በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

በአሁኑ ጊዜ ስለ ኢንፍሉዌንዛ ምን እናውቃለን?

በአሁኑ ጊዜ ስለ ኢንፍሉዌንዛ ምን እናውቃለን?

በአሁኑ ጊዜ ስለ ኢንፍሉዌንዛ ምን እናውቃለን?

ጊዜው 1997 ነበር። አንድ ሳይንቲስት ሱወርድ በሚባል በረዷማ የአላስካ ባሕረ ገብ ምድር በሚገኝ ብሬቪግ የተባለ አነስተኛ የኤስኪሞ መንደር ውስጥ ተቀምጧል። ሳይንቲስቱና ረዳቶቹ የሆኑ አራት ኤስኪሞዎች በረዶውን በመቆፈር ያወጡት የአንዲት ወጣት አስከሬን ከፊቱ ተጋድሟል። በ1918 በተከሰተው የኅዳር በሽታ የሞተችው የዚህች ወጣት አስከሬን ቆፍረው እስካወጡት ጊዜ ድረስ ሳይፈርስ በበረዶው ውስጥ ቆይቷል።

አስከሬኑን መመርመሩ ምን ጥቅም አለው? ሳይንቲስቱ ለበሽታው መንስኤ የሆነው ነገር በሳንባዋ ውስጥ ሊገኝ እንደሚችልና ይህንንም በጄኔቲካዊ የመመርመሪያ ዘዴዎች በመጠቀም ለይቶ ማውጣት እንዲሁም ምንነቱን ማወቅ እንደሚቻል አስቦ ነበር። ይህን ማወቁ ግን ምን ጥቅም አለው? የዚህን ጥያቄ መልስ ለማግኘት የቫይረሶችን ባሕርይና አደገኛ እንዲሆኑ የሚያደረጋቸው ምን እንደሆነ ማወቅ አለብን።

ሊገድል የሚችል ቫይረስ

ኢንፍሉዌንዛ የሚይዘው በቫይረስ ምክንያት እንደሆነ በአሁኑ ጊዜ ታውቋል፤ እንዲሁም ቫይረሱ ከሰው ወደ ሰው የሚተላለፈው በሽተኛው በሚያስልበት፣ በሚያስነጥስበትና በሚነጋገርበት ወቅት ከመተንፈሻ አካሉ የሚወጡ ፈሳሾች ሲረጩ እንደሆነ ግንዛቤ አለን። * በሽታው የሐሩር ክልሎችን ጨምሮ በዓለም ዙሪያ በዓመት ውስጥ በማንኛውም ጊዜ ሊከሰት ይችላል። በሰሜናዊው የዓለም ክፍል በአብዛኛው ኢንፍሉዌንዛ የሚኖረው ከኅዳር እስከ መጋቢት ባሉት ወራት ውስጥ ሲሆን በደቡባዊው የዓለም ክፍል ደግሞ ከሚያዝያ እስከ መስከረም ነው።

በጣም አደገኛ የሆነው የኢንፍሉዌንዛ ቫይረስ ታይፕ ኤ ኢንፍሉዌንዛ የሚባል ሲሆን ከሌሎች በርካታ ቫይረሶች ጋር ሲነጻጸር መጠኑ ትንሽ ነው። በአብዛኛው ክብ ቅርጽ የሚኖረው ይህ ቫይረስ አካሉ ላይ ጉጦች አሉት። በሰው ሴል ውስጥ ሲገባም ብዙውን ጊዜ በአሥር ሰዓታት ውስጥ ተባዝቶ ከ100,000 እስከ አንድ ሚሊዮን የሚደርሱ አዳዲስ የኢንፍሉዌንዛ ቫይረሶች ከሴሉ ይወጣሉ።

ይህን ቫይረስ አስፈሪ የሚያደርገው በፍጥነት የመቀየር ችሎታው ነው። ቫይረሱ በፍጥነት (ከኤድስ ቫይረስ በጣም በሚበልጥ ፍጥነት) ስለሚራባ ከተባዙት ውስጥ አብዛኞቹ መጀመሪያ ካስገኛቸው ቫይረስ ጋር አይመሳሰሉም። አንዳንዶቹ ፍጹም የተለዩ በመሆናቸው በሽታ ተከላካይ ሴሎቻችን አይለዩአቸውም። በየዓመቱ እንግዳ የሆነ ባሕርይ ባላቸው አዳዲስ የኢንፍሉዌንዛ ቫይረሶች የምንጠቃው ለዚህ ነው። ባሕርያቸውን በጣም የሚቀያይሩ ከሆነ ሰውነታችን ለይቶ ስለማያውቃቸው እርምጃ ሊወስድባቸው አይችልም፤ ይህም ዓለም አቀፍ ወረርሽኝ እንዲከሰት ምክንያት ሊሆን ይችላል።

