ከዓለም አቀፍ ወረርሽኝ ጋር በተያያዘ ወደፊት ምን ይከሰት ይሆን?
ከዓለም አቀፍ ወረርሽኝ ጋር በተያያዘ ወደፊት ምን ይከሰት ይሆን?
ከ1918-1919 ተከስቶ ስለነበረው ዓለም አቀፍ የኢንፍሉዌንዛ ወረርሽኝ ያጠኑ ተማሪዎች በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ የሚገኙ ትንቢቶችን አስታውሰው ነበር። ለምሳሌ ያህል ጂና ኮላታ ፍሉ—ዘ ስቶሪ ኦቭ ዘ ግሬት ኢንፍሉዌንዛ ፓንደሚክ ኦቭ 1918 ኤንድ ዘ ሰርች ፎር ዘ ቫይረስ ዛት ኮዝድ ኢት በተባለው መጽሐፋቸው ላይ እንዲህ ብለዋል:- “በ1918 የተከሰተውን ወረርሽኝ ኢንፍሉዌንዛ ያሉት ቢሆንም ከዚያ በፊት ከታዩት ኢንፍሉዌንዛዎች ሁሉ የተለየ ነበር። እንዲያውም የመጽሐፍ ቅዱስ ትንቢት ፍጻሜውን ያገኘ ይመስል ነበር።”
በእርግጥ መጽሐፍ ቅዱስ በሰው ልጆች ላይ ስለደረሰው ስለዚህ መቅሰፍት የተናገረው ነገር አለ? አዎን፣ አለ።
ስለ ቸነፈር የተጠቀሰ የመጽሐፍ ቅዱስ ትንቢት
ኢየሱስ ክርስቶስ ደቀ መዛሙርቱ ስለ “ዓለም መጨረሻ” ምልክት እንዲነግራቸው ጠይቀውት ነበር። (ማቴዎስ 24:3) እርሱም “ሕዝብ በሕዝብ ላይ፣ መንግሥትም በመንግሥት ላይ ይነሣል፤ ታላቅ የመሬት መናወጥ ይሆናል፤ . . . ቸነፈር በተለያየ ስፍራ ይከሠታል” በማለት መልስ ሰጣቸው። (ሉቃስ 21:7, 10, 11) በተጨማሪም በመጨረሻው ዘመን “መቅሠፍት” እንደሚኖር መጽሐፍ ቅዱስ ተንብዮአል።—ራእይ 6:8
በኋላ ላይ አንደኛው የዓለም ጦርነት ተብሎ በተጠራው በታላቁ ጦርነት (1914-1918) ማብቂያ አካባቢ የኅዳር በሽታ ተቀሰቀሰ። መጽሐፍ ቅዱስ ስለ “ዓለም መጨረሻ” የሚናገራቸው ትንቢቶች ፍጻሜያቸውን ማግኘት የጀመሩት በዚያን ጊዜ ነበር። እነዚህ ትንቢቶች ከባድ የሆነ ረሃብና ታላላቅ የመሬት መንቀጥቀጦች እንደሚከሰቱ እንዲሁም ሕገ ወጥነት እንደሚስፋፋና የሰዎች ሥነ ምግባር በሚያስገርም ሁኔታ እንደሚያሽቆለቁል ተናግረዋል። ዛሬ በዓለማችን ላይ እነዚህ ሁኔታዎች እየታዩ መሆናቸውን በሚገባ እንደምታውቅ ምንም አያጠራጥርም።—ማቴዎስ 24:3-14፤ 2 ጢሞቴዎስ 3:1-5
ስለ‘ቸነፈርና’ ስለ “መቅሠፍት” የሚናገረውን ጨምሮ ሌሎች ትንቢቶች ፍጻሜያቸውን ማግኘታቸው ፍርሃት፣ ሥቃይና
ሕይወትን ማጣት አስከትሏል። ማይክሮብስ ኤንድ ኢንፌክሽን የተባለ መጽሔት እንደዘገበው ከሆነ “ወደፊት ሌላ ዓለም አቀፍ ወረርሽኝ አይከሰትም ብለን የምንገምትበት ምንም ምክንያት የለም። መከሰቱ የማይቀር ይመስላል።”ስጋቱ አላከተመም
