣ ብሎ ማሰብ ከእውነታው እጅግ መራቅ ነው። ነገሩን በምሳሌ ለማስረዳት ያህል፣ በአንድ የእግር ኳስ ሜዳ ላይ አሥር ኳሶችን በየአንድ ሜትር ርቀት ቀጥ አድርጋችሁ ደርድሯቸው። ከዚያም በመጀመሪያው ኳስ ሁለተኛውን በመምታት ሁሉም በተከታታይ እንዲመታቱ ለማድረግ ሞክሩ። ከዚህም በላይ እያንዳንዱ ኳስ መጨረሻ ላይ የት ደርሶ እንደሚቆም ገምቱ። ብዙ ሰዎች ፈጽሞ እንደማይሳካ ስለሚሰማቸው መሞከር እንኳ አይፈልጉም።

ሐቁ ይህ ሆኖ ሳለ በተርታ የተቀመጡ ኳሶችን እርስ በርስ ከማመታታት ይበልጥ እጅግ ውስብስብ የሆነው የሰው ሕዋስ ሕይወት ከሌለው ነገር ተነስቶ እንዲሁ በአጋጣሚ እዚህ ደረጃ ላይ ይደርሳል ማለት ይቻላል? ለዚህ ከምንም ይበልጥ ምክንያታዊ የሚሆነው ማብራሪያ ሰዎችንም ሆነ በምድር ውስጥ ያሉ ሌሎች ሕያዋን ነገሮችን የፈጠረው ከሁሉ የላቀ የማሰብ ችሎታ ያለው አካል እንደሆነ የሚገልጸው ነው። ፈጣሪ የሆነው ይህ አካል ሕያዋን ነገሮችን የፈጠረው ያለምንም ዓላማ ነው? አይደለም። አንድ ዓላማ ኖሮት መሆን አለበት፤ መጽሐፍ ቅዱስ ደግሞ ይህን ዓላማ መረዳት በምንችልበት መንገድ ገልጾልናል።

ከዚህ መመልከት እንደምትችሉት ሳይንስና መጽሐፍ ቅዱስ ሕይወትን በተመለከተ ለረጅም ጊዜ ስጠይቀው ለቆየሁት ጥያቄ መልስ እንዳገኝ ረድተውኛል። ከ20 ለሚበልጡ ዓመታት ስትፈልጉት የቆያችሁትን ነገር ስታገኙ ሊሰማችሁ የሚችለውን ከፍተኛ እርካታና ደስታ እስቲ ገምቱ? ሌሎች በርካታ ሰዎች ልክ እንደ እኔ የሕይወትን ትርጉም እንዲያውቁ እንዲሁም ብቻውን እውነተኛ አምላክ የሆነውን ይሖዋን በትክክለኛው መንገድ እንዲያመልኩ አቅሜ በፈቀደው ሁሉ ለመርዳት ልባዊ ጥረት አደርጋለሁ!

[የግርጌ ማስታወሻዎች]

^ አን.17 በዚህ ጉዳይ ላይ ተጨማሪ ማብራሪያ ለማግኘት በይሖዋ ምሥክሮች በተዘጋጀው ወደ ዘላለም ሕይወት የሚመራ እውቀት በተባለው መጽሐፍ፣ ምዕራፍ 10 ገጽ 90-97 ላይ የሚገኘውን “የአምላክ መንግሥት መግዛት ጀምሯል” የሚለውን ርዕስ ተመልከት።

^ አን.18 በይሖዋ ምሥክሮች የተዘጋጀ። አሁን ግን መታተም አቁሟል።

[በገጽ 14 ላይ የሚገኝ የተቀነጨበ ሐሳብ]

የፊዚክስ ሊቅ እንደመሆኔ መጠን ሕይወት የሚመራባቸውን ሕግጋት አጥንቻለሁ፤ እነዚህ ሕግጋት ከሰው ልጆች አእምሮ እጅግ የላቀ የማሰብ ችሎታ ያለው አካል ለመኖሩ ማስረጃ ይሆናሉ

[በገጽ 12 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

የ12 ዓመት ልጅ ሳለሁ

[በገጽ 13 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

በሩቅ ምሥራቆች የማሰላሰል ዘዴ አማካኝነት የሕይወትን ትርጉም ለማግኘት ጥረት አድርጌ ነበር

[በገጽ 15 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

ለሰዎች መስበክ እውነተኛ ደስታና እርካታ አስገኝቶልኛል

[ምንጭ]

የመጽሐፉ ሽፋን ላይ ያለው ፎቶ:- J. Hester and P. Scowen (AZ State Univ.), NASA