ከዚህም በላይ የኢንፍሉዌንዛ ቫይረሶች እንስሳትንም ያጠቃሉ፤ ይህ ደግሞ በሰዎች ላይ የሚፈጥረው ችግር አለ። አሳማ፣ እንደ ዶሮና ዳክዬ ያሉ የወፍ ዝርያዎችን በሚይዘው ቫይረስ እንደሚጠቃ ይታመናል። ከዚህም በተጨማሪ የሰው ልጆችን በሚያጠቁ የቫይረስ ዓይነቶች ሊጠቃ ይችላል።

ስለዚህ አሳማ በአንድ ጊዜ በሁለቱም ዓይነት ቫይረሶች ማለትም እንስሳትንና በአብዛኛው ሰዎችን በሚያጠቁት ቫይረሶች ከተያዘ፣ የሁለቱ ቫይረሶች ጂን ሊደባለቅ ይችላል። ይህም የሰው ልጆች ሊቋቋሙት የማይችሉ ፍጹም አዲስ የሆነ የኢንፍሉዌንዛ ዓይነት እንዲፈጠር ምክንያት ይሆናል። ብዙውን ጊዜ በእስያ እንደሚታየው አዳዲስ የኢንፍሉዌንዛ ቫይረሶች የሚፈጠሩት ዶሮዎች፣ አሳማዎችና ሰዎች ተቀራርበው በሚኖሩባቸው በግብርና በሚተዳደሩ ማኅበረሰቦች ውስጥ እንደሆነ የሚሰማቸው አሉ።

ቫይረሱ ገዳይ የሆነው ለምን ነበር?

አሁን የሚነሳው ጥያቄ ‘ከ1918-1919 የተከሰተው የኢንፍሉዌንዛ ቫይረስ፣ ወጣቶችን ወደሚገድል የሳምባ ምችነት የተቀየረው በምን ምክንያት ሊሆን ይችላል?’ የሚል ነው። የዚያን ጊዜው ቫይረስ አሁን በሕይወት ባይገኝም ሳይንቲስቶች ለናሙና የሚሆን ቫይረስ በበረዶ ቀዝቅዞ ቢያገኙ ውስጡ ያለውን አር ኤን ኤ መርምረው በሽታው ገዳይ የሆነበትን ምክንያት ማወቅ እንደሚችሉ ከረጅም ጊዜ በፊት አንስቶ ሲያስቡ ቆይተዋል። በተወሰነ መጠንም ቢሆን ይህ ሐሳባቸው ተሳክቷል።

በዚህ ርዕስ መግቢያ ላይ እንደተጠቀሰው ሳይንቲስቶች ከበረዶ ውስጥ ተቆፍሮ ከተገኘው አስከሬን በወሰዱት ናሙና ላይ ምርምር በማድረግ ከ1918-1919 የተከሰተውን የኢንፍሉዌንዛ ቫይረስ ምንነት መለየትና የዚህን ቫይረስ አብዛኛውን የጂን ቅንብር ማወቅ ችለዋል። ነገር ግን ሳይንቲስቶች በሽታው ያን ያህል ገዳይ ሊሆን የቻለው ለምን እንደሆነ እስከ አሁን ማወቅ አልቻሉም። ቢሆንም ቫይረሱ አሳሞችንና ወፎችን ከሚያጠቃው የኢንፍሉዌንዛ ቫይረስ ጋር አንድ ዓይነት ሳይሆን አይቀርም።

እንደገና ይከሰት ይሆን?

