በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

ከዓለም አካባቢ

ከዓለም አካባቢ

ከዓለም አካባቢ

እንቅልፍ ችግሮችን ለመፍታት ይረዳናል

“ብዙ ሰዎች ከመተኛታቸው በፊት መፍትሔ ያላገኙለት ችግር ከእንቅልፋቸው በሚነቁበት ጊዜ ግን በቀላሉ የሚፈታ ሆኖ እንደሚያገኙት አስተውለዋል። አእምሯቸው መፍትሔ ለማግኘት ሌሊቱን በጸጥታ ሲሠራ ያደረ ይመስላል” ሲል የለንደኑ ዘ ታይምስ ዘግቧል። በጀርመን የሚገኙ ሳይንቲስቶችም ይህ ትክክል መሆኑን የሚያሳይ ማስረጃ እንዳገኙ የገለጹ ከመሆኑም ሌላ የጥናታቸውን ውጤት ኔቸር በተባለ ጋዜጣ ላይ አውጥተዋል። በጥናቱ ላይ በፈቃደኝነት ለተሳተፉ 66 ሰዎች፣ ለአንድ የሒሳብ ጥያቄ መልስ ማግኘት የሚችሉባቸውን ሁለት መንገዶች አሳይተው ትክክለኛውን መልስ በቀላሉ ማግኘት የሚችሉበትን ሦስተኛ ዘዴ ግን ሳይነግሯቸው ቀሩ። ከዚያም ከመካከላቸው አንዳንዶቹ እንዲተኙ ተደረጉ፤ ሌሎቹ ደግሞ ሌሊቱን ወይም ቀኑን ሙሉ ሳይተኙ አሳለፉ። የለንደኑ ዘ ዴይሊ ቴሌግራፍ በዚሁ ጥናት ላይ ሐሳብ ሲሰጥ “እንቅልፍ አስደናቂ ውጤት ያስገኛል” ሲል ዘግቧል። ተኝተው የነበሩት ሰዎች “ሦስተኛውን ዘዴ በማግኘት ረገድ፣ ሳይተኙ ከቀሩት በሁለት እጥፍ በልጠው ተገኝተዋል።” ይህ ውጤት ሊገኝ የቻለው እንዲተኙ የተደረጉት ሰዎች እረፍት በማግኘታቸውና ሰውነታቸው በመታደሱ ምክንያት አለመሆኑን ለማወቅ ሳይቲስቶቹ ሌላ ጥናት አካሄዱ። ሁለቱ ቡድኖች ጠዋት ከእንቅልፋቸው ሲነሱ ወይም ቀኑን ሙሉ ሳይተኙ ውለው ማታ ላይ ሌላ ጥያቄ ቀረበላቸው። በዚህ ጊዜ ሁለቱ ቡድኖች ባገኙት ውጤት ላይ የታየ ልዩነት አልነበረም፤ በመሆኑም “ለውጥ የሚያመጣው አእምሮ እረፍት ማግኘቱ ሳይሆን በእንቅልፍ ወቅት አእምሮ ራሱን በአዲስ መልክ ማደራጀቱ ላይ ነው” ሲል ዘ ታይምስ ዘግቧል። ተመራማሪው ዶክተር ኡልሪኽ ቫግነር “በመሆኑም እንቅልፍ አዳዲስ ነገሮች የሚታወቁበት የመማር ሂደት ሆኖ ያገለግላል” በማለት ደምድመዋል።

