በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

በሰው ልጅ ታሪክ ከተከሰቱት ሁሉ የከፋው ወረርሽኝ

በሰው ልጅ ታሪክ ከተከሰቱት ሁሉ የከፋው ወረርሽኝ

በሰው ልጅ ታሪክ ከተከሰቱት ሁሉ የከፋው ወረርሽኝ

በጥቅምት 1918 አንደኛው የዓለም ጦርነት ገና አላቆመም ነበር። በወቅቱ ውጊያው ወደ ማብቃቱ ቢቃረብም በየአገሩ ዜናዎችን ሳንሱር ማድረግ አልቀረም። በመሆኑም በየአካባቢው በርካታ ቁጥር ያላቸው ሲቪሎች እየታመሙና እየሞቱ መሆኑ የሚዘገበው በጦርነቱ ውስጥ ባልገባችው በስፔን ብቻ ነበር። በዚህም ምክንያት በሽታው ስፓኒሽ ፍሉ (የኅዳር በሽታ) የሚለውን የዘላለም መጠሪያውን አገኘ።

በዓለም ዙሪያ የተከሰተው ይህ ወረርሽኝ የጀመረው መጋቢት 1918 ነው። ስለ በሽታው ያጠኑ በርካታ ተመራማሪዎች የኅዳር በሽታ ለመጀመሪያ ጊዜ የታየው ዩናይትድ ስቴትስ ውስጥ በካንሳስ ግዛት እንደሆነ ያምናሉ። ከዚያም የዩናይትድ ስቴትስ ወታደሮች በሽታውን ወደ ፈረንሳይ ይዘው እንደገቡ ይገመታል። በኅዳር በሽታ በድንገት የሚሞቱት ሰዎች ቁጥር ቢያሻቅብም ሐምሌ 1918 ላይ ያ አስከፊ ሁኔታ ያቆመ ይመስል ነበር። በጊዜው ሐኪሞች ዓለም አቀፉ ወረርሽኝ የሰው ልጆችን እንደ ቅጠል ለማርገፍ የሚያስችለውን ኃይል እያሰባሰበ መሆኑ ፈጽሞ አልገባቸውም ነበር።

አንደኛው የዓለም ጦርነት ኅዳር 11, 1918 ሲያበቃ የምድር ሕዝብ በጣም ተደስቶ ነበር። የሚገርመው ቸነፈሩ በመላው ዓለም የተከሰተው በዚያኑ ጊዜ ነበር ለማለት ይቻላል። በሽታው በአሰቃቂ ሁኔታ ይገድል ስለነበር በዓለም ዙሪያ ሰፊ የዜና ሽፋን ተሰጥቶት ነበር። በሽታው ያልያዛቸው ጥቂት ሰዎች ቢኖሩም እንኳን በሁሉም ሰው ላይ ፍራቻ ነገሠ። ስለ በሽታው የዘገበ አንድ የታመነ ምንጭ “በዩናይትድ ስቴትስ የነበረው አማካይ የዕድሜ ጣራ በ1918 ከ10 ዓመት በላይ ቀንሶ ነበር” ብሏል። ይህ ቸነፈር ከሌሎቹ የሚለየው በምንድን ነው?