ኢመርጂንግ ኢንፌክሸስ ዲዚዝስ የተባለው መጽሔት በሚያዝያ 2005 እትሙ ላይ “አዎንታዊ አመለካከት ያላቸው ሰዎች፣ ከባድ የሆኑ ተላላፊ በሽታዎች የሚፈጥሩት ስጋት በአሁኑ ጊዜ እንዳከተመለት ይሰማቸዋል” ብሏል። ይሁን እንጂ “ተላላፊ በሽታዎች በተደጋጋሚ መከሰታቸውን እንደቀጠሉ ነው” በማለት መጽሔቱ አክሎ ገልጿል። ኔቸር የተባለው መጽሔት ደግሞ በሐምሌ 8, 2004 እትሙ ላይ “ከተላላፊ በሽታዎች ጋር በተያያዘ በዓለም ዙሪያ በዓመት . . . ወደ 15 ሚሊዮን የሚጠጉ ሰዎች እንደሚሞቱ ይገመታል” በማለት በሽታዎቹ ያስከተሉትን ውጤት ገልጿል።
ኔቸር “የኤድስ መስፋፋት ተላላፊ በሽታዎች መከሰታቸውም ሆነ አስከፊ ውጤት ማስከተላቸው እንደማይቀር ሰዎች እንዲያስታውሱ አድርጓቸዋል” ብሏል። በተባበሩት መንግሥታት ድርጅትና በሌሎች ቡድኖች ድጋፍ የሚንቀሳቀሰው ዩ ኤን ኤድስ የተባለ ፕሮግራም “ከ2000 እስከ 2020 ባሉት ዓመታት በኤድስ ክፉኛ በተጠቁ 45 አገሮች ውስጥ 68 ሚሊዮን ሰዎች በዚሁ በሽታ ምክንያት ያለ ዕድሜያቸው እንደሚቀጩ ይገመታል” ብሏል።
ኤድስ ባለፉት 25 ዓመታት ከ20 ሚሊዮን የሚበልጡ ሰዎችን በመግደሉ አጥፊ መቅሰፍት እንደሆነ ተረጋግጧል። የኅዳር በሽታ ግን ከአንድ ዓመት ትንሽ በሚበልጥ ጊዜ ውስጥ በሚሊዮን ለሚቆጠሩ ሰዎች ማለቅ ምክንያት ሆኗል። በተደጋጋሚ የሚሰጠው ማስጠንቀቂያ እንደሚያሳየው፣ ዓለማችን ለመቋቋም ያልተዘጋጀችበት ገዳይ ኢንፍሉዌንዛ ይከሰታል ከተባለበት ጊዜ በጣም ዘግይቷል።
ግንቦት 19, 2005 ሮይተርስ የተባለው የዜና አገልግሎት ሰጪ ድርጅት፣ በጎ አድራጊ ድርጅቶችን ለአስቸኳይ ሁኔታ ለማዘጋጀት በሚጠቀምበት የዜና አውታሩ ላይ አዳዲስ የኢንፍሉዌንዛ ቫይረሶች በተደጋጋሚ እንደሚከሰቱ አስጠንቅቋል። እነዚህ ቫይረሶች መከሰታቸው “ችግሩ እንደሚቀጥልና ወደፊት ዓለም አቀፍ ወረርሽኝ ሊኖር እንደሚችል የሚያሳይ ነው” በማለት አክሎ ገልጿል። ግንቦት 18, 2005 ዘ ዎል ስትሪት ጆርናል እንዲህ ብሎ ነበር:- “በቅርቡ በእስያ የተከሰተው የወፎች ኢንፍሉዌንዛ ቫይረስ ኤች5ኤን1 ተብሎ ይጠራል፤ ይህ ቫይረስ መጀመሪያ የታየው በሆንግ ኮንግ የዶሮ ገበያዎች ውስጥ በ1997 ነበር። በሽታውን ለየት የሚያደርገው ገዳይ መሆኑ ነው፤ በሽታው ከያዛቸው ውስጥ 80 በመቶ ያህሉ ሞተዋል።” ቫይረሱ በበሽታው ከተያዙ እንስሳት ጋር የቅርብ ግንኙነት ወዳላቸው ሰዎች እንደሚተላለፍ ተነግሯል።
የወደፊቱ ጊዜ ያሰጋል ወይስ ተስፋ ያዘለ ነው?