ዝንጅብል የማጥወልወል ስሜትንና ማስመለስን ይቀንሳል

“ዝንጅብል በእርግዝና የመጀመሪያዎቹ ወራት የሚከሰተውን የማስመለስ ችግር ያስቆማል” ሲል አውስትራሊያን የተባለው ጋዜጣ ገልጿል። የሳውዝ አውስትራሊያ ዩኒቨርሲቲ ያካሄደው ጥናት እንዳሳየው በቀን አንድ ግራም የሚያህል ዝንጅብል መጠጣት በእርግዝና መጀመሪያ ሰሞን ሴቶች የሚያጋጥማቸው ማቅለሽለሽና የማስመለስ ችግር እንዲቀንስ ያደርጋል። በብዙ ቦታዎች ዝንጅብል ለዚህ ዓይነቱ ችግር ባሕላዊ መድኃኒት ሆኖ ሲያገለግል ቆይቷል። ይሁንና ፍቱንነቱ በሳይንስ አልተረጋገጠም ነበር። ይህ ጥናት፣ ዝንጅብል መጠጣት አብዛኛውን ጊዜ የሚታዘዘውን ቪታሚን ቢ6 በየቀኑ የመውሰድን ያህል ጥሩ ውጤት እንደሚያስገኝ አመልክቷል።

በአንግሊካኖች መካከል የተፈጠረ መከፋፈል

በሲድኒ የአንግሊካን ቤተ ክርስቲያን ኃላፊና አውስትራሊያ ውስጥ ከፍተኛ ሥልጣን ካላቸው ጳጳሳት መካከል አንዱ የሆኑት ፊሊፕ ጄንሰን በቅርቡ የካንተርበሪውን ሊቀ ጳጳስ “የውሸት ሰበብ እያቀረበ ደሞዙን የሚበላ ሃይማኖታዊ አመንዝራ” ሲሉ መንቀፋቸውን ዚ ኤጅ የተባለው የአውስትራሊያ ጋዜጣ ዘግቧል። ጄንሰን የቤተ ክርስቲያኒቱ መሪ ግብረ ሰዶምን በተመለከተ ለዘብተኛ አቋም በመያዛቸው አውግዘዋቸዋል። ዚ ኤጅ እንዲህ ሲል ገልጿል:- “በዓለም አቀፍ ደረጃ የአንግሊካን ቤተ ክርስቲያን በግብረ ሰዶም ጉዳይ ላይ በከፍተኛ ሁኔታ ተከፋፍላለች። በካናዳ የሚገኘው ቤተ ክርስቲያን ግብረ ሰዶማውያን የሚፈጽሙትን ጋብቻ በመባረኩና በዩናይትድ ስቴትስ የሚገኘው ደግሞ ግብረ ሰዶም ፈጻሚ መሆኑ በይፋ የሚታወቅ ግለሰብ ጳጳስ እንዲሆን በመፍቀዱ፣ በአፍሪካና በእስያ የሚገኙ ብዙ ቤተ ክርስቲያኖች ከእነርሱ ጋር ያላቸውን ግንኙነት አቋርጠዋል።”

ደም መውሰድ የሟቾችን ቁጥር ይጨምራል

የአሜሪካ የሕክምና ማኅበር መጽሔት ላይ የወጣ አንድ ጥናት፣ በቂ ደም ወደ ልባቸው የማይደርስ በሽተኞች በየጊዜው ደም የሚሰጣቸው ከሆነ ደም ከማይሰጣቸው ሰዎች ይልቅ የመሞታቸው አጋጣሚ እንደሚጨምር አመልክቷል። “የታካሚዎቹን አጠቃላይ ሁኔታ እንዲሁም እንደ ደም መፍሰስ፣ ሰውነትን እንደ መቅደድና ወደ ሰውነት የሕክምና መሣሪያ እንደማስገባት ያሉ የሕክምና ሂደቶች ግምት ውስጥ ገብተውም እንኳ ደም መስጠት ለሞት የመዳረጉ ሁኔታ አልቀነሰም” ሲል ሪፖርቱ ገልጿል። ጥናቱን ያካሄዱት ዶክተሮች “በቂ ደም ወደ ልባቸው ለማይደርስ በሽተኞች በደማቸው ውስጥ ትክክለኛ መጠን ያለው ቀይ የደም ሕዋስ እንዲኖር በሚል በየጊዜው ደም መስጠት አደገኛ መሆኑን እንገልጻለን” ሲሉ የጥናቱን ግኝት ጠቅለል አድርገው አስቀምጠዋል።