ልዩ የሆነ ቸነፈር

በጣም ትልቁ ልዩነት በሽታው ጊዜ ሳይሰጥ ወዲያውኑ የሚገድል መሆኑ ነው። ምን ያህል አጣዳፊ ነበር? ዘ ግሬት ኢንፍሉዌንዛ በተባለ በቅርቡ በወጣ መጽሐፍ ላይ ጆን ቤሪ የሚባሉ ደራሲ በሽታው ጊዜ ሳይሰጥ ወዲያው የሚገድል መሆኑን በተመለከተ በጽሑፍ የሰፈረ አንድ ዘገባ ጠቅሰው እንዲህ ብለዋል:- “ሲሮ ቪዬረ ዳ ኩንያ የተባለ አንድ የሕክምና ተማሪ በሪዮ ዲ ዤኔሮ የከተማ ባቡር እየጠበቀ ሳለ አንድ ሰው ወደ እርሱ ቀርቦ እርጋታ በተሞላበት አነጋገር ጥያቄ ከጠየቀው በኋላ ወደቀና ሞተ፤ በኬፕ ታውን፣ ደቡብ አፍሪካ ይኖር የነበረ ቻርልስ ሉዊስ የተባለ ሰው አምስት ኪሎ ሜትር ርቀት ላይ ወደሚገኘው ቤቱ ለመጓዝ የከተማ ባቡር እንደተሳፈረ ትኬት ቆራጩ ወደቀና ሞተ። ይህ ሰው የሚወርድበት ቦታ እስኪደርስ ሹፌሩን ጨምሮ በዚያ ባቡር ላይ የነበሩ ስድስት ሰዎች ሞተዋል።” ሁሉም የሞቱት በኅዳር በሽታ ነው።

ሌላው ልዩ የሚያደርገው ነገር የበሽታው ምንነት አለመታወቁ የፈጠረው ፍርሃት ነው። ሳይንቲስቶች የበሽታውን መንስኤም ሆነ የሚሰራጭበትን መንገድ አላወቁም ነበር። የሕዝቡን ጤና ለመጠበቅ ሲባል አንዳንድ እርምጃዎች ተወሰዱ:- በወደቦች መግባትና መውጣት ተከለከለ፤ እንዲሁም ፊልም ቤቶች፣ አብያተ ክርስቲያናትና ሌሎች ሕዝብ የሚሰበሰብባቸው ቦታዎች ተዘጉ። ለምሳሌ ያህል በካሊፎርኒያ፣ ዩናይትድ ስቴትስ በምትገኘው ሳንፍራንሲስኮ ከተማ ሁሉም ነዋሪ በፋሻ የተሠራ አፍንጫንና አፍን የሚሸፍን ጭምብል እንዲያደርግ ባለ ሥልጣናት አዝዘው ነበር። ይህንን ሳያደርግ መንገድ ላይ የተገኘ ማንኛውም ሰው ቅጣት ወይም እስር ይጠብቀው ነበር። ነገር ግን የትኛውም ዘዴ መፍትሔ አላስገኘም። የተወሰዱት እርምጃዎች በቂ ካለመሆናቸውም በላይ በጣም ዘግይተው ስለነበር የበሽታውን ስርጭት መግታት አልተቻለም።

በሽታውን አስፈሪ ያደረገው ሌላው ነገር ማንንም ሳይመርጥ የሚያጠቃ መሆኑ ነው። በ1919 የተከሰተው ዓለም አቀፍ ወረርሽኝ እስከ አሁን ባልታወቀ ምክንያት በዋነኝነት ያጠቃውና የገደለው በዕድሜ የገፉ ሰዎችን ሳይሆን ጤናማ ወጣቶችን ነበር። በኅዳር በሽታ የሞቱት አብዛኞቹ ሰዎች በ20 እና በ40 ዓመት የዕድሜ ክልል ውስጥ የሚገኙ ናቸው።

ከዚህም በላይ በሽታው ዓለም አቀፍ ወረርሽኝ ነበር። በሽታው በሐሩር ክልል በሚገኙ ደሴቶች ሳይቀር ተከስቷል። ኅዳር 7, 1918 በሽታው ወደ ዌስተርን ሳሞአ (በአሁኑ ጊዜ ሳሞአ ትባላለች) በመርከብ የገባ ሲሆን በሁለት ወር ጊዜ ውስጥ ከ38,302 ነዋሪዎች መካከል 20 በመቶ የሚሆኑት አልቀዋል። ሁሉም አገራት በበሽታው ክፉኛ ተጠቅተዋል!