ወደፊት ጥሩ ጊዜ የማየት ተስፋችን የተመናመነ ሊመስል ይችላል። ኢየሱስ በመጨረሻው ዘመን ቸነፈሮች እንደሚከሰቱ የተናገረው ሐሳብ ጊዜው አስጨናቂ እንደሚሆን ይጠቁማል። ይሁን እንጂ መጽሐፍ ቅዱስ የሚናገረው ተስፋም አለ። ለምሳሌ ያህል አምላክ የጥፋት ውኃ ከመድረሱ በፊት ለኖኅና ለቤተሰቡ ቃል ገብቶላቸው ነበር። በመጀመሪያ ጥፋት እንደሚያመጣ ለኖኅ አስጠነቀቀው፤ ከዚያ በመቀጠል ግን ኖኅ ራሱና ቤተሰቡ ከጥፋቱ የሚድኑበትን መርከብ እንዲሠራ አዘዘው። (ዘፍጥረት 6:13, 14፤ 7:1) ሐዋርያው ጴጥሮስ ‘በኖኅ ዘመን መርከብ ሲሠራ እግዚአብሔር በትዕግሥት ይጠብቅ’ እንደነበረ ገልጿል፤ ሥራውም ሲጠናቀቅ መርከቡ ውስጥ ገብተው ከጥፋት ተርፈዋል።—1 ጴጥሮስ 3:20
በአሁኑ ጊዜ ስለምናያቸው የዓለም ሁኔታዎች በርካታ ነገሮችን አስቀድሞ የተናገረው ኢየሱስ ክርስቶስ፣ ዘመናችን ከኖኅ ዘመን ጋር እንደሚመሳሰል ገልጿል። በአምላክ ተስፋ የሚያደርጉ ሰዎች ልክ እንደ ኖኅ ከፊታችን ከሚጠብቀን ታላቅ ጥፋት የመትረፍ አጋጣሚ አላቸው። (ሉቃስ 17:26, 27) የኢየሱስ ሐዋርያ የሆነው ዮሐንስ “ዓለምና ምኞቱ ያልፋሉ፤ የእግዚአብሔርን ፈቃድ የሚፈጽም ግን ለዘላለም ይኖራል” ብሎ ጽፏል።—1 ዮሐንስ 2:17
አሁን ያለንበት ሥርዓት ይጠፋል። ከዚህ ጥፋት የሚተርፉት ሰዎች ምን ዓይነት ሕይወት ያገኛሉ? ሐዋርያው ዮሐንስ ምድራችን በአምላክ መንግሥት በምትገዛበት ጊዜ ስለሚሰፍኑት ግሩም ሁኔታዎች ራእይ ተመልክቶ ነበር። እንዲህ ብሏል:- “እርሱ [አምላክ] ከእነርሱ ጋር ይኖራል፤ እነርሱም ሕዝቡ ይሆናሉ፤ እግዚአብሔር ራሱም ከእነርሱ ጋር ይኖራል፤ አምላካቸውም ይሆናል። እንባን ሁሉ ከዐይናቸው ያብሳል፤ ከእንግዲህ ወዲህ ሞት ወይም ሐዘን ወይም ልቅሶ ወይም ሥቃይ አይኖርም፤ የቀድሞው ሥርዐት ዐልፎአልና።”—ራእይ 21:3, 4
የወደፊቱ ጊዜ ጨለማ ሆኖ ሊታይህ አይገባም። ስለ አምላክ ከተማርክና ሙሉ በሙሉ በእርሱ ከተማመንህ ከፊትህ ብሩህ ተስፋ ይጠብቅሃል። አምላክ በሚያመጣው አዲስ ዓለም ውስጥ ሙታንን እንደሚያስነሳ እርግጠኛ የሆነ ቃል ገብቷል። (ዮሐንስ 5:28, 29፤ የሐዋርያት ሥራ 24:15) ቸነፈርም እስከወዲያኛው ይወገዳል። አንድ የመጽሐፍ ቅዱስ ትንቢት “በጽዮን ተቀምጦ፣ ‘ታምሜአለሁ’ የሚል አይኖርም” ይላል። ይህ ትንቢት በዚያ አዲስ ዓለም ውስጥ ፍጻሜውን ያገኛል።—ኢሳይያስ 33:24
[በገጽ 10 ላይ የሚገኝ ሥዕል]
መጽሐፍ ቅዱስ ‘ታምሜአለሁ የሚል የማይኖርበት’ አዲስ ዓለም እንደሚመጣ ተስፋ ይሰጣል