ይህ አሰቃቂ በሽታ በድጋሚ መከሰቱ የማያጠያይቅ እንደሆነ፣ መቼና እንዴት ይከሰታል ለሚሉት ጥያቄዎች ግን መልስ ማግኘት እንደማይቻል በርካታ ባለሙያዎች ይናገራሉ። እንዲያውም አንዳንዶች በአንጻራዊ ሁኔታ ሲታይ ከባድ የሆነ አዲስ ኢንፍሉዌንዛ በየአሥራ አንድ ዓመቱ ገደማ እንደሚነሳና በየሠላሳ ዓመት ገደማ ልዩነት ደግሞ በጣም አደገኛ የሆነ ኢንፍሉዌንዛ እንደሚቀሰቀስ ይገምታሉ። ከእነዚህ ትንበያዎች አንጻር ሲታይ በሰው ዘር ላይ ይከሰታል ተብሎ የሚጠበቀው ሌላው ዓለም አቀፍ ወረርሽኝ መምጣት ከነበረበት ጊዜ በተወሰነ መጠን ዘግይቷል።

ቫክሲን የተባለ የሕክምና መጽሔት በ2003 ላይ የሚከተለውን ዘገባ አውጥቶ ነበር:- “የመጨረሻው ዓለም አቀፍ የኢንፍሉዌንዛ ወረርሽኝ ከተከሰተ 35 ዓመታት አልፈዋል፤ ማስረጃዎች እንደሚያረጋግጡት ዓለም አቀፍ ወረርሽኝ ሳይከሰት የቆየበት የመጨረሻው ረጅም ጊዜ 39 ዓመት ነው። . . . ዓለም አቀፍ ወረርሽኝ የሚያስከትል ቫይረስ በቻይና ወይም በአቅራቢያው ባለ አገር ብቅ ሊል ይችላል፤ ይህ ቫይረስ ከሰውና ከእንስሳት የኢንፍሉዌንዛ ቫይረሶች የተወረሰ እንግዳ ባሕርይ ሊኖረው ስለሚችል ከፍተኛ እልቂት ሊያስከትል ይችላል።”

ቫክሲን መጽሔት ዓለም አቀፍ ወረርሽኝ የሚያስከትለውን ቫይረስ በተመለከተ የሚከተለውን ተንብዮአል:- “ቫይረሱ በዓለም ዙሪያ በፍጥነት ይዛመታል። ሰዎች በተደጋጋሚ ይታመማሉ። በፍጥነትና በስፋት የሚሰራጨው ይህ ቫይረስ በማንኛውም ዕድሜ ላይ የሚገኙ ሰዎችን ያጠቃል፤ በተጨማሪም በሁሉም አገሮች ከባድ ማኅበራዊና ኢኮኖሚያዊ ቀውስ ይከተላል። በሁሉም የዕድሜ ክልል ውስጥ ያሉ ባይሆኑም እንኳን እጅግ ብዙ ሰዎች ያልቃሉ። በኢኮኖሚ በጣም በበለጸጉ አገሮች ያሉት የጤና አጠባበቅ ሥርዓቶች ጭምር፣ የጤና አገልግሎት ፍላጎትን በአጥጋቢ ሁኔታ ማርካት መቻላቸው አጠራጣሪ ነው።”

በእርግጥ ይህ ችግር ምን ያህል አሳሳቢ ነው? ዘ ግሬት ኢንፍሉዌንዛ የተባለው መጽሐፍ ጸሐፊ የሆኑት ጆን ቤሪ “የኑክሌር ጦር መሣሪያ ያለው አሸባሪ የሁሉንም አገራት የፖለቲካ ሰዎች ያስጨንቃል። አዲስ የሆነ ዓለም አቀፍ የኢንፍሉዌንዛ ወረርሽኝም ይህን ያህል ክብደት ሊሰጠው ይገባል” በማለት አስተያየት ሰጥተዋል።

ምን ዓይነት መድኃኒቶች አሉ?

‘በአሁኑ ጊዜ ውጤታማ የሆኑ ሕክምናዎች የሉም እንዴ?’ ብለህ ትጠይቅ ይሆናል። የዚህ ጥያቄ መልስ ጥሩም መጥፎም ዜናዎችን አጣምሮ ይዟል። በባክቴሪያ ምክንያት የሚይዙ እንደ ሳምባ ምች ያሉ ተጓዳኝ በሽታዎችን በአንቲባዮቲክ አማካኝነት በማዳን የሟቾችን ቁጥር መቀነስ የሚቻል ሲሆን የተለየ ባሕርይ ያዳበሩ የኢንፍሉዌንዛ ቫይረሶችን ለመግደል የሚያስችሉ አንዳንድ መድኃኒቶችም አሉ። የቫይረሱ ትክክለኛ ባሕርይ ከታወቀና ክትባቱ በተገቢው ጊዜ ከተሰጠ የኢንፍሉዌንዛ ቫይረሶችን ለመከላከል የሚያስችሉ ክትባቶችም አሉ። ይህ አስደሳቹ ዜና ነው። መጥፎውስ ዜና ምንድን ነው?