በተጨማሪም ይህ መቅሰፍት ያስከተለው እልቂት መጠነ ሰፊ ነበር። ለምሳሌ ያህል በሽታው ቀድሞ ያጠቃውና ከፍተኛ ጉዳት ያደረሰው በፔንስልቬንያ፣ ዩናይትድ ስቴትስ በምትገኘው በፊላዴልፊያ ነው። በጥቅምት 1918 አጋማሽ ላይ ከፍተኛ የሬሳ ሣጥን እጥረት ተከስቶ ነበረ። አልፍሬድ ክሮስቢ የተባሉ የታሪክ ተመራማሪ እንዲህ በማለት ተናግረዋል:- “አንድ ባለፋብሪካ 5,000 የሬሳ ሣጥኖች ቢኖሩት ኖሮ በሁለት ሰዓት ውስጥ መሸጥ ይችል እንደነበረ ተናግሯል። አንዳንድ ጊዜ በከተማው ባለው የሬሳ ማቆያ ቤት ውስጥ የሚገኘው አስከሬን ከሬሳ ሣጥኑ ቁጥር በአሥር እጥፍ ይበልጥ ነበር።”

የኅዳር በሽታ በሰው ዘር ታሪክ ውስጥ ከተከሰቱት ተመሳሳይ ዓለም አቀፍ ወረርሽኞች አንጻር ሲታይ በአጭር ጊዜ ውስጥ በርካታ ሰዎችን ጨርሷል። ብዙውን ጊዜ በዓለም ዙሪያ በበሽታው 21 ሚሊዮን ሰዎች እንደሞቱ ይገመት ነበር፤ አሁን አሁን ግን አንዳንድ ባለሙያዎች ይህ ግምት በጣም እንዳነሰ ይናገራሉ። በዛሬው ጊዜ የሚገኙ ስለ ወረርሽኝ በሽታዎች የሚያጠኑ አንዳንድ ባለሙያዎች በሽታው የገደላቸው ሰዎች 50 ሚሊዮን ምናልባትም 100 ሚሊዮን ሳይሆኑ እንደማይቀሩ ይገልጻሉ! ቀደም ሲል የተጠቀሱት ቤሪ “በአንድ ዓመት ውስጥ በበሽታው የሞቱት ሰዎች ቁጥር በመካከለኛው ዘመን የተከሰተው ጥቁሩ ሞት በአንድ መቶ ዓመት ከገደላቸው ሰዎች ቁጥር ይበልጣል፤ ኤድስ በሃያ አራት ዓመታት ውስጥ ከገደላቸው ሰዎች የኅዳር በሽታ በሃያ አራት ሳምንታት ውስጥ የገደላቸው ሰዎች ይበልጣሉ” ብለዋል።

ለማመን የሚያዳግት ቢሆንም፣ በኅዳር በሽታ የሞቱት አሜሪካውያን ቁጥር በሁለቱ የዓለም ጦርነቶች በውጊያ ላይ ከሞቱት ቁጥር ይበልጣል። ጂና ኮላታ የተባሉ አንዲት ደራሲ እንደሚከተለው ብለዋል:- “የዚያን ጊዜው ዓይነት ወረርሽኝ ዛሬ ቢከሰትና በመቶኛ ሲሰላ ያኔ ካለቀው ጋር የሚመጣጠን ሕዝብ ቢያልቅ 1.5 ሚሊዮን አሜሪካውያን ይሞታሉ፤ ይህ ደግሞ በአንድ ዓመት ውስጥ በልብ ሕመም፣ በካንሰር፣ በአንጎል ውስጥ ደም የመፍሰስ ችግር፣ ስር በሰደደ የሳምባ በሽታ፣ በኤድስና በኦልዛይመርስ በሽታዎች በአጠቃላይ ከሚሞቱት ሰዎች ቁጥር ይበልጣል።”

ጉዳዩን በአጭሩ ለማስቀመጥ ያህል፣ የኅዳር በሽታ በሰው ልጅ ታሪክ ውስጥ ከተከሰቱት ሁሉ የሚበልጥ አጥፊ የሆነ ዓለም አቀፍ ወረርሽኝ ነው። ሳይንስስ ምን እርዳታ አበርክቶ ነበር?

