በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

እንደገና ይከሰት ይሆን?

እንደገና ይከሰት ይሆን?

እንደገና ይከሰት ይሆን?

ዘመኑ ኋላቀር ቢሆንም በጣም ደስ የሚል ነበር። ለምሳሌ ያህል በምዕራቡ ዓለም የፈረስ ጋሪዎች የነበሩበት፣ ከላይ ሹጥጥ ያለ ባርኔጣ የሚደረግበት እንዲሁም በጣም ሰፋፊና ረጃጅም ቀሚሶች የሚለበሱበት ወቅት ነበር። ይሁንና ያ ዘመን በዓለም ዙሪያ በርካታ ሰዎች ያለቁበት አስፈሪ ጊዜም ነበር። እልቂቱን ያስከተለው ምንድን ነው?

በዚያን ወቅት ከባድ ጦርነት የነበረ ቢሆንም ዋናው ምክንያት ይህ አይደለም። የእልቂቱ ዋነኛ መንስኤ በሰው ልጆች ታሪክ ውስጥ ከተመዘገቡት ሁሉ የበለጠ ጥፋት እንዳደረሰ የሚነገርለት ስፓኒሽ ፍሉ ወይም ከ1918-19 የተከሰተው የኅዳር በሽታ የተባለው መቅሰፍት ነው።

ውጤታማ ሕክምናም ሆነ በሽታውን የሚፈውስ መድኃኒት ስላልነበረ ሕመሙ የያዛቸው በጣም ብዙ ሰዎች እንደ ቅጠል ረግፈዋል። ጤናማ የነበሩ በሚሊዮን የሚቆጠሩ ወጣቶች ብዙ መሥራት በሚችሉበት ዕድሜያቸው በድንገት ተቀጥፈዋል። መቅበር አስቸጋሪ እስኪሆን ድረስ አስከሬን ይቆለል ነበር። በአንዳንድ አገሮች የተወሰኑ የገጠር ከተሞችና መንደሮች ነዋሪዎች ሙሉ በሙሉ አልቀዋል።

ይህ ሁሉ የተከሰተው ከ85 ዓመታት በፊት ነው። በሽታው እንዲከሰት ምክንያት ስለሆነው ነገር ምን እናውቃለን? ይህንን የመሰለ መቅሠፍት በድጋሚ ይከሰት ይሆን? በሽታው ቢከሰት ራሳችንን መጠበቅ እንችላለን?

ይህን ጉዳይ አስገራሚ ያደረገው ሌላም ምክንያት አለ። በዘመናችን ስለተመለከትነው ቸነፈር መጽሐፍ ቅዱስ ከረጅም ጊዜ በፊት የተናገረው ነገር እንዳለ ታውቃለህ? (ሉቃስ 21:11፤ ራእይ 6:8) የኅዳር በሽታ አንዱ የመጽሐፍ ቅዱስ ትንቢት ፍጻሜ ነው? የዚህንና የሌሎች ጥያቄዎችን መልስ በሚቀጥሉት ርዕሶች ውስጥ እንመለከታለን።

[በገጽ 3 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

በኅዳር በሽታ የሞቱ ሰዎችን ለመቅበር ዝግጅት ሲደረግ፣ ፊላዴልፊያ፣ ዩናይትድ ስቴትስ

[ምንጭ]

በፊላዴልፊያ የሚገኘው የሐኪሞች ኮሌጅ ቤተ መጻሕፍት