በ1976 ተሞክሮ ካልተሳካው የአሳማ ኢንፍሉዌንዛ ክትባት አንስቶ በ2004 ተዘጋጅቶ በበቂ መጠን ሊዳረስ እስካልቻለው ክትባት ድረስ ያሉት የኢንፍሉዌንዛ ክትባት ታሪኮች ብዙም ተስፋ ሰጪ አይደሉም። ከአንደኛው የዓለም ጦርነት ወዲህ የሕክምናው ሳይንስ ከፍተኛ እድገት ቢያሳይም፣ ዶክተሮች እስከ አሁን ድረስ ኃይለኛ ለሆነ ቫይረስ መድኃኒት ማግኘት አልቻሉም።

ስለዚህ ‘ከ1918-1919 የተከሰተው ሁኔታ ይደገም ይሆን?’ የሚል አሳሳቢ ጥያቄ ይነሳል። የለንደኑ ናሽናል ኢንስቲትዩት ፎር ሜዲካል ሪሰርች ያዘጋጀው ጽሑፍ ምን እንዳለ ተመልከት:- “በአሁኑ ጊዜ በ1918 ከነበረው ጋር የሚመሳሰሉ አንዳንድ ሁኔታዎች አሉ፤ መጓጓዣዎች በጣም እየተሻሻሉ በመምጣታቸው በዓለም ዙሪያ ሰዎች በከፍተኛ መጠን ይዘዋወራሉ፣ ሥር የሰደደ የምግብ እጥረትና ከባድ የንጽሕና ጉድለት ያለባቸው በርካታ የጦርነት ቀጠናዎች አሉ፣ የዓለም ሕዝብ ቁጥር ስድስት ቢሊዮን ተኩል የደረሰ ሲሆን ከዚህ ውስጥ አብዛኛው የሚኖረው ብዙውን ጊዜ ደካማ የሆኑ የቆሻሻ ማስወገጃ መሠረተ ልማቶች ባሉባቸው ከተሞች ውስጥ ነው።”

አንድ የተከበሩ የዩናይትድ ስቴትስ ባለ ሥልጣን “በአጭሩ ለመናገር ዓመት አልፎ ዓመት ሲተካ ወደ ቀጣዩ ዓለም አቀፍ ወረርሽኝ ይበልጥ እየተጠጋን ነው” የሚል መደምደሚያ ላይ ደርሰዋል። እንዲህ ሲባል ግን የወደፊቱ ጊዜ የጨለመና ምንም ተስፋ የሌለው ነው ማለት ነው? በጭራሽ!

[የግርጌ ማስታወሻ]

^ አን.5 ቫይረስስ፣ ፕላግስ፣ ኤንድ ሂስትሪ የተባለው መጽሐፍ እንዲህ ይላል:- “በ1500 ከክርስቶስ ልደት በኋላ ገደማ ኢንፍሉዌንዛ የሚለውን ቃል ያስተዋወቁት፣ በሽታው በከዋክብት ‘ተጽዕኖ’ (ኢንፍሉወንስ) የሚቀሰቀስ ይመስላቸው የነበሩት ጣሊያኖች ናቸው።”

[በገጽ 8 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

አዳዲስ የኢንፍሉዌንዛ ዓይነቶች በግብርና በሚተዳደሩ ማኅበረሰቦች አካባቢ ሊቀሰቀሱ ይችላሉ

[ምንጭ]

BAY ISMOYO/AFP/Getty Images

[በገጽ 8, 9 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

ታይፕ ኤ ኢንፍሉዌንዛ የሚባለው ቫይረስ

[ምንጭ]

© Science Source/ Photo Researchers, Inc

[በገጽ 9 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

ተመራማሪዎች ከ1918-1919 ተከስቶ የነበረውን ቫይረስ ናሙና አጥንተዋል

[ምንጭ]

© TOUHIG SION/CORBIS SYGMA