ችግሩ ከሳይንስ አቅም በላይ እንደሆነ ተረጋገጠ

አንደኛው የዓለም ጦርነት ሲጀምር የሕክምናው ሳይንስ በሽታዎችን በቁጥጥር ስር በማዋል ረገድ ታላቅ እመርታ ያሳየ ይመስል ነበር። በጦርነቱ ወቅት እንኳን ዶክተሮች ተላላፊ በሽታዎች የሚያስከትሉትን ጉዳት መቀነስ በመቻላቸው በጣም ተደስተው ነበር። በዚያን ጊዜ ሌዲስ ሆም ጆርናል የተባለው መጽሔት የአሜሪካ ቤቶች፣ የሞቱ ሰዎችን አስከሬን ወዳጅ ዘመዶች እንዲያዩ የሚደረግበት ክፍል እንደማያስፈልጋቸው ገልጾ ነበር። መጽሔቱ እነዚህ የሬሳ ማረፊያ ክፍሎች ከእንግዲህ ወዲህ ሳሎን ይባላሉ የሚል አስተያየት ሰጥቶ ነበር። ነገር ግን የኅዳር በሽታ ወዲያው ብቅ አለና ችግሩ ከሕክምናው ሳይንስ አቅም በላይ እንደነበረ ተረጋገጠ።

ታሪክ ተመራማሪው ክሮስቢ “በሕክምናው መስክ የታየው ውድቀት የሚለካው በሟቾች ቁጥር ከሆነ፣ በ1918 የነበሩት ሐኪሞች በሙሉ በታሪክ ዘመናት ሁሉ በሕክምናው ዘርፍ ለተከሰተው ውድቀት አስተዋጽኦ ካደረጉት ባለሙያዎች ተርታ ይሰለፋሉ” በማለት ጽፈዋል። ቤሪ ደግሞ የሕክምናውን መስክ ሙሉ በሙሉ ተወቃሽ ላለማድረግ የሚከተለውን አስተያየት ሰጥተዋል:- “በዚያን ጊዜ ሳይንቲስቶች በሽታው ምን ያህል አስፈሪ እንደነበረ በሚገባ ከመገንዘባቸውም በላይ በባክቴሪያዎች አማካኝነት ለሚይዝ የሳምባ ምች መድኃኒት አግኝተዋል፤ እንዲሁም በአሥር ሺዎች የሚቆጠሩ አሜሪካውያንን ሕይወት ለመታደግ የሚያስችሉ የጤና አጠባበቅ ምክሮችን ሰጥተዋል። የፖለቲካ ሰዎች ግን የተሰጠውን ምክር ችላ ብለው ነበር።”

ይሁንና ከ85 ዓመታት በፊት በዓለም ዙሪያ ተከስቶ ስለነበረው ስለዚህ አስከፊ ወረርሽኝ ዛሬ ምን የሚታወቅ ነገር አለ? የበሽታው መንስኤ ምንድን ነው? እንደገና ይከሰት ይሆን? እንደገና ቢቀሰቀስ በተሳካ ሁኔታ ልንቋቋመው እንችላለን? አንዳንዶቹ መልሶች በጣም ያስገርሙህ ይሆናል።

[በገጽ 6 ላይ የሚገኝ የተቀነጨበ ሐሳብ]

በኅዳር በሽታ የሞቱት አብዛኞቹ ሰዎች በ20 እና በ40 ዓመት የዕድሜ ክልል ውስጥ የሚገኙ ናቸው

[በገጽ 4 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

በአንድ ትምህርት ቤት የሚገኙ የአንድ ክፍል ተማሪዎች 1919፣ ካንየን ከተማ፣ ኮሎራዶ፣ ዩናይትድ ስቴትስ

[ምንጭ]

Courtesy, Colorado Historical Society, 10026787

[በገጽ 4, 5 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

ፖሊስ

[ምንጭ]

Photo by Topical Press Agency/Getty Images

[በገጽ 5 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

የመከላከያ ጭምብል ያጠለቁ የቤዝቦል ተጫዋቾች

[ምንጭ]

© Underwood & Underwood/CORBIS